Elections 2021 Ethiopian language In-depth

የወሰን ግፊያ ያየለባት አወዛጋቢዋ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ

ምንም እንኳን የተወሰኑ የተፈናቀሉ ገበሬዎች ከአመታት ቸልታ በኋላ አዲስ ቤት ያገኙ ቢሆንም ፣ አዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ መስፋፋቷ  እሁንም ዋነኛ የውዝግብ ምንጭ ነው።  

የአምስት ልጆች አባት የሆኑት የ47 ዓመቱ ባልቻ ብሩ በትካዜ የተዋጡ አይኖቻቸውን የኢትዮጵያና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ  በሆነችው አዲስ አበባ  በምትገኘው አቃቂ ደቡብ ምስራቅ ዳርቻ ላይ ባለ  አንድ ሰፈር ላይ ተክለዋል።

በአቶ ባልቻ እይታ በዚህ አካባቢ ተፈራራቂ ስሜት ውስጥ የሚከቱ ሁለት እውነታዎች በአንድ ላይ ይገኛሉ።

‹‹ይህ ሰፈር ለኛ ‹ቤታችን› ብለን የምንጠራው ነበር ፤ ጠንካራ የማህበራዊ ግንኙነትም ነበረን። እኛ በዚህ ለዘመናት የቀርሳ መንደር ገበሬዎች ሆነን ተረጋግተን ኖረናል። መሬቱ ሁላችንንም ለመመገብ የሚበቃ ለም ነበር›› ይላሉ አቶ ባልቻ ፤ አሁን ላይ በአዲስ አበባ (ከተማይቱ በበርካታ የኦሮሞ ህብረተሰብ ዘንድ ‹‹ፊንፊኔ›› በመባል ትታወቃለች) ከተማ ስር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፣ ወረዳ 9  ውስጥ ስለሚገኘው ስለዚህ ስፍራ ሲናገሩ።

ይህ አቶ ባልቻ የሚያስታውሱት የ‹ቀርሳ መንደር› አሁን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚያልፈው የአቃቂ ወንዝ ባለበት አካባቢ ይገኝ የነበረና በአንድ ወቅት ጥሩ እንቅስቃሴ የነበረባቸው የእርሻ ስፍራዎችና የኦሮሞ ገበሬ ማህበረሰቦች የሚገኙበት በከተማ ዙሪያ ያለ የገበሬ ቀበሌ ማህበር አካል ነበር።

በዚሁ መንደር ነበር የአቶ ባልቻ 17 የቤተሰብ አባላት 10 ሄክታር ስፋት ባለው መሬታቸው ላይ በማረስ ይተዳደሩ የነበረው።  ይህ መሬት ለትውልዶች የእህል በረከትን ሲለግስ ኖሯል፤ የአቶ ባልቻን አባት ጨምሮ ብዙ ትውልዶችን አሳድጓል። በጉብዝና ከታረሰ ይላሉ አቶ ባልቻ፣ መሬቱ በአመት እስከ 8,000 ኪሎ ግራም (ወደ 18,000 ፓውንድ ማለት ነው) የሚሆኑ የተለያዩ እህልና ጥራጥሬ ምርቶች ይገኝበትም ነበር።

ዛሬ ላይ ግን ይህ ለም መንደር በፍጥነት እየጠፋ ነው። ከላዩ ላይ የተደረበ አዲስ የማኅበረሰብ እና የአካባቢ እውነታ አሁን ተገንብቷል።

ይህ አዲሱ እና ሁለተኛው እውነታ አቶ ባልቻ በአንድ ወቅት ከሚያውቁት በእጅጉ የተለየ የኑሮ ሁኔታን  ያመለክታል (ይወክላል)። በተጨባጭ ሲታይ ብዙ ነገሮችን የቀየረ ከባድ እውነታም ነው። ከኖሩበት አካባቢ መነሳትን፣ ማንነትን ማጣትን ፣በግዳጅ ከአዲስ የማህበረሰብ ቅርፅ ጋር መዋሃድ የመሰሉ ሁነቶች የሚስተዋልበት ሲሆን ፤ በተጨማሪም  ለስራ፣ ለስልጣን ፣ ለመወከል፣ የኔ የሚሉት ቦታና ማንነትን ለማግኘት ብሎም ነገሮችን ለመረዳትና ከአዲስ የማህበረሰብ ዘይቤ ጋር ለመግባባት የሚደረግን ትግል የሚያሳይ ነው።

የከሰሙ መተዳደሪያዎች

ረዥም አመታትን የኖሩ ነዋሪዎች አካባቢው በተለያዩ ለውጦች ውስጥ ሲያልፍ ያስተዋሉ ቢሆንም አብዛኞቹ ግን  በአንድ ወቅት የተፈጠረ  ክስተት ብዙ ነገሮችን  እስከወዲያኛው እንደቀየረ ያስታውሳሉ። ይህን ከሚያስታውሱት መካከል አንዱ የ75 አመቱ ገበሬ አቶ ኤዶ ወርዶፋ ናቸው። ምንም እንኳን አድሜያቸው ቢገፋ፣ እርጅና ሰውነታቸውን ያልተጫጫነውና በአካልም በመንፈስም ብርቱ ሆነው የሚታዩት ኤዶ ፣ ባለፈው ግንቦት ወር ከኢትዮጵያ ኢንሳይት  ጋር አቃቂ በሚገኘው ቤታቸው ደጅ ላይ ባደረጉት ቃለምልልስ ፣ ከስምንት አመታት በፊት በአካባቢው የተከሰተውን ሲያነሱ ‹‹ያች አስከፊ ቀን›› በማለት  ነው ያስታውሱት።

ደጃቸው ላይ ወፍራም ጋቢ ደርበው የተቀመጡት አቶ ኤዶ ፣ አዕምሯቸው ወደ 2005 ዓ.ም ሲመልሳቸው የማለዳዋ ፀሀይ ጨረር ፊታቸውን ታፈካ ፣ አካላቸውን ታሞቅ ነበር። እሳቸው እንደሚያስታውሱት ከአካባቢው  ወረዳ ባለስልጣናት የተዋቀረ ኮሚቴ አባላት መንደርተኞቹን ቀድመው ሳያሳውቁ በድንገት መጥተው ሰበሰቧቸው። የመንግስት ተወካዮቹ በአካባቢው የሚገኙ የእርሻ መሬቶችና መኖሪያ ቤቶች  ‹‹ለልማት አላማ››  ስለተፈለጉ ነዋሪዎቹን እንደሚነሱና ቦታዎቹ  እንደሚወሰዱ ተናገሩ።

አቶ ኤዶ ነዋሪዎቹ ‹‹ለምን የኛ መሬት ይወሰዳል?›› የሚል ተቃውሞ ማሰማታቸውን ይገልጻሉ። እሳቸው ግን ከሁሉም በላይ   የኮሚቴው ዋና ተወካይ የሰጠው ምላሽ ‹‹እስከአሁን ድረስ ውስጤ ያቃጭልብኛል›› ይላሉ። ድምጹን ከፍ በማድረግ ‹‹ሁሉም መሬት ፣ የእናንተንም ጨምሮ የመንግስት ነው›› ሲል ነበር አስረግጦ የተናገረው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቀርሳ መንደርተኞች በመፈናቀልና በስራ አጥነት ከመፈተናቸው በፊት የነበራቸውን ፍሬያማነት እያሰቡ እንዲሰቃዩ ከተፈረደባቸውና በየጊዜውና በየምክንያቱ የሚስፋፋው የኢትዮጵያ ‹የተፈናቀሉ ሰዎች› ስሜትን የሚያውቁ ብሎም የዛው አካል ሆነው ቆይተዋል ። በጊዜው ሲሰራበት በነበረው የእርሻ መሬት ካሳ ክፍያ ተመን መሰረት በአንድ ሜትር ስኩዌር መሬት 18.5 ብር ካሳ የተገመተላቸው ቢሆንም ፣ ካሳው በድጋሚ ይታይላችኋል ከሚል ተስፋ ውጭ አንዳችም ምትክ ቦታ እንዲሁም ቤት መስሪያ ቦታ ሳይሰጣቸው በመቅረቱ በህይወታቸው ብዙ ጎድሏል። ከሁሉም በላይ በመፈናቀላቸው ምክንያት ሰዎች ህይወታቸው መስመር እንዲይዝ የሚያስችል የተሃድሶ ዕቅድ በመንግስት ዘንድ ስላልተመቻቸ ፣ ብዙዎቹ ገበሬዎች ከሚያውቁት የግብርና ስራ ተለያይተው ገቢ ከማጣትም በላይ  የነበራቸውንም በማጣት መና ቀርተዋል።

ከአስር በላይ ቤተሰብ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ኤዶም በዚያው በ2005 ዓ.ም ላይ 5.25 ሄክታር መሬታቸውን ካጡ በኋላ ቤተሰቡ ከህይወት ጋር ትግል ይዞ መንገዳገድ ጀመረ። ምትክ መሬት እና ስራ ባለመሰጠቱ ምክንያት  971,250 ብር ከአራት አመታት ላነሰ ጊዜ ብቻ ነበር ቤተሰቡን መመገብ የቻለው። ከሁሉም በላይ ግን የአቶ ኤዶን ስነልቦና የጎዳው ነገር ፣ ቀድሞ የራሳቸው ይዞታ በነበረ መሬት ላይ በተጀመሩ የግንባታ ስራዎችና ለአዳዲስ ፎቆች መስሪያ ቦታነት በተለወጠው ቦታ ላይ  የአብራካቸው ክፋይ የሆኑት  ልጆቻቸው ስራ ሲፈልጉ ማየቱ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ዛሬ ከስምንት አመታት በኋላ በአካባቢው ሁሉ ነገር አዲስ የሆነ ይመስላል ፤ የወደፊቱን አቅጣጫ የሚወስኑ አዳዲስ ሁነቶችም መታየት ጀምረዋል።  አሁን ላይ ‹ቀርሳ› በአዲስ አበባ ከፍተኛ ውዝግብ ያስከተለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ስፍራ የሆነው የ‹‹ኮዬ ፈጬ ኮንዶሚንየም ፕሮጀክት›› አካባቢዎች አንድ አካል ነው። ኮዬ ፈጬ ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ እንዲሰፍርባቸው ታልመው እንዲገነቡ ከተደረጉ የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ትልቅ ከሚባሉት ማዕከላት አንዱ ሲሆን ይህም ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት ድጎማ በብሔራዊ ደረጃ መተግበር ከጀመረው የተቀናጀ የቤቶች ልማት ፕሮግራም ስኬቶች አንዱ ያደርገዋል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መገንባት

የቱሉ ዲምቱ ኮንዶሚኒየም ፕሮጀክትን ተጎራብተው  የሚገኙት የኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየሞች ከከተማው ማዕከላዊ ስፍራ  በደቡብ ምስራቅ ከ22 እስከ 25 ኪሎሜት ርቀት ላይ ይገኛሉ። በቤቶች ልማት ፕሮጀክቱ አማካኝነት የአስገንቢ ባለቤትነት ሚና ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአካባቢው የቤቶች ግንባታውን ያስጀመረው በ 2006 ዓ.ም በሁለት የግንባታ ምእራፎች ነበር።

በ2012 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የህዝብ አስተዳደር ትምህርት ክፍል በአቶ ኑረዲን ናስር  በቀረበ የድህረ-ምረቃ የጥናት ፅሁፍ ላይ ዋቢ  እንደተደረገው የአዲስ አበባ የመሬት ልማት ኤጀንሲ መረጃ ከሆነ በ2005 እና በ2006 ዓ.ም ብቻ 1,925 ገበሬዎች ከአሁኑ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አካባቢ ተፈናቅለዋል። የከተማ መስተዳደሩ የዛኔ የቱሉ ዲምቱ አካባቢን ጨምሮ በገጠር ቀበሌ ማህበር ይተዳደር የነበረን 854 ሄክታር መሬት የራሱ አድርጓል። ከዚህ ውስጥ ከ658  ቤቶች በላይ ዛሬ ኮዬ ፈጬ ኮንዶሚንየም ፕሮጀክት ተብሎ ለሚጠራው አካባቢ ግንባታ ሲባል ፈርሰዋል።

ኮዬ ተብሎ የሚጠራው የፕሮጀክቱ ክፍል እስከ ወረዳ 9, 10, 11 እና 12 ድረስ ይዘልቃል። አሁን ላይ በፊት የቀርሳ መንደር ተብሎ የሚታወቀውን አካባቢም ሙሉ ለሙሉ ያካትታል። ዛሬ ከወረዳ 9 እስከ 11 እየጠፋ  ለሚገኘው የቀርሳ መንደር፤ የሰፈር ስሞች አዲስ ለነገሰው እውነትና ለተፋቀው የአካባቢው ማንነት ቀጭን ምስክር ሆነው ይገኛሉ። በፈጬ በኩል ያለውና  የቱሉ ዲምቱን ኮንዶሚንየሞችን የሚጎራበተው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ክፍል ደግሞ በወረዳ 13 ይገኛል።

በ 2008 ዓ.ም ነበር የመጀመሪያዎቹ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ስብስብ ወደ ኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም የገቡት። አዲስ ገቢ ነዋሪዎቹ ከ400 ብሎክ በላይ ባሏቸው ባለአራት ፎቅ የመኖሪያ ቤቶች ፤ ስቱዲዮ ክፍሎችን ያገኙ ነበሩ። እነዚህ ፈር ቀዳጅ ነዋሪዎች በወር ከ1,000 ብር በታች የሚያገኙ የመንግስት ሰራተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ባለመውና የተቀናጀ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት አካል  የሆነው የ10/90 መርሃግብር የእጣ አሸናፊዎች ነበሩ። በዚህ የ10/90 መርሃግብር  ውስጥ የቤት እድለኛ የሚሆኑ ሰዎች ከቤቱ አጠቃላይ የግንባታ ወጪ ውስጥ 10 ከመቶ የቅድሚያ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚጠየቁ ሲሆን በ25 አመታት በ9.5 ወለድ የሚከፈል 90 ከመቶ ብድር ደግሞ ከመንግስት ባንክ ጋር በመተሳሰር ቀርቦላቸዋል።

ታዲያ በነዚህ የግንባታና የማስተላለፍ ሂደቶች ውስጥ ያለፈው ይህ የኮዬ ፈጬ አካባቢ የአዲስ አበባ ከተማንና የከተማዋ አጎራባች  በሆነው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስር  የሚተዳደረው የፊንፊኔ ልዩ ዞን ደቡባዊ ድንበርን በሚለዩ የአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳዎች መካከል እንደሚገኝ ማንሳት ያስፈልጋል። በአዲስ አበባ በገጠር ቀበሌ ማህበር ይተዳደሩ የነበሩና ወደ 25 የሚጠጉ ቀበሌዎች ነበሩ። ከነዚህ ውስጥ በአቃቂ ዳርቻ የነበሩት እንደ ቀርሳ፣ኮዬ፣ቂሊንጦ እና ቱሉሙቴ ያሉ መንደሮች ከ15 አመታት በፊት በኦሮሞ ገበሬዎች የሚተዳደደሩ መንደሮች ነበሩ።

ይኸው የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በሁለተኛ ዙር ሲቀጥል ግን የከተማ አስተዳደሩ የፕሮጀክት ዕቅዱን በተሳሳተ መንገድ  አንብቦ የተገበረው ይመስላል። የኮዬ ፈጬ ይዞታን የሚያለሙና ግንባታውን ያካሄዱት ባለሞያዎች ወረዳ 9ን አልፎ  የተዘረጋውን እና ለፈጬ አካባቢ የሚቀርበውን የድንበር መስመር አልፈው ወደ ኦሮሚያ ገብተው ግንባታ አከናወኑ ።

የኦሮሚያን ክልል ድንበር አልፈው ተገንብተዋል የተባሉት እነዚህ በኮዬ ፈጬ የሚገኙት ቤቶች ታዲያ በተቀናጀ የቤቶች ልማት ፕሮጀክትና በከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ልማት ቢሮ  በየካቲት ወር 2011 ዓ.ም በተደረገ የእጣ ማውጣት ስነስርዓት ላይ ለነዋሪዎች ከቀረቡት 32,653 ቤቶች ጋር አንድ ላይ ሲካተቱ ጉዳዩ ከፍተኛ ውዝግብ አስነሳ። እነዚሁ ቤቶች አነስተኛ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ባለመውና ሌላው የተቀናጀ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት አካል በሆነው የ20/80 መርሃግብር ስር በአዲስ አበባ ለ13ኛ ዙር በተደረገ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ስነስርዓት ለአሸናፊዎች ይፋ ተደረጉ።

በግንባታ ላይ ያሉ የኮዬ ፈጬ ኮንዶዎች እና ወደ ቤተክርስትያን የሚያቀኑ ነዋሪዎች፥ ኢትዮጵያ ኢንሳይት፥ ግንቦት 2013

ሁነቱ በኦሮሚያ እንዲሁም ግንባታው በተካሄደበት ስፍራ ሰፊ ተቃውሞዎችን አስነሳ። ተቃውሞዎቹን በግንባር ቀደምትነት ሲመሩ ከነበሩት ውስጥ አሁን በእስር ላይ የሚገኘው የማህበረሰብ አንቂና ፖለቲከኛ ጃዋር መሀመድ አንዱ ነበር። ጃዋር አዲስ አበባ በ19ኛው ክፈለ ዘመን መጨረሻ ላይ በኦሮሚያ መሬት ላይ የተገነባች ናት ብሎ  የሚያምንና በስሱ  የተቀናጀ የኦሮሞ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ አካል ነው።

እነዚህ የኦሮሞ መብትን የሚያቀነቅኑ ብሔርተኞች እንደ መነሻ መስፈርት ከሚያስቀምጧቸው የመብት ጥያቄዎች ውስጥ ኦሮሚያ ከታሪክ ፣ ከጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና ከሌሎች አመክንዮዎች በመነጨ ሁኔታ በአማራጭ ስያሜዋ ‹‹ፊንፊኔ›› ተብላ በምትጠራው የሀገሪቱ መዲና ላይ ልዩ ጥቅም እንዲኖራት ይጠይቃሉ። በዋናነትም አሁን በስራ ላይ ባለውና በ1987ት በተደነገገው የሀገሪቱ ህገመንግስት ውስጥ የተካተተው ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት የልዩ ጥቅም ባለቤትነት መብት ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር ይፈልጋሉ።

በወቅቱ ይህን በኮዬ ፈጬ የተከሰተውን የውዝግብ ሞገድ በተመለከተ መግለጫ የሰጠው  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ቤቶቹ የተገነቡት ወሰን አልፈው በክልሉ ውስጥ በመሆኑ ይህ ጉዳይ ተጣርቶ እስኪለይ ድረስ በድንበሩ ውስጥ የተገነቡ ቤቶችን ማስተላለፍ ‹‹ተቀባይነት የለውም›› ሲል ሞገተ። ይህ ለአመታት ሲንከባለል የቆየው በክልሉ መንግስት እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መካከል ያለውን ወሰን የመለየት ጉዳይ በተደጋጋሚ ከሚከሰቱ የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች ጋር ተዳምሮ አንገብጋቢነቱ እንዲጨምር አደረገው።

ይህ ውዝግብ ከተከሰተ ከአንድ አመት በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቢሮ ሀሳብ አቅራቢነት የኮዬ ፈጬን ጉዳይ ለመመርመር ስምንት አባላትን የያዘ  ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር። ኮሚቴውም ከወራት ቆይታ በኋላ አጣርቼ አገኘሁት ባለው መሰረት ተገንብተው ከተላለፉት ጠቅላላ ቤቶች ውስጥ 9,000 ያህል ቤቶች  በእርግጥም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንደተገነቡ አረጋገጠ

ጃዋር መሀመድን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የማኅበረሰብ አንቂዎች እነዚህ ቤቶች ለተፈናቀሉትና በመሬታቸው ላይ ቤቶቹ ለተሰሩባቸው የኦሮሞ ገበሬዎች መተላለፍ አለባቸው ሲሉ ተሟገቱ። ይህ አቋምም ክልላዊ መንግስቱና የክልላዊ መንግስቱ ገዢው ፓርቲ በአፅንኦት የደገፉት ጉዳይ ነበር

ከጠንካራ ግፊትና ስለአካባቢው ገበሬዎች ችግር ከተሰጠው ትኩረት በኋላ በ2012 ዓ.ም የከተማው ምክር ቤት ውዝግብ ካስከተሉት 9,000 ቤቶች መካከል 1,000 ያህሉን ከአካባቢው ለተፈናቀሉ ገበሬዎችና ለልጆቻቸው ለማስተላለፍ ወሰነ። ኢትዮጵያ ኢንሳይት በግንቦት ወር በአካባቢው ባደረገው ማጣራት የአካባቢው ተፈናቃይ ገበሬዎች በእርግጥም የቤት ባለቤትነት ሰነድ የተሰጣቸው ሲሆን በወቅቱ 80 በመቶ ገደማ ግንባታ ላይ የደረሱት ቤቶች ተገንብተው እንደተጠናቀቁ ቁልፍ ለመረከብ እየተጠባበቁ ይገኙ ነበር።

በዚህ በኩል ደግሞ አመታትን የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ተመዝግበው ከራሳቸውና ከልጆቻቸው ጉሮሮ እያስቀሩ ቆጥበው በየካቲት 2011 ዓ.ም የየ20/80 መርሃግብር እጣ እድለኛ የሆኑ 32,653 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጉዳይ ነበር። እነዚህ በአብዛኛው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የቤት እጣ  አሸናፊዎች የቤት ኪራይ  ዋጋ በየጊዜው በሚንርባትና ለምስኪኖች ኑሮ እንደሰደድ እሳት በሚፋጅባት ዋና ከተማ ለመኖር ይቸገሩ የነበር ሲሆን ለ18 ወራት ያለምንም ውሳኔ ከቆዩ በኋላ ያሸነፏቸው ቤቶች ባለፈው አመት መስከረምና ጥቅምት 2011 ዓ.ም ተላልፎላቸዋል። ዘግይቶም  የከተማ አስተዳደሩ  በአካባቢው ከሚገኙን የኦሮሚያ ስፍራዎች ለተፈናቀሉ ገበሬዎች 22,915 በአዲስ አበባ ስድስት ክፍለ ከተሞች  ውስጥ የተገነቡ ተጨማሪ የኮንዶሚኒየም  ቤቶችንም አስተላልፏል። ይህ ቁጥር ቀደም ብለው የተጠቀሱትን የኮዬ ፈጬ አካባቢ ተፈናቃይ ገበሬዎችንም ያካትታል።

ስጋት የሸበበው አዲስ የኑሮ ምልከታ

አሁን በኮዬ ፈጬ አዲስ አየር መተንፈስ ተጀምሯል። ለረዥም ጊዜ በስፍራው የኖሩ የኦሮሞ ገበሬዎችና ከመሀል ከተማ የመጡት አዲስ ነዋሪዎች በአከባቢው ህይወትን እንደአዲስ እይተላመዱ ይገኛሉ።

‹‹ደስተኛ ነኝ። ቢያንስ ለቤተሰቤ ትቼ የማልፈው አንድ ነገር አለ። እኔን ለመርዳት ብለው ወደ ከተማ እየወጡ ያገኙትን ስራ የሚሰሩ ልጆቼ ወደፊት ጥሩ እድል እንደሚኖራቸው አምናለሁ›› በማለት አዲስ ቤት በካሳ መልክ ማግኘታቸው ስለፈጠረባቸው ስሜት ይናገራሉ አቶ ኤዶ።

የበፊቱ የቀርሳ መንደር ነዋሪ ገበሬው አቶ ባልቻ ብሩም ባለፈው አመት በአካባቢው በተሰጠቻቸው አነስተኛ መሬት ላይ የከተማ ግብርና መስራት ጀምረዋል። ‹‹እንደገና ገበሬ ሆኜ መስራት ጀምሬያለሁ። የማውቀው ነገር ፣ ያለኝም ክህሎት ግብርና ብቻ ነው። ምንም እንኳን ያሁኑ ስራዬ ከ ገቢ አኳያ ትንሽ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የቤተሰቤን ቀለብ መሸፈን ችያለሁ›› ይላሉ አቶ ባልቻ።

አቶ ባልቻ ዛሬ ላይ ምንም እንኳን ዳግም ለችግር የተጋለጡ እንደሆኑ ባይሰማቸውም ቤትና ማንነትን ከማጣቱ ከባድ ትውስታ ጋር ተዳምሮ በአዲስ የከተማ ስፍራ ውስጥ እሳቸውና መሰሎቻቸው ያላቸውን ድርሻ እና ማንነት ለመረዳት የሚያደርጉት ጥረት የዘላቂ ደህንነት ስሜታቸውን ይፈታተኑታል።

‹‹እውነት ከመሀል ከተማ ከመጡት ሰዎች ጋር ተግባብተን መኖር እንችል ይሆን? ከኛ ጋር አንድ አይነት ቋንቋ ያወራሉ? ደግሞስ በዚህ ስፍራ አዲስ የስራ እና ንግድ ትስስር ይኖረን ይሆን?›› በማለት በውስጣቸው የሚመላለሰውን ን ስጋት ያነሳሉ።

ይህ ስጋት ግን በአቶ ባልቻ ዘንድ ብቻ ያለ አይደለም። መልኩን ቀይሮም ቢሆን ከመሀል ከተማ ለመጡ የቤት አሸናፊዎችና አዲሶቹ የአካባቢው ነዋሪዎችም ውጥረትን የሚፈጥሩ ሁነቶች መከሰታቸው አልቀረም። በከተማዋ በቅርብ ጊዜያት የተፈጠረው አስጊ የፖለቲካ ስሜት ቀስ በቀስ ወደአካባቢው እየገባ በመሆኑ የወደፊቱን የኑሮ ሁኔታ በአንዳች ፍርሃት የተሸበበና ያልተረጋገጠ እንዲሆን እያደረገው ነው።

ለዚህ ማሳያው ደግሞ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ምንም እንኳን እጣ የወጣላቸው ውዝግብ በሌለባቸው የኮዬ ፈጬ ስፍራዎች ቢሆንም ቤቶቻቸውን ህጉ እንደሚለው ቢያንስ ለአምስት አመታት ያህል በይዞታቸው ስር ሳያቆዩ  ህገወጥ በሆነ መንገድ ለመሸጥ በመደራደርና በመሸጥ ላይ መጠመዳቸው ነው።

ከዙርያው ለተፈናቀሉ ገበሬዎች በኮዬ ፈጬ የተገነቡ ቅናሽ ዋጋ ያላቸው ኮንዶሚንየሞች፥ ኢትዮጵያ ኢንሳይት፥ ግንቦት 2013

ይህንንም በስፍራው ባሉ እና ግንባታቸው ባላለቁት አዲስ ቤቶች ውስጥ የሚሰራው የ35 አመቱ ኢንቲሪየር ዴኮሬተርና የሁለት ልጆች አባት አቶ ክንዴ አማረ ያረጋግጣል። ክንዴ ውልደቱ አማራ ክልል ቢሆንም በአዲስ አበባ ግን ከሁለት አስርት አመታት በላይ ፣ በኮዬ ደግሞ ላለፉት ሶስት አመታት ተከራይ ሆኖ ኖሯል። ቤቱ ባለአንድ መኝታ ክፍል ሲሆን ኪራዩ ባለፈው አመት ብቻ በእጥፍ በማደግ ሶስት ሺህ ብር ገብቷል።

በአካባቢው ከሚጨምረው የቤት ኪራይ ዋጋ በላይ በሰላም ተረጋግቶ የመኖር ዋጋም በእጥፍ ይጨመራል ፤ ለዚህም ክንዴና ሌሎች መሰሎቹ በተለያየ መንገድ ይከፍላሉ። ምንም እንኳን በግሉ በስፍራው ከሚገኙ ሰዎች ጋር በመግባባትና በአካባቢው ካሉ በርካታ የኦሮሞ ወጣቶች ጋር በጋራ ጥሩ መስራት ቢችልም ፣ በኮዬ ፈጬ የቤቶች እጣ መውጣትን ተከትሎ በመጋቢት 2011 ዓ.ም ከተከሰተው ነውጥ በኋላ ቦታው  ከባድ ድባብ እንደሚታይበት ይናገራል።

‹‹በዚህ ቦታ ምን ፣ መቼ እንደሚፈጠር አታውቅም። እዚህ አካባቢ ቤት ለመግዛትና ለመከራየት የመጡ አንዳንድ ሰዎች ተደብድበው ተመልሰዋል። አንዳንድ ጊዜ ስፍራውን ለመረበሽ የሚመጡም ወጣቶች አሉ። በአካባቢው ያሉት የቀበሌ [ወረዳ] ሃላፊዎች  ብዙ ጊዜ እንኳን ነገሮችን ሊመረምሩ ይቅርና ለቅሬታዎቹ ጭራሽ ምላሽ አይሰጡም›› በማለት ያስረዳል።

ሌሎች ነዋሪዎች ደግሞ በዚህ ሰፊ ይዞታ ውስጥ መጥፎ ስም ስላተረፉ እና ‹‹ለአዲስ መጤዎች አደገኛ›› ናቸው ስለሚሏቸው የኮዬ ፈጬ አካባቢ የጋራ መኖሪያ  ቤት ህንፃዎችና ሰፈሮች ይናገራሉ። ለምሳሌ በኮዬ ፈጬ በሁለተኛው የግንባታ ስፍራ  በመገንባትና በመጠናቀቅ ላይ በሚገኝ አንድ ሳይት አካባቢ ሰዎች ሞተው ቢገኙም  ምንም አይነት ምርመራ እንዳልተደረገ የሚያነሱም አሉ። በአካባቢው እስከ አሁን በፖለቲካ ምክንያት የተቀሰቀሰ የከፋ የብሔር ግጭት እምብዛም ባይኖርም ፣ አሁን አሁን ግን ይህ የመከሰቱ ፍራቻ አይሏል።

አሸናፊዎች እንደ ተሸናፊዎች 

የኢትዮጵያ መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ እተገብረዋለሁ ባለው የተቀናጀ የቤቶች ልማት ፕሮግራም አማካይነት ከ1997 እስከ 2002 ዓ.ም ባሉት አመታት ብቻ  400,000 ቤቶችን ገንብቶ ለማስተላለፍ አቅዶ ነበር የጀመረዉ። ነገር ግን ይህ እቅድ በአዲስ አበባ ሊገነባ ከታሰበው 175,000 ቤቶች መካከል ግማሹን ብቻ በማጠናቀቅ የእቅዱ ጊዜ ተጠያቂነትን ላዘለ ግምገማ ክፍት ሳይሆን አልፏል።

ያለፈው አመት መጨረሻ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ይፋ በተደረገውና ትግበራው ከዚህ አመት ጀምሮ እስከ 2023 ዓ.ም በሚዘልቀው የመስሪያ ቤቱ አዲስ የአስር አመታት መሪ የልማት እቅድ ላይ በተጠቀሰ ያለፉት አመታት እቅድ አፈፃፀም አሃዝ መሰረት በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከአሁን ድረስ 384,107 ቤቶች ብቻ ተገንብተው እንደተላለፉ ተጠቅሷል። ይህም ማለት ሀገሪቱ ከአስር አመት በኋላ እንኳን  በ2002 ዓ.ም የታቀደውን  እቅድ አላሳካችም ማለት ነው።  ይህ የሪፖርቱ አሃዝ ደግሞ የተላለፉ ነገር ግን ተገንብተው ያላለቁ ቤቶችንም ይጨምራል።

ከአጠቃላዩ  አሃዝ ውስጥ ደግሞ 276,502 ያህል ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተገነቡ ሲሆኑ ፣ ከዚህ ቁጥር በርካቶቹ  ቤቶች በ10/80 እና 20/80 መርሀግብሮች ውስጥ ለተካተቱና አነስተኛ እና አነስተኛ መካከለኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች የተላለፉ ናቸው። ነገር ግን ምፀትን የሚያሳይ አሰራር ሊመሰል በሚችል  ሁኔታ በ1997 ዓ.ም በአነስተኛ የቤቶች ግንባታ መርሀግብር ውስጥ ተመዝግበው የቤት እድለኛ ለመሆን  የሚጠብቁ 18,000 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች  ከ18 አመት በኋላ ዛሬም እጣፈንታቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ።

እዚህ ቁጥር  ላይ ደግሞ በ 20/80 እና 40/60 የቤቶች መርሀግብሮች ውስጥ በ2005 ዓ.ም የተመዘገቡ ሌሎች የቤት ባለቤት ለመሆን የሚያልሙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን መደመር ያስፈልጋል። እስከ አምና የነሐሴ ወር ድረስ ባለው አሃዝ መሰረት አጠቃላይ የቤት ተመዝጋቢዎች ሆነው እድለኝነታቸውን የሚጠብቁ ሰዎች ቁጥር ወደ 800,000 እንደሆነ መገመት ይቻላል። ነገር ግን ከዚህ ቁጥር ውስጥ የተወሰኑት ባለፉት አመታት በተካሄዱት የ12ተኛና 13ተኛ ዙር የእጣ ስነስርአቶች ቤቶች አግኝተው ሊሆን ይችላል።

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሀግብር በአንፃራዊነት የገንዘብ አቅምና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ታስበው በጥራትና በጊዜ ተሰርተው የሚጠናቀቁ ቤቶችን ለማስረከብ ያለመ ነበር። ሆኖም ግን እስከአሁን ድረስ ሁለት ዙር የማስተላለፍ ሂደቶች ብቻ የተካሄዱሲሆን ሁለተኛው ዙር የተካሄደው ውዝግብ በነበረበት የ13ኛው ዙር እጣ ማውጣት ጋር ከ20/80 የእጣ አሸናፊዎች ጋር በጋራ  ነው። በዚህ መርሀግብር 40 ከመቶ የቅድሚያ ክፍያ ለመክፈል ገንዘባቸውን ከቆጠቡ 160,000 ሰዎች 20,200ዎቹ (1,200 በመጀመሪያ ዙርና 19,000 በሁለተኛው ዙር) ብቻ ያለሙት ቤት ንብረት ባለቤት ሆነዋል።

በርግጥ ይህ የሚያመለክተው በኮዬ ፈጬ አካባቢ የሚገኙ ከ60,000 በላይ ቤቶች ተፎካካሪ ፍላጎቶች ካሉባቸው ስፍራዎች አንድ ማሳያ ብቻ እንደሆኑ ነው። ነገር ግን የአካባቢው ሁነት በትኩረት እንዲታይ የሚያሻው ውጥረቱን  ተከትሎ ባለፉት አመታት በህዝብ ላይ ጫናንና አስከፊ ሁኔታዎችን ፈጥሮ ከነበረውና አዲስ አበባንና በዙሪያው ያለውን የፊንፊኔ ልዩ ዞን ያካተተው ‹የተቀናጀ ማስተር ፕላን› ፈጥሮት የነበረውን የሚቃረን ኃሳብ በድጋሚ ከመቀስቀስ ጀምሮ፣ ታሪክ ላይ ተመስርተው ከተማዋ ትገባናለች በሚሉ እና ይህንንም በሚቃወም አዲስ ትርክት የሚነሱ ቡድኖች እሰከሚያደርጓቸው ሽኩቻዎች ድረስ የዘለቀ ተፅእኖ ፈጥሯል።

ከዚህም ባሻገር የአካባቢው የአጭር ጊዜ ታሪክ  በሀገሪቱ የከተማ እና ገጠር የእድገት ምጣኔ ብሎም የአቅም ግንባታ አለመጣጣም እውነታን የሚያመለክት ሲሆን ፤ ይህ ደግሞ በከተሞች የማኅበራዊ ፍትህ እጦትን ብሎም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ችግሮችን ያጎላ ነው። በርግጥም ፤ ኮዬ ፈጬ የአዲስ አበባ ችግሮች ትንሿ ማሳያ ነች። ከሁሉም በበለጠ ግን እነዚህ ሁሉ ሁነቶች በበዙ አቅጣጫዎች ችግር እየገጠማት ለምትገኘው ዋና ከተማ ሁሉን አቀፍ የሆነ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሔ አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

መጥፎ ወሰኖች መጥፎ ጎረቤቶች ይፈጥራሉ

54,000 ሄክታር ይዞታ ያላትና ይህ አሃዝ ግን ባለፉት አመታት እዲጠብ ተደርጓል የሚባልባት አዲስ አበባ በጣም ተለዋዋጭ የተፈጥሮ አቀማመጥ ያላት ዋና ከተማ ናት። ምንም እንኳን ባለፉት አመታት ሲንከባለል የቆየ ጥያቄ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል ያለው ወሰን በምን ህጋዊ አግባብ እንደተካለለ ብሎም ከቶውኑ ተካሎ እንደሆነ  ግልጽ አይደለም። ከሁለት አመታት በፊት በይፋ የፈረሰው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በዋና ከተማዋ ላይ ተፅእኖ በነበረው እና ባስተዳደረባቸው ጊዜያት ይህ ጥያቄ በሞጋች ደረጃ ባይነሳም ከአዲስ አበባም ከኦሮሚያም የአስተዳደር አካላት የድንበር ሽኩቻ እና ይገባኛል ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይነሱ ነበር።

በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ መደረስ እንዳለበት መግባባት ቢኖርም አወዛጋቢ ሁነቶችና ስህተቶች ዛሬም ይታያሉ። የሁለቱ አስተዳደሮች ወሰን ናቸው በተባሉ አካባቢዎች የቦታ ይገባኛል ኢ-መደበኛ ጥያቄዎች በይፋ ባይገለጹም መነሳታቸው ግን አልቆመም። አንዳንድ ጊዜ የሁለቱም ወገኖች በቦታ ይገባኛል ጥያቄዎች በማንሳታቸው የሚነሳ አለመስማማት ወደ ግጭት ያመራል።

በዚህም ምክንያት አሁንም ድረስ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሚተዳደረውና ከተማዋን ዙሪያ በከበባት የፊንፊኔ ልዩ ዞን ዙሪያ ወሰን አካባቢ ባሉ ቦታዎች የአዲስ አበባ ወሰንን ማብቂያና መጀመሪያን የሚለዩ ምልክቶችን ለመለየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ በምእራብ በኩል የአዲስ አበባ አስተዳደር አካል ከሆነው የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ስር ከሚገኘው የአየር ጤና መናኸሪያ አካባቢ ተነስተው እርምጃዎን ወደ ደቡብ አቅጣጫ አድርገው ቀጥታ ወደ ወለቴ መስመር ያቅኑ። ወለቴ በፊንፊኔ  ልዩ ዞን የሰበታ ከተማ አስተዳደር ስር ያለች መለስተኛ ከተማ ቀመስ አካባቢ ስትሆን የመጨረሻውን የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ አስተዳደር  ማለትም የአዲስ አበባ ከተማ ወሰን መጨረሻ ሊሆኑ ከሚገባቸው አካባቢዎች ቀጥላ ትገኛለች። ወለቴ ሳይገባም በከተማ መስተደድሩ የተሰሩ የጋራ መኖሪያ ቤት ህንፃዎች ይገኛሉ። ሆኖም ወለቴ ከመደረሱ በፊት ወይንም ወለቴን አልፈው ወደ ከተማው ቢዘልቁ ወደ አዲስ አበባ ወሰን የሚቀበልም ሆነ መውጣትዎን የሚገልፅ ሰሌዳ ተለጥፎ ማየት ወይም በግልፅ የተቀመጠ መስመር ማግኘት አዳጋች ነው።

በሌላ በኩል ወለቴ ደርሰው ጉዞ እንደጀመሩ ብዙም ሳይርቁ በኦሮሚያ ፊንፊኔ ልዩ ዞን ወደምትገኘው  ሰበታ ከተማ አስተዳደር  ሲደርሱ ‹‹ እንኳን ደህና መጣችሁ››  የሚል ሰሌዳ ይቀበልዎታል። ይህ ግን የሚሆነው በሚገባ ማስተዋል ከቻሉ ብቻ ነው። ይህ የከተማ  አስተዳደሩ ሰሌዳ በፈራረሰ ቤት አጠገብ በዛፍ ተሸፍኖ የሚገኝ ፣ ያረጀና ለመለየት የሚያስቸግር ነው። በወለቴ ትንሽ የመቆየት አድል ካገኙ አካባቢው የአዲስ አበባ ወሰን ውስጥ ያለ እስኪመስልዎት ድረስ የተሳሰረ እንደሆነ ይረዳሉ።

ታዲያ በቅርብ አመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተመዘገቡ የመሬት ይዞታዎች ጭምር በፊንፊኔ ልዩ ዞን ውስጥ ባሉ የከተማ አስተዳደሮች ተቃውሞ እና የይገባኛል ውዝግብ እንደተነሳባቸው ማንሳት ያስፈልጋል። ለምሳሌ በቅርቡ በየካ ክፍለ ከተማና በኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል ባለ አንድ አካባቢ የተደረገ የወሰን ምልክት ቦታውን  የክልሉ መንግስት አድርጎ ማሳየቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በዚህ አመት አንድ የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ ቁልፍ ፖለቲከኛ አንዷ የሆኑት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ግልጽ ያልሆነ ምላሽ ነበር የሰጡት። መግለጫውን የተከታተሉ ጋዜጠኞች እንደሚያስታውሱት ጉዳዩ ተነስቶ ኦሮሚያ ወደ ዋና ከተማዋ ገፍታ እየገባች ይሆን የሚል አንድምታ ያለው ጥያቄ ተሰንዝሮ ነበር። የከንቲባዋ  ምላሽም ‹እንደውም በተቃራኒው አዲስ አበባ ነች ወደ ኦሮሚያ ገፍታ እየገባች ያለችው› የሚል እንደነበር ተሰምቷል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ኢንሳይት ባለፈው ሚያዝያ ወር ያናገራቸው አንድ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ከፍተኛ አማካሪ ፣ ክልሉ ወደ አዲስ አበባ ገፍቶ ገብቷል የሚለው ነገር መሰረተ ቢስ ነው፤ ከዛ ይልቅ አዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ገፍታ መግባቷ እንዳይቀጥል ነው ሊያሳስብ የሚገባው ሲሉ ይሞግታሉ።

‹‹በልማት ሰበብ ዋና ከተማዋ ወደ ኦሮሚያ መስፋፋቷን ለመግታት ብዙ ጥረት ተደርጓል። ነገር ግን በፊንፊኔ ዙሪያ ያሉ የመሬት ወረራ ጉዳዮች አሁንም ቢሆን አሳሳቢ ጉዳዮች ተደርገው ሊታዩ ይገባል። የዚህ ምክንያት ደግሞ በመንግስት ሃላፊነት ውስጥ የሚሰሩ ሆነው ይህንን ጉዳይ የሚፈጽሙ ሰዎች ስላሉ ነው›› ብለዋል አማካሪው።

የኮዬ ፈጬን ጉዳይም ስንመለከት ይህን ጥርት ያላለ የወሰን ጉዳይ በድጋሚ በሌላ መልኩ ማንሳት ጠቃሚ ነው። 9,000 ቤቶች ኦሮሚያ ውስጥ ተገንብተዋል የሚለው ውሳኔ አዲስ አበባ የት ጋር እንደምታበቃና ኦሮሚያ የት እንደሚጀምር አስተዳደራዊ ስምምነት ወይም የሚታወቅ መስመር  እንዳለ ምልክት ሊሰጥ ይችላል።

ሆኖም ግን የወሰን መለየት ጉዳይ በሰፊው ሲታይ በከተማ እቅድና ልማት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ አለው።

እዚህ ላይ በድጋሚ ተመልሰን የኮዬ ፈጬን ጉዳይ እንውሰድ። ኢትዮጵያ ኢንሳይት ለዚህ ፅሁፍ ጥንቅር በዋቢነት የተመለከተው ከ2009 እስከ 2019 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ብቻን የተመለከተው ማስተር ፕላንን የሚመራው የአወቃቀር እቅድ ሪፖርት እንደሚጠቅሰው የከተማ አስተዳደሩ እቅድ ‹ኮዬ ፈጬን› ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ ሊሰፍርበት የሚችል መዳረሻ አድርጎ የከተማ ነዋሪዎችን ወደዛ መውሰድ ነው። መስተዳድሩ  በእቅዱ ከአቃቂ ቃሊቲ ደቡብ ምስራቅ የሚገኘው ይህ  ‹የኮዬ ፈጬ› አካባቢን የአዲስ አበባ ሶስተኛ እርከን የከተማ ማዕከል አድርጎ አካቶታል።

ይሁን እንጂ ይህ የከተማዋ ማስተር ፕላን እቅድ ከዚህ  በፊት  1.1 ሚሊዮን ሄክታር [የአዲስ አበባ ይዞታ የሆነውን 54,000 ሄክታር እና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ደግሞ 1.04 ሚሊዮን ሄክታር ጋር በማቀናጀት ስራ ላይ ሊውል  ታስቦ የነበረው ማስተር ፕላን] በመሸፈን ሊተገበር የታሰበውና ሰፊ የህዝብ ተቃውሞ በማስተናገዱ የተሰረዘው የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተለዋጭ ነው። በዚህም የከተማ መስተዳድሩ በራሱ ወሰን የተካለሉ ቦታዎችን ፣ ኮዬ ፈጬን ጨምሮ ማለት ነው፤  ለማልማት ያለመ ነው ያለውን እቅድ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል። ሆኖም ይህ የኮዬ ፈጬ አካባቢ እስካሁን እንዳየነው እንዴት የውዝግብ ምንጭ ሆነ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሁለቱ አስተዳደሮች ህጋዊ ወሰን በሀቀኝነት እና ስርአት ባለው መልኩ አለመወሰኑ አዳጋች ያደረገው ይመስላል።

‹‹የተቀናጀ የማስተር ፕላኑ [በተቃውሞ] ከተሰረዘ በኋላ አሁን በስራ ላይ ያለው የአዲስ አበባ ገለልተኛ የከተማዋ እቅድ የልማት  ቦታዎችን በሚታወቀው ወሰን ስር ገድቦታል። አሁን በአቃቂ ቃሊቲ አካባቢ ውዝግብ ካለባቸው ስፍራዎች ውስጥ የቤቶች ልማት እቅድ ከግምት ያስገባው ከበፊት ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ ስር ይተዳደሩ የነበሩ የገጠር ቀበሌዎችን [ብቻ] እንደሆነ ነው የምረዳው›› ይላሉ ኢትዮጵያ ኢንሳይት ያናገራቸው አንድ በአዲስ አበባ ፕላን ኮሚሽን ውስጥ እስከቅርብ ጊዜ በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ የሰሩ እና የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን በመቅረፅ ላይ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው የከተማ እቅድ ባለሙያ።

‹‹የሁለቱም ወገን አስተዳደሮች እና የመንግስት ሃላፊዎች የሚያውቁት የወሰን ማካለል ላይ የተደረገና ስምምነት ይኖር ወይም አይኖር እንደሆነ ግልፅ መደረግ ነበረበት። በነበሩት ሂደቶች ከተስተዋሉ ትልቅ ችግሮች አንዱ በልማት እቅድና ትግበራ ላይ መግባባትን ያመጣሉ ተብሎ ታስቦ የሚካሄዱ ሁሉም ውይይቶች ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖራቸውና አቋም እንዲያዝባቸው መደረጉ ነው። የፖለቲካ ፍላጎትን ለማስጠበቅ ብቻ የሚደረጉ እንዲህ ያሉ ውይይቶች ደግሞ ማንኛውም አካታችና ሰፊ የልማት ጥረቶችና እቅዶች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ከማሳረፍ የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም›› ሲሉ  እኝህ የከተማ እቅድ ባለሙያ  ቅሬታቸውን አስታውሰው ያስረዳሉ።

የቤቶች ልማትና ግንባታን በተመለከተ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በየስድስት ወሩ የሚያካሂደው የተቀናጀ የዘርፍ መስሪያ ቤቶችና ሃላፊዎች ጉባዔ አለ። በዚህ ጉባኤ ላይ የከተማና የክልል አስተዳደሮች እንዲሁም የፌደራል ሚኒስትሮች ይገኛሉ።

የሰበታ ከተማ የሚጀምርበትን ቦታ የሚያሳይ ቦርድ፥ ያሬድ ጸጋዬ፥ ግንቦት 2013

እንደ የሚኒስቴር መስሪያ  ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ስለሺ ዘገየ ገለፃ ምንም እንኳን ሚኒስቴር  መስሪያ ቤቱ የወሰን ጉዳዮችን በመወሰንና በማካለል ጉዳይ ምንም ስልጣን ባይኖረውም በዚህ የተቀናጀ ጉባዔ ላይ ግን የቤቶች ልማት እቅዶችና ሌሎች እርስ በእርስ የሚገናኙ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ይወያያል፣እቅዶችን ያናብባል ፣ ይገመግማል እንዲሁም ይከታተላል። ሆኖም ግን እነዚህ ውይይቶች ውጤታማ እንዳይሆኑ የሚያደርጉ ነገሮች ጥረቶቹን በአሉታዊ መልኩ ሲሸፍኑ ይታያሉ በማለት ያነሳሉ አቶ ስለሺ።

‹‹እቅዶች መተግበር ከጀመሩ በኋላ ችግሮች ከሚፈጠሩባቸው መንስዔዎች  አንዱ የከንቲባዎችና የከፍተኛ አስተዳደሮች መቀያየርና የሂደቱ አካል በመሆን ለአንገብጋቢ ጉዳዮች መፍትሔ ለመፈለግ የሚመጡ ሰራተኞች በስራ መደባቸው ላይ ብዙ ጊዜ አለመቆየታቸው ነው›› ይላሉ አቶ ስለሺ።

ከፍተኛ የከተማ እቅድ አውጪው የከተማ እድገት ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ኦሮሚያና አዲስ አበባን የበለጠ ሲያዋህዱ የጋራ ልማት አስፈላጊነት እንደሚጨምር ያምናሉ። ሰዎች በተለያዩ ስፍራዎች ለመኖርና ለመስራት  በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ነገሮችን ከወሰንና ከውዝግቡ ባሻገር የመመልከት አስፈላጊነት ይመጣል።

‹‹ከፖለቲካ ተፅእኖ ባሻገር የጋራ እድገት ለማየት በሚያስችል ሁኔታ እንዲሁም አሁን አለምአቀፍ ወረርሽኝ የሚመስለውን የሰዎች መፈናቀልና የሚያስከትለውን ትልቅ ማህበረሰባዊ ቀውስ ለመቋቋም በሚረዱ መፍትሔዎች ላይ መወያየት ከበፊቱ በበለጠ የከተሞች እድገትና የሰዎች እንቅስቃሴ በጨመረበት በአሁኑ ጊዜ እጅግ አስቸኳይ ጉዳይ ነው ›› በማለት እቅድ አውጪው ይናገራሉ።

ነገር ግን እቅድ አውጪው ምንም እንኳን ለጋራ የከተማ ልማት ቀና አመለካከት ቢኖራቸውም አሁን ያለው የከተማይቱ  የእንቅስቃሴ ሚዛን እጅግ የተዛባ ይመስላል። ከአዲስ አበባም ሆነ ከሌሎች ክልሎች ወደ እነዚህ የኦሮሚያ ዙሪያ ከተማዎች በተለይም ወደ ፊንፊኔ ልዩ ዞን  ከፍተኛ ፍልሰት አለ።  ይህ ደግሞ እነዚህ ከተሞች ላይ ከባድ ጫናን ያመጣ ነው።

ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ሰበታ ፣ ሱሉልታና ቡራዩ  ያሉ የልዩ ዞኑ ከተማዎች የዚህ ማሳያ ናቸው። በቅርብ ጊዜ ሰዎች ህጋዊ መረጃ ሳይኖራቸው የተንሰራፋውን ህገወጥ የመሬት ሽያጭና የሙስና መስመሮች በመጠቀም መሬት ለመግዛት ጎርፈዋል። በእርግጥ ከእነዚህ ሰዎች በርካቶቹ በአዲስ አበባ ሰማይ የነካውን የቤት ኪራይ ዋጋ ሸሸተው የመጡ ናቸው።

አልፎ አልፎ በነዚህ ህገወጥ ቤቶች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች ግን አወዛጋቢ ሲሆኑ ይታያሉ። በየካቲት 2011 የለገጣፎ-ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ‹‹ህገወጥ›› ያላቸው ቤቶችን ድንገት ማፍረሱ  ባስከተለው ቁጣ ምክንያት ከበርካታ ያልተነገሩ ሁነቶች መካከል በአንፃሩ ከፍተኛ መጥፎ ስም ያተረፈ አንድ ሁነት ነበር። ከተማ አስተዳደሩ ለአረንጓዴ ልማት በሚል በስፍራው ላይ ለ15 አመታት የኖሩ ሰዎች ድንገት እንዲፈናቀሉ አድርጓል። የከተማ አስተዳደሩ ሰዎቹ ለረዥም አመታት በአካባቢው መኖራቸውን ፣ የሚከፍሉባቸው መሰረተ ልማቶች እንዲገባላቸው መደረጉን፣ ለከተማዋ እድገት እኩል መልፋታቸውን  እውቅና አልሰጠም። ይልቁኑም ለነዋሪዎች ካሳ ከመስጠት ይልቅ እነሱን አፈናቅሎ የመዝናኛ ፓርክ መስራትን መረጠ።

ምርጫ እና ድንበር

በባለፈው ሰኔ ወር በተካሄደ አጠቃላይ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤቶች ቀጣዮቹን አምስት አመታት የሚወከሉ እንደራሴዎችን መርጠዋል። በአዲስ አበባም 23 መቀመጫዎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) እንዲሁም 138 የከተማዋ ምክር ቤት መቀመጫዎች ላይ ምርጫ ተካሂዷል። የገዢው ብልፅግና ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ የ10 ምርጫ ክልሎችን በማሸነፋ ሁሉንም የአዲስ አበባ ምክርቤት  መቀመጫዎች እንዳሸነፈ በዚህ ወር የብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ ገልጿል።

በቅድመ ምርጫ ወቅት በነበሩ የቅስቀሳ አጀንዳዎች አዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የትኩረት ማረፊያ ሆና ቆይታለች።  የከተማይቱ ወሰን ጉዳይ ደግሞ አንድ ነጥብ ነበር። በአዲስ አበባ በስፋት ከሚንቀሳቀሱና የአዲስ አበባን ጉዳይ  በዚህ ምርጫ ካነሱ  ፓርቲዎች አንዱ ህብረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅነው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ነው። ፓርቲው ባለፈው ሚያዝያ ወር 138 እቅዶችን በያዘውና ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ከምርጫ በፊት ማህበራዊ ውል የገባበትን ሰነድ ይፋ አድርጎ ነበር። እንደ እቅዶቹ ከሆነ ኢዜማ የአዲስ አበባና የኦሮሚያን የአስተዳደና የወሰን መስመሮች በህግ ለመለየት አቅዶ ተንቀሳቅሷል። የፓርቲው ሰነድ ‹‹የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ጋር ያለው የወሰን ይገባኛል ጥያቄን የሚያስነሳው ውዝግብ ለከተማዋ  ከፍተኛ የደህንነት ችግር ፈጥሯል››  ይላል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያውና በኢዜማ የፓሊሲ ጉዳዮች አስተባባሪ የሆነው አቶ አማንይሁን ረዳ የወሰኑን ጉዳይ እልባት መስጠት ስኬታማ የከተማ አስተዳደርን ለማምጣት ጠቃሚ እርምጃ እንደሆነ ያምናል።

‹‹የከተማዋ ወሰን በትክክል መታወቅና መሰመር አለበት። ለነዋሪዎች ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ ፣ ሃላፊነት የሚሰማውና ፣ የገባውን ቃል የሚተገብር የከተማ አስተዳደርን የመፍጠር ሂደት ከዚህ  ይጀምራል ›› ሲል ይሞግታል ከምርጫው በፊት ከኢትዮጵያ  ኢንሳይት ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረገው አማን ይሁን።

አዲስ አበባ ላይ ያተኮረ በአብዛኛው በአማራ ብሔር ፖለቲከኞችና ልሂቃን የተሞላ ተደርጎ የሚታሰበውና በቅርቡ በምርጫው ላይ እንዲሳተፍ በተፈቀደለት የቀድሞው ጋዜጠኛና አሁን እስረኛ ፖለቲከኛ በሆነው እስክንድር ነጋ የሚመራው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲም በአዲስ አበባ ካሸነፈ ከተማዋን ራስ-ገዝ ለማድረግ ተስፋ ሰጥቶ ነበር።

ፓርቲው የኦሮሞ የበላይነት ለከተማዋ ስጋት ነው በማለት ይሞግታል። እንዲሁም ኦሮሚያና የኦሮሞ ተፅእኖን ወደ አዲስ አበባ አስፋፍተዋል ሲል የገዢው ፓርቲ ሃላፊዎችንና ምሁራንን ይወነጅላል። ፓርቲው በምርጫው ካሸነፈም የአዲስ አበባ ታሪካዊና ህጋዊ መሬት ነው ብሎ የሚሞግተውን 122,000 ሄክታር መሬት ለማስመለስ ቃል ገብቶም ነበር።

በቅርቡ የተወሰነ እውቅና እያገኘ የመጣውና ለሃገሪቱ ዋልታ ረገጥ የፖለቲካ ስርአት አዲስ ፓርቲ የሆነው ነፃነትና እኩልነት ፓርቲም የከባድ ግጭቶች መንስዔዎች ናቸው በማለት ግልጽ ያልሆኑ ወሰኖችን ይቃወማል። በባለፈው ስርአት ለተጎዱ የኦሮሞ ገበሬዎች የሚያመዘን አቋም ይዟል።

‹‹ባለፉት በርካታ አመታት በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ገበሬዎች ከመኖሪያ ቀዬያቸው፣ ከንብረታቸውና ከሞቀ ቤታቸው ‹በልማት› ስም እንዲፈናቀሉ ፣ ቤተሰባቸውና ማህበራዊ  ኑሯቸው እንዲናጋ ሲደረግ ቆይቷል›› ሲል የፓርቲው ማኒፌስቶ አንድ ክፍል ያትታል። ‹‹ድሀ ገበሬዎች መሬታቸው ‹በነፃ›› ተወስዶ ፖለቲከኞችና የእነሱ ተለጣፊ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች  እንዲበለፅጉበት ተደርጓል። ይህ አሰራር ከአዲስ አበባ አልፎ የሀገራችን ፖለቲካ ከፍተኛ የግጭት መነሻ ሆኗል›› በማለት አፅንኦት ሰጥቶ ሞግቷል።

ምንም እንኳን ጉዳዩን ለመፍታት ሁሉም የየራሱን የመፍትሄ ሃሳብ ቢጠቁምም የወሰን እና ድንበር ይገባኛል ጥያቄዎቹ ግን በዚህ ይቃለላሉ የሚል ምንም አይነት መተማመኛ ካለመኖሩ ባሻገር  ጉዳዩን እልባት ለመስጠት የሚደረጉ ጥረቶች ያለጥርጥር ውስብስብ ይመስላሉ።

በአቃቂ የሚገኘው የኮዬ ፈጬ አከባቢ የካርታ ምስል፥ Google earth

ለምሳሌ በ2011 ዓ.ም የተፈጠረውን የኮዬ ፈጬን ክስተት ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን እንዲፈታ የተመሰረተውን ኮሚቴ እንውሰድ። በአንዳንድ የህግ ምሁራንና የፖለቲካ ልሂቃን ምልከታ የጉዳዩ አያያዝ ፖለቲካዊ ፍላጎት አለው የሚል ጥርጣሬ አምጥቷል። እንዲሁም ጉዳዩ በ2010 ዓ.ም በተቋቋመው የአስተዳደር  ወሰንና የማንነት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚሽን በብሔራዊ ደረጃ መታየት ነበረበት ብለው በሚሞግቱ የህግ ባለሞያዎች ዘንድ የህግ ጥያቄዎችን አስነስቷል። ስምንት አባላትን የያዘው ኮሚቴ የገዢው ፓርቲ አባላትን በመያዙ ምክንያት ገለልተኝነት ይጎለዋል ሲሉ  ብዙ  ባለሞያዎች ሲሞግቱም ተደምጠዋል። ከውሳኔው በኋላ እንኳን የ9000 ቤቶቹ የአስተዳደር ሂደት ላይ ምንም አይነት ገለፃ በሌለው የኮሚቴው ውሳኔ ላይ ጥያቄዎችን ያነሱ የከተማ አስተዳደሩ ሃላፊዎች ነበሩ።

ሆኖም ግን አገሪቱን የሚያስጨንቁ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮችን እንዲያጣራና ችግሮችን እንዲፈታ የተቋቋመው ኮሚሽን እራሱ ለብዙ ጥያቄዎች እምብዛም መፍትሔ ሲሰጥ አልተስተዋለም

የአዲስ አበባ ከተማ መተዳደሪያ  ቻርተር (በ1995 ዓ.ም ስለከተማዋ ወሰን የወጣውን ህግ ያላሻሻለው በ2010 ዓ.ም በትንሹ የተሻሻለው ህግ)  ‹‹አሁን ያለው እንደተጠበቀ ሆኖ ፣ የከተማው ወሰን የከተማው አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚያደርገው ስምምነት  ወይም በፌደራል መንግስት ይወሰናል ፤ የወሰን ምልክትም ይደረግበታል ›› ሲል ያትታል።

ተንታኞች አሁንም በቀጠለው የአንድ ፓርቲ የበላይነት ያለበት መንግስት የሚወስነው ውሳኔ  ብዙ ሁኔታዎች ላይ ተፅእኖ ይፈጥራል ብለው ይሰጋሉ። ነገር ግን የኢትዮጵያ መዲና የሆነችውን አወዛጋቢ ከተማ ወሰን መለየት ላይ ስንመጣ ለብቻ ወሳኝ የመጨረሻ ውሳኔ ማሳለፍ ውሳኔውን ለማስከበር ከበድ ያለ እርምጃ የሚከተለው ይመስላል ምክንያቱም አለመግባባት መከሰቱ ስለማይቀር።

በምትኩ አሸናፊው ፓርቲ ግልጽ ያልሆኑ ወሰኖች መጥፎ ሁኔታዎች እንደሚፈጥሩ ማስተዋል አለበት። የነዚህ ስህተቶች ገፈት ቀማሽ ደግሞ የእህል ውሃ ነገር ፈተና የሆነባቸው ምስኪን ዜጎች እንደሆኑና ህይወታቸው  ደግሞ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ በተግባር ከታዩባቸው እንደ ኮዬ ፈጬ ካሉ ቦታዎች መማርም አለበት።

Query or correction? Email us

Follow Ethiopia Insight
ይህ ጽሁፍ ምርጫ 2013ን በሚመለከት ዘለግ ያሉ ጽሁፎችን ከመላው ኢትዮጵያ በተከታታይ የምናቀርብበት የ “Ethiopia Insight Election Project (EIEP)” ክፍል ነው።

ዋና ምስል: በኮዬ ፈጬ ኮንዶሚንየም ፕሮጀክት ምክንያት በ 2006 ከ ቀርሳ መንደር የተፈናቅሉት ገበሬ አቶ ባልቻ ብሩ፥ ያሬድ ጸጋዬ፥ ሚያዝያ 2013።

Join our Telegram channel

Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished.

We need your support to analyze news from across Ethiopia
Please help fund Ethiopia Insight’s coverage
Become a patron at Patreon!

About the author

Yared Tsegaye

Yared is a freelance journalist based in Addis Ababa. He is a contributor to Ethiopia Insight and various other outlets.

  • The inconvertible fact is that all these messes were created by the now defunct EPRDF, and most of the current issues started on Meles Zenawe’s watch. Who drafted the current land policy? Who sold the land of farmers at the rate you quoted to “developers” that built the shabby and low grade condos? Were not most of the condominiums built by EPRDF itself in 5he beginning? Where is the money contributed by the hard working people pursuing their dreams of one day owning a small place to settle and live a modicum of decent life.

Leave a Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.