ከሁሉም ዋና ዋና ኃይማኖቶች ለፍቅር ውይይትና እርቅ እውነተኛ ጥሪ ቢደረግ የኢትዮጵያን የፓለቲካ ውጥረት ሊያቀል ይችላል፡፡
ኢትዮጲያ እጅግ ሃይማኖተኛ የምትባል ሃገር ናት፡፡ የPew Research Center ግኝት እንደሚያሳየው 98 በመቶ የሚሆኑት የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸው ለእነርሱ እጅግ ጠቃሚ ነገር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህም እነርሱን አለም ላይ እጅግ ሃይማኖተኛ ከሚባሉት ህዝቦች መሃል ያደርጋቸዋል፡፡
በኢትዮጲያ የሚገኙ የእስልምና ፣ የወንጌላውዊ ክርስትና ፣ የካቶሊክ እና የሌሎች እምነቶች ተከታዮችም ሃይማኖታቸውን እንደ ቀላል ነገር ነው የሚያዩት ብሎ ለመናገር የሚያስችል ብዙም ምክንያት የለም፡፡ ሁሉንም ጠቅልለን ስናያቸው ከ97 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኢትዮጲያ ህዝቦች ለሃይማኖታዊ መጽሃፍቶቻቸው ፣ ልምዶቻቸው እና መምህራኖቻቸው ከፍተኛ አክብሮት አላቸው፡፡
የዚህ ውጤት ትልቅና ችላ ሊባል የማይገባው ነው፡፡ ማንም ሰው ወደ ኢትዮጲያ የትኛውም ጥግ ሄዶ ቤተክርስቲያን ፣ መስጅድ፣ ገዳም ወይንም ሌሎች ሃይማኖታዊ አምልኮ የሚካሄድባቸው ስፍራዎችና ትምህርት ሊያገኝ ይችላል፡፡ በመላው ኢትዮጲያ ለሃይማኖት እራስን ማስገዛትና ጥልቅ ስሜትን መሰረት ያደረጉ የቁስ/አካላዊ መሰረተ ልማቶችና የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ይገኛሉ፡፡
እነዚህ የቁስ/አካላዊ መሰረተ ልማቶችና የእርስ በእርስ ግንኙነቶች በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፣ በራዲዮ ጣቢያዎች ፣ በማህበራዊ ድህረገጽ (Facebook) ፣ ቴሌግራም ቡድን ፣ የጽሁፍ መልእክት እና በእውን አለም የመሰባሰቢያ (የመገናኛ) ሰንሰለቶች ሲገናኙ የሚኖራቸው ተደራሽነትና ተጽእኖ የሚያስደምምና እጅግ ሰፊ ነው፡፡
እነዚህ ልዩ የሆኑ ሃይማኖታዊ ልምዶች ኢትዮጲያ አሁን ላለችበትና ለወደፊት ሁነቷ እጅግ ቁልፍ የሆነ ኃያል የሞራል ራእይ ይጋራሉ ፤ ይህም የሞራል ራእይ ሌላው ባልንጀራችን ነው የሚል ነው። የሞራል ራእዩ ኢትዮጲያ አሁን ያለችበትን የጥላቻ ፣ ግጭት እና ጥቃት ቀውስ በቀጥታ ሊዳስስና ለብሄራዊ እርቅ አስፈላጊ የሆነውን መንፈሳዊው ሁኔታ ሊያዘጋጅ ይችላል።
ይህ ግን እንዴት ነው የሚሆነው?
ሌሎችን የምናይበት መንገድ ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት ምን አይነት እንደሆነ ይገልፃል፤ ግንኙነታችን ደግሞ ማህበረሰባችን ምን አይነት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ሌሎችን እንደ መጤና ጠላት ስናይ ግጭት የማይቀር ይሆናል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ዛሬ ከምናየው ሞት እና ውድመት ሁሉ ጀርባ ያለው እይታ፡፡
ነገር ግን ሌሎች ዋጋ እንዳለቸው ስናስብና እራሳችንን ከነሱ ጋር የተጎዳኘን ባልንጀሮች አርገን ስንመለከት አንዳችን የአንዳችንን ዋጋ (ጥቅም) እንመለከታለን። አንዳችን የአንዳችንን ዋጋ (ጥቅም) መመልከታችን ደሞ እርስ በእርስ እንድንቀራረብ ፣እንድንነጋገር እና መልሰን መተማመንንና መተባበርን እንድንገነባ ያነሳሳናል፡፡ እነዚህ የእርቅ ተግባራዊ የእርምጃ ሂደቶች ናቸው ፡፡
ለዚህ አላማ ደግሞ ለብሄራዊ እርቅ ሂደት የበኩሉን ሊያበረክት የሚችል ትሁት ግብዣ ልናቀርብ እንወዳለን፡፡ ይህ ግብዣ ቅጽበታዊ ለውጥ ወይንም ተአምራታዊ መፍትሄ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከሌሎች አማራጮች ጋር በመሆን ኢትዮጲያን ወደ ውይይት ፣ እርቅና ዘላቂ መጪ ጊዜ የሚወስድ አንድ መንገድ በመሆን ማገልገል ይችላል፡፡
ይህን ግብዣ ‘ባልንጀራን የመውደድ ሳምንት ለብሄራዊ እርቅ’ ብለን ሰይመነዋል፤ ሂደቱም እንደሚከተለው ይሆናል፡፡ በግንቦት ወይንም በሰኔ የመጀመሪያዎቹ ቅዳሜና እሁድ ላይ (የምርጫ ቀናቶች ናቸው) ሁሉም ቤተክርስቲያን ፣ ሁሉም መስጅድ ፣ ሁሉም ገዳም እና ሁሉም አይነት ሃይማኖታዊ አምልኮ የሚካሄድባቸው መድረኮች አንድ አይነት መልእክትን ለመስበክ ቢስማማሙስ? መልእክቱ ቀላል ፣ መሰረታዊና ተግባራዊ ይሆናል፡፡
- ሌላ ሰው ምንም አይነት የዘር፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ልዩነት ከኛ ጋር ቢኖረውም ባልንጀራችን ነው፡፡ እኛ ጠላቶች ሳንሆን ባልንጀሮች ነን ፡፡
- እግዚአብሄር ባልንጀራችንን እንደራሳችን እንድንወድ ያዘናል ፡፡ እውነተኛ እምነት አንዳችን አንዳችንን እንደ ውድ ባልንጀራዎች እንድናይና እንድንከባከብ ዘንድ ያዘናል፡፡ (የባልንጀራን መውደድ ስምምነት መፈረም ለዚህ ጉዳይ ቁርጠኛ መሆን የሚቻልበት ቀላሉ መንገድ ነው።)
- እውነተኛ አማኞች ጥላቻን፣ ስድብንና ጥቃትን መኮነንና ለጋራ ስኬታችን ውይይት፣ እርቅ እና ትብብርን በመጠቀም በጋራ መስራት አለባቸው፡፡ (የባልንጀራን መውደድ እንቅስቃሴ ሰባት ተግባራት እያንዳንዳችን ይህንን ስራ በራሳችን አካል እንድንጀምረው ይጋብዘናል)
ይህ የሳምንት እረፍት ቀናት ሊደርስ አንድ ሳምንት ሲቀረው ብሄራዊው የቴሌቪዢን ጣቢያ በየቀኑ አንድ ሰዓት መድቦ የተለያዩ በኢትዮጲያ የሚገኙ ሃይማኖቶችን የሚወክሉ መሪዎች ይህንን መልእክት እንዲያስተላልፉ ማድረግ ይችላል፡፡፡፡ የባልንጀራን መውደድ እንቅስቃሴ “የጋራ የሞራል እይታዎቻችን / Our Shared Moral Vision” የተሰኘው ዶክመንተሪ 5ት ኢትዩጲያዊ ሃይማኖታዊ ትውፊቶች በምን መልኩ ባልንጀራን መውደድን እንደሚያስተዋውቁ የሚዳስስ ሲሆን ለዚህ ሳምንት (በግንቦትና ሰኔ የመጀመሪያዎቹ የሳምንት እረፍት ቀናት ከመድረሱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ) ለሚደረገው ብሄራዊ የቴሌቪዢን ፕሮግራም ተነሳሽነትን መፍጠር የሚችል (የሚያነቃቃ) መግቢያ (ጅማሬ) ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡
ይህ የጋራ እንቅስቃሴ አንጻራዊ የምእራባውያን ሃይማኖታዊ ብዝሃነትን አይፈልግም ፤ ይልቅ ሁሉም የሃይማኖት ማኅበረሰቦች እራሳቸው አምላክ እራሱን የገለጠበት ነው ብለው ከሚያምኑትና ከሚያከብሩት መጽሐፍቶቻቸው ላይ መስበክ ፣ መጸለይ እና መተግበር ይችላሉ። የክርስትና እምነት አባቶች ከመጽሃፍ ቅዱስና ከቅዱስ ልማዶች ተነስተው መናገር ይችላሉ፡፡
“ብቀላን አትሻ፥ ከህዝብህም መካከል ባለ ሰው ላይ ቂም አትያዝ፥ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤….እንግዳውን (ጸጉረ-ልውጡን ) እንደራስህ ውደድ” (ዘሌ 19:18, 34)
“ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሟችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድ ዷችሁም ጸልዩ። (ማቴ 5:43-45)
“ሁሉም የእግዚአብሔር ትዕዛዛት በዚህ አንድ ትዕዛዝ ስር ይጠቃለላሉ፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’። ፍቅር ባልንጀራን አይጎዳም። ስለዚህ ፍቅር ትዕዛዛቱ የሚፈጸሙበት መንገድ ነው።።” (ሮሜ 13:9-10)
“ሌሎችን ከራስህ በላይ አክብር የሁሉም ወንድምም ሁን፡፡ ማንንም ለመጉዳት ወይንም ለማጥቃት ቅርብ አትሁን.. እንዲህ አይነቱ ሰው ቆሻሻ በሞላበት ቦታ ሰውነቱን እንደሚታጠብ ሰው ነው” (ፍትሃ ነገስት ክፍል 1, ገጽ. 78)
የእስልምና ሃይማኖት አባቶች ደግሞ ከቅዱስ ቁርአንና ከሃዲስ በመውሰድ እንዲህ መናገር ይችላሉ፡
“ህዝቦች ሆይ እኛ እናንተን ከአንድ ወንድና ከአንዲት ሴት ፈጠርናችሁ፤ እርስ በእርሳችሁ ትተዋወቁ ዘንድም ዘርና ጎሳ እንትድትሆኑ አደረግናችሁ” (ቅዱስ ቁርአን 49:13)
“በቅርብም በሩቅም ላሉ ባልንጀሮቻችሁ መልካምን አድርጉ” (ቅዱስ ቁርአን 4:36)
“ማናችሁም ለራሳችሁ የምትሹትን ነገር ለባልንጀራዎቻችሁ መሻት እስክትጀምሩ ድረስ እምነት የላችሁም… ባልንጀራው ከእርሱ መልካም ያልሆነ ባህርይ ስጋት ነጻ ያልሆነ ማንም ቢሆን ጀነት አይገባም” (ሙስሊም, ኪታብ አል-ኢማን [የእምነት መጽሃፍ], መጽሃፍ 1, #72 እና #74)
“ማንም ሰው አንድ ሰውን ቢገድል…ሁሉንም የሰው ዘር እንደገደለ ይቆጠራል ፣ ማንም ሰው የአንድ ሰውን ህይወት ቢያድንም የሰውን ዘር ህይወት በሙሉ እንዳዳነ ይቆጠራል” (ቅዱስ ቁርአን 5:32).
“እጅግ የተመሰገነው (ግብረገብ ያለው) ባህርይ ዝምድናን ከሚቆርጡ ጋር መገናኘት ፣ ለሚነፍጓችሁ ሰዎች መስጠት እና ለሚበድሏችሁም ይቅርታ ማድረግ ነው፡፡” (ሃዲት አል-ታባራኒ ቁጥር. 282)
የባሃኢ እምነት አባቶች ደግሞ ይህን ከአብዱል ባሃ አስተምህሮ ጠቅለል ተደርጎ የተወሰደውን ትምህርት ማስተማር ይችላሉ፡፡
“ማንም ከአንተ ጋር ቢጋጭ ከእርሱ ጋር ጓደኛ መሆንን ሻት ፣ ማንም ልብህን ቢወጋህ ለቁስሉ የፈውስ ዘይት ሁንለት ፣ ማንም አንተ ላይ ቢያላግጥና ቢተችህ አንተ በፍቅር ቅረበው….. እነዚህ ናቸው የአምላክ አስተምህሮት ስረ-መሰረቶች ፤ እነዚህ በጥቅሉ የባሃ አስተምህሮቶች ስሮች ናቸው፡፡”(አብዱል ባሃ ፣ ከአብዱል ባሃ ጽሁፎች ተመርጦ የተሰበሰበ ገጽ 34)
ከሁሉም ሃይማኖቶች የሚተላለፉት መልዕክቶች ባልንጀራን የመውደድ ሳምንት መልዕክቶች ጋር በተሳካ ሁኔታ ተመሳሳይ ይሆናሉ፡፡ (1) እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራችን ነው (2) እግዚአብሄር ባልንጀራችን እንድንወድ ያዛል፡፡ (3) ጥላቻና ግጭት ወደ ውይይትና ትብብር መቀየር አለባቸው፡፡
ይህ መልእክት ለአንድ ሳምንት ያህል በብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በየእለቱ እና በዛው ሳምንት የእረፍት ቀናት በራሳችን መድረኮች በሁሉም ከተላለፈ በኢትዮጲያ ባሉ ጠንካራ ሃይማኖታዊ ትስስሮችና ማህበረሰቦች ዘንድ ከጫፍ እስከ ጫፍ ማስተጋባት ይችላል ፡፡ እያንዳንዱ ፕሮግራም ማህበረሰባችንን ይህንን ተመሳሳይ መልእክት እንዲሰብክ ፣ እንዲጸልይበት እና እንዲተገብረው ያበረታታዋል፡፡ተሳታፊዎችም የማህበራዊ ድህረገፆችን ሌላውን ሰው እንደባልንጀራ በሚያሳየው ይህ የጋራ የሞራል እሳቤ ለማጥለቅለቅ ሊነሳሱ ይችላሉ ፡፡ ቀላል የሆኑ #ፍቅርለባልንጀራዬእንቅስቃሴ (#NLMEthiopia) ኢትዮጵያ የሚሉ መለዮዎች አሁን የምናያቸውን መርዛማ መልእክቶች ለመቃወም አገልግሎት ላይ ሊውሉ ይችላሉ ፡፡
በዚህ ሂደት ምናልባትም ተዓምር ሊፈጠር ይችላል። በጋራ መላው አገሪቷ ፓለቲካዊ ያለሆነ ነገር ግን ኃይማኖታዊ ስልጣንን የተላበሰ ቁርጠኛ የሞራል ጥሪ ትሰማ ይሆናል ይህም ምንም አይነት ልዩነት ቢኖርም የሌላ ሰውን ዋጋ (ጥቅም) ለማየትና የሻከረ ግንኙነትን ለማደስ ይረዳል። የፌደራሉ ምርጫ እየተቃረበም ስለሆነ ይህ ምክረ ሃሳብ ሰላምን ለማበረታታት ተግባራዊ እርምጃ መሆን ይችላል ፤ በተለይ ፍቅር ለባልንጀራዬ የተሰኘው ሳምንት በሰኔ ላይ (ልክ ከምርጫው በፊት ወይንም በኋላ) ከተደረገ።
ተግባራዊ አንደምታው ለሁላችንም ግልጽ ነው፤
- ጠላትነትን የሚፈጥሩ ቃላት በእግዚአብሄር እና በባልንጀራችን ላይ እንደሚፈጸም ሃጢያት ተቆጥረው ከአንደበታችን መወገድ አለባቸው፡፡
- ጠላትነትን የሚፈጥሩ ምስሎች በእግዚአብሄር እና በባልንጀራችን ላይ እንደሚፈጸም ሃጢያት ተቆጥረው ከአእምሯችንና ከሚድያዎቻችን መወገድ አለባቸው፡፡
- ህግን የሚተላለፉና ባልንጀራዎቻችንን የሚጎዱ የጥቃት ድርጊቶች አምላክ ለሁላችን ያለውን ክብር ፣ ፍትህና ሰላም የሚጎዱ ናቸውና ልንቃወማቸው ይገባል፡፡
በዚህ መንገድ ፍቅር ለባልንጀራዬ የተሰኘው የብሄራዊ እርቅ ሳምንት ለጋራ መግባባት ፣ ግልጽነት እና ቁርጠኝነት የሚያገለግል ህዝባዊ ወቅት ይሆናል፡፡ ከዚህ በሁዋላም ተግዳሮቶችና ግጭቶች ሲያጋጥሙን እርስ በእርስ “ፈሪኃ እግዚአብሄር የለንም? እግዚአብሄር ለእኛ የሚናገረውን ቃል ሰምተናል፡፡ እንዲህ ከቀጠልን እጅግ እናከብረዋለን የምንለውን ነገር ነው የምንክደው። በእግዚአብሄር ስም የተሻለ ነገር እንስራ” በማለት መጠያየቅ እንችላለን፡፡
አስቡት ከሁነቱ በኋላ በአገሪቷ በሚገኙ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ የሚፈጠረውን መልካም ነገር፡፡ “የሰውን ስብዕና የሚያራክሱ ቋንቋዎችን እንተው ምክንያቱም ያ ሰው ወይንም ቡድን ምንም ቢሆን ባልንጀራችን ነውና። አዲስ የማክበርና የእርቅ ቃላትን እንናገር።” “ግባችንን ለማሳካት ጥቃትን መጠቀም እንተው ምክንያቱም ያ ሰው ወይንም ቡድን ምንም ቢሆን ባልንጀራችን ነውና ፤ ለውይይትና ትብብር የተሻለ መንገድን እንፈልግ፡፡” “በጥላቻ ከተናገርንና አንድ ድርጊትን ካደረግን ቤተክርስቲያን ፣ መስጅድ ወይም መቅደስ መሄዳችን እርባና ቢስ ነው ምክንያቱም በአምላክ ላይ አምጸናልና፡፡”
ለማጠቃለያ የኢትዮጲያ የሃይማኖቶች መማክርት ጉባኤ የኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ ጉባኤን ፣ የእስልምና ጉዳዮች የበላይ ካውንስልን ፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ህብረትን እና ሌሎች ሁሉንም ሃይማኖታዊ አካላት ፍቅር ለባልንጀራዬ ለተሰኘው ሳምንት በግንቦት ወይንም በሰኔ መጀመሪያ ላይ ማስተባበር ቢችልስ? ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያውም ይህንን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ለአንድ ሳምንት በየእለቱ የሚተላለፍ ፕሮግራም ስፓንሰር ቢያደርግስ (ወጪውን ቢሸፍንስ)? በአካባቢዎቻችን ያሉ የሃይማኖት ምእመናን እና የማህበራዊ ድህረ ገጾቻችን ይህንን ክንውን በራሳቸው ስብከት ፣ ጸሎትና ልማድ ቢደግፉስ?
ለአንድ ሳምንት መላው ሃገሪቷ ተመሳሳይ መልእክትን ታስተጋባለች ፡፡ “ሌላው ሰው የአምላክ ፍጥረት በመሆኑ ብቻ ውድ ባልንጀራችን ነው፡፡ በልባችን ልንጠላውና በአንደበታችን ልንረግመው በድርጊታችንም ጉዳት ልናደርስበት የምንዳዳው ሰው ሳይቀር አምላካችን የፈጠረው ባልንጀራችን ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም ልዩነቶቻችንን ከግምት ሳናስገባ መዋደድ አለብን”
ኢትዮጲያ ባለጸጋ ሀገር ናት፡፡ ከኢትዮጲያ ሃብቶች መሃል ህዝቦቿ በፈጣሪ ላይ ያላቸው እምነት አንዱ ነው፡፡ ከሌሎች ቁሳዊ ከሆኑና ግላዊነት ከሚያጠቃቸው ህብረተሰቦች በተቃራኒው ከአስሩ ኢትዮጲያውያን አስሩ ከራሳቸው አሻግረው አምላክን እንደሚመለከቱና የአምላክን ፈቃድ ለህይወታቸው ትርጉም የሚሰጥ ነገር አድርገው እንደሚቆጥሩ ይናገራሉ፡፡
ስለዚህ ይህንን ብሄራዊ ሃብት በሁሉ ቦታ ከሚገኝ መሰረተልማቱና ብርቱ የግንኙነት መረቡ ጋር በማገናኘት በዚህ አስቸኳይ የቀውስ ወቅት አንጠቀምበትም? ለምን በስፋት በብሄራዊ ቴሌቪዥንና ታች ባለው ማህበረሰብ ዘንድ ሃይማኖቶቻችን በየግል ነገር ግን በአንድነት የሚስማሙበትን ነገር አናስተጋባም ፤ ሌላው ሰው በአምላክ አይኖች ፊት የእኛ ባልንጀራ ነው ፣ የጥላቻ ቃላቶችና ድርጊቶች በእውነተኛ አማኝ ህይወት ውስጥ ምንም ቦታ የላቸውም ፤ በአምላክ ማመን ፍቅርን ፣ መከባበርን እና ለግጭቶቻችን ሰላማዊ መፍትሄን መፈለኝ ይሻል ይህም ለጋራ ስኬታችን ይረዳልና ፡፡
ማንም የማያምንበትን ነገር እንዲሰብክ አይጠየቅም፡፡ ይህ ፍቅር ለባልንጀራዬ የተሰኘው ሳምንት ቀድሞውኑ የእምነቶቹ ማዕከላዊ መልእክት የነበረውን ነገር ነው መልሶ ወደ መኃል የሚያመጣው እና በጣም አስፈላጊ በሆነበት ወቅት ለአንድ ሳምንት በጋራ የሚያውጀው፡፡
እያንዳንዱ ቀን ምርጫ ነው ፣ ምርጫዎቻችን ደግሞ የውሳኔ ድምጾቻችን ናቸው፡፡ ባልንጀራችንን እንደራሳችን ለመውደድ ስንመርጥ የጋራ ክብራችን ይመለሳል ፡፡ የዛን ጊዜ መወያየት የሚቻል ይሆናል፡፡ መተማመን እንጀምራለን ፡፡ ትብብርና አዳዲስ ፈጠራዎች ያብባሉ፡፡ እርቅ የህይወት ዘይቤያችን ይሆናል እና ይህም እርቅ በእያንዳንዳችን ፣ በአካላችንና በአካባቢያችን ማህበረሰብ ፣ እንዲሁም ከኛ ጋር የተለያዩ ልዩነቶች ያላቸውን ሰዎች ከምናይበትና ከምናስተናግድበት መንገድ ይጀምራል፡፡
እባክዎን ባልንጀራን መውደድ ለአገራዊ እርቅ ሳምንትን እውን እንድናደርግ ያግዙን፡፡
Query or correction? Email us
Follow Ethiopia Insight
This is the author’s viewpoint. However, Ethiopia Insight will correct clear factual errors.
Join our Telegram channel
Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished.
Please enough of this religious narratives it’s gotten us no where but backward. Religion is not necessary for co existence in peace and respect but strong government institutions, laws, implementation and punishment. I don’t need religion to dictate to me how i should treat my neighbour as long as I have sound mind it’s ingrained in our nature. The colonialist came with the Bible to Africa and we can all see what they did.
a correction : come out of the churches: instead of come out the churches.
The vast majority of Ethiopians are religious people who frequent churches and mosques;at the same, the vast majority of their actions are contrary to the teaching of their religions, even with the top religious figures of the country; some fifteen years ago during the time of Melese zenawi, everybody who lived in Ethiopia must have witnessed what kind of hateful, divisive and agitating sermons, against Islam religion, used to come out the churches day in and day out all over the country! and the government of the time intentionally looked the other way, setting religion against religion, and people against people. Nonetheless, now is the time for all religions and people to come together and save the country from following in the footsteps of the Rowandan genocide.