Elections 2021 Ethiopian language In-depth

በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ውስጥ የአማራ ብሔርተኝነት

ሌላ የዘር ብሔርተኝነትን መፍጠር ወይስ ወደ አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ማምራት?

የካቲት 23 ቀን ከሙሉዓለም አዳራሽ ውጭ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሰባስበዋል። ሙሉዓለም አዳራሽ ለታላላቅ የፖለቲካና የባህል ዝግጅቶች ተመራጭ አዳራሽ ሲሆን ከባህር ዳርቻ በምትገኘው የአማራ መዲና በሆነችውና ከክልል ከተሞች በህዝብ ቁጥር ብዛት ሁለተኛ ደረኛን በምትይዘው ባህርዳር የሚገኝ ነው። በደርዘን የሚቆጠሩ ያሸበረቀ ልብስ የለበሱ ፈረሰኞች የበዓል ድባብ ፈጥረዋል፤ ጥሩምባ እየተነፋ፤ የአገር ፍቅርን የሚያወሱ ዘፈኖችም እየተዘፈኑ ነው። ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢዋን ጣሊያንን በአድዋ ጦርነት ያሸነፈችበት 125ኛው አመት የማክበሪያ ስነ-ስርዓት ነበር።

ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሁል ጊዜ በህዳር የተመሰረተበትን በግንቦት ደግሞ ወደ ስልጣን የወጣበትን ጊዜ የሚያከብረው በዚሁ ሙሉዓለም አዳራሽ ነው። ብአዴን ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በ2012 ዓ.ም እስከ ሚፈርስ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግን) ሩብ ያህል የሚይዝ ፓርቲ የነበረ ሲሆን ኢህአዴግ ኢትዮጵያን በአምባገነንነት የመራና የተለያዩ ክልሎች ፓርቲ ኅብረት የነበረ ፓርቲ ነው።

ይህ አዳራሽ ተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሰኔ 3, 2010 ዓ.ም የመጀመሪያ ስብሰባውን ያደረገበትም ስፍራ ነው። ዝግጅቱም የዘር ብሔርተኝነት በይፋ የተስተዋለበት ነበር።
በመጋቢት ወር በመድረኩ ላይ አቶ አገኘሁ ተሻገር በኩራት ቆሙ፤ ስራ ከጀመረ ገና 4 ወሩ ነበር። በጭብጨባ ታጅበው ‘’የዚህ አመት ክብረ-በዓል የዘላለም ጠላታችንን በቀበርንበት ማግስት መከበሩ በዓሉን በጣም ልዩ ያደርገዋል።’’ በማለት አቶ አገኘሁ ተናገሩ። የዘላለም ጠላታችን ሲሉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሶስት አስርት አመታት ገደማ የበላይነትን ይዞ የነበረውን ህወሃትን ማለታቸው ነበር።
በህዳር ወር የህወሃት የክልል አስተዳደር ከኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ ገባ። ግጭቱ ከኤርትራ እንዲሁም አጎራባች ከሆኑት የአማራና የአፋር ክልሎች ታጣቂዎችን የጋበዘ ነበር።
‘’ትህነግን [ህወሃትን] በቀበርንበት ማግስት ይህን ቀን አስበን በመዋላችን እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ’’ አቶ አገኘሁ በድጋሚ ተናገሩ።

አቶ አገኘሁ ፕሬዝደንት ሆነው ሲሾሙ የትግራይ ቀውስ አራተኛ ቀኑን ይዞ ነበር። ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቅርብ አጋር አንዱ የሆኑትና አሁን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን የሚመሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህን ለተኩት ሰው ደግሞ የመጀመሪያው ስራ የአማራ ኃይልን ከፌደራል ሰራዊት ጋ በጋራ በመምራት የህወሃትን ሽንፈት ማረጋገጥ ነበር።
በሳምንታት ውስጥ የአማራ ኃይሎች በምዕራብና ደቡብ ትግራይ የሚገኙ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን ስፍራዎች መቆጣጠር ቻሉ። ስፍራዎቹ ለአማራ እንደሚገቡ የሚያውጁ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን አቆሙ እንዲሁም ጊዜያዊ አስተዳዳሪዎችን ሾሙ። በታህሳስ ወር መጨረሻ ቀደም ሲል የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ አገኘሁ ‘’የተቀማነውን ማንነት ለማስመለስ ነው የታገልነው። እዛ የሄድነው መሬት ፍለጋ አይደለም፤ የፍትህ ጥያቄ ነው’’ ሲሉ ተናገሩ።

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ: አዲስ ታሪክ ፍለጋ

በትግራይ የሚገኘው ግጭት ከብሔራዊው የሰኔ ምርጫ በፊት የአማራ ክልልን ለሚገዛው የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት እሙን ነበር።

የህወሃት መወገድ የበለጠ ድጋፍ ለሚያስፈልገው አማራ ብልጽግና ፓርቲ ጠቃሚ ነው፤ ስለዚህ ወታደራዊ አካሄድን መደገፉ እምብዛም አያስገርምም። አሁን በህይወት የሌሉት የቀድሞ የአማራ ፖሊስ ኃላፊ አበረ አዳሙ የአማራ ኃይል በትግራይ ድንበር አካባቢ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት መሰባሰቡን የገለጹበት ንግግር የትግራይ መንግስት የፌደራል መንግስትን በጥቅምት 24 ከማጥቃቱ በፊት ለግጭቱ ቢያንስ የተወሰነ ዝግጅት እንደተደረገ ይጠቁማል።

የአማራ ብልጽግና ባለፉት አመታት የተለያዩ ለውጦችን አስተናግዷል። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሆኖ የተመሰረተው ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅነው ድርጅች በ1980ዎቹ ጨካኙን ሶሻሊስት የደርግ አገዛዝ በመቃወም ከተመሰረቱት በርካታ የትጥቅ ትግሎች መካከል አንዱ ነው። ዘግየት ብሎ ከህወሃት ጋር በመዋኃድ ብአዴን የሚል ስም ተሰጠው፤ ይህም ደርግን ተክቶ ሲገዛ የነበረው የኢህአዴግ ኅብረት የአማራው ክንፍ ነው።

ፓርቲው ለውጡ ያስፈለገው ስማቸው በተደጋጋሚ ሲነሳና ያላግባብ ጥቅም ላይ ሲውል የነበሩትን ነገር ግን አሁንም በድህነት የሚዳክሩትን የአማራ ህዝቦች መሻሻል ለማረጋገጥ እንደሆነ ይናገር ነበር። አብዛኛዎቹ አማራዎች አላመኑበትም ነበር፤ የፓርቲው ተቺዎች ብአዴንን የህወሃት ሎሌ አድርገው ይመለከቱት ነበር ይህም በትግራይ የገዢ ፓርቲ ሃሳብ አመንጪነት የሚወጡ ፓሊሲዎችን በማስፈጸም ብቻ ሳይሆን እወክላቸዋለሁ የሚለውን ህዝቦች ታሪካዊ ጨቋኞች አድርጎ የሚፈርጅ የፖለቲካ አመለካከት በመከተሉ ነው።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ወጀብ በ2010 ተቀየረ።

ለዚህም ምክንያቱ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የነበረው የመንግስት ተቃውሞ እንዲሁም በኢህአዴግ ውስጥ ህወሃት ላይ ተቃውሞ የሚያነሱ የአማራና የኦሮሞ ባላስልጣናት በመበራከታቸው ነው። ይህን ተከትሎም አብይ መጋቢት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ። በፍጥነት አስገራሚ ለውጦችን ማድረግ ጀመሩ፤ ከነዚህም አንዱ የገዢው ፓርቲ ኅብረት አባላት የነበሩትን ፓርቲዎች ስም መቀየር ነበር። የአማራ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የአማራ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሆነ።

ይህ እንቅስቃሴ በአንዳንዶች ያለፉትን ሁለት አስርት አመታት ከግማሽ የጭቆናና የአፈና ታሪክን የማስወገድ ጥረት ተደርጎ ነበር የታየው። ነገር ግን የፓርቲውን አወቃቀር እንዲሁም ከፍተኛ ድርሻ የሚይዝ የስራ መደቦችንና ፋይሎችን ባሉበት ነበር የተወው። ስሙ አልቆየም። ከአመት በኋላ ብልጽግና ፓርቲ ተመሰረተ። ከዚያም ጋር ተያይዞ አዴፓ ወደ የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክንፍ ተቀየረ።
ህወሃትንከ1980ዎቹ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፌደራል መንግስት የገዢ ቡድን ውስጥ ማውጣትና ፓርቲውን በማስፋፋት ሌሎች እንደ ሶማሌ፣ጋምቤላ፣ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ሀረሪና አፋር ያሉ የአጎራባች ክልሎች ገዢ ፓርቲዎችን ማካተት አዲሱ ፓርቲ በአስቸኳይ የወሰደው እርምጃ ነበር።

ነገር ግን ምንም እንኳን የፓርቲዎቹ ወደ ‘’አንድ’’ ‘’ብሔራዊ’’ ፓርቲ ‘’መዋሃድ‘’ ተደጋግሞ ቢነሳም የብልጽግና ፓርቲ የተወሰነ ክልላዊ ማንነትን ይዞ እንዲቆይ ተገዷል። ይህም ለክልል ቅርንጫፍ ፓርቲዎች የማይናቅ እራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነት እንዲያገኙ አስችሏል። እንደእውነቱ ከሆነ በርካቶች የብአዴን አባላት ወደ አማራ ብልጽግና ደጋፊነት የተቀየሩት ምንም የአመለካከት፣ አወቃቀርና ፍላጎት ለውጥ ሳይደርጉ ነው የሚል አመለካከት አላቸው።

በሞንትሪያል ካናዳ የሚገኘው ኮንኮድሪያ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ተማሪ፣ በአማራ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሰጪና በአሜሪካ የአማራ ማኅበር የቅስቀሳ ሃላፊ የሆነው ሆነ ማንደፍሮ ‘’ኢህአዴግ የብልጽግና ፓርቲ ሆኖ እንደ አዲስ መዋቀሩ፤ በተለይም ደግሞ ትህነግ[ህወሃት] ብልጽግናን ላለመቀላቀል መወሰኑ’’ በመጀመሪያ አካባቢ ፓርቲው በአማራ ክልል ድጋፍ እንዲያገኝ እንዳደረገ ያምናል።

ነገር ግን የአማራ ብልጽግና አባላት ‘’አዲስ የተገኘውን የተሻለ አመለካከት ለመጠቀም ድፍረቱ አልነበራችውምና የአማራ ብልጽግናን መስፈርት በማሟላት የአማራን ፍላጎት ወደፊት የሚያራምዱ መሆን አልቻሉም። በዚህም የተነሳ በፓርቲው ውስጥ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች በገዛ ፍቃዳቸው ‘’አዲስ ሎሌነት’’ ውስጥ እንደገቡ ተደርጎ ይታሰባል፤ በእነሱ ላይ የሚሰነዘረው ተቃውሞ የጨመረ ሲሆን ተቃውሞውም በመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ካሉ የፓርቲው አባላት ጭምር የሚመጣ ነው።

የብልጽግና ፓርቲ በቀጣዩ ምርጫ ጥሩ መስራት እንዲችል በተለይም በአንፃራዊነት ሲታይ ጠንካራ የሆኑ ተቃዋሚዎችንና ፍላጎታቸውን የሚያውቁ አማራ መራጮችን መጋፈጥ ስለሚኖርበት የታዛዥነትና የበታችነትን ስሜት ከራሱ ላይ ማራገፍ ይጠበቅበታል።

በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ የአካባቢው ባለስልጣናት የህወሃት ርዝራዦች በማለት ከገለጿቸው ኃይሎች ጋር ግጭት ከተካሄደበት በሰሜን አማራ ከሚገኘው ዋግ ህምራ ዞን የመጣችው ተረፉ ብሩ በአሁኑ ጊዜ ባህርዳር የምትኖር ሲሆን ከሁለት አመታት በፊት ስለምርጫው ጉጉት ነበራት። አሁን ግን ምርጫው መካሄድ እንዳለበት እራሱ እርግጠኛ አይደለችም። ‘’በየስፍራው ግድያ አለ። ማነው ለምርጫ የሚሄደው? ሁሉም ሰው እየሞተ ነው‘’ በማለት በአገሪቷ የተለያዩ ስፍራዎች ያሉ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ጥቃቶችን አንስታለች።

‘’ምንም አዲስ ነገር አልጠብቅም፤ ከእግዚአብሔር ካለሆነ በስተቀር ከመንግስት ምንም አይጠበቅም‘’ በማለት ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግራለች። ገዢው ፓርቲ አመጣቸዋለሁ ብሎ በኩራት የሚናገራቸው ለውጦች በቂ አይደሉም በማለት ትሞግታለች ‘’አሁንም ድረስ የህወሃትን ታሪክ እያስቀጠለን ነው’’ በማለት ታክላለች፤ ይህም በእሷ አመለካከት ችግር ነው።

ነገር ግን የአማራ ብልጽግና ጥረት እያደረገ ነው። ለምክር ቤት በዚህ አመት ከቀረቡት 138 እጩዎች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው አዲስ ያልሆነው። ፓርቲውን በፌደራልና በክልል ደረጃ ከሚወክሉት ውስጥ እንደ ማሞ ምህረቱ (ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪዎች አንዱ ናቸው) ያሉ ቴክኖክራቶች እና እውቅ የስነ-ጥበብ ታሪክ ምሁር የሆኑት አበባው አያሌው ይገኙበታል።

አዲስ መሆን ብቻ ግን በቂ አይደለም። የአማራ ብልጽግና ዋና ተቀናቃኝ አብን በአብዛኛው በከተማው አካባቢ ከፍተኛ የወጣት ተከታዮች ቁጥር አሉት፤ከተመሰረት ሶስት አመታት ብቻ ያስቆጠረ ስለሆነም እንደ አማራ ብልጽግና ያለ የፖለቲካና ታሪካዊ ኮተት የለውም።

የአማራ ብልጽግና አዲስ ታሪክ ያስፈልገው ነበር። አዲስ ድል አስፈለገው። ህወሃት በፌደራል መንግስት ላይ የነበረው የበላይነት መወገድ አንድ ሁሉን የሚያስተባብር (አንድ የሚያደርግ) ድምጽ የሚፈጥር ነበር። የትግራይ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ በአማራ ብልጽግና በተዘጋጁ ሰልፎችና ዝግጅቶች ላይ በትግራይ የተገኘው ‘ድል’ መድረኩን መቆጣጠሩ አይቀሬ ነበር።

ከትግራይ ጋር ያለው ፍጥጫ

የአማራ ብልጽግና-ኣዴፓ-ብአዴን ከህወሃት ጋር መቃቃር በአንድ ፓርቲ ውስጥ ያለ የኃይል ጉዳይ ብቻ ተደርጎ ሊገለጽ አይችልም። በአማራ ብሔርተኝነት የተነሳ ብአዴን ማምለጥ ወደ ማይችልበት ቅርቃር ውስጥ የገባ ሲሆን ንቅናቄው ለአማራ ብሔርተኝነት መንገድ ጠርጓል። ይህንንም ያደረገው የአማራ ብሔርተኝነት የህወሃትን የበላይነት መገዳደር ስለሚችል ነበር።

አማራውን በዘር ለማደራጀት በኢህአዴግ የመጀመሪያ ጊዜያቶች ተሞክሮ የነበረ ሲሆን እነዚህ ጥረቶች ግን ውጤት ያሳዩት እጅግ ዘግይተው ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የመላው አማራ ህዝቦች ፓርቲን በ1980ዎቹ መጀመሪያ ያቋቋሙት እውቅ የቀዶ ህክምና ባለሞያ የሆኑት አስራት ወልደየስ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው።

የአማራ ብሔርተኝነት እንደ ጠቃሚ የፖለቲካ ኃይል ቅርጽ መያዝ የጀመረው በ2002 አጋማሽ ሲሆን፤ በወቅቱ በርካቶች በማንነታቸው ላይ የተመሰረተ መገለልና ጭቆና እየደረሰባቸው እንደሆነ ይሰማቸው ነበር።

መገለልና ጭቆና ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ጀምሮ ነበሩ ሲባል የነበረ ቢሆንም ከሁለት አስርት አመታት ከግማሽ በኋላ የአማራ ብሔርተኝነት ከፍ ላለበት በምክንያትነት ሁለት እውነታዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ። አንደኛው ከትውልድ ጋር የተያያዘ ሲሆን ይህም የሆነው በርካታ ወጣቶች የዘር ማንነትን ከብሔራዊ ማንነት በበለጠ ሁኔታ በምትሰብከው የኢህአዴግ ኢትዮጵያ በማደጋቸው ነው።

ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ከኦሮሞ ብሔርተኞች የተገኘ ተነሳሽነት ነው። በዚያ ጊዜ የኦሮሞ ብሔርተኞች የዘር ቅስቀሳን እንደ መሳሪያ በመጠቀም መንግስት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ማሰማት ችለው ነበር። በአንድ በኩል ህወሃትን ወደ ስልጣን ያመጣውና አሁን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ለፈጠረው እጅግ ለጎለበተው የትግራይ ብሔርተኝነት ምላሽ ነበር። በተጨማሪም በኢህአዴግ ለተስፋፋው ነፍጠኛን (አብዛኛውን ጊዜ አማራ ማለት ነው) ለሚቃረን አመለካከት ምላሽ ነበር።

ኢህአዴግ አብዛኛውን ጊዜ ነፍጠኛ የሚለው ቃል የገዢ መደቦች ጠመንጃን በመጠቀም ብሔሮችንና ብሔርብሔረሰቦችን የንጉሳውያን አስተዳደር የገዙበትን ስርዓት እንደሚያመለክት ነገር ግን ሰፊውን የአማራ ህዝብ እንደማይወክል ያናገራል። ነገር ግን በርካታ የአማራ ብሔርተኞች ህወሃት ዘራቸው ላይ በማነጣጠር የህዝብ ቁጥር ውጤትን በማጭበርበር የማኅበረሰቡን ቁጥር ከሁለት ሚሊየን በላይ አሳንሶታል የሚል አመለካከት አላቸው።

ይህን የሚሉትም በ 1999 በተደረገው የኢትዮጵያ የመጨረሻው የህዝብ ቆጠራ የአማራ ህዝብ ከተገመተው በታች ዝቅተኛ የህዝብ ቁጥርና አነስተኛ የእድገት መጠን ማሳየቱ ላይ ተመስርተው ነው። ልዩነቱ ለምን እንደተፈጠረ የያኔዋ የማዕከላዊ ስታትስቲካል ኤጀንሲ ኃላፊ ሳሚያ ዘካሪያ ሲገልጹ በክልሉ ያለው አነስተኛ የህዝብ ቁጥር ኤችአይቪ በስፋት በክልሉ በመኖሩ የመጣ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል። ይህ ግን በርካታ አማራዎችን አላሳመነም። ውዝግቡን ተከትሎ የህዝብ ቆጠራ ጥናት የተደረገ ሲሆን እንደ ኤጀንሲው ከሆነ ከበፊቱ በመጠኑ የበለጠ የህዝብ ቁጥር እድገት መጠን ታይቷል።

የተቃውሞ ሰለባ በነበሩት ከ2007 እስከ 2010 በነበሩት አመታትም የተነቃቃ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ምሳሌን መጠቀስ ይችላል። የአማራ ብሔርተኝነት የበለጠ የዳበረውም ኢመደበኛ የማኅበራዊ አንቂዎች ስብስብ የነበረው ወደ መደበኛ የፖለቲካ ፓርቲ (አብን) በተለወጠ ጊዜ ነበር። እነዚህ አመታት አማራነታቸውን የሚናገሩ ሰዎች በቁጥር ጨምረው የታዩባቸው ጊዜያት ነበሩ አብዛኛውን ጊዜም ይህ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በከፊል ከግምት ውስጥ ባለማስገባት የሚደረግ ነበር።

አብን መጀመሪያ እንደተጀመረ የቀድሞው ብአዴን የመጀመሪያ ምላሽ ፓርቲውን ተዓማኒነት ማሳጣት እንዲያውም ማጥፋት ነበር ነገር ግን የለውጥ ጊዜ እንደ መሆኑ ከጊዜው ጋር ለመሄድ በማሰብ የፓርቲውን መኖርና እንቅስቃሴውን ተቀበለ። በህወሃት ላይ ብአዴን ያመጸበት ምክንያት በከፊል በኢህአዴግ የኦሮሞ ክንፍ በሆነው የኦሮሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ድርጊት የተነሳሳ ሊሆን ይችላል በተጨማሪም የአማራ ህዝብ ለዘሩ የበለጠ እውቅና መስጠቱንና መንግስትም አማራነትን እንዲያከብር በመጠየቁ ምክንያት የተሰጠ ምላሽ ነበር።

የአማራ ብሔርተኝነት ከህወሃት ጋር ያለው ችግር ጣምራ ነው። በመጀመሪያ በአማራና በትግራይ ድንበር ላይ ያሉት በርካታ የአማራ ብሔርተኞች በ1980ዎቹ ወደ ትግራይ በኃይል የተጠቃለሉ ናቸው ብለው የሚያምኗቸው እንዲሁም የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው መሬቶችና በዚህ አካባቢ ያሉ ሰዎች የማንነት ጉዳይ አለ። እነዚህ መሬቶች በምዕራብ፤ ወልቃይት፣ጠገዴ፣ሁመራና ጠለምትን ሲያካትቱ በምስራቅ ደግሞ ራያን ያካትታሉ።

በነሐሴ 2008 ዓ.ም ታሪካዊቷ የአማራ ከተማ የሆነችው ጎንደር የመንግስት ተቃውሞ ትዕይንት የሚታይባት ስፍራ ነበረች። ተቃውሞው ዘግየት ብሎ ወደ ሌሎች የክልሉ ከተማዎች ተስፋፋ፤ ዋና ምክንያቱም በወልቃይት አካባቢ የሚገኙ አማራነትን የሚሰብኩ የማኅበረሰብ መሪዎችን መንግስት በቁጥጥር ስር ለማዋል መሞከሩ ነበር። ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ ከነዚህ መሪዎች መካከል እውቁ ሲሆን ከዛን ጊዜ ጀምሮም በአማራዎች ዘንድ እንደ ጀግና ይወደሳል፤ በቁጥጥር ስር መዋልን በመቃወሙም የእምቢተኝነት ስሜት የሚታይበት ዘመን እንዲፈጠር አድርጓል። በምዕራብ ትግራይ አካባቢ በሚገኘውና የአማራ ብልጽግና የአማራ ክልል ዞን ነው በሚለው ወልቃይት ጠገዴ አሁን የደኅንነት ኃላፊና ምክትል አስተዳዳሪ ብሎ ሰይሞታል።

በዚህ አመት በጥር ወር፤ የአማራ ብልጽግና በወልቃይት ባዘጋጀው ልዩ የገና ዝግጅት ላይ ኮለኔል ደመቀ የክብር እንግዳ ነበር። ዝግጅቱ በክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ ተላልፎ ነበር። ‘’አዲስ ማንነት አልጠየቅንም። አዲስ መሬት አልጠየቅንም‘’ ሲል ሰራዊቱን፣ የክልሉን ፓሊስ እንዲሁም ብልጽግና ፓርቲን በጋራ በማመስገን ተናገረ። በርካታ አማራዎች ከእነዚህ ቦታዎች ተገፍተው በመውጣት በዘዴ ተጋሩ እንዲሰፍሩብት የተደረገበት ጊዜ በመሆኑ በህወሃት ጊዜ የነበረውን ህይወት ‘’የጨለማ ዘመን‘’ በማለት ነበር የገለጸው።

ከዚያ ቀጥለው ባሉ ሳምንታት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተጋሩ ከነዚህ አካባቢዎች ሸሽተው በመካከለኛው ትግራይ በሚገኙ እንደ ሽሬ ወዳሉ ከተማዎች መጠለያ ፍለጋ ፈለሱ፤ የአማራ ኃይሎች በኃይል አስወጥተውናል ሲሉም ወነጀሉ። የአማራ ክልል መንግስት አሁን ስፍራውን እያስተዳደረ እንደሆነ የተናገረ ሲሆን የአማራ ብልጽግናም የነዚህ አወዛጋቢ ስፍራዎች ‘መመለስ’ ድጋፍ እንዲያስገኝለት ለማድረግ ያለመ ይመስላል። ‘’በኃይል ነበር የተወሰዱት፤ አሁን በኃይል ተመልሰዋል’’ ሲሉ የክልሉ ቃል አቀባይ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በአጽንዖት በመጋቢት ወር አጋማሽ ተናግረዋል።

በሁለተኛ ደረጃ የአማራ ብሔርተኝነት አቀንቃኞች ህወሃት አማራ ሌሎች ብሔሮችን የጨቆንና ከአማራ ጋር ያለፍቃዳቸው እንዲዋሃዱ ያደረገ ታሪካዊ ጠላት ሆኖ በመታየት እንዲገለል ያደረገ የመንግስት አስተዳደር ዘርግቷል ሲሉ ይወነጅላሉ። የአማራ ብሔርተኞች ይህ የተሳሳተ የታሪክ አረዳድ በአማራ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ምክንያታዊ ለማስመሰል (ልክ ለማስመሰል) ጥቅም ላይ ውለዋል በማለት ይሞግታሉ።

አሁን የአማራ ብልጽግናና የአብን ባለስልጣናት እንዲያውም ከፓርቲዎቹ ጋር ግንኙነት የሌላቸው የአማራ ብሔራዊ አንቂዎችም በጋራ አሁን ያለው ስርዓት ግንዛቤና የታሪክ አረዳድ አማራዎች ላይ ማንነት ላይ ካተኮሩ ጥቃቶች ጀምሮ እስከ በኃይል ማፈናቀል ያሉ በርካታ ቀውሶችን እንደፈጠሩ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው። የአማራ ብልጽግና ባለፉት አመታት ተኮትኩቶ ያደገውን ፀረ-አማራ አስተሳሰብ ስለማስተካክል ብዙ ጊዜ ሲናገር ይደመጣል።

ነገር ግን እንዲህ አይነት የማሳመን ሙከራ ብቻ በቂ ነው? ከመንግስት ስራ በጡረታ ለተገለሉትና አሁን በባህርዳር አነስተኛ ምግብ ቤት ለሚያስተዳድሩት አቶ ወርቁ አለሙ ይህ በፍጹም በቂ አይደለም። የሚመጣው ምርጫ ከበፊቱ የተሻለ ነገር እንደሚፈጥር ተስፋ የሚያደርጉት አቶ ወርቁ ትኩረታቸውንም ስርዓታዊ ለውጥ እንዲመጣ በሚገፉ ፓርቲዎች ላይ ያደርጋሉ። ‘’አቋሜ ግልጽ ነው። እንደ አማራ ይህ ጨቋኝ ተጨቋኝ አመለካከት ላይ የተመሰረተ ህገ-መንግስትን የሚደግፍ ፓርቲን የምመርጥ አይመስለኝም’’ በማለት ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግረዋል።

ለህገ መንግስቱ ያላቸው ጥላቻ ሰፋ ተደርጎ ሲታይ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ያመጣውን የዘር-ቋንቋ ፌደራል አወቃቀር ስርዓትን የሚወነጅል ነው። የዘር ብሔርተኝነት በመላው አገሪቱ እየጨመረ ቢሆንም ይህን አመለካከት በርካታ አማራዎችና እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የሚኖሩ ከተሜዎች አሁንም የሚጋሩት ነው።

ተቺዎች ባለፉት አስርት አመታት የዘር ማንነት እንደ ቀዳሚ የፖለቲካ መቀስቀሻ ሆኖ ጥቅም ላይ መዋሉ አገሪቷን አሁን የሚያሰቃዩ በርካታ ችግሮች ስረ መሰረት ሲሆኑ ችግሮቹም ከማያባራ የማኅበራዊ ግጭት ትግራይ እስካለው ግጭት ድረስ ይደርሳሉ ። ‘’የዘር ፖለቲካ ምን እንዳመጣብን እናውቃለን’’ በማለት በተቃውሞ አቶ ወርቁ ይናገራሉ።

የዘር ፖለቲካ እንቆቅልሽ

የብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት ተቺዎቹ ‘’ወደ ኢትዮጵያ ማዕከላዊና አንድ አይነት የኋላ ታሪክ መመለስን የሚያልም ነው’’ በማለት ወንጅለውት ነበር ይህም ማለት በዘር ላይ የተመሰረተ የፌደራል ስርዓትን ለመተው እያሴረ ነው ማለት ነው። ነገር ግን በምርጫ ቅስቀሳው ‘’የዘር ብዝኃነት ላይ የተመሰረተ ወንድማማችነት ለጋራ ብልጽግና’’ በሚል መርህ በጋራ የተሰባሰበው ፓርቲ የፌደራል ስርዓትን እንደሚከተል ቃል ገብቷል።

የአማራ ብልጽግና ባለስልጣናት በአብን ደጋፊዎች የሚንጸባረቁ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርዓት አማራዎችን በተለይ ጎድቷል የሚለውን አመለካከት በከፍተኛ ሁኔታ ሊያስተጋቡ ይችላሉ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ አይቃወሙትም። ይልቅ የስርዓቱ ጉድለት በትግበራ ካለ ጉድለት የመጣ ነው ይላሉ።

ከገዢውና ምሁራኑ የሚገኙ በርካታ ሰዎች የአማራ ክልል ከኦሮሚያና ትግራይ ክልል በተቃራኒ በክልሉ ለሚገኙ አነስተኛ ቁጥር ላላቸው ብሔሮች እራሳቸውን በልዩ ዞንና ወረዳዎች የማስተዳደር እድል ሰጥቷል የሚል አመለካከት አላቸው። ስለዚህም የፌደራል ስርዓቱን በአግባቡ በመተግበር ቀዳሚ ነው። ይህ ሙግት ተጋሩና ኦሮሞ ብሔርተኞች አማራ በአጠቃላይ ስርዓቱ እንዲቀየር ወይም እንዲለወጥ ነው የሚፈልገው ብለው ለሚያቀርቡት አስተያየት የሚሰጥ ምላሽ ነው።

እነዚህ አመለካቶቶች ግን መሰረት የለሽ አይደሉም። የመንግስት ሰራተኛ የሆነው ተመስገን አብይ፤ በርካታ ስርዓቱን የሚጠራጠሩ በክልሉና ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ አማራዎችን አመለካከት ሲያንጸባርቅ ‘’እኔ በዘር ፖለቲካ አላምንም’’ ይላል።’’የዘር ፖለቲካ በአሸናፊነት ከቀጠለ፤ በሚቀጥለው ምርጫ የአገሪቷ መኖር ያጠራጥረኛል’’ በማለት ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግሯል።

በዘር ተኮር ፌደራሊዝም ላይ ያሉ ጥርጣሬዎችን ለራሱ ጥቅም ላይ ለማዋል ከሚያልሙ ፓርቲዎች አንዱ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ በተለምዶ ኢዜማ ተብሎ የሚታወቀው ፓርቲ ነው። ለምርጫው በመላው አገሪቷ ለፌደራልና የክልል መቀመጫዎች የሚወዳደሩ 1,385 እጩዎችን በማስመዝገብ ከገዢው ፓርቲ ቀጥሎ ከፍተኛ እጩዎችን ያስመዘገበ ፓርቲ ነው።ከ547 የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ በ446ቱ ኢዜማ እጩዎችን ያወዳድራል ይህም በአማራ የሚገኙት 138 የምርጫ ስፍራዎች ያካትታል።

ኢዜማ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በንጽጽር የተሻለ አወቃቀርና ድርጅታዊ አቅም እንዳለው በኩራት ይናገራል። ‘’ሰዎች ቢወዱህም እጩዎች ከሌሉህ ትርጉም የለውም’’ ሲል በባህርዳር የፓርቲው የክልል ምርጫ አስተባባሪ የሆነው መንግስቱ አማረ ለኢትዮጵያን ኢንሳይት ተናግሯል።

ኢዜማ ህገመንግስቱ እንዲሻሻል ለሪፈረንደም ማቅረብ ይፈልጋል ብሏል መንግስቱ። ፓርቲው በአገሪቷ የተለያዩ ክፍሎች ያለውን የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈውን ማንነት ተኮር ጥቃትና ግጭት የህገመንግስቱ ድክመት አድርጎ ይመለከታል። ጥገናዊ መፍትሔዎች ችግሩን አያቃልሉትም በማለት ይሟገታል። ወደ ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት እንደ መመለስ ያሉ ትልቅ ለውጦች ያስፈልጋሉ ይህም ኢዜማ ከሚያስተዋውቀው አንዱ ትልቅ ለውጥ ውስጥ ሲሆን ከነዚህ ትልቅ ለውጦች መካከል የክልል ግዛቶችን የበለጠ ለማስተዳደር የሚመቹና የብሔር ብዝኃነት ያለባቸው ማድረግ ይገኛሉ።

ገዢው የአማራ ብልጽግና አሁን ያለውን የፌደራል ስርዓት የሚደግፍ ከዚህም ጋር ተያይዞ የተወሰነ የዘር ፖለቲካን የሚያበረታታ እንደሆነ የሚሞግተው መንግስቱ እንደ ተመስገን ያሉ ተጠራጣሪዎችን ፍርኃት በማስተጋባት ኢዜማ በዘር ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገሪቱ ‘’ስጋት’’ ናቸው ብሎ እንደሚያምን ይገልጻል። ችግሩ እነዚህን አሳሳቢ ጉዳዮች ወደ ምርጫ ድምጽ መቀየር ነው።

ኢዜማ ሁለት መሰናክሎችን ማለፍ ይጠበቅበታል። አንዱ የገጽታ ችግር ነው። አንዳንድ አማራዎች ኢዜማ ከማኅበረሳባቸው ፍላጎቶች በተቃራኒው እንደቆመ አድርገው ይመለከታሉ። ይህ አመለካከት በከፊል የተመሰረተው ፓርቲው ወይም የፓርቲው አመራሮች አንጋፋ ፖለቲከኛ የሆነው ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ ከመንግስት ጋር በተለይም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አላቸው ተብሎ በሚታሰበው ቅርበት ላይ ነው። በተጨማሪም የፓርቲው አመራሮችና ከፓርቲው ጋር ግንኙነት ያላቸው እውቅ ሰዎች አማራ እንደ አንድ ብሔር አለ ወይ ብለው ጠይቀዋል መባሉ ላይ ያተኩራል።

አማራ እንደ አንድ ብሔር አለ ወይ የሚለውን ነገር መጠራጠር አዲስ ክስተት አይደለም፤ ከአንድ ፓርቲ ጋር የተያያዘ ጉዳይም አይደለም። ይህም የፌደራል ስርዓቱ አማራን የራሱ ድንበርና ባህል ያለው እንደ አንድ የተለየ ብሔር እውቅና ከሰጠው ጀምሮ በተለይም በምሁራን ዘንድ አወያይ ጉዳይ ሆኗል። አማራዎችና ቋንቋቸው (አማርኛ) ሌሎች የተለያየ ብሔርና ቋንቋ ያላቸው ህዝቦች በመቀላቀል ከብሔር ከፍ ያለ ኢትዮጵያዊ ማንነት የፈጠሩበት የሁሉም ብሔሮች መሰባሰቢያ ተደርገው መታየት አለባቸው ሲሉ ይሞግታሉ።

በ1997 ዓ.ም ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ የነበረው ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ (በርካቶች ለኢዜማ ፈር ቀዳጅ አድርገው ይመለከቱታል) በአማራዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ነበረው፤ ዶክተር ሲግፍሪድ ፓውስዋንግ አማራዎች ማንነታቸውን የሚመለከቱበትን ጣምራ አመለካከት ገልጸውታል። በአንድ ጎኑ በአገሪቱ እንደሚገኙ ሌሎች ብሔሮች አማራነትን የማንነታቸው መሰረት አድርገው የሚመለከቱ የገጠር አማራዎች አሉ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ማጉላት የሚፈልጉ በአጠቃላይ የተማሩ፣ ከሌሎች ብሔሮች ጋር የተዋኃዱ ከተሜ አማራዎች አሉ።

ኢዜማ ለአንዳንዶች ኢትዮጵያዊነትን የሚወክል ሲሆን ይህም ማንኛውንም አይነት ብሔር መኖሩን የሚክድ (አሌ የሚል)ነው። አማራ ለኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ብቻውን በመታተሩ ከሌሎች ብሔሮች በተለይም ከኦሮሞና ተጋሩ ጋር ሲነፃፀር ተጎድቷል ብለው የሚያምኑ በክልሉ የሚገኙ በርካታ ሰዎችን ልብና አዕምሮ ማሸነፍ አለበት። እስከ ሁለት አመታት በፊት ኢዜማ በተለያዩ የአማራ ከተሞች የአካባቢው ወጣቶች ፓርቲው ላይ ያዘሉትን ምሬት የስብሰባ አዳራሾችን በመዝጋትና የፓርቲው አባላትና አመራሮች ስብሰባዎችን እንዳይታደሙ በማድረግ በመግለጻቸው የተነሳ ስብሰባ ለማካሄድ ይቸገር ነበር።

ባለሁለት ስለት ቢላ

የአማራ ብሔርተኝነት ከኦሮሚያና ትግራይ አቻዎቹ በተቃራኒው የአስርት አመታት ታሪክና እድገት የለውም። ከ1950ዎቹ ጀምሮ በኦሮሞና ተጋሩ ዘንድ ያሉ የብሔር እንቅስቃሴዎች በንጉሳውያን ዘመን ገዢ ነበሩ የሚባሉትን አማራዎችን በመቃወም ነው የተቃኙት። እውን የሆነ የአማራ ብሔርተኝነት የመጣው ገና ባለፉት አምስት አመታት ለሌሎች ብሔርተኝነት ምላሽ በመሆን ነው። በጎንደር ዩኒቨርስቲው ተዘራ ታዘበው እንደተገለጸው ለምሳሌ የአማራ ብሔርተኝነት ‘’በአንድ ወቅት ይጠላ የነበረ የማንነት ምድብ የእውነታና እውቅና ጥያቄን ያነሳበት’’ ተቃራኒ ምልከታ ሆኖ የተመሰረተ አተያይ ነው።

የአማራ ብሔርተኝነት አሁን የተለየ ማንነት አለን በሚልና ይህንንም በሚገልጹ ጉዳዮች የሚታወቅ ሆኗል። እንደ ሌሎች ብሔርተኝነት የድንበር/ወሰን ጥያቄ ያነሳል። በትግራይ ካሉት አወዛጋቢ ስፍራዎች በተጨማሪ የአማራ ብሔርተኞች አብዛኛውን ጊዜ የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱት በቤንሻንጉል ጉሙዝ በሚገኘው የመተከል ዞን ላይ ነው። በርካታ አማራዎች የሚኖሩበትና ቀደም ሲል ፌዴሬሽኑ ሲቋቋምም የአማራ ክልል በሆነው በጎጃም ክፍለ ሐገር የነበረው ይህ ዞን አማራን ለማሳነስ ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ተጠቃሏል በማለት ይሞግታሉ።

የአማራ ብሔርተኝነት በተጨማሪም በታሪክ በመኩራት ይገለጻል። እንደ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ያሉ ግለሰቦች እና እንደ አድዋ ድል ያሉ ክስተታት በአማራ ዘንድ ዳግም ጉልህ ስፍራ ተሰጥቷቸዋል። ይህ የአማራ ብሔርተኝነትን ከኦሮሞ አቻው ጋር ግጭት ውስጥ ያስገባዋል። ምክንያቱም ኦሮሞዎች ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በኃይል እንድንገባ ያደረጉን ናቸው ብለው ስለሚያስቡ ነው።
የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ሌላ ክርክር የሚያስነሳ ጉዳይ ነው።

አብን የኦሮሞ ብሔርተኞች መዲናዋ የኦሮሞ ታሪካዊ ርስት ናት በሚል የሚያነሱትን የይገባናል ጥያቄ ይቃወማሉ። የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲና የኦሮሞ የፖለቲካ ሰዎች የአማራ ብሔርተኝነትን ሰዋዊ ቁመና ይዟል ብለው የሚያስቡትን አብን ደጋግመው ይተቻሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር የሆነው የአብን ሊቀመንበር በለጠ ሞላ አማራዎች ኢትዮጵያን በመመስረትና ከዛም ሉዓላዊነቷን በማስጠበቅ እጅግ ጠቃሚውን ሚና ተጫውተዋል ሲል ይሞግታል፤ የኢትዮጵያን ግዛት በመመስረት ሂደትም ‘’ከአማራ ይልቅ ኢትዮጵያዊ ሆነናል’’ ይላል። ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ሲናገርም ‘’ሌሎች በዋናነት ስለብሔራቸው ሲያውቁና በዛም ረገድ ሲደራጁ ከአማራ ይልቅ ኢትዮጵያዊ መሆን ለእኛ ጉዳት እንደሆነ አሁን አውቀናል’’ ብሏል።

የአማራ ብልጽግና የምርጫ ቅስቀሳ ምስሎች በኢንጂባራ፣ አማራ ክልል፥ ግንቦት 2013፥ኢትዮጲያ ኢንሳይት

በዛው ልክ የአብን የአማራ ማንነት ይቀድማል ብሎ ማመን ኢትዮጵያዊ ማንነትን መካድ ማለት አይደለም። ስጦታው ቀሬ በባህርዳር የአብን የምርጫ አስተባባሪ ሲሆን የፓርቲው የመጨረሻ ግብ ኢትዮጵያ ናት ሲል ተናግሯል። በባህርዳር በሚገኘው ቢሮው ሆኖ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ’ትግላችን ሁለት መልክ ያለው ነው፤ አንደኛው አማራን ማዳን ነው’’ በማለት ባለፉት ሶስት አስርት አመታት የነበሩ ሁሉም በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አማራ ጠል ናቸው’ በማለት በአጽንኦት ይሞግታል፤ ‘’ሁለተኛው ትግላችን ደግሞ ኢትዮጵያን ማዳንና ሁሉም ብሔሮችና ብሔርብሔረሰቦች እኩል የሚከበሩበትን አገር መገንባት ነው’’ ብሏል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ይፋ የወጡ የዘር ብሔርተኛ ፓርቲዎች በአንድም ይሁን በሌላ ጊዜ መገንጠል የሚለውን ኃሳብ አስበውታል፤ አብን ግን ይህን አላደረገም። እድሜው በ30ዎቹ መካከል የሚገኘውና በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆነው ስጦታው ፓርቲው ከምርጫው በፊትም ሆነ በኋላ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር መስራት እንደሚችል በአጽንኦት ይናገራል ነገር ግን ‘’የኢትዮጵያ አንድነት ላይ አንደራደርም’’ ሲል ያክላል።

አብን በተቋቋመ በመጀመሪያው አመት በበርካታ ወጣቶች አባልነትና ድጋፍ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የተለያዩ መድረኮችን ማግኘት ቻለ። የአስርት አመታት ምሬትን የገለጸበት መንገድ፣ ህገመንግስቱ እንዲሻሻል ወይም እንዲለወጥ መጠየቁ እና ስለአማራ ድንበር አንድነት ያደረገው ዘመቻ (ማለትም ከአማራ ተወስዷል የተባለውን መሬት ስለማስመለስ) የብዙዎችን ስስ ብልት የነካ ነገር ነበር።

አብን በሚመጣው ምርጫ በተግባር ስራውን ማሳየት ይችላል? ለክልልና የምክር ቤት መቀመጫዎች 491 እጩዎችን አስመዝግቧል። ይህም ገዢው ፓርቲ ካቀረበው 2,432 እና እናት ፓርቲ ካቀረበው 573 እጩዎች አንፃር ብዙ የማይባል ነው። እናት ፓርቲ በአንጻሩ ሲታይ እምብዛም የማይታወቅ ድርጅት ሲሆነ ኢትዮጵያዊነትን ያራምዳል። ይሁን እንጂ የአብን ትኩረት የአማራ ክልልና ህብረት ለመፍጠር ከሚያስብባቸው እንደ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ያሉ ፓርቲዎች ከሚገኙበት አዲስ አበባ ላይ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማራዎች በሌሎች ክልሎች ኦሮሚያ፣የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል (ደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ) እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ የሚገኙ ቢሆንም አብን በነዚህ ስፍራዎች ምን ያህል በነጻነት ቅስቀሳ ማድረግና ድምጽ ማግኘት እንደሚችል ግልጽ አይደለም።

ሰኔ 15, 2011 በወቅቱ የክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አምባቸው መኮንንና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በባህርዳር ተገደሉ። የፌደራል መንግስቱ መፈንቅለ መንግስት ብሎ ከጠራው ድርጊት በስተጀርባ ነበሩ የሚባሉት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ከጥቂት ቀናቶች በኋላ ተገደሉ። ሆኖም በሚያዝያ ወር በተካሄዱት በርካታ ሰልፎች ላይ እንደታየው አሁንም በበርካቶች እንደ ጀግና ይታያሉ። ክስተቱ ግን በአማራዎች ዘንድ የዘር ፖለቲካ ያለውን ጥርጣሬ አነሳስቷል።

ድብልቅ እድሎች

ለበርካታ የአማራ ብሔርተኞች የአብይ ዘመን የዲከንስን አገላለጽ በመጠቀም ሲገለጽ ካለፉት ዘመናትም ሁሉ እኩዩ፥ ካለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ግሩሙ ነው። የተስፋና የፍርኃት፣ የሀዝን፣ደስታ፣በራስ መተማመን እና እርግጠኝነት ማጣት ዘመናት ነበሩ። በህወሃት የፖለቲካ ሞት የተፈጠረውን ደስታ ብዙውን ጊዜ በተለያዩ ስፍራዎች በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን ባሉ አማራዎች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ ጥላ ያጠላበታል።

ከምርጫው ሰባት ሳምንታት ቀደም ብሎ በአማራ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአገሪቱ በተለያዩ ስፍራዎች የሚደርሱ የአማራ ግድያዎችን በመቃወም ወደ አደባባይ ወጥተው ነበር። ባነሮችንና መፈክሮችን በመያዝ ገዢውን ፓርቲና በግድያዎቹ እጁ አለበት ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር አወገዙ።

በይፋ ጥቅምት 24 የትግራይ ግጭት ከመጀመሩ በፊት የአማራ ብልጽግና ድምጸት ኮስተር (ኮምጨጭ) ያለ ነበር። ኮሮና ከመጣ ጊዜ ጀምሮ የምክር ቤት ስብሰባዎች በተካሄዱበት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በሚገኝ አዳራሽ የተሰባሰቡ አማራውን የሚወክሉ ህግ አውጭዎች ከ50 በላይ አማራዎች በምዕራብ ኦሮሚያ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ሰራዊት ታጣቂዎች ፈፅመውታል በተባለ ጥቃት መገደላቸውን በመስማታቸው ተረብሸው ይታዩ ነበር።

በአገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች ላይ ለሶስት አመታት ያህል በተደጋጋሚ እንዲህ አይነት ጥቃቶች በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና የተወሰኑ የደቡብ ክፍሎች መከሰታቸው፤ የገዢው ፓርቲ የአማራው ክንፍ በሆነው ፓርቲ ላይ የሰላ ትችት እንዲሰነዘር አድርጓል። ይህም የሆነው በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ አማራዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ አልቻለም በሚል ነው። የአማራ ብሔርተኞች በቤንሻንጉል ጉሙዝ የአካባቢ ነባር ነዋሪዎች ናቸው ተብለው ለሚታሰቡ ቡድኖች የተሰጡ ህገ መንግስታዊ መብቶችን አጥብቀው ይተቻሉ እንዲሁም የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ያነሳሉ።

ከለውጡ (አብይ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ጊዜ ያመለክታል) በኋላ በአማራ ላይ የሚደርሱ ማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች በብዙ ጨምረዋል፤ የፓርላማ አባል የሆኑት ብርትኳን ሰብስቤ ከእንባቸው ጋራ እየታገሉ ‘’ተስፋ እየቆረጥኩ ነው፤ ሰዎች በጅምላ እየሞቱ ነው። ይህን ማቆም አለብን’’ በማለት በስሜት ተናግረዋል። የአማራ ብልጽግናም የምክር ቤት አባላት ጥያቄዎችን ለመመለስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መገኘት አለባቸው በማለታቸው ምክንያት ፓርላማው የተለመደውን ስብሰባውን ለማካሄድ አልቻለም።

የመከላከያና የደህንነት ኃይሎች የት ናቸው? ለምንድነው እነዚህን ጭፍጨፋዎች ማስቆም ያልቻሉት? ለምንድነው እነዚህ ሁሉ ጥቃቶች አማራ ላይ እየደረሱ ያሉት? እነዚህ በበርካታ አማራዎች ዘንድ ያሉና የነበሩ ጥያቄዎች ናቸው።

እንደ አብን ላሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ የብልጽግና ፓርቲዎች ክንፍ በጭፍጨፋዎቹ ውስጥ በቀጥተኛ ተሳትፎም ሆነ መከላከልን ቸል በማለት ተሳታፊ ናቸው፤ ሰፋ ሲልም የአማራ ብልጽግና የገዢው ፓርቲ የአማራ ክንፍ በመሆኑ የችግሩ አካል ነው።

‘’የአማራ ብልጽግና ፓርቲ በሌሎች ክልሎች ለሚኖሩ አማራዎች ምንም ሲያደርግ አላየንም’’ ሲል የአብኑ ስጦታው ይናገራል። ለሱ የአማራ ብልጽግና በሌላ ክልል የሚኖሩ አማራዎች ሰፋሪዎች ወይም ጭራሽ ያለፈ ጨቋኝ ስርዓት ርዝራዦች ናቸው የሚለውን ታሪክ የሚያስቀጥል ነው። እነዚህ ጥቃቶች ምርጫው እየተቃረበ ባለበት ሰዓት መቀጠላቸው የምርጫውን ውጤት ከሚወስኑ በርካታ ጉዳዮች መኃል እጅግ ወሳኞቹ ሊሆኑ ይችላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ላይ ሲወጡ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫን ለማካሄድ ቃል የገቡ ሲሆን ይህም ሰው ከምርጫው የሚጠብቀውን ነገር ከፍ አርጎት ነበር። አሁን ተከታታይ ግጭቶች ፣ እጅግ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች እናየእውቅ ተቃዋሚ ሰዎች ከታሰሩ በኋላ የነበረው ጉጉት ቀንሷል። እንደዛም ሆኖ የአማራ ክልል፣ አዲስ አበባ እና በተወሰነ ደረጃም የደቡብና ሱማሌ ክልል ምንም እንኳን ምቹ ያልሆነ ሁኔታ ቢኖርም ጥሩ የሚባል ፉክክር የሚታይበት ምርጫ ሊካሄድባቸው ይችላል።

በትግራይ ባለው ችግር የተነሳ ምርጫ ተራዝሟል። በኦሮሚያ ሁለቱ ዋና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአባላቶቻቸው እንዲሁም በተወሰኑ እውቅ ፖለቲከኞቻቸው መታሰር ምክንያት ከስረ መሰረታቸው ተዳክመዋል። በተደጋጋሚ ትንኮሳ ደርሶባቸዋል በዚህም የተነሳ መሳተፍ እንደማይችሉ አሳውቀዋል።

የአማራ ጫካዎችና ተራሮች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች የሉም። ተቃዋሚው (በሰኔ 26, 2011 ማግስት ግጭት ተከስቶ በርካቶች በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ቢሆንም) በአብዛኛው ነፃ ነው፥ ነገር ግን የክልሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ከሌሎች ስፍራዎች ባልተናነሰ ሁኔታ ውስብስብና መጨረሻቸው ያልታወቀ ሆነው ይገኛሉ።

ጥያቄ ወይም እርማት? ኢሜል ይላኩልን

ኢትዮጵያ ኢንሳይትን ይከተሉ

ይህ ጽሁፍ ምርጫ 2013ን በሚመለከት ዘለግ ያሉ ጽሁፎችን ከመላው ኢትዮጵያ በተከታታይ የምናቀርብበት የ “Ethiopia Insight Election Project (EIEP)” ክፍል ነው።

ዋና ምስል: በራያ ቆቦ ያሉ አማራዎች በልዩ ልዩ አከባቢዎች የሚኖሩ አማሮችን ግድያ ሲቃወሙ፥ ሚያዝያ 2013፥ amharagenocide.net.

የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ

በ Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 ዓለም አቀፍ ፈቃድ ስር የታተመ፡፡ licence. እንደገና ካተሙ የኢትዮጵያ ኢንሳይትን ስም ጠቅሰው ይህንን ገጽ ያገናኙ።

ከመላው ኢትዮጵያ የሚመጡ ዜናዎችን ለመተንተን ድጋፍዎን እንፈልጋለን
እባክዎን የኢትዮጵያ ኢንሳይትን ሽፋን ይደግፉ
Become a patron at Patreon!

About the author

Mistir Sew

This is a generic byline for all anonymous authors. The anonymity could be because they fear repercussions, as they are not authorized by their employers to express their views publicly, or for other reasons.

4 Comments

Leave a Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.