Elections 2021 Ethiopian language In-depth

የፍትህ ስረአት ማሻሻያ በኢትዮጵያ፡ ወደ ፍትህ ማዝገም

ፍርድ ቤቶች አሁንም ድረስ በአዝጋሚ ለውጥ ላይ ቢሆኑም እንደ ድሮው ለመንግስት ፍላጎት የሚያጎበድዱ ከመሆን ተላቀዋል።

This is an Amharic language translation of EIEP article Judicial reform in Ethiopia: Inching towards justice.

በኢትዮጵያ ያለው የፍትህ አካል ገለልተኛ፣ታማኝና ብቁ ባለመሆኑ ይታወቅ የነበረ ሲሆን በዚህ የተነሳ ፍትህን ለሚሹ በርካታ ኢትዮጵያውያን ፍትህ ሊሰጥ አልቻለም ነበር።

ፍርድ ቤቶች ረዥም መጓተቶች መገለጫቸው የነበረ ሲሆን አንዳንድ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ፖለቲከኞች እና የመንግስት ባለስልጣናት አዘውትረው ጣልቃ ይገቡ ነበር።

በ1997 ዓ.ም ስለህግ ማሻሻያ የወጣ ዘገባ እንዳለው ከሆነ የፍትህ አካሉ ተደራሽ ያልነበረ፣ሙስኝነት የተንሰራፋበት፣በፖለቲካ አመለካከት የተቃኘ እና በቂ የገንዘብ ድጋፍ የማያገኝ ነበር። የፍትህ አካሉን ነፃነት አለማክበር (በተለይም መንግስትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ) በግልጽ የሚታይ ነገር ነበር።

ለምሳሌ በ1997 ዓ.ም የነበረውን የምርጫ ቀውስ ተከትሎ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሆኑት ዳኛ ተሻለ አበራና የፌደራል ዳኛ የሆኑት ወልደ-ሚካኤል መሸሻ የምርጫ መጭበርበርን እንዲያጣሩ መሾማቸውን ተከትሎ ከአገር ሸሽተዋል።

በ1998 ዓ.ም አቶ ተሻለ በፍትህ ስርዓቱ በአጠቃላይ አዲስ ለመንግስት ታማኝ የሆኑ ዳኞችን ለመሾም ስለመታቀዱ ለቢቢሲየተናገሩ ሲሆን አቶ ወልደ-ሚካኤል ደሞ በተቃውሞ ምክንያት የሞቱ ሰላማዊ ሰዎችን ቁጥር እንዲቀይሩ ግፊት ከተደረገባቸው በኋላ ከማይታወቁ ሰዎች የግድያ(ማስፈራሪያዎች) ዛቻዎች እንደደረሱባቸው ይናገራሉ።

እንደዚህ አይነት ክስተቶች ማሻሻያው ምን ያህል አንገብጋቢ እንደሆነ የጠቆሙ ሲሆን ማሻሻያ ግን ለኢትዮጵያ አዲስ ኃሳብ አልነበረም። ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ በተወሰኑ የገንዘብ ለጋሾች እርዳታ መንግስት የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል ሞክሯል።

በ1994 ዓ.ም አቅም ግንባታ ሚኒስቴር የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም ያካሄደ ሲሆን ይህም የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም በ1997 ዓ.ም በተካሄደ የመነሻ ጥናት ላይ በፍትህ ስርዓት ውስጥ ለሚገኙ ተዋናዮች በሙሉ—ማለትም ለህግ አውጪዎች፣ፍርድ ቤቶች፣የህግ አስከባሪ ኤጀንሲዎች እና የህግ ትምህርት ለሚሰጡ ተቋማት—በርካታ ጥቆማዎችን አቅርቧል።

ምንም እንኳን በአካባቢና (በዞን፣ወረዳና ቀበሌ) በመንግስት ደረጃ ላሉ ዳኞች በርካታ ትምህርታዊ ጉባዔዎች ቢካሄዱም በመነሻ ጥናቱ የተጠቀሱት መሰረታዊ ችግሮች ባለመፈታታቸው የተነሳ እምብዛም ውጤት ማምጣት አልተቻለም። የህግ ምሁር የሆነው አቶ ሄኖክ ጋቢሳ (መኖሪያውን በአሜሪካ ያደረገ በኦሮሞ ጉዳዮች ላይ ማኅበረሰብ አንቂ የሆነ እውቅ ተቃዋሚ ነው) በ2007 ዓ.ም በጻፈው ጽሁፍ ላይ እንደተገለጸው ስለፍትህ ስልጠና መስጠት በሚል ስም ለማሻሻያ የተመደበው በጀት ዳኞችን በፖለቲካዊ መንገድ ለማጥመቅ ውሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፍትህ የማይጨበጥ ሆኖ ቆይቷል ዘርፉም እምብዛም የመሻሻል ምልክቶችን አላሳየም። መሻሻያው የተንሰራፉ ዲሞክራሲያዊ ያልሆኑ ተግባራትን ለመደበቅ የሚሞክር መከለያ ይመስል ነበር።

ማሻሻያዎች በአዲስ መልክ

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት በፍትህ፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ (ምጣኔ ሀብት) ዘርፎች ማሻሻያዎችን አስጀምሯል።

የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ባካሄደው ጥናታዊ ምርምር መሰረት ቀደም ብለው የተደረጉ ማሻሻያዎች የህዝብና የባለሞያዎች እውነተኛ ተሳትፎ ይጎላቸዋል። አማካሪ ጉባዔው በማሻሻያዎች ንድፍና አተገባበር ላይ መንግስትን ለማማከር በ2010 ዓ.ም ነው የተቋቋመው።

ከዛን ጊዜ ጀምሮ ከረዥም ጊዜያት በፊት መካሄድ የነበረበትን ተሃድሶ ለመተግበር ጥረቶች መደረግ ጀምረዋል።

አሁን ባሉት ፕሬዝደንት መዓዛ አሸናፊ ስር ጠቅላይፍርድ ቤት የሶስት አመት ፕሮጀክት እየተገበረ ይገኛል።

የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ሰለሞን እጅጉ ማሻሻያዎቹ የበለጠ ምቹ የሆኑ የስራ ስፍራዎችንና ፍርድ ቤቶችን ከመፍጠር ጀምሮ አዲስ ህጎችን ማለትም የፌደራል ፍርድ ቤት አዋጅና የፌደራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ እስከመቅረጽ ያሉ እቅዶችን እንደሚይዙ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግረዋል።

የጊዜ መጓተቶች ከዋናዎቹ ጉድለቶች አንዱ ስለነበር ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የጉዳይ ፍሰት ማስተዳደሪያ መመሪያ ያወጣ ሲሆን መመሪያውም ጉዳዮችን በባህሪያቸው የሚከፍልና የፍታብሄር ጉዳይ ክሶች በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እልባት ማግኘት እንዳለባቸው የሚያስቀምጥ ነው። ከመስከረም 2014 ዓ.ም ጀምሮ መመሪያው በሁሉም የፌደራል ፍርድ ቤቶች ተግባር ላይ ይውላል።

ባለፈው የበጀት ዓመት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ለ166,758 ጉዳዮች እልባት ለመስጠት አቅደው የነበረ ሲሆን 171,276 ጉዳዮችን በመዳኘት እቅዳቸውን በ2.7 በመቶ አልፈዋል። በያዝነው በጀት አመት ደግሞ የአዲሱ መመሪያ መተግበር የክስ ጊዜን የበለጠ የሚያሳጥር ይሆናል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞችንና የፍትህ አካሉን ገለልተኝነት ለማረጋገጥ እርምጃዎችን እየወሰደም ነው። ከእነዚህም እርምጃዎች ውስጥ የፌደራል ዳኞች የስነምግባር ደንብና የቅጣት ሂደት መመሪያን ማሻሻል የሚገኝበት ሲሆን ይህም የፌደራል ዳኞችን ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማሻሻል ታስቦ የተደረገ ነው።

በተጨማሪም ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል ፍርድ ቤት ተቀጣሪዎች የሆኑ 4,000 ሰራተኞችን የማስተዳደር ኃላፊነት ከሲቪል ኮሚሽን ለመውሰድ እየተዘጋጀ ሲሆን ለዚህም የሚሆን ተገቢ መመሪያም አርቅቋል። ይህ እርምጃ የፍትህ አካላት ነፃ መሆን አለባቸው ከሚለው ህገ መንግስታዊ መርህ ጋር እብሮ የሚሄድ ነው።

ነሐሴ 7 በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ክብርት መዓዛ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰሩ ጥናቶች ተገልጋዮች 70 በመቶ የእርካታ መጠን እንዳላቸው ያሳያሉ ብለዋል።

ፌደራል ፍርድ ቤቶች የምርጫ ውዝግቦችን በመመልከት ያላቸው ሚና በጋዜጣዊ መግለጫው ከተነሱት ጉዳዮች አንዱ ነበር። በሶስት የፌደራል ፍርድ ቤት ደረጃዎች ለምሳሌ በመጀመሪያ፣በከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃ በአጠቃላይ 24 ልዩ ችሎቶች የተመሰረቱ ሲሆን 74 ከምርጫ ጋር የተያያዙ ውዝግቦችም ተዳኝተዋል፤ የተወሰኑትም ውሳኔ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

ምንም እንኳን ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ክብርት መዓዛ የክሶቹ ብዛት ከሚጠበቀው በታች እንደሆነና ወደ ልዩ ችሎቶች የመጡ ጉዳዮችም ውስብስብ ስላልሆኑ ያለከባድ ችግር ወደ ፍርድ ሂደት እንደሚያመሩ አትትዋል።

በሮያል አፍሪካን ሶሳይቲ መጋቢት 6 በተካሄደው ዌቢናር ክብርት መዓዛ የማሻሻያው ትኩረት እንደ ተቋም ፍርድ ቤቶችን እንዲሁም የዳኞችን ነፃነት ማረጋገጥ እንደሆነ አብራርተዋል።

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ከተወሰዱት የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች አንዱ የበጀት ጥያቄን በፋይናንስና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር እንዲገመገም በማድረግ ምትክ በቀጥታ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ማድረግ ነው—ይህ ቀደም ሲል ይካሄድ የነበረ ህገ መንግስታዊ ያልሆነ ተግባር ነው።

በቀድሞው አስተዳደር የነበሩ መሰል ከህገ መንግስቱ የሚያፈነግጡ ነገሮች በቂ በጀት ካለመኖሩ ጋር ተዳምረው የፍትህ አካሉ ጉድለት እንዲኖርበት ያደረጉ ናቸው። በዌቢናሩ ክብርት መዓዛ ባለፉት ሁለት የበጀት ዓመታት የፌደራል በጀት ላይ ከ30 እስከ 40 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል ያሉ ሲሆን በዚህ ዓመት የተመደበው በጀት 970 ሚሊዮን ብር ፤ ባለፈው ዓመት የተመደበው ደግሞ 660 ሚሊዮን ብር ነው።

የበጀት ጭማሪውን አስፈላጊ ያደረጉት የሰራተኛ አስተዳደር ስራዎች ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መዛወራቸው፣የተጨማሪ ችሎቶች መቋቋምና ህንጻዎችና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሞች መሻሻላቸው ነው።

ተስፋ ሰጪ ጅምር

አሁንም ብዙ ስራዎች መከናወን ቢኖርባቸውም እንደ እውቅ የህግ ሰዎች ከሆነ ማሻሻያዎቹ ቀደም ሲል ከተካሄዱ ጥረቶች ጋር እንዲሁም ከስራው ትልቅነት ጋር ሲተያዩ መልካም ጅማሮ አላቸው።

ጠበቃዎች እስከአሁን ድረስ ፍርድ ቤቶች የአገልግሎት አቅርቦት ላይ ደካማ ቢሆኑም መሻሻሎችን ግን እንዳስተዋሉ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት የተናገሩ ሲሆን ይህ ከአስርት ዓመታቶች በኋላ የፍትህ አካሉን ለማሻሻል የተደረገ የመጀመሪያ እውነተኛ ጥረት እንደሆነ ይጠቁማሉ።

ሙሉጌታ በላይ (ችሎት በተሰኘው የቴሌቪዥን ተከታታይ ጭውውት ላይ ዳኛ ሆኖ በመስራት ይታወቃል) የተወሰኑትን ችግሮች ያተተበት አንድ ጽሁፍ ጽፏል። እንደሱ ከሆነ ፍርድ ቤቶች በመንግስት በከፍተኛ ሁኔታ ችላ ተብለው ነበር በተጨማሪም የዳኞች ሹመትና እድገት ብዙ ጊዜ ያለተገቢ ጥንቃቄ ነበር የሚካሄደው።

‘’በተደጋጋሚ የሚባለው አባባል ‘’ከመክሰስ መከሰስ ይሻላል’’ ነው፤ምክንያቱ ደግሞ አንዳንድ ጉዳዮች ለዓመታት ሲለሚጓተቱ  ፍትህ ለማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በርካታ ኃይልና ገንዘብ ማውጣት ስላለበት ነው። ይህን በሙሉ ውጣ ውረድ ካለፈ በኋላም ከሳሹ በውሳኔው ደስተኛ ላይሆን ይችላል’’ በማለት ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግሯል።

እንደ ቃለምልልሱ ከሆነ ለዚህ መፈጠር ምክንያቶች የሆኑ የተወሰኑ ነገሮች ተገቢው የጊዜ ምደባና የበጀት አስተዳደር አለመኖር፣ የፍርድ ቤቶችና ዳኞች እጥረትና እንደ ድምጽ መቅረጫ ያሉ ቀላል መሳሪያዎች እጥረት ናቸው።

ሙሉጌታ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ክምችቶችን ዘመናዊ (ዲጂታል) ለማድረግና በድረ-ገጽ አገልግሎት ለመስጠት እየተካሄደ ያለውን ስራ እንዲሁም የህግ መሻሻሎችን ያደነቀ ሲሆን አሁንም ድረስ ግን የፍርድ ቤት ቦታ እጥረትና ረዥም ተደጋጋሚ ቀጠሮዎች አሉ ብሏል።

‘’የፍትህ ስርዓቱ መሻሻል እውን እንዲሆን የህጉ መሻሻል አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን የህግ ለውጦችን በሚገባ ሁኔታ የሚተገብር አስተዳደር ያለ አይመስለኝም። ስርዓቱን እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሰዎች አስተሳሰብ ለመቀየር በርካታ ነገሮች ሊደረጉ ይገባል’’ በማለት ያጠቃልላል።

አዲሱ የፌደራል ፍርድ ቤት አዋጅ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቁሳዊ ንብረት ላይ ያላቸውን የዳኝነት ስልጣን በመገምገም ቀደም ሲል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይወስንባቸው የነበሩ እስከ 10 ሚሊዮን ብር የሚደርሱ የሲቪል ጉዳዮች አሁን በአንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤቶች እንዲዳኙ አድርጓል። ‘’ይህ በእርግጠኝነት ለይግባኝ ያለውን ተደራሽነት ይጨምራል ነገር ግን ጥያቄው ቀድሞውንም ስራ የሚበዛባቸው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ተጨማሪ ግፊት መቋቋም ይችላሉ ወይ የሚለው ነው’’ ይላል ሙሉጌታ።

ጠበቃ ፋሲል ስለሺ ‘’ምንም እንኳን አሁንም መጓተቶች ቢኖሩምና እውነተኛ ተጠያቂነትን ለመፍጠር በርካታ ስራዎች ቢቀሩም የፍትህ አካላት ያላቸው ነፃነት እየጨመረ ነው’’ ይላል።

ከሰራተኛ ለውጦች ጎን ለጎን “ቀደም ሲል መንግስት ፍርድ ቤቶችን ተቃዋሚዎቹን ለማስፈራራትና ለመቅጣት ተጠቅሞባቸዋል። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ እውቅና በመስጠት ይቅርታ ጠይቀዋል፤ ይህም በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ያሉ ሰዎችን አመለካከትና አስተሳሰብ ለማስተካከል አግዞ ሊሆን ይችላል” በማለት ፋሲል ጠቁሟል።

ከድር ቡሎ ሌላ ጠበቃ ሲሆን (ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከሰሱ የፖለቲካ መሪዎችን በመወከል ጥብቅና የቆመ ነው) “አሁንም ከአስፈጻሚ ቅርንጫፎች በኩል በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ግፊት ሊኖር ይችላል ነገር ግን የነፃነት እጦት የኢትዮጵያ የፍትህ አካላት አሁን የሚታወቁበት ባህሪ አይደለም” ሲል ያትታል።

መንግስታዊ ባልሆነው የኢትዮጵያ የማግባባትና የድርድር ማዕከል የፕሮግራም አስተባባሪ የሆነችው ሜሮን ካሳሁን በዚህ ኃሳብ በአብዛኛው ትስማማለች። “በፍርድ ቤቶች የሚገኙ ችግሮች ሙሉ ለሙሉ አልተቃለሉም ነገር ግን ክሶች ቀደም ሲል ይወስዱ የነበረውን ያህል ጊዜ አይወስዱም እንዲሁም ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍርድ ቤት የሚካሄዱ ማስማማቶች ላይ የጀመረው ፕሮጀክትም (ይህ በዳኝነት ፋንታ በፍርድ ቤት ድጋፍ በስምምነት የተወሰኑ የፍታብሄር ጉዳዮች መፍትሄ የሚያገኙበት መንገድ ነው) የሚደነቅ ነው፤ ምክንያቱም ከመደበኛ የፍትህ መፍትሄዎች ይልቅ በፍርድ ቤት ድጋፍ  የሚደረጉ ማስማማቶች አነስተኛ ጊዜና ገንዘብ የሚወስዱ በመሆናቸው ነው’’ ብላለች።

የፍትህ ማሻሻያ ስራ በፍትህ እንቅስቃሴ የሚደገፍ ሲሆን ይህ እንቅስቃሴ በዩኤስ ኤይድ ድጋፍ የሚደረግለትና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱንና ዐቃቤ ህጎችን የሚያግዝ ድርጅት ነው።

የፍትህ እንቅስቃሴ ኃላፊ ዴቪድ ዲ ጃይልስ እስከ አሁን ድረስ ማሻሻያዎቹ በተለይም ሁለቱ አዲስ አዋጆች ስኬታማ እንደሆኑ ያምናል “አሁን ዳኛዎች ከበፊቱ የበለጠ ነፃነት አላቸው፣ ስርዓቱ ከበፊቱ በበለጠ ግልጽ ነው እንዲሁም ክስ አያያዝ እየተሻሻለ ነው’’ ብሏል። “በሌሎች አገራት ሰርቼያለው፥ በኢትዮጵያ የማደንቀው ነገር ለለውጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖሩን ነው’’ ሲልም ያክላል።

በቃለምልልሶች ላይ በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የወንጀለኛ ችሎት ውስጥ የነበሩ የተከሳሽ ቤተሰቦች የዳኞችን ብቃትና ፍትሀዊነት ያደነቁ ቢሆንም ከታደሙት ችሎት ውስጥ ግን አንዱም እንኳ በቀጠሮ ሰአት አለመጀመሩን በመጥቀስ በጊዜ አጠቃቀም ላይ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅና የፌደራል የፍትህ አካል አስተዳደር ጉባዔ አዋጅ (ሁለቱም በጥር ወር የወጡ ናቸው) ለማሻሻያው የህግ ድጋፍ የሚሰጡ ሲሆኑ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ በመጀመሪያ ደረጃና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የሚገኙ የሲቪልና የወንጀለኛ ችሎቶች ያላቸውን የዳኝነት ስልጣን እንደ አዲስ የሚያዋቅር ነው።

አዋጁ በፍርድ ቤት ለሚካሄድ የማስማማት ስራም አዲስ መልክ የሰጠ ሲሆን ይህም የፍትህን ተደራሽነት እንደሚጨምርና የመደበኛ ችሎቶችን መጨናነቅ እንደሚቀንስ ተስፋ ተጥሎበታል። አዋጁን ተከትሎም እስከአሁን ድረስ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አምስት ልዩ ችሎቶች ተመስርተዋል።

የፍትህ አስተዳደር ጉባዔ አዋጅ የጉባዔው አባላቶችን ስብስብ እንደሚቀይርና ከፍትህ ተቋማት ውስጥ የተውጣጡ አባላትን ቁጥር እንደሚጨምር ይጠበቃል።

ባለፉት ጊዜያት የፍትህ አስተዳደር ጉባዔ የመንግስት ጣልቃ ገብነትን በተቃወሙ ዳኞች ላይ ተገቢ ያልሆነ እርምጃ በመውሰዱና ስለፍርድ ቤት እንቅስቃሴዎች በቂ እውቀት ስለላልነበረው ትችት ይደርስበት ነበር።

የፍትህ አስተዳደር ጉባዔ ቀደም ሲል 12 አባላቶችን ይይዝ የነበረ ሲሆን ለመጀመሪያ ደረጃና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችንና ፕሬዝደንቶችን የመምረጥ ኃላፊነት ነበረበት። በተጨማሪም እድገት፣ደሞዝ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችም በጉባዔው የሚወሰኑ ሲሆን በዳኞች ላይ የሚወሰኑ የቅጣት ሂደቶችን የሚቀበለውና የመጨረሻ ውሳኔ የሚያሳልፈውም ጉባዔው ነበር።

ምንም እንኳን በጉባዔው የሚተላለፉ ውሳኔዎች በድምጽ ብልጫ ላይ የተመሰረቱ ቢሆንም ከጉባዔው 12 አባላቶቹ 5ቱ ብቻ ዳኞችና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶች ነበሩ።

የፖሊስ ስራ

በአጠቃላይ የህግ አውጪዎችና የፍትህ አካላትን የማሻሻል ጥረቶች በትክክለኛው መንገድ እያመሩ ነው። ነገር ግን በህግ አስፈጻሚ (አስከባሪ) ተቋማት ላይ ያለው ችግር የተደርጉ ማሻሻያዎችን ዋጋ እያቀቀጨ ይገኛል።

በዚህም የተነሳ የበለጠ ትኩረት እዚህ ስፍራ ላይ ሊደረግ ይገባል። የፍትህ አካሉ ስርዓት ከፍትህ ስርዓቱ ሰፊ ድርሻ የሚይዙትን የመርማሪና (የፖሊስ ተግባራትን የሚያከናውኑና) የከሳሽ ተቋማቶችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ብዙ ይቀረዋል።

በህግ አስፈጻሚዎች በዘፈቀደ የሚወሰዱ እርምጃዎች አንዳንድ ጊዜ በግላጭ የሚካሄዱ ናቸው። አንዱ የዚህ ምሳሌ የጃዋር መሀመድን ከፍተኛ እውቅና ያለውን የክስ ጉዳይ ጋዜጠኞች እንዳይከታተሉት የህግ አስከባሪዎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መከልከላቸው ነው።

በተጨማሪም የፍርድ ቤቶች ህገ መንግስቱን ለመተርጎም ያለመቻል ሁኔታ እንዲሁም የአስፈጻሚ አካል ስልጣንን ተቆጣጣሪ ሆነው ለመስራት አለመቻላቸው ለፍትህ እክል ነው።

እውቅ ጠበቃና ተመራማሪ እንደሆነው ስሜነህ ከሆነ “የፍርድ ቤቶች ስልጣን እንደማይከበር በግልጽ ይታያል፤ ሌላው ቀርቶ ‘ፍርድ ቤት’ የሚለው ቃል እራሱ የነሱን ሁኔታ አይገልጽም ምክንያቱም ፍርድ ቤት ስህተት በሚፈጠር ወቅት የመንግስት አካላትን ተጠያቂ ማድረግ መቻል አለበት’’ ይላል።

የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች በእርግጥም ዋና ዋና ችግሮችን በመቅረፍ ሂደት ላይ ቢሆኑም የፍትህ አካሉ መንግስትን (የአስፈጻሚውን አካል) በመደበኛነትና በተሳካ ሁኔታ የሚመረምርበት ደረጃ ላይ መድረስ አለበት።

የፌደራል ፍርድ ቤቶች በቅርቡ ለሁሉም ፍትህ መስጠት ይችሉ ይሆናል፤ ይህ ግን ተከሳሹ መንግስት እስካልሆነ ድረስ ብቻ ነው።

Query or correction? Email us

Follow Ethiopia Insight

ይህ ጽሁፍ ምርጫ 2013ን በሚመለከት ዘለግ ያሉ ጽሁፎችን ከመላው ኢትዮጵያ በተከታታይ የምናቀርብበት የ “Ethiopia Insight Election Project (EIEP)” ክፍል ነው።

ዋና ምስል: የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት።

Join our Telegram channel

Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished.

We need your support to analyze news from across Ethiopia
Please help fund Ethiopia Insight’s coverage
Become a patron at Patreon!

About the author

Leul Estifanos

Leul is a freelance court reporter and a law graduate of Addis Ababa University. He previously worked as a case reviewer at the Public Procurement and Property Disposal Service.

Leave a Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.