Elections 2021 Ethiopian language In-depth

የድሬዳዋ ግራ አጋቢ ጉዳይ፡ የስልጣን ክፍፍል በብዝሃዊቷ ምስራቃዊ ከተማ

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ላይ የምትገኘው ከተማ በብዝሃነቷ የተነሳ ሁከት ለነገሰበት ለቲካ የተጋለጠች ናት።

ኤፍሬም ሙላት ጥቅምት 2፣ 2012ን ከዚህ በፊት አይቶ የማያውቀው አይነት “ጨለማ ቀን” በማለት ይገልጻታል። ለተቃውሞና ለመንገድ ላይ አመጽ እንግዳ አልነበረም፤ ነገር ግን ከሞት ጋ ተጋፍቶ አያውቅም ነበር። “ከፍተኛ ቀውስ ነበር” ይላል ሁኔታውን ሲያስታውስ። “ጥይት ወይም ድንጋይ ይመታህ እንደሆነ ማወቅ አትችልም ነበር።’’

አብዛኛውን ጊዜ በርካታ ባህሎች በጋራ የመኖራቸው ማሳያ ተደርጋ የምትሳለው የትውልድ ከተማው የሆነችው ድሬዳዋ በዚያ አመት በርካታ አመጾችን ያስተናገደች ሲሆን በርካቶቹ አመጾችም የብሔርና የሃይማኖት ይዘት የነበራቸው ናቸው።

በጥቅምት 2012 ዓ.ም የደህንነት ኃይሎች ከተለያዩ የእምነት ቡድኖች በተውጣጡ ወጣቶች መሃል የተከሰተ ሰፊ ግጭትን ለመቆጣጠር የአስለቃሽ ጭስ ተኮሱ። ወደ ከተማዋ የሚያስገቡና ከከተማዋ የሚያስወጡ መንገዶች ሲዘጉ የከተማው የመጓጓዣ ዘዴ ደሞ ተስተጓጉሎ ነበር። ህንጻዎች በተለይም ቀበሌ 5 በሚባለው አካባቢ የሚገኙ ህንጻዎች በእሳት ጋይተዋል። አምቡላንሶች ተጎጂዎችን በመያዝ ወደ ድል ጮራ ሆስፒታል ይከንፉ ነበር። ሁኔታው የተፈጠረው ከጥምቀት ክብረ-በዓል (በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው) በሚመለሱ ምዕመናን ኖች ላይ ድንጋይ በመወርወሩ ምክንያት ነው።

በሰኔ 2012 ዓ.ም ደቻቱና አምስተኛ ሰፈሮች በድጋሚ አመጽ ሲቀሰቀስ ቢያንስ ሁለት ሰዎች ተገደሉ። በሁለቱ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ተነሱ፤ የተወሰኑ ነዋሪዎች ግጭቱ የብሔር መልክ ነበረው ይላሉ። ንብረት ወድሟል፣ ሱቆች ተዘርፈዋል እና ቢሮዎች ተዘግተዋል። ግጭቱን ለማስቆም የፌደራል ፖሊስና የፌደራል መከላከል ኃይል ድጋፍ አስፈልጎ ነበር።

ነገር ግን በጥቅምት ወር፤ የከተማ አስተዳደር ሰራተኛ የሆነው ኤፍሬም (ስሙ ተቀይሯል) ራሱን በበራሪ ጥይቶች መኃል አገኘው፤ እናም ሞት ደጃፉን አንኳኳ። ይህን ጊዜ ደግሞ ግጭቱ የተቀሰቀሰው በመቶዎች በሚቆጠሩ ማይሎች ርቀት በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ (ከድሬዳዋ ውጪ በአገሪቱ ከሚገኙ የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ብቸኛዋ ከተማ ናት) ሲሆን ልክ እንደ ድሬዳዋ የተለያዩ ማኅበረሰቦች የሚጋጩባት ናት።

በድሬዳዋ የተከሰተው የጥሩ ግጭት ቤተክርስቲያን ይሄዱ በነበሩ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን አማኞች ላይ በደረሰ ትንኮሳ የተቀሰቀሰ ነው፥ ጥር 16፣2011 ፥ ዶቼ ዌሌ

ታዋቂው የኦሮሞ የፖለቲካ ሰው ጃዋር መሃመድ ሰፊ ቁጥር ላላቸው የማኅበራዊ መገናኛ ተከታዮቹ በመንግስት የተቀጠሩለት ጠባቂዎች በአጣራጣሪ ሁኔታ በእኩለ ሌሊት በአዲስ አበባ የባለፀጋዎች  ሰፈር ከሚገኘው ቤቱ እንዲወጡ እየተደረገ እንደሆነ ባሳወቀ ጊዜ በርካታ ደጋፊዎቹ ህይወቱን አደጋ ላይ የመጣል ሴራ እንዳለ ተሰማቸው። በተከታዮቹ ሰዓታት ጥበቃ ለማድረግና አጋርነታቸውን ለማሳየት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ቤቱ ጎረፉ። በተመሳሳይ ሁኔታም በኦሮሚያና በሀረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ በሚገኙ በርካታ መንደሮችና ከተሞች ግጭቶች ተቀሰቀሱ። በኦሮሞዎችና ኦሮሞ ባልሆኑ እንዲሁም በደኅንነትና ኃይሎችና በተቃዋሚዎች መካከል በተከሰተ ግጭት መንግስት ራሱ ባመነው በመላው አገሪቷ የ84 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ የኤፍሬም ጓደኞች ናቸው።

“አብረን ነው ያደግነው፤ አንድ ላይ ነው የተማርነው አብረንም ብዙ ጊዜ እናሳልፍ ነበር’’ በማለት የ25 አመቱ ወጣት በድሬዳዋ ቢሮው ሆኖ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግሯል። “እንደ ወንድማማቾች ነበርን’’።

ከነዚህ ከሞቱት ጓደኞቹ አንዱ አጠገቡ እንደተገደለና ይህም የሆነው ወጣቶች የደኅንነት ኃይሎች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ የደኅንነት ኃይሎቹ በተኩስ ምላሽ በመስጠታቸው እንደሆነ ኤፍሬም ይናገራል። ኤፍሬም ጓደኛው ድንጋይ ከሚወረውሩት መሃከል አልነበረም ይላል።

በተከተሉት ቀናት ኤፍሬም በዘመድ ቤት ለተወሰኑ ቀናቶች ተሸሸጎ መቆየት ነበረበት። የአመጽ ጥቃቱ ምን መልክ ሊይዝ እንደሚችል አላወቀም፤ በተጨማሪም የደኅንነት ኃይሎች ሊያሳድዱት እንደሚችሉ ፈርቶ ነበር።

ከአመት ከመንፈቅ በኋላ ተመልሶ ሲያስበው በተከሰተው ነገር ከንቱነት ይደመማል። “በኃይል ጥቃቱ፣ በአለመግባባቱ ምንም ያተረፍነው ነገር የለም’’ ሲል በምሬት ይናገራል። ‘’ያተረፍነው ነገር ቢኖር የሰው ህይወት ማጣት ነው።’’

በርካታ ገጽታ ያላቸው ውጥረቶች

ምናልባትም ድሬዳዋ የበርካታ ብሔሮችና ሁለት ክልሎችኦሮሚያና ሶማሌየሚፎካከሩባት ከተማ እንደመሆኗ ለግጭት ተጋላጭ መሆኗ አያስገርምም።

በድንበርና ሀብት የሚነሱ አለመግባባቶችና ግጭቶች በተለይም በከተማዋ ውስጥና በከተማዋ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያና ሶማሌ ማኅበረሰቦች ዘንድ አስርት አመታትን ያስቆጠረ ነው።

በ2013ቱ Governing Contested Cities in Federations መጽሐፉ ምሁሩና ፖለቲከኛው  ሚልኬሳ ሚዴጋ ከ1920ዎቹና 30ዎቹ ጀምረው ያሉ የሰው ህይወት መጥፋትን ያስከተሉ ግጭቶችን ዝርዝር ያቀርባሉ።

ይህም በ1980ዎቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር  የማርክሲስት የደርግ አገዛዝን በመጣሉ ምክንያት ኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ አፋፍ ላይ በነበረች ወቅት የበለጠ ተፋፋመ። በነዛ ጊዜያት ሁለቱንም ማኅበረሰቦች በሚወክሉ (የኢሳና ጉርጉራ ነጻነት ግንባር (አይኤስጂኤል) እና የእስልምና ግንባር ለኦሮሚያ ነጻነት (አይኤስኤልኦ) የተባሉ የታጠቁ ቡድኖች መካከል የትጥቅ ትግል ከከተማዋ በስተምዕራብ በስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በመልካ ጀብዱ ተካሄደ።

በኦሮሚያ ክልል ለተወሰነ ጊዜ ከተዳደረች በኋላ ድሬዳዋ በ1985 ዓ.ም ለፌደራል መንግስቱ ተጠሪ እንድትሆን ሆነች። አንዱ ቁልፍ ምክንያት ተብሎ የተሰጠው የቦታና የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ነው ይህም የሆነው ያለኤርትራ ወደብ አልባ ለሆነችው አዲስ አገር ከጅቡቲ የባህር ወደብ ጋር የምትገናኝ ዋና የመግቢያ መንገድ በመሆኗ ነው። ነገር ግን እርምጃው በዋናነት በመንግስት የተወሰደው በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ያለውን የይገባኛል ጥያቄና ግጭቶች ለማርገብ ነው።

ስለግጭቶቹ ታሪኮች የተጠኑ በርካታ ጥናቶች የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ሀዲድ በ1894ዓ.ም ከተሰራ በኋላ ያለው ጊዜ ላይ ነው የሚያተኩሩት፤ ነገር ግን ግጭቶቹ ከተማዋ ከመመስረቷ በፊት የነበሩ እንደሆኑ ይታመናሉ። የባቡር ሀዲዱ ራሱ ነው በተግባር ድሬዳዋን የፈጠረውና በኦሮሞና በሶማሌ መካከል ብቻ ሳይሆን ኢሳና በአካባቢው የሚገኘውን የአፋር አርብቶ አደሮችን ወደ ቅራኔ የመራው።

ነገር ግን በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ የቅርብ ጊዜ የይገባኛል ጥያቄዎች “በህገ መንግስቱ መሰረት ገና አልተፈቱም’’ በማለት ይሞግታሉ ሚልኬሳ። እናም ከአስር አመት በኋላ ቁርጥ ያለ መፍትሔ ሳይሰጥ ከተማዋ የኢትዮጵያ አስተዳደር ሆነች ይህም ማለት የፌደራል መንግስት አካልና ለፌደራል መንግስት ተጠሪ ሆነች ማለት ነው።

በምትኩ በኢህአዴግና በሶማሌ ህዝቦች ዴሚክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ) (የኦሮሚያና የሶማሌን ግዛቶች የሚያስተዳድሩ ፓርቲዎች ናቸው) መካከል የስልጣን ክፍፍል ስምምነት እንዲተዋወቅ ተደረገ።

ይህን ተከትሎም የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) (የኢህአዴግ ሲሶ ነው) እና ሶህዴፓ በጠቅላላው በከተማዋ ካሉ የመንግስት ስልጣኖች ውስጥ 40 ፐርሰንቱን ወሰዱ። ቀሪው ሃያው ለሌሎች የኢህአዴግ ፓርቲዎች ነበር የተተወው። ይህ ዘዴ በተለምዶ 40፡40፡20 በመባል ይጠራል።

ሌላ አቅጣጫ

አብዛኛውን ጊዜ ግጭት ያለባቸው ከተማዎች ውስጥ እንደሚደረገው የአስተዳደር ሁኔታውን የሥነ-ህዝብ አወቃቀርን በመቀየር ለመገዳደር ጥረቶች አሉ።

የማኅበራዊ ሥነ-ሰብዕ ባለሞያ የሆኑት ደረጄ ፈይሳ ጉልህ የሆነ የሥነ-ህዝብ ለውጥ በቅርብ አመታት እንደተስተዋለ፥ ይህም የሚታየው ጉርጉራ (ሁለቱንም የሶማሌና የኦሮሞ ማንነቶችን የሚጋሩ ማኅበረሰቦች) ከኦሮሞ ወደ ሶማሌ ማንነት መምጣታቸው ነው በማለት ይሞግታሉ። ይህ ምናልባት በ1986 እና 1999ዓ.ም መካከል በተደረጉት የህዝብ ቆጠራዎች መካከል የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር በሁለት ፐርሰንት ሲቀንስ የሶማሌ ህዝብ ቁጥር ከአስር ፐርሰንት በላይ የጨመረበትን ምክንያት ይገልጻል።

ነገር ግን በ2011 ዓ.ም የነበሩት ተከታታይ ግጭቶች ሌላ አይነት ውጥረት እንዳለ ይጠቁማሉ፤ ይህም በሁለቱ ሰፊ በሆኑ ክልሎች መካከል ባሉ ግጭቶች ብቻ የመጣና በአንድ ጉዳይ የተፈጠረ አለመግባባት አካል የሆነ ነገር አይደለም።

ድሬዳዋ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ የባቡር ሀዲድ መገንባቱን ተከትሎ የንግድና የኢንዱስትሪ ከተማ ሆና ነው የተቋቋመችው። ይህም ከተማዋን ከአብዛኛው የኢትዮጵያ የከተማ ማዕከላት ልዩ ያደርጋታል፤ ምክንያቱም ሌሎች ከተሞች ከጦር ሰራዊት ከተሞች ተነስተው ያደጉ ከተሞች ናቸው። በከተማዋ ያረጁና አዲስ ስፍራዎች በደቻቱ ወንዝ ይከፈላሉ፤ ይህ ወንዝ በ1998 ድልድዩን ጥሶ በመውጣት የ200 መቶ ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ በሺህዎች የሚቆጠሩትን አፈናቅሏል። የተባበሩት መንግስታት ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የባቡር ሀዲዱ ምስጋና ይድረሰውና ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥ በማሳየቷ የተነሳ ድሬዳዋን “የምትደንቅ በዕቅድ የተገነባች ከተማ’’ በማለት ጠርቷታል።

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተዘጋጁ ሰነዶች የከተማዋን የህዝብ ቁጥር በ2009 ዓ.ም ከ460,000 በላይ ያስቀምጡታል። ከአስር አመት በፊት እንደተካሄደው የኢትዮጵያ የመጨረሻ የህዝብ ቆጠራ ከሆነ ከህዝብ ቁጥሩ 46 ፐርሰንቱን በመያዝ ኦሮሞዎች በከተማዋ ከሚገኙ ብሔሮች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ። እነሱን ተከትለው የሚገኙት ደግሞ ሶማሌ (24 ፐርሰንት) እና አማራ (20 ፐርሰንት) ናቸው።

በቅርብ አመታት የከተማዋን ህዝብ ከመሰረቱት ብሔሮች መካከል በተለይም በአማራዎችና (ማዕከላዊ የመኖሪያ ስፍራዎችን ይይዛሉ) ኦሮሞዎች መካከል ፍትጊያ ይታያል። ከተማዋ ዘጠኝ የከተማና ሰላሳ ስምንት የገጠር ክፍለ ወሰኖች (ቀበሌዎች) ያሏት ሲሆን በርካቶቹ የገጠር ክፍለ ወሰኖቹ የኦሮሞ ብሔሮች የሚኖሩበት ነው። አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ህዝብ እነዚህ የገጠር ክፈለ ወሰኖች (አውራጃዎች) ውስጥ ይኖራል።

ድሬዳዋ በወፍ በረር ቅኝት

በኦሮሞና በአማራ (አልፎ አልፎ ቁጥራቸው አናሳ የሆኑት ጉራጌዎች ይቀላቀሏቸዋል) መካከል የሚፈጠሩ ቅራኔዎች አዲስ ክስተቶች አይደሉም። እንደ ሚልኬሳ ከሆነ በ1980ዎቹ አጋማሽ ኦሮሞዎች በሚበዙበት ለገሃርና አማራዎች በሚበዙበት አዲስ ከተማ ሰፈሮች የተቀሰቀሰ ግጭት በሁለቱም በኩል ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል።

ነገር ግን የቅርብ ጊዜው የአማራና-ኦሮሞ የከተማና-ገጠር ውጥረት በአገሪቱ በአጠቃላይ በነበረው የማኅበራዊ ለውጥ ምክንያት የተጋጋለ ነው።

የ2002ዓ.ም ሁለተኛው አጋማሽ በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሞዎች ዘንድ ከፍተኛ የወጣቶች ንቅናቄ የተስተዋለበት ነው። በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መገለል ስሜት ተገፋፍተው ከ2006ዓ.ም ጀምሮ የኦሮሞ ወጣቶች በርካታ ተቃውሞዎችን አካሄዱ። በሶስት አመታት ውስጥ ተቃውሟቸው በ2010ዓ.ም የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው እንዲለቁና ተተኪያቸው አብይ አህመድ ወደ ስልጣን እንዲመጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አደረገ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከመንግስት ጋር ግንኙነት ያለው የሶማሌ ክልል ወጣት ታጣቂዎች በ2010 እና በ2011ዓ.ም በከተማዋ እየታየ ነበር። በኢትዮጵያ እንደሚገኙ በርካታ ብዝሃነት እንደሚታይባቸው ከተሞች በድሬዳዋም በብሔር የሚደረግ እንቅስቃሴ በብዙዎች በጥርጣሬ የመታየት ሁኔታው ጨምሯል። የ30 ዓመቷ የመንግስት ሰራተኛ የሆነችው ሄለን ሽጉጤ ይህን በከተሜዎች ዘንድ ስር የሰደደ አስተሳሰብ “በድሬዳዋ ዋና ችግር ነው ብዬ የማየው የብሔር ፖለቲካ ነው’’ በማለት ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ገልጻዋለች።

ነገር ግን ከበፊቱ በበለጠ አቋማቸውን በአፅንዖት የሚገልፁ የኦሮሞ ወጣቶች በመላ አገሪቷ ለውጥ እንዲመጣ ሲያስገድዱ በከተሜዎች ዘንድ ፍርሃትና የመወረር ስሜት እያደገ መጣ። አንዱ የዚህ ፍርሃት ማሳያ መደበኛ ያልሆኑ (ኢ-መደበኛ) የወጣት ቡድኖች እጅግ የተደራጁ የኦሮሞ ወጣቶች እንቅስቃሴን ለመቀልበስ በሚመስል መንገድ በድንገት መፈጠራቸው ነው።

የተቃራኒ ቡድኖች መኖር ግጭቶችን አባባሰ ፤ ይህም የማይቀር ነበር። ከነዚህ ብቅ ካሉት ቡድኖች ዋነኛው የሆነው ሳተናው ለ2013 ዓ.ም ምርጫ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች አንድነት ፓርቲ በሚል የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ ቢሞክርም አልተሳካለትም። ከቡድኑ መስራች አንዱ የሆነው ሲሳይ አየለ በከተማዋ ካሉ ሌሎች ሰዎች ሁሉ ለይቶ ኦሮሞ እና ሶማሌን የሚጠቅም የፖለቲካ ስርዓት ነው የሚለው 40፡40፡20 የተሰኘው ስርዓት የአማራ ጣዕም ያለው ቡድን ከሚያነሳው ጉዳይ ዋናው እንደሆነ ይናገራል።

“በድሬዳዋ አፓርታይድ- ነዋሪዎችን፣ እዚህ የተወለዱ ሰዎችን የሚያገል የአስተዳደርና የስልጣን ክፍፍል ስርዓት እንደሚገኝ ይታወቃል’’ ሲል ሲሳይ በህዳር ወር 2013 ዓ.ም ለአማራ ሚዲያ ማዕከል ተናግሯል፤ ይህንንም ያለው ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ መልዕክቶችን በማኅበራዊ ትስስር በማሰራጨት ተወንጅሎ ከሶስት ወራት በላይ ታስሮ ከተፈታ በኋላ ነው።

“ይህንን እንቅስቃሴ የጀመርኩት በዚህ ምክንያት ነው’’ ይላል።

በተወሰነ መልኩ የድሬዳዋ የከተማው ክፍል ከገጠራማው ጋር ያለው ፉክክር በአዲስ አበባ ያለውን ሁኔታ ይመስላል። ሳተናው ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ጋር የአመለካከት ወንድማማችነትን ይጋራል።

ባልደራስ በ2013 ዓ.ም የተጀመረ ከማኅበራዊ እንቅስቃሴ ወደ  ፖለቲካ ፓርቲ የተቀየረ እንቅስቃሴ ሲሆን የተመሰረተውም አሁን እንደገና የታሰረው ፖለቲከኛው እስክንድር ነጋ የፌደራል ህገ-መንግስቱ  በአዲስ አበባ ላይ ለኦሮሚያ የሚሰጠውን ‘ልዩ ጥቅም’ ለብቻው በመቃወሙ ነው።

አንዳንድ ጊዜ ባልደራስ የአማራ ኦርቶዶክስ ምልከታ እንዳለው ተደርጎ ይሳላል፤ ይህም በአብዛኛው ኦሮሞዎች ከሚኖሩበት ቢዮ አዋሌ የገጠር ቀበሌ እንደተገኘውና ሳተናውን በሚቃወመው እንደ አሊ አብደላ ባሉ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ዘንድ የሚነሳ ጉዳይ ነው። “እነዚህ ሰዎች የብዝኃነት ጠላቶች ናቸው’’ ሲል ለኢትዮጵይ ኢንሳይት ተናግሯል። “የአንድ ኃይማኖትና የአንድ ብሔር የበላይነትን ነው የሚፈልጉት።’’

የተዋጽኦ ለቲካ

የእርስ በእርስ የስልጣን ክፍፍል ቀመሩ 40፡40፡20 የሶማሌና ኦሮሞ ቡድኖች ያሉ ተፎካካሪ ምሁራን ስልጣን ውስጥ ከፍ ያለ ነገር ግን የተወሰነ ውክልና እንዲኖራቸው በማድረግ ግጭትን ለማስወገድ ያለመ ነበር። ለከተማዋ ከንቲባዎች ከሁለቱ ፓርቲዎች ነበር የሚሾሙት፤ አንዱም ሌላኛውን በየሁለት አመቱ ይተካዋል።

ተችዎች ስርዓቱ ከሁለቱም የብሔር ቡድኖች ውስጥ ለሌሉ ሰዎች ስልጣን፣ የመኖሪያ ቤትና የስራ እድሎች በእኩልነት እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኗል ይላሉ።

የከተማዋ የቀድሞ ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን ፋራህ በመጋቢት ወር በ2012 ዓ.ም በሰጡት ቃለምልልስ ስርዓቱን 40፡60 በማለት ነው የገለጹት ፤ በስርዓቱም ኢህአዴግ አብላጫውን ድርሻ ይይዛል።

ሶዴፓና  ኢህአዴግ ከተማዋን በዙር “ለማስተዳደር ተስማሙ፤ ይህም የሆነው የከተማው ዋና ነዋሪዎች በነዚህ ሁለት ፓርቲዎች የሚወከሉ ስለሆነ ነው’’ በማለት ኢብራሂም ያስረዳሉ። ስርዓቱም “ብዝኃነት እንዳላቸው የሚወክሏቸው ነዋሪዎች የተለያየ ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች ባሏቸው ቡድኖች መካከል ፍቱንና ውጤታማ የስልጣን መጋሪያ ወይም ክፍፍል ማድረጊያ መንገድ በመሆነ አገልግሏል።’’

ኢብራሂም በስርዓቱ ደስተኛ ያለመሆን ሁኔታ እንዳለ አልሸሸጉም ነገር ግን ይህ የመጣው እውነትን በሚያንሻፍፉ “ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ’’ ባላቸው ሰዎች ቀስቃሽነት ነው ይላሉ።

በስርዓቱ ደስተኛ አለመሆናቸውን ከማይሸሽጉት መካከል አንዱ ዳንኤል ሲሳይ ሲሆኑ፤ ድሬዳዋ ለአራት አስርት አመታት ኖሬያለሁ ሲሉ ፊታቸው ላይ ኩራት ይንጸባረቃል። ሆኖም ግን በደንብ ያልተያዘ በመውደቅ ላይ ያለ ከተማ አድርገው ነው የሚመለከቱት። ሌሎች ከተሞች እድገታቸውን የሚያፋጥን ትልልቅ ፕሮጀክቶች ሲገነቡባቸው ወይም እንደሚገነቡባቸው ቃል ሲገባ ፤ ድሬዳዋ ቸል በመባሏ ተደላድላ የተቀመጠች ትመስላለስች።

“ከተማ ነው። ትንሽ ነው። ከትልልቆቹ የክልል ከተሞች ለማስተዳደር እንዲሁም በተገቢው መንገድ የሚያስተዳድሩትን ሰዎች ለማግኘት የበለጠ እንዴት ቀላል አይሆንም?’’ በማለት ከኢትዮጵያ ኢንሳይት ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ በአግራሞት ይጠይቃሉ። ለዚህም በብሔር ተዋጽኦ ስርዓት የፖለቲካ ተሿሚዎች የሚመረጡበት የአስተዳደር ስርዓቱን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

የብልጽግና ፓርቲ ስምንት በአብዛኛው በብሔር ላይ የተመረኮዙ ፓርቲዎች በ2012 ዓ.ም መጨረሻ በመቀናጀት ሲመሰረት ዳንኤል የ40፡40፡20 ቀመር ማብቂያ እንደሚሆን ተስፋ አድርገው ነበር። ይህም ሶዴፓና  ኦህዴድ በይፋ አብቅቶላቸው ነበርና ነው። ነገር ግን ብልጽግና ፓርቲ የክልል አጋሮቹን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲጠብቅ ተገደደ በዚህም የተነሳ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲና የሶማሌ ብልጽግና ፓርቲ የቀደምት ፓርቲዎቻቸውን ታሪክ ማስቀጠል ይዘዋል።

ዳንኤል አሁንም ተስፋ እንዳለ ማሰብ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ለማየት የሚጓጉለት ለውጥ ከላይ መምጣት እንዳለበት ይረዳል። ምናልባትም ከምርጫው በኋላ የሚመሰረተው መንግስት “ህገ-መንግስቱን ያሻሽለው’’ ይሆናል በዚህም የፖለቲካ አወቃቀሩን ዳግም በማዋቀር ያሻሸለዋል ይላሉ። ነገር ግን “በከተማ አስተዳደር ደረጃ ብዙ ለውጥ አልጠብቅም’’

በድሬዳዋ የገጠራማው ክፍል ያለው አመለካከት በርካታ ብሔሮች ከሚገኙበት የከተማው ክፍል ያሉ ከተሜዎች ካላቸው አዝማሚያ ሙሉ ለሙሉ የሚቃረን ነው። ከኢትዮጵያ ኢንሳይት ጋር ባደረገው ቆይታ ከገጠር ቀበሌ የመጣው አሊ በኦሮሞና በሶማሌ ምሁራን መካከል ከተማዋን በዙር ለማስተዳደር የተደረገው ስምምነት ሌላው ቀርቶ በ2008 ዓ.ም በነበረው የበርካታ ሰዎች ህይወትን የቀጠፈውና በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያፈናቀለው የኦሮሚያና የሶማሌ የወሰን ግጭት ጊዜ ራሱ ዋና ዋና ግጭቶችን ለማስወገድ ረድቷል ይላል። በተጨማሪም የሁለቱንም ቡድኖች ባህላዊ ማንነት ለማጎልበት ይረዳል፤ የነዚህ ቡድኖች ባህላዊ ማንነት ያለዚህ ስርዓት ተረስቶ ይቀር ነበር ሲል ይሞግታል። ልክ እንደ ዳንኤል ሁሉ አሊ ከምርጫው በኋላ ለውጥ ይኖራል ብሎ እምብዛም ተስፋ አያደርግም። ለሱ በዚህ ረገድ ዋናው ጉዳይ ተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉ ምርጫዎች መታጣቸው ነው።

በድንበር ግጭቱ ወቅት ከኦሮሚያ የተሰደዱ የሶማሌ ሴቶች ከድሬዳዋ ውጭ በሚገኝ ካምፕ ውስጥ፥ ታህሳስ 2010 ዓ.ም፥ ፐብሊክ ሬድዮ ኢንተርናሽናል

የምርጫ ጉዳይ

በድሬዳዋ ለፌደራል የፓርላማ መቀመጫ ብልጽግና ፓርቲን በመፎካከር ለመወዳደር ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አንድ ገለልተኛ እጩ ተወዳዳሪዎች ተመዝግበው ነበር። የተወዳዳሪዎች ዝርዝር ኢትዮጵያዊነትን በሚያቀነቅኑ እንደ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፣የመላው ኢትዮጵያውያን የአንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ህብር) ባሉ ፓርቲዎች የተሞላ ነበር።

በይፋ ብሔር ተኮር ከሆኑት ፓርቲዎች ውስጥ በከተማዋ የሚንቀሳቀሰው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ነው። በተወሰኑ ሰዎች ዘንድ የኃይማኖት አዝማሚያ እንዳላቸው ተደርገው የታሰቡ ፓርቲዎችም ነበሩ። እናት ፓርቲ የኦርቶዶክስ ክርስቲያንን፤ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ ደግሞ ሙስሊም መራጮችን ወክለው ቀርበዋል የሚል ምልከታ ነበር።

የኦሮሞና የሶማሌ ብሔር ቡድኖችን የሚወክሉ ፓርቲዎች አልነበሩም። ሁለት ዋና ዋና ኦሮሞ ተኮር የሆኑ የመንግስት ተቃዋሚ ቡድኖች የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በ2013 ምርጫ ላይ አልተገኙም፤ ምክንያታቸውንም በገዢው ፓርቲ ተደጋጋሚ ትንኮሳ እንደረሰባቸው እንዲሁም አባላቶቻቸው ቁልፍ ሰዎችን ጨምሮ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ በመጥቀስ እጩዎችን ለማቅረብ ፍቃደኛ አለይደለንም በማለት ገልጸዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ ከሶማሌ ዋና ተቃዋሚ የሆነው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ውስጥ በርካታ አመታትን ያስቆጠሩት አህመድ መሀመድ እጩዎችን ለማስመዝገብ ያደረጉት ጥረት በገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት እንደተስተጓጎለባቸው በሚያዝያ ወር ላይ ተናግረዋል።

ይህ እውነታ ለከተማው ምክር ቤት መቀመጫም የተለየ አይደለም፤ ከ189 የምክር ቤት ወንበሮች 114ቱ ለገጠር አውራጃዎች የተመደቡ ሲሆን እያንዳንዱ ክፍለ-አውራጃም ሶስት ተወካዮችን ይመርጣል። ይህ ስርዓት በተወሰኑ ሰዎች ዘንድ ለገጠር ክፍለ አውራጃዎች ከፍ ያለ ድምጽ በመስጠት የተወሰኑ እርምጃዎችም እነሱ የሚጠቅም ተደርጎ እንዲወሰድ የሚያደርግ እንደሆነ ሆኖ ይታያል። የህግ ባለሞያና የፖለቲካ አስተያየት ሰጪው ውብሸት ሙላት ስርዓቱ የአውራጃ ወሰን በመፍጠር አንድ ፓርቲን በማሳነስ ሌላውን እንደ ማጎልበት ሂደት ሊታይ ይችላል በማለት ይሞግታሉ።

የከተማዋን ድምጽ ለማግኘት ከተወዳደሩት ፓርቲዎች የተወሰኑት ከምርጫው ቀደም ብሎ የነበሩት ጊዜያት በአመዛኙ ምቹ እንደነበሩ ይገልጻሉ። ይህም በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ እንደሆኑት ሱራፌል ጌታሁን ከሆነ “ከከተማዋ ወጥታችሁ 50 ኪሎ ሜትር ብትጓዙ ከምታዩት ነገር እጅግ የተለየ ነው” በማለት ዋና ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ  መሳደድና ማስፈራሪያ ስለደረሰባቸው የኦሮሚያ ክልል ይናገራሉ።

የኢዜማው ያሬድ አለማየሁ ከምርጫው በፊት ለኢትዮጵያ ኢንሳይት እንደተናገረው የተወሰኑ የምርጫ ቅስቀሳ ማስታወቂያዎች ባልታወቁ ሰዎች ከመነሳታቸው ውጪ ፓርቲው ጉልህ ችግር እንዳላጋጠመው ይናገራል።

“በድሬዳዋ አባሎቻችን እየጨመሩ ነው” ያላል ያሬድ። የአባላቶች ቁጥር የሚወሰነው የሚቀርቡት የፖለቲካ ሰነዶችና የፖለቲካ አስተሳሰቡ ያለው ተቀባይነት ላይ ተመርኩዞ ነው። በድሬዳዋ ቁጥሩ ቢሮ ከከፈትን ጀምሮ እየጨመረ ነው። ለውጥ አለ።’’

ቃልኪዳን አዳነ ከከተማዋ ዘጠኝ የከተማ ክፍለ-አውራጃዎች በስምንቱ ከሚወዳደረው እናት ፓርቲ ናት። “ምንም አይነት ችግር አላጋጠመንም’’ ትላለች።ነገር ግን ከአብን የመጣው ኑርልኝ ፀጋዬ በፓርቲው አባላትና በደጋፊዎች ዘንድ የፍርሃት ስሜት አለ ይህም የመጣው ባለስልጣናትን ጨምሮ ፓርቲውን የሚቃወሙ የተወሰኑ ሰዎች ፓርቲውን መርዛማ ድርጅት ብለው በመግለጻቸው ነው ይላል። “ይህ ጫና ይፈጥራል’’ ይህም ማለት አባላትና ደጋፊዎች ሀሳባቸውን በይፋ ለመግለጽ ይቸገራሉ ሲል ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግሯል። እንደዛም ሆኖ ከፓርቲው ዋና መቀመጫ አማራ ክልልና አዲስ አበባ ውጪ ካሉ ከሌሎች ክልሎች ጋ ሲነጻጸር የተሻለ ለመስራት ምቹ የሆነ ስፍራ እንደነበር አልካደም።

ነገር ግን ውጤቱ ሐምሌ 3 ይፋ ሲደረግ ሁሉም የከተማዋ ምክር ቤትና አንድ የተለቀቀ የፓርላማ መቀመጫን ብልጽግና ነበር ያገኘው።

በቋፍ ያለ እድገት

ከማርክሲስት አብዮት አስርት አመታት ቀድሞ በ60ዎቹ መጨረሻ ድሬዳዋ በደንብ የተደራጀ የውጭ ዜጎች ማኅበረሰብ ነበራት ይህም ከአዲስ አበባ በስተቀር የትኛውም የኢትዮጵያ ከተማ ያልነበረና ለከተማዋ እውነተኛ የብዝሃነት ቀለም የሰጠ ነበር። በድሬዳዋ የመጀመሪያዎቹ የተወሰኑ አስርት አመታት ወቅት በደቻቱ የሚለያዩት ከዚራና መጋላ መንደሮች የየራሳቸው ቀለም ነበራቸው፤ ከዚራ አውሮፓውያንን መጋላ ደግሞ በአብዛኛው የአገሪቱ ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችን ይይዙ ነበር። አማርኛ የከተማ አስተዳደሯ የስራ ቋንቋ ቢሆንም፥ በከተማዋ ሶስት ቋንቋዎች ማለትም ኦሮምኛ እና ሶማሌኛ በርካታ ነዋሪዎች ይነገሩባታል።

ወንደሰን ዘለቀ የቀድሞ የከተማዋ የንግድ ምክር ቤት ኃላፊና በአሁን ወቅት የድሬዳዋ የዲያስፖራ ህብረትን እየመሩ የሚገኙ ሲሆኑ “የንግድ ከተማ’’ በማለት ይጠሯታል። “ከመጀመሪያውኑ በንግድ ዙሪያ የተገነባች ከተማ ናት’’ በማለት ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግረዋል።

ነገር ግን ድሬዳዋ የባቡር ሀዲድን ማዕከል ያደረገው ኢኮኖሚዋ ጠቃሚነት በመቀነሱ የተነሳ አሁን ታሪካዊ የኢኮኖሚ ጠቃሚነቷን በአብዛኛው አጥታለኝ። ቢያንስ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች የሚሰማቸው ስሜት ይህ ነው ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት አስርት አመታት እንደ ሀዋሳ፣መቀሌና ባህርዳር ባሉ ከተሞች ፈጣን የከተማ እድገት ያየች ቢሆንም ድሬዳዋ ያለመግባባት ያለባት ከተማ ሆና ቆይታለች። እንደ ምሁሩ ደረጄ ፈይሳ እነዚህ አለመግባባቶች “በቋፍ ያለ የፖለቲካ’’ ሁኔታ በመፍጠር የከተማዋን የማደግ አቅም አቀጭጨዋልይህ አመለካከት በርካታ ነዋሪዎች የሚጋሩት ነው።

ተጨማሪ ዘገባ፡ ዳግማዊ ፈቃዱ

Query or correction? Email us

Follow Ethiopia Insight

ይህ ጽሁፍ ምርጫ 2013ን በሚመለከት ዘለግ ያሉ ጽሁፎችን ከመላው ኢትዮጵያ በተከታታይ የምናቀርብበት የ “Ethiopia Insight Election Project (EIEP)” ክፍል ነው።

ዋና ምስል: የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ድርጅት ቢሮ በድሬዳዋ

Join our Telegram channel

Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished.

We need your support to analyze news from across Ethiopia
Please help fund Ethiopia Insight’s coverage
Become a patron at Patreon!

About the author

Mistir Sew

This is a generic byline for all anonymous authors. The anonymity could be because they fear repercussions, as they are not authorized by their employers to express their views publicly, or for other reasons.

2 Comments

  • There would have been no city of Dire Dawa to talk about until Menelik founded it during his railway construction.

  • There is no as such Amhara orthodox Church, correct it with Ethiopian Orthodox church
    It’s misleading

Leave a Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.