In-depth

በኢትዮጵያ የፈረጠመ የኃይል መዳፍ ውስጥ የቀጠናው የትብብር ኮረንቲ ያንጸባርቃል

የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያን ከመለወጥ አልፎ ለጎረቤቶቿም የሀብት ማማ ነው

ዳሴ ግድቡን አስመልክቶ የከረሩ ሙግቶች ሊካሄዱ የሚችሉባቸው በርካታ አማራጮች ይኖራሉ፤ ‹ጉልህ ጉዳት ምንድን ነው› ከሚለው ሙግት አንስቶ ‹አወያዮች ወይስ እጅ ጠምዛዦች› እስከሚለው ውንጀላ ድረስ፣ ወይም ደግሞ በገራገሩ ግን የዋህነት በሚስተዋልበቱ የናይል ተፋሰስ ሀገራትን የ“ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት” (Cooperative Framework Agreement ወይም Undugu) መንፈሱን አስጠብቆ ውይይቱን የማስቀጠል ፍላጎት፣ ከዚያም አልፎ ‹‹በ2015 የተወሰነውን ‹ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ› ልንከተል ይገባል›› እስከሚለው ነባራዊ ሁኔታን  ያገናዘበ ውትወታ ድረስ፤  እነዚህ ሁሉ ለጽሁፍ የሚመቹ አማራጮች ናቸው፡፡

የጉዳይ ምርጫዎቹ ይብዙ እንጂ፣ በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ የተራዘመ ቀውስ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ይህ ጽሁፍ በሚከተሉት ሶስት ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፤

  • የሕዳሴ ግድቡ ኢትዮጵያን በወንዝ ለተጋመደቻቸው ወገኖቿ የክፉ ቀን መከታ እንደሚያደርጋት ማስረዳት
  • በድርቅና ዝናብ እጥረት ወቅት ለስምምነት እንቅፋት በሆኑት የሕዳሴ ግድቡ የውሃ አለቃቀቅ አኃዞች ዙሪያ
  • ከሁሉም በላይ ደግሞ ለቀጠናው ፖለቲካ ጉልሁ ርዕሰ ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ በአስገዳጅ የውል ስምምነት እና በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ለምን እንደማትስማማ፡፡

በተለይ በመጨረሻው ክፍል ላይ፣ በሙግት አፈታት መንገዶቹ ላይ ትኩረቴን በማድረግ ኢትዮጵያ፣ ይህን የሕዝቧ ኩራት የሆነውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ዕጣ ፋንታ፣ ጎልባታ እንዳሻው ለሚዳኝበት የዓለም ስሪት ለመተው እምቢተኛነቷ ተገቢ መሆኑን አስረዳለሁ፡፡

ከዚህ አስቀድሜ ግን የዓባይን ደመ ቁጡዎች ሊያስከፋ የሚችልን ጉዳይ ላንሳ፡፡

የ ‹‹በረሀ ሲሳይ›› ወይስ የክፉ ቀን መከታ ምርጫችን

ፍርጥርጥ አድርጌ ልናገርና፤ የሕዳሴ ግድቡ ውሃ፣ ይህ እጅግ ብዙ ውሀ፣ ከኛ ይበልጥ ለሱዳንና ለግብጽ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሀቅ ግን ስለ ግድቡ ውሀ ይናገር እንጂ ስለ ዓባይ ወንዝ የውሀ ድርሻ ክፍፍል ምንም አይልም፡፡ የአባይ ወንዝ ወደ ሱዳን ድንበር ከመሻገሩ በፊት የገነባነው ይህ ታላቅ ግድብ በአማካይ በዓመት ከሚፈሰው የወንዙ የውሀ መጠን እጥፉን አካባቢ የመያዝ አቅም ያለው መሆኑ፣ የሕዳሴ ግድቡን እንዴት በጋራ ትብብር እንጠቀም የሚለውን ቁልፍ ጉዳይ ያደርገዋል፡፡

የሕዳሴ ግድባችን ከባህር ጠለል በላይ 640 ሜትር ከፍታ ላይ 74 ቢሊየን ሜትር ኩብ ውሀ የማጠራቀም አቅም አለው፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ የሙሊት ግባችን በ625 ሜትር ከፍታ 49 ቢሊየን ሜትር ኩብ መከተር ሲሆን፤ ይሄም በየትኛውም ዓመት የበጋ ወራት መገባደጃ  ወይም የክረምት ወራት መባቻ የሚፈጸም ነው፡፡ የሀገሬ ሰው እንደሚለው ዳመናው ካልዋሸ፣ ቢሻን ዋቃም ከፈቀደ፣ እናም ሁሉም በታቀደለት መልኩ ከተከናወነ፣ ለሁሉም ደህንነት እንደሚበጅ ሆኖ የመጀመሪያው ሙሊት የዛሬ አምስት ዓመት እ.ኤ.አ. በ2025 ዓ.ም. ይገባደዳል፡፡

በዚያው ዓመት ክረምት ግድቡ ጢም ብሎ ይሞላል፣ ለጥቆም ኢትዮጵያ በመረጠችው ዓመታዊ መርሀ ግብር መሠረት ቢያንስ 25 ቢሊየን ሜትር ኩብ ውሃ እየተለቀቀ እስከ ጠለል 625 ሜትር ተመልሶ ይጎድላል፡፡ ይህም ኃይል ከማመንጨት ፍሰቱ በተጨማሪ ለክረምት ጎርፍ ውሃ ቦታ ለመልቀቅ የሚከናወን ተግባር ሲሆን በዚህ የውሃ ማስተንፈስ ሂደትም ኤሌክትሪክ ከማመንጨት ሥራ ጋር በተጓዳኝ የሱዳን እና የግብጽን ተገቢ ሊባል የሚችል የውሃ ፍላጎትም ያሟላል፡፡

ከግድቡ አስከ ሱዳን ድንበር ባለው የ20 ኪሎ ሜትር ርቀት እዚህ ግባ የሚባል በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት የለም፡፡ ኢትዮጵያ ቀድሞውንም ቢያንስ ለራስዋ ግድቡን ለመስኖ ልማት የመጠቀም አላማ አልነበራትም፡፡ ቢሆንም ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚውለውን የተስተካከለ የውሃ ፍሰት በግድባችንና በሜዲትራንያን ባሕር መካከል የሚገኝ ሁሉ ለመስኖ ሊጠቀምበት እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ሱዳን በርከት ያሉ ግድቦችና በመስኖ የሚለሙ መሬቶች ያሏት እንደመሆኑ ከዚህ በሰፊው ተጠቃሚ ትሆናለች፡፡ ግብጽም እንዲሁ፣ የአባይ ወንዝ በተንጣለለበት የ1,200 ኪሎ ሜትር መስመር የሚገኙትን የአስዋን ግድብና የናስር ሐይቅ እንዲሁም ሰባት ሌሎች ውሃ ማቆሪያ ግድቦችዋንና በአጠቃላይ ርዝማኔያቸው 13,000 ኪሎ ሜትር የሚሆኑ ቦዮችዋን ይዛ እንደ ሱዳን ሁሉ ከዚህ ፍሰት ተጠቃሚ መሆን ትችላለች፡፡

ሁለቱ ሀገራት የአባይ ወንዝን ለመጓጓዣ፣ ለኤሌክትሪክ ሃይል፣ ከዚህም ይበልጥ ወሳኝ ለሆኑ እንደ መጠጥ ውሃ ዓይነት የከተማ አገልግሎትም ይጠቀሙታል፡፡ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በጥቁር አባይ ወንዝ ዳርቻ የሰፈሩን ሁሉ በክረምት ከገደብ በላይ በሆነ ጎርፍ እንዳይጥለቀለቁና ከሚፈለገው በላይ የሆነ የአፈር ደለል እንዳያውካቸውም ይታደጋቸዋል፡፡ የግድቡ አጠቃቀም ዓመት ሙሉ ወጥ የሆነ የውሃ ፍሰት እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ፣ የአስዋን ግድብ በረሀማ የአየር ንብረት በማይስተዋልበት አካባቢ የሚገኝ እንደመሆኑና ከሚከትረው የውሀ መጠን አንጻር በንጽጽር የገጽ ስፋቱ መለስተኛ ምጣኔ ስለሚኖረው (lower surface area per volume) ጉልህ መጠን ያለው ውሀን ከትነት በማዳን ለጎረቤት ጥቅም ያበረክታል፡፡ የአፈር ደለል ማቀቢያ መጠናቸው የቱንም ያህል ግዙፍ ቢሆን፣ መቼም አንድ ቀን ከኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ተሸርሽሮ የሚሄደው ደለል የሱዳንና የግብጽን ግድቦች መሙላቱ አይቀሬ ነው፡፡ የሕዳሴ ግድብ መኖር ይህን ደለል ይከላከላል፡፡ ለአብነትም የአስዋን ግድብ በ2150 ዓ.ም በደለል ይሞላ የነበረ ሲሆን፣ የሕዳሴ ግድብ ይህን ክስተት በ60 ዓመታት ያዘገየዋል፡፡

እንዲያም ሆኖ ለተፈጥሮ ጥበቃ የቆመ ሁሉ የሚመሰክረው ሐቅ አለ፣ የሕዳሴን ያክል ግዙፍ ግድብ እንኳን እንደ ምስራቅ አባይ ባለ የተራቆተ ተፋሰስ ይቅርና በማንኛውም ጅረታዊ ስርዓተ ምህዳር (riverine ecosystem) ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው፡፡ ደለልን የመከላከልን ያህል ቀላል ጉዳይ እንኳን የታችኛውን ተፋሰስ ረግረጋማ ቦታዎች በመጠኑም ቢሆን ማራቆቱ አይቀርም፡፡ የደለሉ ሸክም የተቀነሰለት የወንዙ ውሃ ይበልጡን ጉልበታማ ይሆንና ስሱን የጥንታዊ ወንዝ አጥንት ስርዓተ ምህዳር ሊግጠውና ሊቦረቡረው ይቀለዋል፡፡ ‹የሱዳን ገበሬዎች የግድቡን ወጥነት ያለው የውሀ ፍሰት ቢጠቀሙ ወይስ ጎርፉ ሲሸሽ ሞፈራቸውን ይዘው በመመለስ የራሰውን ሸለቆ በማረስ ይበልጥ ይጠቀማሉ› የሚለውም ክርክር ገና አልተቋጨም፡፡

አንድ ጉዳይ ግን ለጎረቤቶቻችን ያለው በጎነት አያከራክርም፡፡ የሕዳሴ ግድቡ ከሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች ሁሉ ለጎረቤቶቻችን የላቀው፣ በ‹ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንስፕልስ› መሰረት ግድቡ በሚያመነጨው የሐይል አቅርቦት ውል ላይ ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚኖራቸው የቅድሚያ ተጠቃሚነት መብት ነው፡፡ የመርህ ተኮር ስምምነቱ የሶስት አቻዎች ስምምነት እንደመሆኑ የቅድሚያ ተጠቃሚነት መብቱ የኢትዮጵያን ልዩ ጥቅም እስከመግፋት ሊያደርስም ይችላል፡፡ ይህንን ስምምነት በመመርኮዝ ግብጽና ሱዳን፣ ለምሳሌ አወዛጋቢ በሆነው የአካባቢያዊ ፍሰት መጠን (environmental flow) ምትክ የሕዳሴ ግድቡ ወጥ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍጆታ እንዲኖረው ሊያስገድዱን ይችላሉ፡፡

በእርግጥ ከግድቦች የሚለቀቅ አካባቢያዊ ፍሰት ዓለም አቀፍ የስሌት ፕሮቶኮል ተከትሎ የሚዘጋጅ ቀጥር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ግብጽ ባቀረበችው በሰከንድ 500 ሜትር ኩብ ፍሰት ይኑር የሚለው ጥያቄና ኢትዮጵያ ልታሟላው ዝግጁ በሆነችበት በሰከንድ 200 ሜትር ኩብ መካከል ያለው ልዩነት በሕዳሴ ግድቡ አቅራቢያ በ90 ዓመት መረጃ ከተጠናከረው የአባይ ከፍተኛ እና ዝቅተኛ የበጋ ፍሰት ግምት ጋር መመሳሰሉ፣ ጉዳዩ የእልህ ሙግት ወይስ የሳይንስ ክርክር ነው ያስብላል፡፡ ለሁሉም ወገን የተሻለው አማራጭ ግድቡ በአካባቢው ተፈጥሮ ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ የሚመረምር ጥናት በማካሄድ ዝቅተኛውን የውሃ መስፈርት በሳይንሳዊ ዘዴ መተመን ቢሆንም፣ ከ‹ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕል› ስምምነት በኋላ ተደራዳሪ ወገኖች ይህን ጥናት ለማካሄድ በሚያስፈልጉት መነሻ የተፈጥሮ ሁኔታዎች (baseline environmental conditions) ላይ ሊስማሙ አልቻሉም፡፡

የኤሌክትሪክ ምርትና የውሀ ፍሰት ቁጥሮቹ ግን ለበጎ ትብብር ያጓጓሉ፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የተካሄዱ ይፋዊ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ቢያንስ 750 ጊጋ ዋት-ሰዓታት ወርሃዊ አቅርቦት እና ዓመታዊ አማካዩ በወር 1000 ጊጋ ዋት-ሰዓት የሆነ የኤሌክትክ አቅርቦት የውል ስምምነት ከተከናወነ፣ ከግድቡ በየወሩ በትንሹ 2.4 ቢሊየን ሜትር ኩብ እንዲሁም በዓመት ደግሞ በድምር 38 ቢሊየን ሜትር ኩብ ውሃ አንደሚለቀቅ ያረጋግጣል፡፡ ተደራድረው ወርሀዊ አማካዩን ወደ 1227 ጊጋ ዋት ሰዓታት ከፍ ማድረግ ቢችሉ በአጠቃላይ ሕዳሴ ግድቡ በዓመት 15000 ጊጋ ዋት ሰዓታት ኃይል እንዲያመነጭላቸውና ከ47 ቢሊየን ሜትር ኩብ በላይ ዓመታዊ የውሀ ፍሰት እንደሚኖር መተማመኛቸውም ሊሆን ይችላል፤ ይህም ከወንዙ አማካይ ዓመታዊ ፍሰት በ2 ቢሊየን ሜትር ኩብ ብቻ ያነሰ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በዚህ መልኩ ድርቅም ሆነ የተራዘመ የዝናብ እጥረት በሚከሰትበት ወቅት ተጽዕኖውን ለመቀነስ በሚያስፈልገው የማካካሻ የውሃ ልቀት (mitigation releases) ዙሪያ የሚደረጉ ዝርዝር ድርድሮች ሁለቱንም ወገኖች የሚያስማሙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ግብጽ በቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠችው የተፈጥሮ ጥበቃ ፍሰትም ለኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሬ ለማስገኘት በሚደረግ የስምምነት ሂደት አብሮ ሊሟላ ይቻላል ማለት ነው፡፡

ውሎ አድሮ ኢትዮጵያ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ማማዋ ተሰይማ  በታሪክ ለተዛመዷት ጎረቤቶቿ የክፉ ቀን የውሀ መከታነትዋ፣ ዛሬ ግራ ቀኝ ከተፋጠጡ ወገኖች የሚከተሉ መጻኢ ትውልዶች ነገ የሚቀኑበት ታላቅ የክብር እድል እንደሆነ እና የክልላዊ ትብብር ዘረ ግንድንም እንደሚተክል መገንዘብ ያሻል፡፡

ድርድሩ ወደ ውጤት እንዳያመራ እንቅፋት የሆኑትን አኃዞች በጥሞና ስንመለከት ግን ተደራዳሪዎቹ ለአመታት ሲደራደሩ ከርመው ሲያበቁ ለምን አሁንም ከመስማማት ይልቅ በባሰ ፍጥጫ ተጠመዱ የሚለው ጥያቄ ጠንካራ መልስ ያሻዋል፡፡

የምድር ውሀ፣ የሰማይ ውሀ እና አኃዞች

በድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ከተቆራኙ ሀገራት የትኛውም ሀገር ብቸኛ የይገባኛል መብት የለውም፡፡ ደግሞም  ኢትዮጵያን ማንም በወንዝዋ መስመር እና በላዩ ላይ በምትሰራው ንብረትዋ ላይ ያላትን ሉዓላዊነት ሊቀናቀን አይሞክርም፡፡ ማኅበረሰቡ ከእነዚህን ነባራዊ ሁኔታዎች የሚቃረኑ አስተሳሰቦችን ቢያንጸባርቅ ላይገርም ይችላል፤ ይሁን እንጂ የተዛቡ እምነቶች በየትኛውም ወገን ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ ሲበረታቱ ደግሞ ከፍ ባለ ደረጃ የሚካሄዱ ቴክኒካዊና ጂኦፖለቲካዊ ድርድሮችን ያሰናክላሉ፡፡

በወንዝ የተዛመዱትን ሦስት ሀገረት በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ተባብረው እንዲሰሩ ሊያግባቡ ይችለሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች በተደጋጋሚ የቀረቡ ቢሆንም ድካሙ እምብዛም ተሳክቶ አያውቅም፡፡ ከነዚህ መካከል በተሻለ  የተሳካው የካርቱሙ ጉባኤ ‹ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ› የተሰኘውን ስምምነት አስገኝቷል፡፡ ከዚህ ስምምነት አስቀድሞም የአለም አቀፍ ኤክስፐርቶች ለግድቡ የግምገማ መድረክ በመባል የሚታወቀው አደረጃጀት መዘጋጀቱ ሌላ ታላቅ ስኬት ነበር፡፡ ይህ የግምገማ መድረክ ከሶስቱም ሀገራት የተውጣጡ ከያንዳንዳቸው አንድ ጥንድ የሀገሪቱ ዜጋ የሆኑ ኤክስፐርቶች ከአራት ተጨማሪ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶች ጋር በመሆን ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ከተለያዩ እይታዎች በጥሞና የመረመረ ቢሆንም በቀጣይ ጥናትና ምርምር እንዲከናወኑ የተመከረባቸው ጉዳዮች በበርካታ የሐሳብ ልዩነቶች ምክንያት መቋጫ ሳይበጅላቸው በመቅረታቸው ምክንያት በከፊልም ቢሆን አሁን ላይ ለሚስተዋሉት ችግሮች የዳረገ ቀዳዳ ትቶ አልፏል፡፡

ባለፈው የካቲት ወር ላይ ትግስት አልባው የአሜሪካ በጅሮንድ የድርድሩ ዋነኛ ተጽእኖ ፈጣሪ በመሆን የአባይን የዲፕሎማሲ በውሃ አኃዞችና ሠንጠረዦች ሊመሩ ከች አሉ፡፡ ለነገሩ ግብጽ የአለም አቀፍ የግምገማ መድረኩ ከተዘጋጀበት ከ2013 አንስቶ በዩናይትድ ስቴትስና በዓለም ባንክ ጣምራ አደራዳሪነት በ2020 ዓ.ም እስከ ተሞከረው የተጨናገፈ ውል በነበሩት ዓመታት በአባይ ላይ ከነበራት ፈርኦናዊ የአባ ጠቅል እሳቤዋ ርቃ በመጓዝ ከሕዳሴ ግድቡ የጥቅም ተጋሪ ለመሆን አዝማሚያ አሳይታለች፡፡ ከሁሉም የሚደንቀው ደግሞ፣ ግብፅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፣ በዓባይ ጉዳይ ላይ የተፈረመ ሰነድ ወደ ድርድሩ ይዛ መቅረቧ ነበር፡፡ ይህ ያልተለመደ ድርጊቷ አስቀድማ ትከተል በነበረው ጥረቶችን ሁሉ የማሰናከል ስትራቴጂ ለታከቱት ሁሉ ግራ ያጋባ ነበር፡፡ ነገር ግን እስቲ እንዲያው ግልጽ ጠብ መጫሪያዎቹን፣ ማለትም ውሉን የዝንተ-ዓለም ለማድረግ የተቀመጠውን የሦስት ወገን ሙሉ ድምጽ ሥውር ወጥመድ እና ዓለም ዓቀፍ የግልግል ዳኝነቱን ጉዳይ ወደ ጎን ተወት አድርገን ብመለከተው በግብፅ ቅድመ ፊርማ የታጀበው የስምምነት ሰነድ፣ ኢትዮጵያ ልታጤናቸው የሚገቡ መልካም ሀሳቦችንም የያዘ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ትልቅ ፋይዳ ያለው ደግሞ ግብጻውያኑ በዚህ ሰነድ ረዘም ላሉ ዓመታት የዝናብ እጥረትና ድርቅ ሲያጋጥም ጉዳቱን ለማቃለል ከግድቡ መለቀቅ አለበት ብለው ያቀረቡት የውሃ መጠን ከዚህ ቀደም ከያዟቸው አቋሞች አንጻር የቀለለ መሆኑ ነው፡፡

በርግጥ ግድቡ በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ የሚያስፈልገውን የ640 ሜትር ከፍታ እና የ74 ቢሊየን ሜትር ኩብ ውሃ ክምችት ግብ በበርካታ ዓመታት የማራዘም ሥጋቱ በሰነዱ እንደተጋረጠ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከአማካይ ፍሰቱ በታች የሆነ የዝናብ እጥረት በቀጣይ አምስት አመታት አጋጥሞ ይህ ችግር ቢከሰት እንኳ፣ ከሕዳሴ ግድቡ ከሚገኘው ተጠቃሚነት አኳያ ሱዳንና ግብጽ ከኢትዮጵያ ይልቅ በውሃና በኃይል እጥረት ምክንያት ለከፋ ጉዳት ይጋለጣሉ፡፡ ኢትዮጵያም ልትጠቀመውም ይሁን ልትሸጠው ኃይልን የማምረት ግዴታ ውስጥ መሆንዋ እና ከማንም መልካም ጎረቤት በሚጠበቅ ሰብአዊነትዋም የክፉ ቀን መከታነትዋን የሚያንጸባርቅ ውሃም የመልቀቅ ዕድልዋ ያመዝናል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ወቅት ሱዳንና ግብጽም በግድቦቻቸው ባለው የውሃ መጠንና በገጠማቸው የውሃ እጥረት የአስከፊነት ደረጃ ላይ በመመስረት ውሃውን በየግድቦቻቸው ለማቆየት ወይም ደግሞ ኃይል ለማምረትና ቁልቁል ፍሰቱን የመልቀቅ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባሉ፤ በተለይ ሱዳን እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የድንበር ተሻጋሪ ፍሰትን ጉዳይ ለማጤን ትገደዳለች፡፡ የ‹‹ጀምበር መጥለቅ አንቀጽ›› ተብሎ የሚታወቀው ስምምነቶች የጊዜ ገደብ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሐረግ አለመኖር (በ10 አመት ፍጻሜ እንዲኖረው የመፍትሔ ሐሳብ ቢቀርብም ይህ እንዲጸድቅ በሁሉም ወገኖች የሙሉ ድምጽ ድጋፍ ማግኘት አለበት የሚል ቅድመ ሁኔታ በግብጽ ተካቷል) መመሪያዎቹና ደንቦቹ ቋሚ የጥቁር አባይ የውሃ ክፍፍል ተመን እንዲያጸኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ተግባራዊ የትብብር ማዕቀፉ ከያዘው ጠቀሜታ አኳያ ግን እኒህ ጉዳዮች ሁሉ በድርድር ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው፡፡

ልብ ለሚል አስተዋይ፣ አከራካሪዎቹ ቁጥሮች ወይ በጊዜ መርሃ ግብር አልያም በውሃ ከፍታ ዙሪያ ያጠነጥናሉ፡፡ በጊዜ መርሃ ግብሩ ላይ የሚነሱት ውዝግቦች መቼ በጥቂት ተርባይኖች ኃይል የማመንጨት ሙከራው ይጀመር፣ ወይም ደግሞ መቼ የሕዳሴ ግድቡ በሙሉ የትግበራ አቅሙ ሥራ እንዲጀምር ይደረግ፣ በሚሉት ነጥቦች ያተኩራሉ፡፡ የውሃ ከፍታ ላይ ያሉት ልዩነቶች ደግሞ መቼና ምን ያህል ውሃ ከመጠባበቂያ ክምችቱ ጥቅም ላይ ተቀንሶ ማዋል ይገባል በሚል ርዕሰ ዙሪያ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ማለትም በአንድ ወገን ከማማው ላይ የተከማቸው ውሃ (ለምሳሌ ከባሕር ጠለል በላይ አስከ 610 ሜትር) ለነገ የኃይል አቅርቦት እንደተከተረ ይቆይ ወይስ አሁኑኑ ለታሕታይ ተፋሰስ ወገኖች ከዛሬ የኃይል ማመንጨት ሥራ ጋር ይለቀቅ የሚለው ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ የሚደረግ ስምምነት በወደፊት ልማትና ለውጦች ላይ ሊያስከትል ስለሚችለውም ማዕቀብ ስጋት ያለ ሲሆን፣ ይህ ጉዳይም ከተገቢው በላይ የተጋነነ ይመስለኛል ፡፡ የሕዳሴ ግድቡ ምንም ያህል ታሕታይ ተፋሰስ አካባቢዎችን በመስኖ ለማልማት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ቢሆን፣ በሱዳን ከሚገኛው የአባይ ሸለቆ በመስኖ መልማት የሚችለው መሬት የሚፈልገው ውሀ እጅጉን ቢበዛ በአመት 4 ቢሊየን ሜትር ኩብ ተጨማሪ ውሃ ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ውስጥ በመስኖ ልማት ዙሪያ የሕዳሴ ግድቡን የውሀ መጠን አደጋ ውስጥ የሚጥል አዲስ የልማት ለውጥ ሊፈጠር የመቻሉን ዕድል ስንመረምር ደግሞ ትኩረት ባደረግንበት የጥቁር አባይ ሸለቆ አካባቢ በሚያዋጣ ኢኮኖሚ ልማት በመስኖ ሊለማ የሚችለው መሬት ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር ብዙም ያልበለጠ እንደሆነ ተገምቷል፡፡ አንድ ሄክታር አምስት ሺ ኩቢክ ሜትር ውሃ የሚያስፈልገው መሆኑን በመገመት ለዚህ ሸለቆ የመስኖ ልማት ሊውል የሚችለው የውሃ መጠን 2.5 ቢሊየን ሜትር ኩብ አካባቢ እንደሚሆን እንረዳለን፡፡ ይህ ደግሞ የታላቁ ግድብ የውሃ ክምችት አምስት በመቶ ብቻ ነው፡፡

ከሁሉ በላይ ሊተኮርበት የሚገባው፣ ለግብጽ 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብና ለሱዳን 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ድርሻ አድርጎ የሚሰጠውን የ1959 ዓ.ም የአባይ ውሃ ስምምነት መልሶ ማጽናት ነው ከሚባለው ያልተገባ ውንጀላ ይቅርና፣ የዋሽንግተኑ ስምምነት እንደሚፈልገው ግድቡ በዝናብ እጥረት ወቅት ለማካካስ መልቀቅ የሚጠበቅበትን የውሃ መጠን ቢያሟላ እንኳን ዘወትር ግማሹ ባዶ ይሆናል የሚባለውም ሥጋት እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ የድርቅን ተጽእኖ ለመቀነስ በሚለቀቀው የውሃ ተመንና በአማካይ የወንዙ ፍሰት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ የአባይ አማካይ የውሃ ፍሰት መጠን 49 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን፣ በመጀመሪያዎቹ ዙሮች በሚኖረው ሙሊት ወቅት ከግድቡ እንዲለቀቅ የሚጠበቀው አነስተኛ የውሃ መጠን 31 ቢሊየን ሜትር ኩብ ብቻ ነው (በዚህ አመት ይጠበቅ የነበረው የ560 ሜትር ከፍታ እንግዲህ ተከናውኗል፣ በቀጣይ ዓመት የሚጠበቀው ደግሞ ከባሕር ጠለል በላይ 595 ሜትር ነው፡፡

አራት አመት የዘለቀ ድርቅን ለመግለጫነት የተተመነው የአራት ዓመት አማካይ የፍሰት ምጣኔ 37 ቢሊየን ሜትር ኩብ ሲሆን አምስት አመት ለሚዘልቅ የዝናብ እጥረት ደግሞ ተስተካካይ ቁጥሩ 40 ቢሊየን ሜትር ኩብ ተተምኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ለአራት ዓመቱ (ድርቅ) ወይም ለአምስት አመቱ (የዝናብ እጥረት) ማቃለያ የሚጠበቀው የውሃ ልቀት መጠን በየትኛውም አመት ቢያንስ ግማሹን እስካሟላች ድረስ ቀሪውን መጠን መቼ እንደምትለቅ የመወሰን ድርሻዋ የኢትዮጵያ ይሆናል፡፡ በቁጥር ስናሰላው ይሄ ግዴታ በየአመቱ እንዲለቀቅ የሚጠበቀው የውሃ መጠን በተራዘመ የአራት ዓመት የድርቅ ወቅት እንዲለቀቅ ከተስማሙበት ከፍታ በላይ (ለምሳሌ ከባሕር ጠለል 610 ሜትር በላይ) ከሚኖረው መጠን አንድ ስምንተኛ ሲሆን፣ አምስት የተራዘመ የዝናብ እጥረት በሚከሰትበት ወቅት ከሚኖረው ክምችት ደግሞ አንድ አስረኛው ብቻ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ በየትኛውም መልኩ ትልቅ ጫና የሚያሳድር ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡

በርከት ያለው የጥቁር አባይ ውሃ የሚፈሰው ከሐምሌ እስከ ጥቅምት ነው፡፡ ታዲያ ወደ ታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚሄደው የውሃ መጠን እንዳይቀንስ የማድረጉ ሥራ በበጋ የሚፈጠረውን ጉድለት በክረምት ከጠራቀመው በመተካት ይከናወናል፡፡ ለዚህም ይመስላል፣ የግድቡን የሙሊትና የሥራ መርሀ ግብር አዘጋጆች የፈጣሪን ውሀ መርሀ ግብር በሐምሌ እንዲጀመርና የግድቡ ሠሪ የውሀ ማካካሻ መርሃ ግብር ደግሞ በሕዳር እንዲጀምር ተደርጎ የድርድሮቹ መነሻ ሐሳብ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ይህ መሆኑ በክረምት ምን ያህል ውሃ አቅቦ ማቆየት እንደሚገባ እስከህዳር ጊዜ ይሰጣል፡፡ አልያም ምን ያህሉን በአራቱ ወራት ከተጠራቀመው ክምችት መልቀቅ እንደሚገባ ለመወሰን ይረዳል፤ በመሆኑም ለማካካሻ የሚለቀቀው ፍሰት ላይ የሚኖረው አጠራጣሪ ሁኔታ ቀድሞ መፍትሄ እንዲያገኝ ያስችላል፡፡ ለምሳሌ በክረምት ወራት የሚገኘው የውሃ መጠን ከሚፈለገው በላይ ከሆነ፣ ለጎርፍ ማቃለያ የሚወሰዱት እርምጃዎች ለድርቅ ወራት ከህዳር በፊት ባለው መርሃ ግብር የሚጠበቀውን የማካካሻ ፍሰት ኮታ ለማሟላት መጠቀም ይቻላል፡፡ ለጎርፍ ማቃለያ ከግድቡ የሚለቀቀው ውሃ የሚታሰበው በዚያው ዓመት ኢትዮጵያ እንድትለቀው ከተተመነው መጠን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የአባይ ውሃ ከሚጠበቀው አማካይ መጠን ያነሰ ሲሆን ደግሞ በቀጣዩ ዓመት እንዴት የውሃ መጠን መዛባቱን ማካካስ እንደሚቻል መላ ለመዘየድ አስከ ህዳር መባቻ ቅድሚያ ጊዜ ይሰጣል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አንድ ትንሽ የሚቆረቁርም ቢሆን እንኳን ብሩህ መሆኑ የሚደነቅለት ሐሳብ ይናፈሳል፡፡ ሐሳቡ የሕዳሴ ግድቡ በዓመት ከሚያመነጨው 15,000 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ውስጥ አብዛኛውን ከሰኔ እስከ ጥቅምት ባለው የክረምት ወቅት በሚፈሰው ውሀ ቢከናወንስ የሚል ነው፡፡ 15000 ጊጋ ዋት-ሰዓት እንግዲህ ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት በዓመት ከምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ጋር ከሞላጎዳል አንድ ነው፡፡ ይህም ሕዳሴ ግድቡ እንደ ጣና በለስ ከወንዝ የሚመጣን የውሀ ፍሰት፣ ለከፍታ ሲባል በተገነባ ግምብ በማጎልበት ብቻ፣ ከሞላ ጎደል የሚመጣውን ውሃ ምንም ሳይከማች በቀጥታ ወደ ተርባይኖቹ እንዲያሳልፍ በማድረግ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ማድረግ እንደማለት ነው፡፡ የዚህ ሐሳብ አቀንቃኞች እንደሚሉት ከሆነ፣ በዚህ መልኩ የሚመነጨው ኃይል መጠን ኢትዮጵያ ከአባይ ሌላ ባሏት ወንዞቿ ላይ ያሏትን ግድቦች በሙሉ አቅም ውሃ እንዲያከማቹ በማድረግ እኒህን ማመንጫዎች በበጋ ወራት ኃይል እንድታመነጭ ያስችላታል፡፡

እንዲህ ያለ ከተለመደው ወጣ ያለ ሐሳብ መንስዔው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኃይል የማመንጨት አቅም በቀደምት ጥናቶች ከታቀደው በእጅጉ ከፍ ማለቱን ተከትሎ ሳይሆን አልቀረም፡፡ የኃይል ማመንጫው የማምረት የውጤታማነት ምጣኔ ወይም ፕላንት ፋክተር (በወንዙና የግድቡ የውሃ ፍሰት ሊመነጭ የሚችለው አስተማማኝ ዓመታዊ የኃይል መጠን፣  የውሃ እጥረት ባይኖር ኖሮ በሙሉ አቅሙ ማምረት ለሚቻለው የኃይል መጠን ተካፍሎ የሚገኝ አኃዝ ነው) 35 ፐርሰንት ብቻ መሆኑ የሕዳሴ ግድቡ በአንጻራዊነት ዝቅ ያለ ውጤታማነት አለው ተብሎ እንዲተች አደርጎታል፡፡ እኔ የሕዳሴ ግድቡ ባለቤት ደግሞ፣ ግድቡ ‹‹ውፍረትም፣ ርዝመትም›› እንዳለው፣ ማለትም በአንድ ጊዜ የሚያመነጨው ከፍተኛ ኃይልም ሆነ አጠቃላይ ዓመታዊ አቅርቦቱ ከፍተኛ እንደሆነ በመግለጽ እሞግታለሁ፡፡

የግድቡ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለስልጣን ያዘጋጀው አንድ ለሕትመት ያልበቃ ሪፖርት እንደሚያሳየው 60 ፐርሰንት ውጤታማነት ካለው ከጣና በለስ በስተቀር ሌሎቹ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ያላቸው የውጤታማነት አቅም ከሞላ ጎደል ከሕዳሴ ግድቡ አይበልጥም፡፡ በ2017 ዓ.ም ጊቤ ቁጥር 3 የኃይል ማመንጫ ፕላንት ፋክተር 30 ፐርሰንት የነበረ ሲሆን፣ የተከዜም 26 ፐርሰንት ብቻ ነበር፡፡ አገሪቱ ባጠቃላይ ያሏት የኃይል ማመንጫዎች አማካይ ፕነት ፋክተር 35 በመቶ ሲሆን፣ የሕዳሴ ግድቡ የማመንጨት አቅሙ 5,150 ሜጋ ዋት ሲደርስም ይህንኑ ያህል ይሆናል፡፡

ከላይ በተቀመጠው አመክንዮ ከጎረቤት ተፋሰስ ሀገራት ጋር የረጅም ጊዜ የኃይል አቅርቦት ውል መኖሩ በአንድ ወገን ለኃይል አቅርቦት ውሎቹ የሚያስፈልገውን ዓመታዊ የውሃ ፍጆታ አስቀድሞ ለማቀድ የሚያግዝ ሲሆን በሌላ ወገንም በድርቅ ወቅት የሚያጋጥም የውሃ እጥረትን ለማካካስ ሊለቀቅ የሚገባውን የውሃ መጠን ለማስላት ይረዳል፡፡ አስቀድሞ መነሻ፣ አማካይ እና ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ግብ የተቀመጠበት ውል ሲኖር በተጓዳኝ ከወንዙ የተገደበውን ውሃ ለማካካሻ ሊለቀቅ የሚገባውን የውሃ ፍሰትንም በክፉው የደረቅ ቀን ለማሳካት ያስችላል፡፡

የሚያሳዝነው የውሃ ባለቤትነት አታካሮ እንደ ድንበር ውዝግብ የመረረ እና ተያያዥ ጠቡም ሥልጣኔንም ሆነ ውድቀቱን ተሻግሮ የሚዘልቅ አበሳ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ አሳማኝ በሆኑ አኃዞች ላይ ተመርኩዞ የሚደረግ ዘመናዊ የኃይል አጠቃቀም ስምምነት ምንም ያህል የተራቀቀ ይሁን ለረጅም ዘመን ስር ሰዶ ከቆየ የውሃ ልዕልና የሚመነጭ ፍርሃትን አይታደግም፡፡

የሕግ ወይስ የጉልበት የበላይነት

የዋሽንግተን ትግስት አልባ አማላጅነትና እጅግ ችኩል አዋላጅነት ተስፋ የተጣለበትን ስምምነት እንዴት ባጭሩ እንደቀጨ ውሉም ገና ሳይወለድ እንደሞተ ዛሬ ላይ ፀሐይ የሞቀው ወሬ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዋሽንግተኑ ስምምነት ላይ በርካታ ቅሬታዎች ቢኖራትም የስምምነቱን አስገዳጅነት እና የግልግል ዳኝነትን መቃወሟ፣ ታላቁን ግድብ መገንባት ከጀመረች ጀምሮ ለአስር ዓመታት የከረመችበትን፣ በናይል ምድር ፖለቲካ የፈረጠመ መዳፏን ለሁሉም የምታሳይበት አቋቋሟን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

በሩጫው የመጨረሻ ዙር፣ ክሩን ለመበጠስ መቃረቧ እና በአቋሟ በመጽናቷ የድርድሩ ሚዛን ወደሷ እንዲያጋድል ያስቻለ እንደመሆኑ መጠን ደግሞ ፈጽሞ ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ አንገቷን የምትደፋበት ጊዜ አይደለም፤ አይሆንምም፡፡

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ እና ሱዳን በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት በዘላቂነት ለመፍታት በላቀ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት የተሞላ ሀገራዊ አመራር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ እነዚህ ሀገራት፣ ምንም እንኳን በአባይ ውሃ ላይ ከምዕተ ዓመት በላይ በእሰጥ አገባ ተፋጥጠው ቢኖሩም፣ ዛሬ በሦስተኛው ሺህ፣ ስንኳንስ ግጭትን ለመፍታት ይቅርና ጥያቄዎችን እንኳን ለመመርመር የሚያስችሉ ጥቂት ዘላቂ ስምምነቶች ብቻ ነው ያሏቸው፡፡ ዛሬ ባለው ይፋዊ መረጃ ከሆነ ግብጽ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን በጣምራ ያደረጉት የቅርብ ጊዜ ውል፣ የማርች 2015ቱ የህዳሴ ግድቡ የዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ› ስምምነት ነው፡፡

በወቅቱ ይህ የህዳሴ ግድቡን መርሆች የማወጅ ስምምነት ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነበር፡፡ ፋይዳው ዳግም ጎልቶ የታየው ዋሽንግተን ስፖንሰር ባደረገችው ሰነድ መግቢያ ላይ ‹‹የመርህ ስምምነቱን በማጽናት›› የሚል መስፈሩ ሲሆን በመቀጠልም ‹‹የመርህ ተኮር ስምምነቱ አላማ እየፈጸምነው ያለውን ይህን ስምምነት ለማሳለጥና ለመገየድ የሚሆኑ ጠቅለል ያሉ መርሆችን ለማስቀመጥ ነው›› በማለት ይህንኑ የሶስትዮሽ ስምምነት ያጠናክረዋል፡፡ መርሁ ደግሞ በአንቀጽ ቁጥር 10፤ “ሰላማዊ የሙግት አፈታት መርሆች” የተባሉትን ሲዘረዝር “ሙግት በምክክር ወይም በድርድር” አንዲፈታ ይህ ካልተሳካም ‹‹በሽምግልና ወይም በአስታራቂ  እንዲያልቅ፣ አልያም ጉዳዩን እንዲያጤኑት ለሶስቱ ሀገራት ርዕሰ ብሔሮች መመራት›› እንዳለበት ይናገራል፡፡

መርህ ተኮር ስምምነቱ በተፈረመበት ጊዜ አካባቢ፣ የካይሮ ዩኒቨርስቲ ምሁር የሆነችው ራፊያ ተውፊቅ ‹‹ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለግብጽ የዘመናት የናይል ልዕልና በኢትዮጵያ የተሰጠ አጸፋዊ ምላሽ ነው›› የሚለውን አባባል ትመረምራለች፡፡ ይህች ምሁር በጂኦ-ፖለቲካ ግንኙነት የእንካ-በእንካ አጸፋዊ አመላለስ ዘላቂ የውሀ ፍትህን ማስፈን ይችል እንደሆነም ትጠይቃለች፤ በውስጠ ወይራም ኢትዮጵያ የወሰደችው የአጸፋ ርምጃ ከግብጽ ኢፍትሐዊ ልዕልናም በከፋ መልኩ የናይልን አካባቢ አለመረጋጋት ሊያባብሰ እንደሚችል ትጠቁማለች፡፡ በርግጥ ራፊያ ተውፊክ ከወገናዊነት ውጭ በሆነ ትንታኔዋ የውሃ ባለቤትነት መብቶችና አካባቢያዊ መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊረጋገጡ የሚችሉት የጥቅም ተጋሪነት ማዕቀፍ ላይ ሲመሠረቱ ነው የሚለውን ምክረ ሀሳብ ጠንከር አድርጋ አስረድታለች፡፡ ቢሆንም ግብጽ በአባይ ውሃ ላይ የነበራትን ልዕልና ለመቃወም የተወሰደው የህዳሴ ግድብ አጸፋዊ ርምጃ ዋጋ ቢስ ሊሆን እንደሚችል መገለጹ በመሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አሳማኝ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ እንዲያውም ኢትዮጵያ ስትጓዝበት የቆየችው የኃይል ጎዳና ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱ በገሃድ እየታየ ነው፡፡

የራፊያ ተውፊቅን ምሁራዊ አገላለጽ ልጠቀምና፣ ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ያራመደችው ፖሊሲ “በአደባባይ አንገት ከመድፋት” ወደ “ስውር ሽኩቻ” ብሎም በስተመጨረሻ “ይፋዊ ወደ ሆነ [የናይል ፖለቲካ] ፍልሚያ” የተለወጠበት ሂደት፣ ምኒልክ ‹በጥቁር አባይ ላይ የውሃውን ፍሰት የሚያግድ ምንም አይነት ግንባታ›› ላለማካሄድ ከተስማሙበት በብሪታንያው ኤድዋርድና በኢትዮጵያው ንጉሥ መካከል ከተደረገው የ1902 ስምምነት አንስቶ በወረቀት ተከትቦ ይገኛል፡፡ የ1902ቱ ስምምነት ዓላማ በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው ‹‹በሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል ድንበር ለማካለል›› ነበር፡፡ ጥቁር አባይን አስመልክቶ በብልጣብልጥነት የተሰነቀረው የዓባይ አንቀጽ ግን ‹‹የአባይን የውሃ ፍሰት የሚያግደው ፈጣሪ ብቻ ነው›› በሚለው የሟቹ መለስ ዜናዊ የምጸት ንግግር መንፈስ፣ ላዕላይ ሀገሪቱ ይህን ጊዜ ያለፈበትን ስምምነት መሳለቂያ አድርጋ አስቀርታዋለች፡፡

በንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት፣ የዩናይትድ ስቴትስ የሸለቆ ልማት ቢሮ (USBR) ያቀረበውን ምክረ ሀሳብ ተከትሎ ያኔ ‹‹የድንበር ላይ ግድብ›› (ኋላ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የተባለውን ማለት ነው) ጨምሮ በአባይ ላይ የታለሙ ግድቦች የውሀ ሽታ ሆነው ለዘመናት ከረሙ፡፡ ከአጼው በኋላ በነበረው ዘመን የውሃ ዘመዳሞቹ ሶስት ሀገራት በእጅ አዙር ጦርነት ባደረጉበት በሰሜን ለአሥስርተ ዓመታት በቆየው ትርምስ ምክንያት ‹‹አባይን ማገድ›› ጭራሽ የማይታሰብ ሆኖ ቆየ፡፡ ጦርነቱ ካከተመ በኋላ በሁለቱ ሀገራት ኤክስፐርቶች ውይይት አማካኝነት ለሁለቱም ወገኖች በሚበጅ መልኩ የአባይን ዝርዝር አጠቃቀም ለማመቻቸት እንዲሁም ‹‹ሁለቱንም በሚጠቅሙ ፕሮጄክቶች ላይ ተባብሮ ለመስራትና የአባይን የውሃ ፍሰት መጠን ሁሉን ባገናዘበና ባስተሳሰረ የልማት ስልት ለማሳደግ›› በሚል ዓላማ ‹‹በግብጽና ኢትዮጵያ መካከል አጠቃላይ የትብብር ማእቀፍ ስምምነት›› በመለስና በሆስኒ ሙባረክ ተደርጓል፡፡ ይህም ስምምነት የ‹‹ስውሩ ሽኩቻ›› የመክፈቻ ምዕራፍ በመሆን ከማገልገሉም በላይ፣ በሂደት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እንዲገነባና በ2015 ዓ.ም ‹‹የዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ›› ስምምነት ላይ እንዲደረስም አስችሏል፡፡

‹ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ› በተሰኘው ስምምነት ውስጥ በሃገራቱ የሚኒስትሮች ከሚቴ የተፈጠረ ውዝግብ በርዕሳነ ብሔር መካከል በሚደረግ ድርድር እንዲፈታ መደንገጉ በአባይ ላይ የሚነሳ ሙግት በጂኦ-ፖለቲካዊ ሽኩቻ እንደሚመነዘር አመልካች ነው፡፡ ልዕልናውን የያዘው ወገን ሁሌም ‹‹የጨዋታውን ህግ እንዳሻው እንደሚወስን›› እና በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ በሚኖረው ውይይት ላይ ‹‹ጽኑ ቁጥጥር›› በማድረግ ወንዙን በጋራ የሚጠቀሙ ሀገራት መቃወም የሚችሉበት ምንም ክፍተት እንዳይኖርና በዚህም የወቅቱን ፍትህ በወቅቱ ጎልባታ እንደሚያስተረጉም፣ የውሀ ፍትህ ሊቃውንቱ ይናገራሉ፡፡

ይህን የተረዳ ሁሉ፣ ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በዘላቂነት በውል ብቻ ለመታሰርም ሆነ በዓለም አቀፍ ግልግል በሙግት ለመዳኘት እንድትስማማ መጠየቅ ያልተገባነቱን ይረዳል፡፡ የሉሊቱ ኑሮ የከበዳቸው ታዳጊ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለክፍለ ዘመናት የሰፈነውን የተዛባ የፍትህ ሥርዓት በጥርጣሬ ቢመለከቱት ከቶ ምንም አይደንቅም፡፡ ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣት ዘወትር የሚዳክረው አዲሱ የኢትዮጵያ አመራር ደግሞ ከውጪ የሚመጣን ጫና እና ማባበያ ወግድ ለማለት ይበልጡን ምክንያት ይኖረዋል፡፡ እንዲያውም ግብፅ ባቀረበችው ቅድመ ፊርማ በሠፈረበት ሰነድ ላይ ተመርኩዛ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ቢያንስ ለሶስት ተከታታይ ክረምት  የሕዳሴ ግድቡን የመጀመሪያ ዙር የሙሊት ሒደት እያከናወነች፣ ጎን ለጎን ደግሞ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ወደፊት በሚካሄዱ ውይይቶች ይበልጥ ውጤታማ ወደሆነ ስምምነት ይደርሱበታል፡፡ ይህም የሕዳሴ ግድቡን በውጤታማ ትብብር መስፈርት በአባይ ሸለቆ ከተሰሩት ግድቦች ሁሉ እጅግ የላቀው እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

‹‹ድጋፋችንን እናጓትታለን፣ አስከናካቴውም እንነፍጋቹሀለን›› በማለት የሚዝቱብን የሀገራችን አጋሮችም፣ እስከአሁን ለዚህ ትጉህ ሕዝብ ያሳዩት ደግነት ምንም ይሁን ምን፣ የህዝቡ ብርታት መሠረቱ ጣልቃ ገብነትን ለመመከት ሕብረቱ እና በውስን አቅሙም ቢሆን ራሱን በራሱ መቻሉ መሆኑን መገንዘብ ይገባቸዋል፡፡

በመጨረሻም፣ የሕዳሴ ግድቡን ዛሬ ካለበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሲያስተውሉት የዓለም አቀፉ የግልግል ዳኝነት ፍትሐዊነት ኖረው አልኖረው ለቀጣዩ ሂደት ጭራሽ ትርጉም የለሽ ጭምር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ የኢትዮጵያ እምቢታ ሀገሪቱ ከሥር መሠረቱ ያደራጀችው የናይል ፖለቲካን ልዕልና የሚተገዳደር ሥሪት ከማጠናከርዋ በፊት በተፈጠረው ዓለም አቀፋዊ የውሀ ፍትህ ሥርዓት ‹‹እምቢ አልዳኝም›› ማለቷ ነው፡፡ ሙግቱ አሁን ካለበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት ገና ድሮ ትክክልና ስህተት የሆነውን አስቀድሞ ለወሰነው የዓለም አቀፉ የውሃ አጠቃቀም ሥርአት እምቢተኛ በመሆን በአባይ ሸለቆ ፖለቲካ ውስጥ ተገቢው ቦታ እንዲሰጣት እየሞገተች ነው፡፡ አብዛኞቹ ወንዙን የሚጋሯት ሀገራት ይህን እውነታ ይረዳሉ፡፡ ችግሩ በጥቅምት ወር ውይይቱን ሲያደራድሩ የነበሩት አካላት ይህን መዘንጋታቸው ነው፡፡ ቢያንስ በአህጉራዊ አማራጭነት የቀረቡት አደራዳሪዎች፣ ከእንግዲህ በየዋሂቱ፣ የተብረቀረቀች የአፍሪካ ቀንድ የንግሥት ወፍ ዓይነ ርግብ ውስጥ አሁንም የማይበገረውና፣ ደመ-ቁጡው የአባይ ሸለቆ አንበሳ መቀመጡን ይረዳሉ ብለን እስቲ ተስፋ እናድርግ፡፡

በቀጠናው ሰላምና የጋራ ልማት ላይ ከጎረቤቶቻችን ሁሉ ጋር በትብብር መስራት በሩቅ ካሉ ሀገራት ጋር ከመሰረትነው ዝምድና የበለጠ ማህበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው፡፡ የጋራ ሕልውናችንን መቼ መጥቶ መቼ እንደሚነፍስ በርግጠኝነት ሊገመት በማይችል ዝናብ ላይ ጥገኛ እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ አንዳችን የሌላችንን እውነተኛ ስጋት በቅንነት በመረዳት ብልሀት በተሞላበት ሁኔታ ተስፋ የተጣለበትን የግድቡን መርህ ተኮር ስምምነት ወደ ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ውህደት እንዲስፋፋ ልንሰራ ይገባናል፡፡ በዚያውም እኛ ኢትዮጵያውያን በዚህ የናይል ፖለቲካ ክርክር ለጊዜውም ቢሆን የበላይነቱን ያስጨበጠንን፣ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ የፈጠርነውን የአንድነት ጮራ ሳናደበዝዝ ለልማት ችግሮቻችንን ሁሉ መፍቻነት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

Query or correction? Email us

Follow Ethiopia Insight

Editor: William Davison

Main photo: The GERD reservoir after the first filling.

Join our Telegram channel

Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished. 

We need your support to analyze news from across Ethiopia
Please help fund Ethiopia Insight’s coverage
Become a patron at Patreon!

About the author

Tsedeke Yihunie Woldu

Tsedeke is the founder of Flintstone Engineering & Homes, the President of the Ethiopian Chess Federation, and a long-time economic policy activist.