Ethiopian language Viewpoint

የኮሮና በሽታን ለማሸነፍ ኢትዮጲያውያን ከሌሎች ሀገሮች መማር አለባቸው

“እንደ ኢትዮጲያ ያሉ ደሃ ሀገሮች ፈፅሞ-ከቤት-ያለመውጣት ክልከላ (“ሎክ ዳውን”) ሊያደርጉ አይችሉም፣ የኑሮ ዘይቤያቸውም ሆነ ድህነታቸው አይፈቅድም” ከተባለ ይህን የሚተካ እርምጃ የመውሰድ ሀላፊነት ተጨመረልን እንጂ ነገር ቀለለ ማለት አይደለም።

ትዮጲያ የምታደርገው ምርመራ በቁጥር ትንሽ ቢሆንም እሱም እንደሚያሳየው የኮሮና በሽታ አምጪ ተህዋስ ከአዲስ አበባ አልፎ በኢትዮጲያ እየተዛመተ ስለሆነ በሽታውን ለመቆጣጠር ከሌሎች ሀገራት ስህተት እና መልካም ውጤት መማር እጅግ አስፈላጊ ነው።

ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የገቡባቸውን ህንፃዎች በሙሉ ለሁለት ሳምንት ዘግታለች። የአለማችን መንግስታት በሽታውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ወይ 1) እንደ ደቡብ ኮሪያ ፈጣን እና ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ በብዛት መመርመር፣ በሽታው ከያዛቸው ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸውን ተከትሎ የመለየት እና ቀሳ የማስገባት ስራ በስፋት እንዲሰራ አድርገዋል፣ ወይም 2) እንዲህ አይነት ውሳኔ ለመስጠት ሲያወላውሉ ችግሩ ከፀናባቸው በኋላ ኢኮኖሚያቸውን የሚገሉ ፈፅሞ-ከቤት-ያለመውጣት-ክልከላዎችን ለማወጅ ተገደዋል።

ኢትዮጲያ ሁለተኛውን አካሄድ እየተከተለች ነው። የሚደረጉት ምርመራዎች ጥቂት ናቸው፣ የተወሰዱት እርምጃዎችም ልል ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ እንደተገነዘቡት፣ እንደ ኢትዮጲያ ያሉ ደሃ ሀገሮች ፈፅሞ-ከቤት-ያለመውጣት ክልከላ የኑሮ ዘይቤያቸውም ሆነ ድህነታቸው አይፈቅድም። ግን ደግሞ ኢትዮጲያ አሁን እየተከተለች ያለችው ወላዋይ አካሄድም መጨረሻው ያው ነው። ኢትዮጲያ ጥሬ መረጃ በስፋት የላትም፣ አማራጮቿ ጥቂት አደጋዎቿ ብዙ ናቸው፣ ስለዚህ ሀገራዊ በሽታውን የመከላከል ስራው ፈፅሞ-ከቤት-ያለመውጣት ክልከላን ሊቀንስና ሊያስቀር በሚችል መልኩ መጠናት እና መዘየድ አለበት ማለት ነው።

በአለም ላይ ከሳይንሱ እኩል ፖለቲካውም በሽታውን ለመግታት የተደረገው ጥረት ውስጥ ሚና ነበረው። የወረርሺኙ ፍጥነት መድሐኒት የሚሰራበትን ፍጥነት በብዙ አጥፎት፣ መድሐኒት ፈጣሪ ድርጅቶችን አደናብሯል፣ ጤና ጣቢያና ሆስፒታሎች ደግሞ ከአቅማቸው በላይ ሆነዋል። እንደ እንግሊዝ፣ አሜሪካና ቻይና ያሉ ጠንካራ የጤና ስርዓት ያላቸው ሀገራት እንኳን መቋቋም አቅቷቸዋል።

ቻይና ዶክተሮቿ ስለችግሩ ለዓለም እንዳያሳውቁ ሞክራለች፣ ታይዋን በክልሏ ስለተከሰተ ምንነቱ ያልታወቀ ኒሞኒያ በሽታ ለአለም የጤና ድርጅት እንዳታሳውቅ አድርጋለች፣ አሁንም ቢሆን በበሽታው ዙሪያ መረጃና ሳይንሳዊ ምርምርን እያደናቀፈች ትገኛለች። እንግሊዝ ደግሞ ሰዎች በሂደት በሽታውን  “በመንጋ የመቋቋም ችሎታ” (“ኸርድ ኢሚዩኒቲ”) ያዳብራሉ ብላ ለወራት ምንም እርምጃ ሳትወስድ ቀርታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ሲበዛ ብቻ ነበር እርምጃ ወደመውሰድ የገባችው።

አሜሪካ በበኩሏ መጀመሪያ ችግሩን አቃለለች፣ ከዘገየ በኋላ ደግሞ የጉዞ እገዳዎችን ጣለች። አሁን ግን አሜሪካ በነፍስ ወከፍ ከቻይና 24 እጥፍ የሚሆን ህዝቧ በኮሮና ተይዟል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ የችግሩ ግዝፈት የተገለፀላቸው በሰፈራቸው ያሉ ሆስፒታሎች አስከሬኖችን ለማስወገድ ምግብ ለማጉዋጉዋዝ የሚያገለግሉ ባለፍሪጅ መኪናዎችን ሲጠቀሙ ባዩ ጊዜ ነበር። አሁን “አሜሪካ ውስጥ በኮሮና የሚሞቱ ሰዎች ከ100-200,000 ካልበለጠ ተመስገን የሚባል ነው” ማለት ላይ ደርሰዋል። ፖለቲከኞች ለነሱ የሚመቻቸውን አካሄድ እስከሚያስቡ የሚጠፋው ጊዜ በሽታው አንድን ሰው ይዞ እስከሚገድለውና በሽታው ሀገር ውስጥ ራሱን እንደአዲስ ለማማከል ከሚፈጀው ጊዜ ይበልጣል።

የኢራን ማመንታት

በዚህ ላይ ደግሞ የመንግስትና የኢኮኖሚ አቅም ደካማ ከሆነ የችግሩ ብዛት ልብ ያዝላል። ኢራን የሆነው ይህ ነው።

በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ሌሎች ሃይማኖተኛ መንግስታት በፍጥነት የውስጥና የውጪ ድንበሮቻቸውን እና የሃይማኖት ጉዞዎችን ሲዘጉና ከበሽታው ራሳቸውን ሲከላከሉ፣ በሽታው መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ መጀመሪያ የገባው ኢራን ቢሆንም፣ ኢራን ለመወሰን አመነታች። መጀመሪያ ችግሩ ሀገር ውስጥ መከሰቱን ሸፋፈነች፣ ከዚያ ኮሮና የአሜሪካ ባዮሎጂካዊ ጥቃት ነው አለች፣ በመጨረሻ ደግሞ በሽታውን ለመከላከል የሚሰራው ፀሎት ነው አለች። አሳሳች መረጃው አላዋጣ ሲል ፕሬዝዳንት ሃሳን ሩሃኒ ለፖለቲካቸው ቀላል የሆነላቸውን ውሳኔ ወሰኑ። አስፈላጊ ያልሆኑ ንግድ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲዘጉና ባይተገበሩም የጉዞ እገዳዎችን ጣሉ። ኮም የተባለችው ከተማ ለሀገሪቱ የኮሮና ማሰራጫ ማእከል እንደሆነች ግልፅ ቢሆንም፣ የሃይማኖት መሪዎች በከተማዋ ያሉ የሃይማኖት ቦታዎች አይዘጉም ሲሉ መንግስት ዝም ነበር ያለው። በአጭር ጊዜ ውስጥ በሽታው በመላ ሀገሪቷ ከተዳረሰ በኋላ ከተማዋን መዘጋት ብዙም አልጠቀመም።

ፕሬዝዳንት ሩሃኒ የተዳከመው የኢራን ኢኮኖሚና ማእቀቦች ላይ አሳበቡ። ይህ እውነትነት ቢኖረውም፣ የፕሬዝዳንቱም ነገሩን የፖለቲካ ጉዳይ ማድረግና አጉል የሀገር ኩራት ይዟቸው የውጪ እርዳታ አልቀበልም ማለት ሌላ ጥፋት ነበር። በሚዲያ የሚቃወመው ሲበዛባቸው፣ የጦር ሀይሎቹም ተደረቡባቸው። በዚህ ጊዜ የሀገሪቱ የበላይ መሪ ስልጣን ለጦር ሀይሎቹ ሲሰጡ በሽታውን ለመከላከል የህዝቡ እንቅስቃሴ ላይ ጥብቅ ክልከላዎች ማድረግ አለብን እያሉ መከራከር ጀመሩ።

ሩሃኒ ሽንፈት ስለሆነባቸው እንቢ አሉ። የአለም የጤና ድርጅት በኢራን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በይፋ ከተነገረው አምስት እጥፍ አካባቢ እንደሚሆን ይገምታል። በይፋ እንደተነገረው 3,300 ሰዎች ሞተዋል ቢባልም የቪዲዮ እና የሳተላይት ምስሎች የሚያሳዩት የአስከሬኖች እና መቃብሮች ብዛት ኢራን ችግሩን እየሸፋፈነች እንደሆነ ነው። በዚህ ሂደት መንግስት ተዓማኒነቱን ስላጣ ኢራናውያን የታወጁትን እገዳዎች ብዙም ማክበር አልቻሉም።

የኢራን የጤና ስርዓት ከኢትዮጲያ የጤና ስርዓት በጣም የተሻለ ነው። ግን የኢራን ልምድ፣ በሽታ መቆጣጠርን ትቶ ስለሌላ ሌላው ማውራት የሚያመጣውን አደጋ የሚያስተምር ነው። ድሮም ችግር ያለበት መሪ ከተቃዋሚ ቡድኖች፣ ኢኮኖሚ ወይም ተቀባይነት ከማጣት ጋር በተያያዘ በሽታው ሲከሰት የችግሩን መጠን ለመደበቅ መሞከሩ የማይቀር ነው። በበሽታው የተያዙት ሰዎችን ቁጥር አሳንሶ መናገርም ጤና ስርዓቱ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ እንዳይታይ ይሸፍናል፣ የውሳኔ ሰጪነትን ችግር ይደብቃል፣ የሰዎች ኑሮ እና ኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰው ጫናም ለጊዜው ይቀንሳል።

የሰው ልጆች ለፖለቲካ አላማ ተብሎ የማያስተማምን መረጃ ተነግሯቸው አይደለም እንዲሁም ችግር በጣም አፍጥጦ ካልመጣ በስተቀር አደጋን ችላ የማለት ባህሪ አላቸው። ከዚያ በተሳሳተ መረጃ ጆሮው የዛለ ህዝብ ትእዛዝ አላከብር ሲል ለመንግስት አሳፋሪ ይሆናል ማለት ነው። ሀይልና ስልጣን ፈላጊ ቡድኖች ደግሞ አጀንዳቸውን የሚያግዝ ነገር አገኙ ማለት ነው። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የሟቾች ቁጥር አስደንጋጭ እየሆነ ቢመጣ መሪዎች ሽንፈት ስለሚሆንባቸው “ትክክለኛው አካሄድ ይህ ነው። የእስካሁኑ ስህተት ነበር” ለማለት አይፈልጉም።

አሁን አሁን የኢትዮጲያ ፖለቲከኞች የችግሩን ክብደት እየተረዱ የመጡ ይመስላል፣ በየእለቱ ጤና ሚኒስቴር መግለጫ ይሰጣል፣ የኢንተርኔት ውይይትም ይካሄዳል። ግን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ለማመን በሚከብድ መልኩ ትንሽ ነው፣ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችም በቂ አይደሉም። ሀኪሞችና ነርሶች ኮሮናን እየተጋፈጡ ያሉት በአንድ፣ እሱም በበቂ ሁኔታ ደህንነታቸውን በማይጠብቅ፣ አንዴ ብቻ ተጠቅሞ በሚጣል ጭምብል (“ማስክ”) ነው። የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ታካሚዎችን ይፈራሉ፣ ራሳቸውም በሽታውን ሊያስተላለፉ የሚችሉ ስጋት ናቸው። በዚህ ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ ከተማውን ከበሽታ አምጪ ተህዋሶች አፀዳለሁ እያለ በየቦዩ መድሐኒት ይረጫል፣ ሰዎች መንገድ ለማፅዳት በነቂስ እንዲወጡ ያበረታታል።

እንደዚህ ያለ የተሳሳተ አካሄድ ለማንኛውም ሀገር አደጋ ነው። እንደ ኢትዮጲያ ላሉ ሀገሮች ደግሞ የበለጠ አደጋ ነው ምክንያቱም የጤና ስርዓቱ በቋፍ፣ የማህበራዊ ዳረጎት ስርዓቱ ስስ፣ ነባር የጤና ችግሮች ያሉዋቸው ሰዎች ብዙ፣ ከቤት ሆነው መስራት የሚችሉ ወይም ሳይሰሩ መብላት የሚችሉ ሰዎች ጥቂት፣ ብዙዎች የሚኖሩት በተጨናነቁ እና ብዙ የቤተሰብ አባላት ባሉባቸው ቤቶች ውስጥ ስለሆነ ነው። ኢትዮጲያ አንድ ያላት ነገር ቢኖር ሰዎች በአካል ተገናኝተው በሽታውን አንዱ ለአንዱ እንዳያስተላልፍ ማድረግ ብቻ ነው።

ፈጣን እርምጃ

ደሃ ሀገሮች ፈፅሞ-ከቤት-ያለመውጣት ክልከላ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚቋቋሙበት አቅም የላቸውም የሚለው የውይይት ነጥብ በጣም አስፈላጊ ነው። ግን ደግሞ በመረጃ ሊደገፍ የማይችል ሲሆን በደፈናው “ነው” ተብሎ ከተወሰደ ደግሞ ለበሽታው ከፍ ያላ ተጋላጭነት ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጲያውያንን እጣ ፈንታ ላይ የሚፈርድ ሃሳብ ነው። ሃሳቡ በተዘዋዋሪ በደሃና ደካሞች ላይ ሊመጣ የሚችለውን መሰረታዊ የምግብ ችግር ሊያስቀር የሚችል እርምጃ በአፋጣኝ እንዲወሰድ የሚከራከር ነው። ወይም በሌላ አገላለፅ እርምጃ መውሰድም ሆነ አለመውሰድ በምንወዳቸው ሰዎች ህይወት ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል የሚያሳይ ነው። በቂ እርምጃ አለመውሰድን እና ጉዳዩን የፖለቲካ ጉዳይ ማድረግን በፅኑ የሚቃወም ሃሳብ ነው።

በሽታውን ለመቆጣጠር ኢትዮጲያ ልትወስድ የምትችላቸው እርምጃዎች አሉ። እየተተገበሩ ያሉም ፖሊሲዎች አሉ ለምሳሌ የጉዞ እገዳዎች፣ መጠጥ ቤቶችን መዝጋት፣ ትምህርት ቤቶችን እና ዩኒቨርሲቲዎችን መዝጋት፣ የማረሚያ ቤቶችን መጨናነቅ መቀነስ እና ከውጪ ሀገር የሚገቡ መንገደኞችን በግዴታ ቀሳ ማስገባት። ግን እነኚህ እርምጃዎች ተቃውሞ ሊያስነሱ የማይችሉ አይነትና ፕሬዝዳንት ሩሃኒ በኮም በሽታው ሲዛመት የወሰዱትን ወላዋይ እርምጃ ይመስላል። በብዙ ሀገሮች ችግር እንዳየነው፣ የግማሽ ልብ ውሳኔ መጨረሻው መራራ ነው። የደሃ ኢትዮጲያውያን ቁጥር መብዛት እና የሚብሰውን ማበላለጥ ማስፈለጉ በራሱ ጥብቅ ክልከላዎች፣ እገዳዎችና እርምጃዎችን መውሰድ በጣም አስፈላጊ ያደርገዋል።

ከአዲስ አበባ ውጪ በሽታው ስምንት ሰዎች ውስጥ ተረጋግጧል። የኮሮና ተህዋስ ሳናውቀው በሀገሪቷ እየተዛመተ እንደሆነ ብዙ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። የበሽታውን ምልክት ከሚያሳዩት ውስጥ የተወሰኑት ብቻ ሲሆኑ የሚመረመሩት እንደሚታወቀው ሰዎች በኮሮና ተይዘው ምንም ምልክት ሳያሳዩ (ግን ለሌሎች እያስተላለፉ) ለ14 ቀናት ሊቆዩ ይችላሉ፣ ምልክት ማሳየት ሲጀምሩም ቀለል ያለ ጉንፋን ብቻ ሊመስል ይችላል። ግን አሁንም ቢሆን የኢትዮጲያ አንዳንድ የገጠር ክፍሎች ውስጥ እስከ አሁን ድረስ ኮሮና አልደረሰም ብሎ መውሰድ ይቻላል።

ቤላ፥ አዲስ አበባ  ፎቶ በዊሊያም ዴቭሰን መጋቢት 23፥ 2012 ዓ.ም.

ከከተማ በተራቀ ቁጥር፣ የጤና ስርዓቱ እየደከመ፣ ሰዎችም ምግብ የሚቸገሩበት እድል እየሰፋ ነው የሚሄደው። እቃዎችና እርዳታን ከመሳሰሉ አስፈላጊ ነገሮችን ለማጉዋጉዋዝ ካልሆነ በስተቀር ሙሉ የጉዞ እገዳ የበሽታውን መዛመት ገትቶ ኢኮኖሚው ግን ብዙ እንዳይጎዳ ሊረዳው ይችላል። አንዳንድ ክልሎች የህዝብ ትራንስፖርትን ቢከለክሉም የአየር እና የግል ጉዞን መፍቀድ አሁንም ቢሆን በሽታውን ያዛምታል። እንቅስቃሴዎችን ሙሉ በሙሉ አሁን ማቆም በበሽታው ያልተነኩ ቦታዎች ጋር እንዳይደርስ ሊያደርግ ይችላል። በሽታ አምጪ ተህዋሱ በተወሰነ ክልል ገድበን እንዳይወጣ ማድረግ ከቻልን፣ በኋላ ላይ ፈፅሞ-ከቤት-ያለመውጣት ክልከላ ቢያስፈልግ ይህ ክልል ብቻ ላይ ተለይቶ ይተገበራል ማለት ነው፣ ይህም ኢኮኖሚውና ደካሞች ላይ የሚመጣውን ጫና ይቀንሳል። የበሽታው ምልክቶች እና ሞት እስኪመዘገብ ከጠበቅን፣ ተህዋሱ ብዙ ቦታ ደርሶና ጉዳት አድርሶ ነው የምናገኘው።

በተህዋሱ የተበከሉ ቦታዎች ውስጥ ማህበራዊ እንቅስቃሴ መቆም አለበት። ሰዎች እየሞቱ ነው። እንግሊዝ ምንም አይነት እርምጃ መውሰድ አያስፈልግም ከማለት የ13 ዓመት ህፃን ፈፅሞ-ከቤት-ያለመውጣት ክልከላውን ተላልፏል ብላ ወደ ማሰር የደረሰችው በሁለት ሳምንት ልዩነት ነው። አሁን ቤተሰብ መጎብኘት እንኳን አይፈቀድም። ኢትዮጲያ ውስጥ ጥብቅ የሆኑ እገዳዎችን ማወጅ ሲያስፈልገን፣ ይሄ በራሱ ሰዎችን ለሞት እንደሚዳርግ ስለምናውቅ፣ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ በጣም አስፈላጊ ነው። በአሁን ሰዓት ሀይማኖታዊ መሰባሰቦች አዲስ አበባ ውስጥ በአብዛኛው ቆሟል፣ በሽታው በታየበት ሁሉም ሊቆም ይገባል። ይህ ነገር ሲያልፍ ደካሞች ተመልሰው ሰርተው ወደመብላት እንዲመለሱ ከፈለግን ለአስገዳጅ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር ከቤት መውጣት በአስቸኳይ መቆም አለበት።

ኮሮና በሽታ ላይ የትምህርት ዘመቻዎች በፍጥነት መጀመር አለባቸው። እየተሰሩ የነበሩ እጅ የመታጠብና ንፅህና አጠባበቅ ፕሮጀክቶች ተስፋፍተው መቀጠል አለባቸው። ኢትዮጲያውያን በህይወታቸው ውስጥ በብዛት የሚያደርጉዋቸው ተግባሮች ላይ መመሪያ ማውጣትና በሚዲያ ማስተላለፍ ያስፈልጋል፣ ለምሳሌ በትሪ ሳይሆን በየራስ ሳህን መመገብ፣ ተህዋሱን ላለማስተላለፍ እንጀራ ስንይዝ እንዴት መሆን እንዳለበት፣ አዛውንትና  ደካሞች ከብዙ የቤተሰብ አባላት ጋር በሚኖሩባቸው ቤቶች ውስጥ በሽታው ቢከሰት ምን ማድረግ እንዳለብን፣ በፆም ወቅት እንዴት መመገብ እንዳለብን እና ከቤት ሳይወጡ የአካል እንቅስቃሴ እንዴት እንደሚደረግ። ባጠቃላይ ተጠንቅቆም ቢሆን ከቤት መውጣት አደጋ እንደሆነ፣ ለቅሶና ቀብር ላይ በአካል ሳይገኙ እንዴት የሃዘን ተካፋይ መሆን እንደሚቻልና ከቤት ሳይወጡ መንፈሳዊ ህይወት ሊቀጥል እንደሚችል ማስተማር ያስፈልጋል። ሰዎችን ማስፈራራትና ማሸበር፣ ሰዎች “ቤተክርስትያን መሄድ አለብኝ” እንዲሉ የሚያደርጋቸው ከሆነ አይሰራም። ከዚያ ይልቅ ኢትዮጲያውን ለእርስ በርስ ያላቸው አዛኝነትና ያላቸውን ችግርን የመቋቋም ችሎታ መጠቀም አለብን።

በገንዘብ ኖቶች እና የክፍያ ሰልፎች በሽታው እንዳይዛመት ከባንኮች ሌላ የገንዘብ ድርጅቶች የስልክ ክፍያ አገልግሎት እንዲሰጡ የተፈቀደውን መመሪያ ኢትዮ-ቴሌኮም በአስቸኳይ መተግበር አለበት። ይሄን ማድረግ ሰዎች ከቤት ሳይወጡና የሰዎችን ጤና አደጋ ላይ ሳይጥሉ የገንዘብ አገልግሎት ሰዎች እንዲያገኙ ያደርጋል።

ሀብታም ሀገሮች እንደሚያደርጉት ጥራቱን የጠበቀና በጣም ብዛት ያለው ምርመራ ለማድረግና በበሽታው ከተያዙት ጋር ንክኪ የነበራቸውን ተከትሎ የመለየት ስራ በሰፊው ለመስራት ኢትዮጲያ አቅም የላትም። ረከስ ያለ መመርመሪያ በብዛት ሲመረት ይህን ማድረግ ይቻል ይሆናል። ቴክኖሎጂ ግን ውድ ያልሆኑ በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ አገልግሎቶች አሉት። “ትሬስ ቱጌዘር” የሚባል መተግበሪያ በሲንጋፖር መንግስት ስራ ላይ የዋለ ሲሆን አንድ ሰው በተህዋሱ እንደተያዘ ሲረጋገጥ አብሯቸው ሰላሳ ደቂቃ አካባቢ ጊዜ ያጠፉትን ሰዎች በሙሉ መንግስት መረጃውን የሚያየው ይሆናል። ንክኪ የነበራቸው ሰዎች በሙሉ ይገኛሉ፣ ይደወልላቸዋልም። ደቡብ ኮሪያ የሁሉንም ነዋሪዎችዋን እንቅስቃሴ በቴክኖሎጂ እየተከታተለች በበሽታው የተያዘ ሰው ሌላ ከተማ ወይም አካባቢ ሲገባ በዚያ አካባቢ ላሉ ሰዎች በሙሉ መልእክት ይላክላቸዋል። በሽታው የመዛመት እድሉ የማይተዋወቁ ሰዎች በብዛት በሚገናኙበት በከተማ አካባቢ ነው፣ ስማርት/ተች ፎን የሚበዛውም ከተማ ነው። “ትሬስ ቱጌዘር” የሚባለው መተግበሪያ ደግሞ ይጠቅማል፣ አውርዶ በነፃ ለመጠቀም ዛሬም ክፍት ነው።

ኤል ሳልቫዶር ሁሉንም የመብራት፣ ውሃ፣ የቤት እዳ፣ የባንክ እዳ፣ የስልክና ኢንተርኔት ክፍያዎችን ለሦስት ወር እንደማትጠይቅ ተናግራለች። እዚህ እንደዚያ ማድረግ ላይቻል ይችላል፣ ግን ተመሳሳይ እርምጃዎች ባንኮች ውስጥ ለወረፋ ሰዎች እንዳይሰበሰቡ ያደርጋል። ሁሉንም የትምህርት መፅሐፎች ኢንተርኔት ላይ አድርጎ እነሱን ማውረድ ኢቲዮ-ቴሌኮም ነፃ ሊያረገው ይችላል። ይህን ማግኘት ለማይችሉት ደግሞ የታተሙ መፅሐፎች በቶሎ እንዲደርሷቸው ማድረግ ያስፈልጋል።

ደሃ ሀገሮች በዚህ ወረርሺኝ የተነሳ የሚመጣባቸው ችግር ገና ሙሉ በሙሉ አይታወቅም፣ አንዱ እንደዚህ ስለሆነ ሌላውም እንደዛ ይሆናል ማለት አይቻልም። ግን ደግሞ ሀብታም ሀገራት ፈፅሞ-ከቤት-ያለመውጣት ክልከላን እየተገበሩ፣ ጠንካራ ማህበራዊ፣ መንግስታዊና የጤና ስርዓት አደረጃጀት ኖሯቸው እንኳን እነሱን አያርገን የሚያስብል መከራ እያሳለፉ ነው። የደሃ ሀገሮች የፖለቲካ፣ የመረጃ አቅርቦት እና ውሳኔን ተግባራዊ የማድረግ ችግር ሲታሰብ የበለጠ መከራ ይጠብቃቸዋል ያስብላል። ደሃ ሀገሮች ብዙ ህዝባቸው በህይወት እና ሞት መሃል አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ድህነት ላይ ስለሆነ ያሉት ትንሿ ስህተት ገደል ልትከታቸው ትችላለች።

Follow us on Twitter @EthiopiaInsight and join our Telegram channel here

አዘጋጅ: ዊሊያም ዴቭሰን. Translated by Linda Yohannes ትርጉም በሊንዳ ዮሐንስ

ዋና ፎቶ: መኪና ፀረ-ተዋህስያን የአዲስ አበባ መንገድ ላይ ሲረጭ፤ የካቲት 22 የገባ

በኢትዮጲያ ውስጥ ስላለው የኮሮና በሽታ ሁኔታ ወቅታዊ መረጃ እዚህ ያገኛሉ፥

Query or correction? Email us

Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished. 

Related Insight

13 April 2020 COVID-19 state of emergency and the federal balance of power

8 April 2020 Dealing with COVID-19’s impact under Ethiopian labor law

3 April 2020 Ethiopia needs a State of Emergency to combat COVID-19

1 April 2020 Ethiopia’s COVID-19 quandary

We need your support to deliver news from across Ethiopia

Become a patron at Patreon!

About the author

Chris Preager

Chris has degrees in computer science and international development, and works applying technology to development issues. He has lived in Addis Ababa since 2012. Follow him on Twitter @technicaltitch

  • With all due respect, I don’t see the relevance of the Iranian case for us. Every country has unique challenges and circumstance and Iran is not an exception. It could be true try that Iran has underestimated or minimized the number of infected people just like others did such as China and the USA. They did it for economic, political and strategic reasons and it has nothing do with theocracy or anything . Besides this pandemic has caught many nations with little notice or surprise, especially in its early phase. They had little time to prepare for it or experience to go by.. I believe in this second phase countries like Ethiopia have plenty of time to mobilize whatever resources they can mount against it and see the devastation that lies ahead. Urban areas should be primary target for the fight before it spreads further into the countryside.

Leave a Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.