Elections 2021 Ethiopian language In-depth

መስመሩን በሳተው በዚህ የሽግግር ወቅት አፋኝ የኢትዮጵያ ህጎች ላይ ማሻሻያ እየተደረገ ነው

ህጎችን ማሻሻል ትክክለኛ ጅማሬ ቢሆንም የዲሞክራሲ ስርዓቱ ማሻሻያ ግን ገና ረዥም መንገድ መጓዝ ይጠበቅበታል።

በኢትዮጵያ በሚገባ የሚያገለግል የፍትህ ስርዓት አለመኖሩ ለበርካታ አስርት አመታት ቅሬታ ሲቀርብበት የኖረ ነገር ነው። ችግሩ በህግ አተረጓጎም፣ትግበራ እና አፈጻጸም ላይ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን ከህጎቹ ከራሳቸው ያሉ ጉድለቶች ጭምር የሚመነጭ ነው።

የተወሰኑት ህጎች ዘመን ያለፈባቸው ሲሆኑ አንዳንድ ጊዜ ጠባብ የፖለቲካ አላማን ለማስፈጸም ተግባር ላይ የሚውሉ ናቸው። ይህም አላማ ምክንያታዊ ያልሆነ የመንግስት ስልጣን ተስፋፊነትና ተቃውሞን ማፈን ነው። ለምሳሌ በ 2001 ዓ.ም በኢህአዴግ የተመረጠው ፓርላማ የፀረ-ሽብርና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅን አጽድቋል። የፀረ-ሽብር ህጉ የፖለቲካ ተቃውሞን ለማዳከም ያለመ ሲሆን የሲቪል ማኅበራት አዋጁ ደግሞ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ከመብት ተሟጋችነት ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዳይሳተፉ ለመገደብ ያለመ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታም የተሻሻሉት የ 2001 ዓ.ም የምርጫ ህጎች መንግስት ባለፉት ምርጫዎች ውጤቶችን እንዲወስን ሰፋ ያሉ እድሎች ሰጥተውታል።

በተጨማሪም ሌሎች ከ 1997 ዓ.ም በኋላ የተተገበሩ ንብረትን፣መሬትን፣ግብርንና ጉምሩክን የተመለከቱ ህጎች ለህግ አውጪው የበለጠ ስልጣን የሚሰጡ ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ይህም የሆነው ብስለት የተሞላበት የተጠያቂነት ዘዴ ባልተዘረጋበት ሁኔታ ነበር።

የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት የህግ ማሻሻያ ስራዎችን በመስራትና አዲስ ህጎችን በማርቀቅ ላይ ይገኛል። በሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም አብይ ከተሾመ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ የተቋቋመ ሲሆን ኃላፊነቱም ከህግና ፍትህ ስርዓት ማሻሻያዎች ጋር በተያያዘ የፌደራል ዐቃቤ ህጉን ማማከር ነበር።

ጉባኤው 13 የህግ ባለሞያዎችን እንዲሁም በዐቃቤ ህግና 200 በጎ ፍቃደኛ ባለሞያዎች በሆኑ የጥናት ቡድኖች የተቋቋመ ጽህፈት ቤት ይይዛል። ከቀድሞ የማሻሻያ ዘዴዎች በተለየ መልኩ ጉባኤው የተቋቋመው ገለልተኛ አማካሪ አካል በመሆን ሲሆን በስራውም ሰፊ ነጻነት አለው።

ከተቋቋመ ጀምሮ ጉባኤው ተከታታይ ጥናቶችን ያደረገ ሲሆን ከህገ መንግስቱ ጋር አይሄዱም ያላቸውንና ሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አላቸው ያላቸውን 16 ህጎች እንዲሻሻሉ አነሳስቷል። እውቅ ጠበቃ፣ ጸሀፊና የወንጀለኛ ህግ ተመራማሪ የሆነውና ቀደምትና አሁን ያሉ አስተዳደሮች ያደረጉትን የህግ ማሻሻያ ያገዘው ስሜነህ ኪሮስ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ሲናገር ‘’ፓርላማው በኢህአዴግ ጊዜ ህገ መንግስታዊ ያልሆኑ ህጎችን አጽድቋል እናም አሁን ያለው አስተዳደር ማስተካካያ መውሰዱ ተገቢ ነው። ይህም ዜጎች መብታቸውን እንዲጠቀሙና ‘’በህግ መግዛት’’ ከሆነው ያለፈው አስተዳደር ስርዓት ‘’የህግ የበላይነት’’ ወደሚነግስበት ስርዓት እንዲሸጋገሩ ከተፈለገ መተግበር ያለበት ነገር ነው’’ ይላል።

ነገር ግን የፌደራል ዐቃቤ ህጉ የሚሰጡ ሃሳቦችን እንዲሁም ህጎችን የመቀበል፣የማሻሻልና ሙሉ ለሙሉ የመቃወም ነጻነት ስላለው ጥቂት ህጎችን ከማሻሻል የበለጠ ብዙ ነገር ማረግ ይችል ነበር። ቢሆንም በጉባኤው ከተካሄዱ ማሻሻያዎች አራቱ በተለየ መልኩ ጠቃሚ ናቸው፤ እነዚህም የምርጫ ህጎች፣የሲቪል ማኅበረሰብ ህግ፣የፀረ-ሽብር ህግና የመገናኛ ብዙሃን ህጎች ናቸው።

የምርጫ ህጎች

በ 2010 ዓ.ም አዲሱ አስተዳደር ከወሰዳቸው ዋና ዋና ማሻሻያዎች ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን በተፋጠነ ሁኔታ ክፍት ማረግ አንዱ ነበር። ይህን ተከትሎም የ2012 ምርጫ (በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ወደ 2013 ተራዝሟል) እየተቃረበ በመጣ ጊዜ የምርጫ ህጎች ዋና መወያያ ጉዳይ ነበሩ።

እውቅ ፖለቲከኞችን፣ምሁራንና ባለሞያዎችን የያዘ የዲሞክራሲያዊ ተቋማት የጥናት ቡድን ከተመሰረተ በኋላ የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ ሁለት አዋጆችን ማለትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ኢብምቦ) ማቋቋሚያ አዋጅን (ቁጥር 1133/2019) እና የኢትዮጵያ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅን (ቁጥር 1162/2019) አርቅቋል። እነዚህ አዋጆች የቀድሞ የምርጫ ህጎችን ያሻሻሉ ሲሆን የምርጫ ህጎቹ ቀደም ሲል በታወጁ ሶስት አዋጆች ምክንያት የመጡ ነበሩ።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት የሚሾሙበትና የሚሻሩበት መንገድ እንዲሁም የአባልነት ዘመን ተሻሽሏል። ቀደም ሲል በነበረው ህግ የቦርድ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይመረጡ የነበረ ሲሆን ይህንን ለማድረግም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ብቻ ነበር እንዲያማክሩ የሚጠበቀው።

ፓርላማው ሁልጊዜም የገዢው ፓርቲ አብላጫውን መቀመጫ የሚይዝበት የነበረ በመሆኑ የተነሳ የቦርድ አባላቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በራሳቸው የሚመረጡ ነበሩ።

አዲሱ ህግ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማኔጅመንት ቦርድ አባላትን እንዲመርጡ ስልጣን የሚሰጥ (የሚያስችል) ሲሆን ሂደቱ ግን የተለየ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ተወካዮች እና ሌሎች ፖለቲካዊ ያልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ አባላትን የያዘ ገለልተኛ ኮሚቴ እንዲያቋቁሙ ይጠበቅባቸዋል። ኮሚቴው ከህዝብ፣የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪል ማኅበራት የሚመጡ እጩዎችን የመቀበልና ፉክክርና ግልጽነት ባለበት መንገድ ከተሰጡት እጩዎች የመምረጥ ኃላፊነት አለበት። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተቀበሏቸው የእጩዎች ዝርዝር ውስጥ የተሻሉ ናቸው በማለት የሚመርጧቸውን እጩዎች ከማቅረባቸው በፊት ከተመዘገቡ የፓለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር መማከር ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስራ ዘመንና አባላትን ከቦርዱ የማንሳት ስርዓትም ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል፥ በዚህም የተነሳ የቦርድ አባላቱ የስራ ዘመን ከአምስት አመታት ወደ ስድስት አመታት ተራዝሟል፣ ሆኖም ግን የቦርድ አባላት ለአንድ ተጨማሪ የስራ ዘመን መወዳደር ይችላሉ።

ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ የተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ቦርድ አባላትን ከስልጣናቸው ማንሳት ይችል የነበረው በህመም ወይም በከባድ የስነ-ምግባር ጉድለት ብቻ ነበር። የብቃት ማነስ ከስራ መደብ የሚያስነሳ ምክንያት አልነበረም እናም አንድ ዜጋ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አንድ የምርጫ ቦርድ አባል ከስራ መደቡ እንዲወገድ የሚያደርግ ምክንያት ቢያገኝበትም ለምክር ቤቱ የሚያሳውቅበት ሂደት አልነበረም።

አሁን ያለው አዋጅ ግን ማንኛውም ሰው ወይም አካል በጤና፣በስነ-ምግባር ጉዳይ ወይም በተረጋገጠ የብቃት ማነስ ምክንያት አንድ የቦርድ አባል ከኃላፊነቱ መነሳት እንዳለበት ካመነ ለምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ እንዲያሳውቅ እድል የሚሰጥ ሲሆን የቦርድ አባሉ ከኃላፊነት መነሳት አለበት ተብሎ የሚቀርበው መረጃ ክብደት (ጠቃሚነት) ግን አፈ ጉባኤው እንዲወስነው የሚተው ጉዳይ ነው። የሚቀርበው ጥቆማ ተቀባይነት ካገኘ ምክር ቤቱ ሶስት አባላትን ማለትም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛን፣ በሚጣራው ጉዳይ ላይ ባለሞያ የሆነ ሰው እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተወካይን የሚይዝ አጣሪ ኮሚቴ የሚሾም ይሆናል።

ህጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የገንዘብ ነጻነት ላይም ለውጥ አርጓል። የተሻረው ህግ የበጀት ህግን በአንድ አረፍተ ነገር  ‘’ቦርዱ በጀቱን ካዘጋጀ በኋላ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ አለበት’’ በሚል የደመደመ ሲሆን ይህ ግን በጭራሽ በተግባር ላይ አልዋለም። በተጨማሪም የቦርዱ በጀት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር እንዲገመግመው ከቀረበ በኋላ ነው እንዲጸድቅ ለምክር ቤት ይቀርብ የነበረው።

አሁን ቦርዱ በአንድ ጊዜ የሶስት አመት በጀት እንዲመደብለት ጭምር መጠየቅ የሚችል ሲሆን ገለልተኝነቱን የማይጎዳ እስከሆነ ድረስም ስጦታዎችና የገንዘብ ድጋፎችንም እንዲቀበል ተፈቅዶለታል። እነዚህ አቅርቦቶች የቦርዱን የገንዘብ አቅምና ነጻነት ማሻሻል አለባቸው። በተጨማሪም ቦርዱ ራሱ የራሱን ጽህፈት ቤት ዋና እና ምክትል ስራ አስኪያጅ እንዲሾም ስልጣን ተሰጥቶታል ይህም ቀደም ሲል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይደረግ የነበረ ነው።

በምርጫ ህግ ሌላው ዋና ለውጥ ማንኛውም ለምርጫ የሚቀርብ እጩ የሚወዳደርበትን ክልል ወይም ስፍራን ቋንቋ ማወቅና መናገር አለበት የሚለው የቀድሞው መስፈርት መሻሩ ነው፥ ይህ ህግ ከህገ መንግስቱ ጋርም ሆነ ከዓለም አቀፍ መስፈርቶች ጋር የማይሄድ ነበር። ነገር ግን መስፈርቱ የማይመለከተው ለፌደራል ስልጣን (ኃላፊነት) የሚወዳደሩትን እጩዎች ብቻ ነው። የክልል ህገ መንግስቶች በክልል መንግስት ውስጥ ማንኛውንም የስራ ቦታ ለመያዝ የሚፈልግ ሰው የክልሉን የስራ ቋንቋ መናገር እንዳለበት ይጠቅሳሉ።  ከዚህ ጋር ተያይዞም በክልል ደረጃ የሚወዳደሩ እጩዎች አሁንም የሚወዳደሩበትን ክልል ቋንቋ ማወቅ ይጠበቅባቸዋል።

በድሮው የምርጫ ህግ የነበሩት የተወሰኑት የህግ ጉድለቶች የተስተካከሉ እንዲሁም ኢብምቦ እንደገና የተዋቀረ ቢሆንም እነዚህ ለውጦች በቂ እንዳልሆኑ የሚገልጹ ግን አሉ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የህግ ጉዳዮች ክፍል ኃላፊ የሺዋስ አድማሱ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ሲናገሩ ‘’ህገ መንግስቱ ከተሻሻለ በኋላ እጩ የማቅረብ ሂደቱ የበለጠ መሻሻል አለበት። የአስተዳደር (የማኔጅመንት) ቦርድ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመረጡ ከሆነ የምርጫ ቦርዱ ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ቢገባ አያስገርምም’’ ብለዋል። ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የህዝብ ግንኙነት ሰው በቃሉ አጥናፉ ‘’በዝቅተኛ ስፍራ ላይ ያሉ የምርጫ ቦርዱ ሰራተኞች የማኔጅመንት አባላት ጋር ያለውን ታማኝነት አይጋሩም በዚህም የተነሳ ከምርጫው ቀደም ብሎ የነበረው ሂደት የተቀናጀ አልነበረም። በርካታ የምርጫ ጣቢያዎች አልተከፈቱም ነበር፤ አብዛኛው ሂደቱም የዲሞክራሲ ስርዓትን የሚያንጸባርቅ አልነበረም’’ ሲል ተናግሯል።

በእርግጥም ከምርጫው በፊት የነበሩ የኢብምቦ እንቅስቃሴዎች በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያስደሰቱ አልነበሩም፤ የጥበቃ እጥረትና በተወሰኑ ስፍራዎች የመራጮች ምዝገባ ዘግይቷል የሚሉ ቅሬታዎች ተደጋግመው ተነስተዋል።

ነገር ግን የኢዜማው የሺዋስ ከምርጫው በፊት በሰጠው ቃለምልልስ ‘’ከምርጫው በፊት ችግር የነበረ ቢሆንም እንኳን’’ የ2013 ዓ.ም ምርጫ ቀደም ሲል ከነበሩ ምርጫዎች  የበለጠ ፍትሀዊ ይሆናል ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል።

የሲቪል ማኅበራት ህጎች

የአሁኑ አስተዳደር የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ ፍትሀዊ ባልሆነ መልኩ እገዳ የሚጥል ነው በማለት መሻሻል አለበት ብሎ የመረጠው ሌላው ህግ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ህግ ነበር። ከ 2001 ዓ.ም በፊት የነበረው የደንብ ሁኔታ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የበጎ አድራጎት እና የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች በአንጻራዊነት ሲታይ ሊያሰራ የሚችል ነበር። የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ላይ፤ በተለይም በመብት ጥበቃና መብትን በማስከበር ላይ ተሰማርተው የነበሩ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ላይ የተለያዩ ገደብ የሚጥሉ ህጎችን የያዘው የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች አዋጅ በ2009 ዓ.ም  እስኪወጣ ድረስ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ቁጥር ወጥ በሆነ ደረጃ  እየጨመረ ነበር። የ2009 ዓመተ ምህረቱ አዋጅ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ተሟጋች በመሆን የሚያገለግሉ አገር በቀል የሆኑ ድርጅቶች 90 ፐርሰንት ያህል የገንዘብ ፍጆታቸውን አገር በቀል ከሆኑ ምንጮች መሰብሰብ አለባቸው ሲል ይደነግጋል። በተጨማሪም የአስተዳደራዊ ወጪዎችን ገደብ 30 ፐርሰንት ያደረገ ሲሆን ይህንንም ያደረገው እነዚህ ወጪዎች ምን ምን እንደሚያካትቱና አስተዳደሪያዊ ወጪ ሲባል እራሱ ምን ማለት እንደሆን ግልጽ ሳያደርግ ነው።

የተሻሻለው የሲቪል ሶሳይቲ አዋጅ (1113/2019) ስራ ላይ ከዋለ በኋላ ከ1,800 በላይ አዲስ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ በኩል የተመዘገቡ ሲሆን ባለፈው አመት ስራ ላይ የዋለው የኤጀንሲው የ10 አመት እቅድ በ2022(እ.ኢ.አ) የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችን ቁጥር በአራት እጥፍ ለማሳደግ ያልማል። በተጨማሪም ሐምሌ 6 የቀረበው የኤጀንሲው ያለፈው የበጀት አመት (2012-13) የእቅድ ግምገማ ላይ ጉድለቶች ብሎ ያስቀመጣቸው ከድርጅቶች ለቀረቡ ሪፖርቶች የሚሰጥ ምላሽና የድጋሚ ምዝገባ መዘግየት ናቸው።

ለቀጣዩ (2013-14) የበጀት አመት ኤጀንሲው ግልጽነትና ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ተቋማዊ አቅምን ለመገንባት፣የአገልግሎት አቅርቦትን ለማሻሻል፣ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል እና አስተዳደራዊ ችግሮችን ለማቃለል ጥረት ለማድረግ አቅዷል። የተወሰኑ ተቺዎች ግን ኤጀንሲው በቅርቡ ባወጣው ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ያላቸውን ስጋት የገለጹ ሲሆን ይህ መመሪያ በ2001 ዓ.ም የነበሩትን የተወሰኑ ገደብ የሚጥሉ ደንቦችን ምናልባት በድጋሚ ስራ ላይ ሊያውል ይችላል።

በውጭ የገንዘብ ድጋፍ የሚደገፈው ሴንተር ፎር አድቫንስመንት ኦፍ ራይትስ ኤንድ ዲሞክራሲ (ሲኤአርዲ) ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት እንደገለጸው ድርጅቱ በ2003 ዓ.ም ለመመዝገብ ፈልጎ የነበረ ቢሆንም በጊዜው በነበረው እገዳ ምክንያት አልቻለም ነበር። ‘’የድሮው አዋጅ ላይ የነበረው ዋናው ችግር 90 ፐርሰንት የገንዘብ ድጋፍ ከአገር ውስጥ እንዲሰበሰብ የነበረው አስገዳጅነት ነው። የአገር ውስጥ ለጋሾች ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ልገሳ የማድረግ ዝንባሌ ቢኖራቸውም ከግንዛቤ ማስጨበጫና ከሰብዓዊ መብት ጋር ለተያያዙ ፕሮግራሞች መለገስ አልለመዱም ፤ ሲኤአርዲ ደግሞ በዋናነት መሰል ፕሮግራሞች ላይ ስለሚያተኩር እስከአሁን ድረስ በውጭ ለጋሾች ብቻ ነው እይተደጎመ ያለው። ነገር ግን በሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ስለሚደረጉ ከመብት ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎች ጥቅም ግንዛቤ በመጨመር የአገር ውስጥ ለጋሾችን ለማግኘት እያሰብን ነው’’ ሲል በፍቃዱ ተናግሯል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ያልተገደበ ስልጣን ሌላኛው ችግር ነው። ‘’ድርጅቶች በሁሉም ስራቸውና የገንዘብ ሁኔታቸው ላይ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይጠየቁ ነበር፤ስለላ ነበር ይካሄድባቸው የነበረው’’ በማለት በፍቃዱ ያክላል። በተጨማሪም ‘’የፕሮጀክት ዘገባዎች ቀደም ተብለው ይረከቡ የነበረ ሲሆን ገንዘብም ይሰባብሰብ የነበረው ኤጀንሲው ይሁንታውን ከሰጠ በኋላ ነበር። ድርጅቶች ስራቸውን ሲያቋርጡም ንብረቶቻቸው በኤጀንሲው ይወረስ የነበረ ሲሆን ኤጀንሲውም በቀላሉ ድጋሚ ምዝገባን አልቀበልም በማለት የድርጅትን ሙሉ ንብረት ሊወርስ ይችል ነበር። ነገር ግን አሁን የምዝገባ እደሳ አስፈላጊ ነገር አይደለም እንዲሁም አንድ ድርጅት ስራው ሲቋረጥ ንብረቱ ለሌሎች የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ሊተላለፍ ይችላል’’ ብሏል።

አሁን ያለው አዋጅ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች የአስተዳደራዊ ወጪንም በድጋሚ በመወሰን ወሰኑን ከ30 ወደ 20 ፐርሰንት አውርዶታል። በፍቃዱ ይህንን በደስታ የሚቀበለው ሲሆን ‘’ገደቡ አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ሁሉም በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ ሰዎች ተመሳሳይ አላማ የላቸውም። ቀድሞ በነበረው ህግ ሁሉም የፕሮግራም (የስራ) ወጪዎች የአስተዳደር ወጪዎች ተደርገው ይወሰዱ የነበሩ ሲሆን ይህም በስልጠና መርሃ ግብሮች ላይ ለአሰልጣኞች የሚከፈለውን ክፍያ ጭምር ያካትታል። አሁን የፕሮግራም ወጪዎች ከአስተዳደራዊ ወጪዎች እንዲለዩ ተደርገዋል’’ በማለት ይናገራል።

ኢትዮጵያ ኢንሳይት ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ኮሚሽን የፕሮግራም ሀላፊ የነበረችውን ሜሮን ካሳሁንን የ2001 ዓ.ም አዋጁ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች እንቅስቃሴ ላይ ምን ተጽእኖ እንዳሳረፈና ከአዲሱ አዋጅ በኋላ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አወንታዊ ተጽእኖ አርፎበት እንደሆነ ጠይቆ ነበር።

ሜሮን ስለጉዳዩ ስትናገር ‘’የገንዘብ ድጋፍ በመቀነሱ ምክንያት የተወሰኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በርካታ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቻቸውን ለመዝጋት የተገደዱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የስራ ዘርፋቸውን ለመቀየር ተገደዋል ይህም የሆነው የሴቶች፣ ወጣቶች፣ ሰብዓዊ መብት፣ ሰላምና እርቅ ተሟጋች ሆኖ ለመስራት ያለው አቅም አነስተኛ በመሆኑ ነው። አሁን ለሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሆኖ ለመስራት የተሻለ ህግ አለ፤ የፀረ-ሽብር ህጉ ተሻሻሏል፣ የማረሚያ ቤት አስተዳደር አዋጅም እንደዚሁ። ይህም በማረሚያ ቤቶች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቀንሱ ያግዛል’’ ብላለች።

የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ነጻ እንቅስቃሴ ላይ የነበረው ህጋዊ ገደብ በከፍተኛ ሁኔታ የተቃለለ ሲሆን የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችም እንደገና እያበቡ ነው። የዲሞክራሲ ስርዓትን በመተግበር በጅማሬ ላይ ባሉ አገራት ውስጥ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ያላቸው ሚና መናገር ከሚቻለው በላይ ነው። በኢትዮጵያ በአሁን ጊዜ በአንጻራዊነት ደካማ የሆነው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ ከፖለቲካ ሽግግር ጋር የሚያያዝ ቢሆንም የሰብዓዊ መብት የላቀ ጥበቃ እንደሚያስፈልገውና መንግስትም ህግን ማስከበር እንዳለበት የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም። የሲቪል ማኅበራት ድርጀቶች ለመስራት የላቀ ነጻነት ማግኘታቸው በዚህ ረገድ የሚረዳ ይሆናል።

ፀረ-ሽብር ህግ

ሌላኛው የተቀየረው ህግ ፀረ-ሽብር ህግ (652/2009) ሲሆን ይህም “የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ” (1176/2020) በተሰኘው አዋጅ ተቀይሯል።

የቀድሞው ፀረ-ሽብር ህግ ህግ ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት በኢትዮጵያ ፀረ-ሽብር ህግ ያስፈልጋል አያስፈልግም የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ነበር።

ኢህአዴግ የፀረ-ሽብር ህግ መኖሩ አስፈላጊ እንደሆነና የህጉም ዋና ዋና ሃሳቦች ከዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር እንደሚሄዱ እንዲሁም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ሽብርተኝነት ላይ ያወጣውን ስምምነትን በመፈረሟ ይህን ማድረግ ግዴታዋ እንደሆነ በመጥቀስ የፀረ-ሽብር ህግ እንዲወጣ ተሟግቶ የነበረ ሲሆን በተጨማሪም ኢትዮጵያ የምትገኘበት የጂኦግራፊ አቀማመጥ፣ የፖለቲካ ሁኔታ፣ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ችግሮች የፀረ-ሽብር ህጉን አስፈላጊ ያደርገዋል ሲል ሞግቷል።

ከዚህ በተቃራኒው ይቀርቡ የነበሩ ሙግቶች ደግሞ መሰል ህጎች ለሽብርተኝነት ሰፊ ትርጉም በመስጠት የግለሰቦችን መብቶች ይጋፋሉ እንዲሁም የመንግስትን የደኅንነት መዋቅር በማስፋት በህጉ ተወንጅለው የሚቀርቡ ሰዎችን ህገ መንግስታዊ መብት ይሸረሽራል የሚሉ ነበሩ።

ቀደም ሲል የነበረው የፀረ-ሽብር አዋጁ በትክክል አሸባሪዎችን ከመቅጣት ይልቅ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችንና ጋዜጠኞችን ለማፈንና ለመቅጣት ጥቅም ላይ ውሏል በሚል በሰፊው ይተች ነበር።

እውነትም የተሻሻለው አዋጅ ያለፈው ህግ ተጨባጭና የአፈጻጸም ክፍተቶች የነበሩበት እንደነበረና ይህም የዜጎች መብትና ነጻነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳረፉን ይጠቅሳል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሽብርተኝነት ተግባር ተቀባይነት ያለው ትርጉም ስለሌለው አዋጁ ሽብርተኝነትን ሰፋ ባለ መልኩ ነው የተረጎመው። በዚህም የተነሳ ሃሳብን በነፃነት በመግለጽ ስር የሚካተቱ ሀይል የማይቀላቅሉ እንቅስቃሴዎች (ለምሳሌ የተቃውሞ ሰልፍ ማደረግ እና ሂሳዊ አስተያየቶችን ማሳተም) በቀላሉ ሽብርተኝነት ተደርገው ሊፈረጁ ይችሉ ነበር። ህጉን ለሚተላለፉ ሰዎችም ይሰጡ የነበሩት ቅጣቶች አብዛኛውን ጊዜ ከባድና ወጥ የነበሩ በመሆናቸው የተነሳ ከወንጀሉ አይነትና ካስከተለው ጉዳት ጋር በማይገናኝ ሁኔታ ፍርድ ሊሰጥ የሚችልበት ሁኔታ ነበር።

በተጨማሪም በፀረ-ሽብር ህጉ ለተከሰሱ ማናቸውም ሰዎች የዋስ መብትን መከልከል አንዱ ተግባር ነበር። አዲሱ አዋጅ የሽብርተኝነት ተግባር ምን ምን ያካትታል የሚለው ላይ እምብዛም ለውጥ አላደረገም፣ ነገር ግን የህዝብ አገልግሎት ላይ እክል እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ የሚላቸውን እንቅስቃሴዎች በህጉ ውስጥ እንደማይካተቱ የሚያትት ሲሆን እነዚህ እንቅስቃሴዎችም የሽብርተኝነት ተግባር ተደርገው የማይታዩት ከስራ አድማ ጋር ግንኙነት ካላቸውና የህዝብ አገልግሎት ላይ የሚፈጠረው እክልም ከአገልግሎት ሰጪ ተቋም ወይም ከአድማ መቺዎቺ ስራ ጋር የተያያዘ ከሆነ ነው።

ሌላው ሽብርተኝነት ተደርጎ የማይቆጠረው ተግባር ተብሎ የተጠቀሰው ደግሞ ችግሩ ሰዎች በህግ እውቅና የተሰጣቸውን እንደ ተቃውሞና ስብሰባ የመሰሉ መብቶች ሲተገብሩ የሚከሰት ከሆነ ነው።

እነዚህ ህጎች ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ የተካተቱ አልነበሩም፥ ይህም የፖለቲካ ተቃውሞዎች ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ከፍተኛ የእስር ፍርድ እንዲጋረጥባቸው ክፍተት የፈጠረ ነበር።

የሽብርተኝነት ተግባርን ‘’ማበረታታት’’ የሚለው ህግ አሁን የተሻሻለው ህግ ከተሻረው ህግ ውስጥ አሳሳቢ አድርጎ የተመለከተው ሌላ ህግ ነበር። ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ የነበረው ‘’ማበረታታት’’ የሚለው ግልጽ ያልሆነና ወጥ ፍቺ የሌለው መስፈርት ጋዜጠኞችና ዜጎች ገዢ ፓርቲውን በይፋ እንዳይቃወሙ በማድረግ መብታቸውን የነፈገ ነበር።

አዋጁ ማንኛውም በህትመት የወጣ ጽሁፍ በተወሰኑ ወይም በሙሉ ህዝቦች ዘንድ የሽብርተኝነት ተግባርን ለመፈጸም በቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ትዕዛዝ የሚያስተላልፍ፣የሚያዘጋጅ ወይም የሚያነሳሳ ሆኖ ከተወሰደ ከህትመቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች በሙሉ ከ10 እስከ 20 አመታት ድረስ የእስር ፍርድ ሊጠብቃቸው ይችላል ይላል።

ይህም በተለያዩ መንገዶች ሊተረጎም የሚችል ሲሆን መንግስትን የሚተቹም በህግ ሊጠየቁ ይችላል። ለምሳሌ የተቃዋሚው ሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ ቃል አቀባይና አሁን የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ የሆነው ዮናታን ተስፋዬ የተለያዩ ጽሁፎችን በማኅበራዊ ሚድያ በመጻፍ የ2016ቱን የኦሮሚያ ወጣቶች ተቃውሞን ቀስቅሷል (አስነስቷል) ተብሎ ተከሶ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቶ ነበር።

አሁን የወጣው አዋጅ ‘’ማበረታታት” የሚለውን “ማነሳሳት/መቀስቀስ’’ በሚለው የቀየረ ሲሆን ሽብርተኝነቱን የቀሰቀሰው አካል አላማ እንዲሁም በሽብሩ የታቀደው ነገር ተፈጥሯል አልተፈጠረም የሚለውን ከግምት ያስገባል። ህዝባዊ ያልሆኑ ቅስቀሳዎች የሚያስከስሱ የሚሆኑት ህዝቦች በአዋጁ የተጠቀሱትን የሽብር ተግባራት እንዲፈጽሙ ታቅደው ከተከናወኑ ነው ሲልም ይደነግጋል።

በይፋ የሚወጡ መግለጫዎች ሽብርተኝነትን የሚያነሳሱ/የሚቀሰቅሱ ተደርገው የሚታሰቡት በግልጽ መንገድ ሽብርን የሚያነሳሱ ሆነው ሲዘጋጁና የመግለጫው ታዳሚዎችም ቅስቀሳውን እንደ ሽብር ቅስቀሳ አርገው ሲረዱት ሲሆን ሽብርተኝነትን በማነሳሳት የሚፈረደው ፍርድም የታቀደው ወንጀል መፈጸም አለመፈጸሙ ላይ ይመረኮዛል።

በቀድሞ ህግ የመረጃ ምንጫቸውንና መረጃው የተሰበሰበበትን መንገድ የማይገልጹ ያልተረጋገጡ የስማ በለው ወሬዎችና የምርመራ ዘገባዎች በፍርድ ቤቶች ተቀባይነት ያላቸው ማስረጃዎች ተደርገው ይወሰዱ ነበሩ። በሁለቱም መሰል ሁኔታዎች የተከሳሽ ፍትሀዊ ፍርድ የማግኘትና ማስረጃውን የመሞገት መብት ጥያቄ ውስጥ የሚወድቁ ነገሮች ነበር።

አሁን የወጣው አዋጅ የስማበለው ወሬ ማስረጃ ተቀባይነት እንደሌለው የሚገልጽ ሲሆን የምርመራ ውጤቶችም ተቀባይነት የሚኖራቸው በተመሳሳይ መስፈርት ከተገመገሙ በኋላ እንደሆነ ይገልጻል። በህግ አስፈጻሚዎች የመረጃ ጠለፋ የሚገኙ ማስረጃዎችም ራሳቸው መረጃወቹ ሲቀርቡ ብቻ ነው ተቀባይነት የሚኖራቸው። ቀደም ሲል ፖሊስ በመጥለፍ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ የብሔራዊ ደኅንነት አገልግሎት የሚጽፈው ዘገባ በቂ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።

እነዚህ ማሻሻያዎች በቀላሉ ሊታዩ የማይችሉ ቢሆኑም አሁን ያለውን ህግ መንግስት ከህግ አግባብ ውጭ መንግስትን የሚተቹ ሰዎችን ለማፈን ጥቅም ላይ ሊያውለው ይችላል። አንዳንድ ህጎች ለሰፊ ትርጓሜ የተጋለጡ ሲሆኑ የፀረ-ሽብርተኝነት ህጉ አያካትታቸውም ተብለው የተዘረዘሩ ነገሮች ሃሳብን በነፃነት ለመግለጽ መብት ሙሉ ለሙሉ ዋስትና የሚሰጡ አይደሉም።

የተቃውሞዎችና የስብሰባዎች ህጋዊነት አሁንም ቢሆን የመንግስት በጎ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ ሲሆን የተቃውሞ አስተባባሪዎች ቀደም ብለው ስለተቃውሞው ማሳወቅ አለባቸው፤ ባለስልጣናትም ሊቃወሙት አይገባም። ምንም እንኳን አዲሱ ህግ ከቀድሞው ህግ ጋር ሲተያይ አንድ እርምጃ ወደ ፊት የተራመደ ቢሆንም ችግሮች አሉበት።

አምሃ መኮንን ጠበቃ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እንዲሁም አሁን በተሻሻለው የቀድሞው ፀረ-ሽብር ህግ ለተከሰሱ 100 ተከሳሾች ጥብቅና የቆሙና የ2012 ዓ.ም ህግን ካረቀቁ ሰዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን የሚከተለውን ይላሉ፡ “ፀረ-ሽብር ህጉ ላይ የተደረገው መሻሻል አንድ ትልቅ እርምጃ ሲሆን ይህም ህጉ አላግባብ ሊውልበት ይችልበት የነበረውን ክፍተት በተወሰነ መጠን ይቀንሰዋል፥ ነገር ግን ህጉ ብቻውን የመንግስት ጣልቃ ገብነትንና ህግን ያለአግባብ መጠቀምን ስለማይከላከል መንግስት የዜጎችን መብት ማክበርና ህጉን አላግባብ ከመጠቀም መቆጠብ አለበት።”

የመገናኛ ብዙኃን ህግ

የመገናኛ ብዙኃን ህግ ማሻሻያ ያተኮረው ሁለት ህጎች ላይ ሲሆን እነሱም የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ተደራሽነት አዋጅ (590/2008) እና የብሮድካስት አገልግሎች አዋጅ (አዋጅ 533/2007) ናቸው።

ቀደም ሲል የነበረው ህግ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽን መብት የሚከለክሉ ደንጋጌዎች የነበረው ሲሆን ፤ህጋዊ ያልሆኑ ተግባራትን ማነሳሳትን፣ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨትን፣ ስም ማጥፋትና የጥላቻ ንግግር ማሰራጨትን ግልጽ ባልሆነና በሰፊ መንገድ ወንጀል እንዲሆኑ በማድረጉ ይተቻል።

አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/2021 የስም ማጥፋት ከወንጀል የማይፈረጅ እንደሆነ የሚደነግግ ሲሆን ይህም የመንግስት የህግ አውጪ፣አስፈጻሚ እና ተርግዋሚ አካላት ላይ የሚሰነዘርን የስም ማጥፋት ያካትታል። በአዲሱ ህግ ስር የስም ማጥፋት የፍታብሄር ተጠያቂነትን ብቻ የሚያስከትል ሲሆን ለዚህም የሚከፈለው የካሳ ክፍያ ቀደም ሲል በነበረው ህግ ይከፈል የነበረውን አንድ ሶስተኛ ነው።

በአዲሱ ህግ የብሮድካስት ባለስልጣን የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በሚል በድጋሚ የተቋቋመ ሲሆን የአስተዳደር ቦርድ አባላቱም ከምንም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው አይገባም። አዲሱ አዋጅ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሚያደርግ ሲሆን ቀድም ሲል በነበረው ህግ የብሮድካስት ባለስልጣን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነበር።

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ግንቦት 16 ባወጣው መግለጫ መንግስት ለፕሬስ ነጻነትና ሃሳብን በነፃነት ለመግለጽ ያለውን ቁርጠኝነት በመግለጽ አሁን ያለው አስተዳደር የታሰሩ ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን ከእስር እየፈታ እንደሆነ ጠቁሟል። ባለስልጣኑ በተጨማሪም ቀደም ሲል በነበረው ህግ ተካተው የነበሩ እገዳዎች እንደተነሱና አዲሱ ህግ ለውጭና የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ለመረጃ የተሻለ ተደራሽነትን እንደሚሰጥ ገልጿል።

የቀድሞው ህግ የውጭ ዜጎች የመገናኛ ብዙሃን ባለቤት እንዳይሆኑ የሚያግድ የነበረ ሲሆን አሁን ያለው ህግ ግን የውጭ ዜጎች በከፊል የመገናኛ ብዙሃን ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ይፈቅዳል። አሁን የውጭ ዜጎች የመገናኛ ብዙሃንን 25 ፐርሰንት መጋራት ይችላሉ። ነገር ግን አሁን ያለው ህግ በብሮድካስት አገልግሎት ውስጥ ድርሻ ያላቸው የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኢትዮጵያውያንን ብቻ ያቀፉ መሆን አለበት ይላል።

የድረ-ገጽ የመገናኛ ብዙሃንም አሁን ባለው ህግ ነው የሚተዳደሩት። ቀደም ሲል የነበሩ አዋጆች ስለድረ-ገጽ የመገናኛ ብዙሃን ምንም የጠቀሱት ነገር የለም አሁን ግን የድረ-ገጽ የመገናኛ ብዙሃን ቁጥጥር የሚደርግባቸውና ፍቃድ የሚያገኙበት መንገድ ከሌሎች መገናኛ ብዙሃን ጋር ተመሳሳይ ነው።

በተጨማሪ የብሮድካስት ባለስልጣን ያልተገደበ ስልጣን ስለነበረው የምዝገባና የፍቃድ ሁኔታዎችን በመጠቀም ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሃን እንዳይኖር ያደርግ ነበር። ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ተገቢ ፍቃድና የምዝገባ ማረጋገጫ ከመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

ይህ ባለስልጣኑ ለመገናኛ ብዙሃን ፍቃድ ለመስጠት የሚያስችለው ያልተገደበ ሰፊ ስልጣን በአዲሱም ህግ ቀጥሏል። አዲሱ ህግ የመገናኛ ብዙሃን ፍቃድ ለማውጣት መስፈርቶችን ያስቀምጣል ነገር ግን ዝርዝሩ የተሟላ አይደለም እናም የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በመመሪያዎችና ደንቦች ላይ ተመርኩዞ ተጨማሪ መስፈርት የማስቀመጥ መብት አለው።

በፍትህ አማካሪ ጉባኤ የሚሰራው የመገናኛ ብዙሃን ማሻሻያ የጥናት ቡድን ሊቀመንበር የሆነው ሰለሞን ጎሹ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ሲናገር ‘’ጣልቃ ገብነትንና ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀምን ያበረታቱ የነበሩ ግልጽ ያልሆኑና አሻሚ ድንጋጌዎች በአዲሱ ህግ ላይ ተሻሽለዋል። በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣናት የሚሾሙት በስራው ባላቸው ብቃትና ልምድ ነው’’ ብሏል።

በቂ ለመሆን እጅግ የሚቀረው ማሻሻያ

ከላይ የተዘረዘሩት ህጎች የመሻሻላቸው ነገር ምንም እንኳን እንከን የሌለበት ባይሆንም ጥሩ ጅማሬ ነው። ኢትዮጵያ ኢንሳይት አሁን ባለው የህግ ማሻሻያ ተግባራት ላይ ምን አይነት ጉድለቶች እንዳሉ ስሜነህ ኪሮስን ጠይቆ ነበር። ስሜነህ ሲመልስ ‘’መሻሻያው የተጀመረው መልካም ሃሳብ በማሰብ ነው፥ ነገር ግን ቀድሞ በነበሩ ተቋማት የሚተዳደር ሲሆን የተወሰኑትም ያለፈውን አስተዳደር አስተሳሰብ ያያዙ ናቸው። በሃላፊነት ስፍራዎች ላይ ያሉ ሰዎችም እምብዛም አልተቀየሩም፣ አብዛኞቹ ባለስልጣናትም ከቀድሞው የገዢው ፓርቲ የተውጣጡ ናችው’’ ብሏል።

‘’ምንም እንኳን በርካታ ተቋማትን ከፖለቲካ ተጽእኖ ለማላቀቅ ጥረቶች ቢኖሩም የተቋማቱ የተወሰኑ ባለስልጣናት ይህን ለመቀበል ከብዷቸዋል። የፌደራል ዐቃቤ ህግና የስራ ባልደረቦቹ የማሻሻያ ሂደቱ በቀና መንገድ እንዲያመራ ለማድረቅ እቅድ ያላቸው ቢሆንም አላማቸውንና ሃሳባቸውን ዝቅ ባለ ደረጃ ያሉ ባለስልጣናት የሚጋሩት አይደለም’’ ይላል ስሜነህ።

ሌሎች የተቀየሩና እየተቀየሩ ያሉ ህጎች ሙሉ ለሙሉ አጥጋቢ አይደሉም። ለምሳሌ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የመገናኛ ብዙሃን ህጉ እንደገና መታየት አለበት።

እነዚህ ህጎች እንዴት ነው ተግባር ላይ የሚውሉት የሚለውም ሌላው ትልቅ ጥያቄ ነው። ሰብዓዊ መብትን ለማስጠበቅና ዲሞክራሲን ወደ ፊት ለማራመድ ተግባር ዋነኛው ነገር ነው። አባባሉ እንደሚለውም ‘’ነፃነት የሚገኘው ሁልጊዜ ንቁ በመሆን ነው።”

Query or correction? Email us

Follow Ethiopia Insight

ይህ ጽሁፍ ምርጫ 2013ን በሚመለከት ዘለግ ያሉ ጽሁፎችን ከመላው ኢትዮጵያ በተከታታይ የምናቀርብበት የ “Ethiopia Insight Election Project (EIEP)” ክፍል ነው።

ዋና ምስል: የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በስብሰባ ላይ፥ ሰኔ 24፣ 2011፥ ሮይተርስ።

Join our Telegram channel

Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished.

We need your support to analyze news from across Ethiopia
Please help fund Ethiopia Insight’s coverage
Become a patron at Patreon!

About the author

Leul Estifanos

Leul is a freelance court reporter and a law graduate of Addis Ababa University. He previously worked as a case reviewer at the Public Procurement and Property Disposal Service.

Leave a Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.