ምንም እንኳን የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ምህዳር ምስቅልቅል ውስጥ ቢሆንም የዚህ ዓመት ከፊል ምርጫ የተወሰኑ የአሰራር ማሻሻያዎች ታይተውበታል።
This is an Amharic language translation of the EIEP article EIEP: One vote forwards, two steps back for Ethiopian democracy
‹‹ኢትዮጵያ ትናንት አሸነፈች። ኢትዮጵያ በአሸናፊነት ትቀጥላለች!›› ሲል ይነበባል ፦ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የገዢው ብልጽግና ፖርቲ መሪ የሆኑት አብይ አህመድ ባለፈው ሰኔ 14 ቀን ከተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ማግስት በማህበራዊ ትስስር ገፆቻቸው የለጠፉት አጭር ፅሁፍ። ይህንኑ የምርጫ ቀንም ‹‹ታሪካዊ›› ሲሉ ለሃገሬው ህዝብ አውጀዋል።
የሰኔ 2013ቱ ምርጫ የኢትዮጵያን የፌዴሬሽን ቅርፅ አሁን ባለበት መንገድ እንዲቀረጽ ካደረገውና እስከአሁን ገዢ ህግ የሆነው ህገ መንግስት ከፀደቀ ጀምሮ በሃገሪቱ የተካሄደ ስድስተኛ አጠቃላይ ምርጫ ነው። ቀጥለውም ጠ/ሚሩ በፅሁፋቸው ይህንኑ ምርጫ ‹‹የሃገራችን የመጀመሪያው ነፃ እና ፍትሀዊ ምርጫ›› ነበር ሲሉ ገልፀውታል።
ሆኖም ግን ጠ/ሚሩ ስለምርጫው የሰጡት ይህ ብያኔ አጠቃላይ ምርጫው በመላው አገሪቷ ባልተካሄደበት ሁኔታ ፣ ከሁሉም በላይ የምርጫው ክንውን ያልተቋጨና ገና በሂደት ላይ በነበረበት ሁኔታ የተሰጠ እንደሆነ ግልፅ ነው። ብያኔው በራሱ ለአከራካሪነት የበዙ አመክንዮዎችን ሊያስነሳ ይችላል። ከነዚህ ማሳያዎች አንዱ የጠ/ሚሩ መልእክት ሲተላለፍ በአዲሷ የሲዳማ ክልል የሚገኙ 19 የምርጫ ክልሎችን ጨምሮ በሌሎች የክልል አካባቢ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ በቅንጅት፣ የምርጫ ቁሳቁሶች ጥራትና የክምችት እጥረት እንዲሁም የመጓጓዣ ጉድለትን በመሳሰሉት ጉዳዮች የተነሳ በሰኔ 14ቱ የምርጫ ቀን አለመምረጣቸው ነው።
ከእነዚህ የምርጫ አካባቢዎች የተወሰኑት የመረጡት በሰኔ 15 እንዲሁም በኋላ ነበር። በተጨማሪም በሃሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ከ100 በላይ የምርጫ ክልሎች በደህንነት ስጋትና በሌሎች መስተጓጎሎች ምክንያት በሰኔ 14 ምርጫ አልተካተቱም።
ቢሆንም ግን በሰኔ 14ቱ ምርጫ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በስምንት ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በ425 የምርጫ ክልሎች ወደሚገኙ 40,365 የምርጫ ጣቢያዎች በመጉረፍ ድምፃቸውን ለመረጡት ሰጥተዋል።
ከምርጫው ሂደት በኋላ ተከታትለው በመጡት ሳምንታት ‹‹ኢትዮጵያ አሸንፋለች›› የሚለው ሃረግ ስልጣን ላይ ያሉ ፖለቲከኞች ንግግር ማድመቂያ ፣ የመንግስት አፍ የሆኑት ‘የህዝብ’ መገናኛ ብዙሃን የዘገባ እይታ እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያው ንቁ በሆኑ የሚያደርጉ ግለሰቦች የሚጠቀሙት አዲስ ትርክት ተደርጎ ቀረበ። ይህ ትርክት በአንድ በኩል የምርጫውን ሂደት ሰላማዊነት አፅንኦት ለመስጠት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በምርጫ ጣቢያ የነበረውን ህዝብ ፍላጎት መገለጫ ተደርጎ ሊታይም ይችላል። ለዚህ ተነሳሽነት ማረጋገጫው ከተመዘገበው መራጭ ውስጥ አብዛኛው በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ መገኘታቸውና በሰላምና በፍላጎት ድምፅ መስጠታቸው ነው።
በምርጫው ከ38.2 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለመምረጥ የተመዘገቡ ሲሆን ይህም ቁጥር ቀደም ሲል ከነበሩት አምስት ምርጫዎች በሙሉ የሚበልጥ ነው። በርግጥ የሃገሪቱ የህዝብ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ከመሆኑ አኳያ የመራጩ ህዝብ በዛው ልክ መጨመር የሚያስገርም ነገር ላይሆን ይችላል። በአገሪቷ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ከተመዘገቡት ከ1.8 ሚሊየን በላይ ከሚሆኑ መራጮች 99 በመቶ (በምርጫ ቦርዱ አሃዝ መሰረት) የሚሆኑት በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት እስከ እኩለ ለሊት ድረስ በመሰለፍ መርጠዋል። ይህም የሆነው ቁጥራቸው የበዙ መራጮች እንዲመርጡ ለማስቻል የድምፅ መስጫ ሰዓቱ በመራዘሙ ነው።
የምርጫ ቦርድ አሃዞች እንደሚያሳዩት ከ32 ሚሊየን መራጮች ውስጥ በአማካይ 94.5 በመቶ የሚሆኑ በአፋር፣አማራ፣ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣የደ/ብ/ብ/ህ/ክልላዊ መንግስትና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ መራጮች በሰኔው ምርጫ መርጠዋል።
ነገር ግን መራጮች ከተመዘገቡባቸው ክልሎች የሶማሌና ሀረሪ ነዋሪዎች በየክልሎቹ ባለው ሁኔታ እንዲሁም በሂደቱ በተነሱ ተቃውሞና ቅሬታዎች ሳቢያ በምርጫው ቀን ያልመረጡ ሲሆን በቤንሻንጉል-ጉሙዝ ከተመዘገቡት 162,609 መራጮችም 55 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ወደ ምርጫ ጣቢያ ያመሩት። ይህም የፀጥታ ሁኔታው አስተማማኝ ባልሆነበት በዚሁ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች ምርጫ ባለመካሄዱ ነው።
ታዲያ የምርጫው ቀን እየተቃረበ በመጣ ጊዜና በሂደቱም በርካታ ኢትዮጵያውያኖች ላይ ጭንቀት ይነበብ ነበር። ይህ ምርጫ በሰላም ይለፍ የሚሉና መሰል የስጋት ድምፆች ከምርጫው ወራት፣ሳምንታት እና ቀናት በፊት ከበርካቶች አንደበት ሲሰነዘሩ ሰምቼያለሁ።
በእርግጥም ኢትዮጵያ በብሔር ልዩነት ፣ በትጥቅ ትግል ባመኑ ቡድኖች ፣ በክልል መንግስታት መሃል በሰፈኑ ውጥረትና አለመግባባቶች ፣ ደግሞ ከሁሉ በላይ በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልላዊ መንግስት መካከል በተፈጠረ የግንኙነት መሻከር ምክንያት በትግራይ እና በአካባቢው በተፈጠረው ደም አፋሳሽ ጦርነት የተነሳ ቀውስ ውስጥ ነው የከረመችው።
በመላው አገሪቱ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የነበሩ የደህንነት ስጋቶች የምርጫውን ቀን ትርክቶችንም ያጨለሙ (የድምፅ መስጫው ቀን ላይም ጥላ ያጠሉ) ነበሩ። በርግጥ የስጋት አስተያየቶች በሙሉ ተገቢና ምክንያታዊ ሊሆኑ ይችላል። የምርጫው ቀን ግን በአንጻሩ በሰላማዊ መንገድ ያለፈና ለከፊል የሃገሬው ዜጎች የተስፋ ጮራን ፈንጥቆ ያለፈ ነበር።
‹‹የድምፅ መስጫው ሁነት ከምርጫው በፊት፣ ስለምርጫ ቀን እና ከምርጫ በኋላ አመፅና አለመረጋጋት ይፈጠራል በሚል ሲሰሙ የነበሩ አሉታዊ ትርክቶችን ውድቅ ያደረገ ነበር። ከሁሉም የምርጫው ተዋናዮች በበለጠ ሁኔታ መራጩ ህዝብ ከሁሉም በላይ ሰላምንና ሃገርን እንደ ሃገር ማስቀጠልን እንደሚያስቀድም በማስመስከር ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ እንዲደረግ ጉልህ ሚና ተወጥቷል›› በማለት የህግ ባለሞያውና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ በስፋት የሚሰራው ደበበ ሃይለገብርኤል በሐምሌ ወር ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግሯል።
‹‹ምንም እንኳን በምርጫው ሂደት ላይ ከአሰራርና ቅንጅት እንዲሁም ከፓርቲዎች ጋር ተያይዞ አንዳንድ ግልጽ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም፤ ምርጫው በአጠቃላይ በሃገራችን እንዲጀመር ለምንፈልገው የዴሞክራሲ ሂደት ተስፋ የሚሰጥ ተሞክሮ ሆኖ ያለፈ እንደነበር ይሰማኛል›› ሲል ያክላል ደበበ።
ይሁን እንጂ አስቀድሞ ስለዚህ አመቱ ምርጫ ይነሱ ከነበሩ የተወሰኑ ትንበያዎች በከፊል እውነት የሆኑ ሁነቶች ያሉ ይመስላል። ዴሞክራሲ እንዲያብብ ሊረዳ በሚችለው የምርጫ ፖለቲካ መሰረታዊ መርሆዎች መሰረታዊ የሆነው ‹ነፃና ፍትሀዊ ፉክክር› መጠላለፍና ቅራኔ በበዛበት የሃገሪቱ የፓርቲ ፖለቲካ ምክንያት ፈተና ውስጥ ወድቋል። በመጨረሻም የምርጫው ውጤቶች ስለሂደቱ ብዙ ነገር የሚናገሩ ሆነው ተገኝተዋል።
በሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ፣ ከምርጫው 18 ቀናት በኋላ ፣ ነበር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የስድስተኛውን ሃገራዊ ጠቅላላ ምርጫን ውጤት ያሳወቀው።
በውጤቱም የብልጽግና ፓርቲ ለውድድር ከቀረቡ 436 የፌደራል መቀመጫዎች ውስጥ ከ26ቱ በስተቀር የተቀሩትን ሁሉንም ማሸነፍ ችሏል። በተመሳሳይ ለውድድር ከቀረቡ የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ሊነፃፀሩ በማይችሉ ሰፊ የቁጥር ልዩነቶች ብልፅግና ተፎካካሪዎቹን በልጦ ሲወስድ ፣ የሁለቱን ከተማ አስተዳደሮች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) መቀመጫዎች ያለተቀናቃኝ ጠቅልሎ የራሱ አድርጓል ።
ሃገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በሆነው ‹‹የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል›› ዳይሬክተር የሆነው በፍቃዱ ኃይሉ ‹ኢትዮጵያ አሸነፈች› የሚለው ትርክት በአግባቡ ሊታይ የሚገባውና ጥያቄ የሚያነሳ እንደሆነ ያምናል። ‹‹በዋነኛነት የነበረው ተስፋ የምርጫ ሂደቱ ከዚህ በፊት ከነበሩ አካሄዶች የተለዩና የተሻሉ ነገሮችን እንዲያሳይ ነበር። በዚህ ረገድ እንደ ጥሩ መለማመጃ ሊታይ የሚችል ሂደት ነበር›› ይላል ለኢትዮጵያ ኢንሳይት አስተያየቱን ያጋራው በፍቃዱ።
‹‹ነገር ግን የተቃዋሚ ፖለቲካ ፖርቲዎች ምርጫውን በማሸነፍ መንግስት ይመሰርታሉ ወይም የክልል ምክር ቤቶችን ይቆጣጠራሉ የሚል ምንም አይነት እምነት አልነበረም። በተጨማሪም ፍፁም ባልተመጣጠኑ ሃይሎች መካከል በተካሄደው በዚህ ምርጫ ኢትዮጵያ አሸንፋለች ለማለት ይከብዳል›› ሲል በፍቃዱ ሞግቷል።
የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ‹‹ኢትዮጵያ አሸንፋለች›› የሚለውን ብያኔ በማስተጋባትና የምርጫውን ሂደት ለማደናቀፍ ሞክረዋል የሚሏቸውን የውስጥ ኃይሎች ፣ በዋነኝነትም ህወሃት እና ኦነግ ሸኔን ፣ በመወንጀል ተጠምደው ቆይተዋል። ነገር ግን የሰኔው ምርጫ በአንፃራዊነት ሰላማዊ የሆነ ምርጫ ማድረግ ማለት በሃገሪቱ ሰላማዊ ፖለቲካ እንዳለ የሚገልፅ አለመሆኑን ያሳያል።
ከዚህም በላይ ፣ እንደ በፈቃዱ ምልከታ ፣ የብልጽግናን አሸናፊነት እንደ ኢትዮጵያ አሸናፊነት አድርጎ ለማቅረብ የሚሞከረው ነገር ‹‹በጣም አደገኛ ነው›› ።
የምርጫው ሂደት ምልከታ
‹‹[የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ] በዚህች ሃገር ምርጫ ለማካሄድ መቻሉ በራሱ ድል ነው›› በማለት የምርጫውን ውጤት በይፋ ማሳወቂያ መርሃግብር ላይ የተናገሩት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ነበሩ። ንግግራቸው ውስብስብና ረዥም ጊዜያትን በፈጀው የምርጫ ሂደት ላይ ዋና ተዋናይ የሆነው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተወጣውን ከባድ ሃላፊነት ከግምት ያስገባ ብቻ ሳይሆን ስለሃገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ አፅንኦት የሚሰጥም ጭምር ነው።
ቦርዱ ምርጫውን በሚያካሂድ ወቅት በተቋማዊና ህጋዊ ማሻሻያዎች ውስጥ እያለፈ ነበር። በተጨማሪም ከተቃዋሚ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ ውስጥ ከሚገኙ የፖለቲካ ልሂቃን በሚሰነዘር ግፊትና ትችት ምክንያት በአስቸጋሪ የስራ ፀባይ ውስጥ ሆኖ ሂደቱን መምራት ነበረበት።
በርግጥም ለምርጫ ቦርድ አባላቱ እንዲሁም ቀደም ሲል የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኛና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ለነበረችው ፤ ከዛም ትልቁን ሃላፊነት በህዳር ወር 2011 ዓ.ም ለተረከበችው የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ት ብርትኳን ሚደቅሳ አስቸጋሪ ጉዞ ነበር።
በወቅቱ ብርትኳን በጠ/ሚሩ መሾሟ በራሱ አስገራሚ ነገር ነበር። ጠ/ሚር አብይ የቀድሞ ፓርቲ የሆነውና ሃገሪቱን ለሶስት አስርት አመታት ገደማ የመራው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ተቃዋሚ የነበረች እንደመሆኗ ለዚህ ኃላፊነት መመረጧ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሻሻያ አንድ አካል ተደርጎ ነበር የተወሰደው።
በጊዜው ቦርዱን በድጋሚ ለማዋቀር ይቻል ዘንድ ህጉን ለማሻሻል ይሰራ የነበረው የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ የህግ ማሻሻያውን ሳያጠናቅቅ የብርትኳን ወደ ስራ ሃላፊነቱ መምጣትም እንግዳ ነበር። ነገር ግን እርሷ ቦርዱን ሰብሳቢ ሆና ማገልገሏ ትልቅ እርምጃ ነበር፤ በቦርዱም የተቀሩትን የቦርድ አባላት የማሟላትና ከምርጫ ጋር የተያያዙ ህጎችና ደንቦችን ከሚከልሱ አካላት ጋር ለመስራት ትልቅ እድል ሰጥቷታል።
ምንም እንኳን አድካሚና በሁከት የታጀበ ሂደት ቢኖርበትም ፣ ምርጫ ቦርድ በስኬት እንዲካሄድ ያስቻለው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ እንደ ናሙና በመሆን ቦርዱን ለአጠቃላይ ምርጫው እንዲዘጋጅ ሳያደርገው አልቀረም። ነገር ግን አጠቃላይ ምርጫው (ሶስት ጊዜ የተላለፈ ነው) ለቦርዱ ያልታሰቡ ፈተናዎች እንዲደቀኑበት ያደረገ ነበር።
በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በእጅግ ከባድና ሃገሪቱን እድለቢስ ባደረገ ከመምጣቱ በላይ የምርጫውን ጊዜ ለማዘግየትና የፌደራልና የክልል መንግስታትን የስራ ዘመን ለተጨማሪ አመት ለማራዘም ሰበብ ሆኗል። ይህም በተራው በፖለቲካው ውስጥ ያሉትን ውጥረቶች በተለይም በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግታት መካከል የነበሩ ውጥረቶች እንዲባባስ አድርጓል።
በተጨማሪም የምርጫ ቦርድ ገዢው ፓርቲውን ጨምሮ በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ፈተዎች ገጥመውት ነበር። መሰናክሎቹ ግን ከቦርዱ ውስጣዊ ችግርም የመነጨ ነበር። በተለይም አንድ የቦርዱ አባል ባለፈው አመት ለመልቀቅ ከወሰነ በኋላ በቦርዱ ውስጥ አለመግባባት ስለመኖሩ ጠቋሚ እንደሆነ ያስረዱ ታዛቢዎች መኖራቸው አያስገርምም።
በዚህ ሁሉ ሂደት ነው እንግዲህ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርትኳን ወደ ፊት መጓዝ የቀጠለችው።
‹‹ገለል ማለት እራስን በጣም ቀዝቃዛ ቦታ ማስቀመጥ ማለት ነው። ገለል ማለት እና ያንን የስራ ነፃነትን ለማስከበር መስራት ማለት በብዙ ፍጭት ውስጥ ፣ በብዙ ግጭት ውስጥ ማለፍ ማለት ነው። እኔና ባልደረቦቼ ፣ ሌሎችም እዚህ የምታዩዋቸው በዚህ ሂደት ውስጥ ብዙ ነገር አይተናል፤ ብዙ ተምረናል ፤ ብዙ ተቸግረናል›› ስትል ነበር የቦርዱ ሰብሳቢ በውጤት ማሳወቂያው ዝግጅት ላይ ባደረገችው ንግግር ያነሳችው ።
ወ/ሪት ብርትኳን በንግግሯ ቦርዱ የቱንም ያህል ግልጽ ለመሆን ቢሞክርም ፤ ምርጫው ግን ‹ነፃና ፍትሃዊ› ለመሆን እጅግ ብዙ እንደሚቀረው አልሸሸገችም። ስለምርጫ ሂደቱ በርካታ ነገሮችን የተቸች ሲሆን ለምሳሌ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ለምርጫ ቅስቀሳና ለፓርቲ ፕሮግራም ማስተዋወቂያዎች እኩል ሚዛንና ሰዓት አለመስጠታቸውን ፤ በተለይም ለገዢው ፓርቲ ፍፁም ያደሉ እንደነበሩ፤ በመጠቆም ተችታለች።
የሚገርመው ነገር ግን አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንና አንዳንድ የሃገር ውስጥ የግል መገናኛ ብዙሃን በይፋዊ የውጤት ማሳወቂያ ስነ-ስርዓት እንዲታደሙ አልተፈቀደላቸውም። በዚህም የተነሳ የተወሰኑ ጋዜጠኞች በቦርዱ አሰራር ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። በተቃራኒው ቦርዱ ሰብሳቢ ሚዛናዊ ስላልነበረው የምርጫ ፕሮግራሞቻቸው ቅሬታ የቀረበባቸው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዝግጅቱን እንዲታደሙና በቀጥታም እንዲያስተላልፉ ልዩ ፍቃድ ተሰጥቷቸው ነበር።
እዚህ ላይ ግን የምርጫው ፉክክር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ፣ ምንም እንኳን የተወሰኑ የህዝብ ግንኙነት ችግሮችና በመጨረሻም ትልልቅ ጋዜጠኞች ቦርዱን የመውቀሳቸው ነገር ቢኖርም፣ የምርጫ ቦርዱ መገናኛ ብዙሃን ምርጫውን የመዘገብ መብታቸውን አክብሯል ፤ በሌሎች እንዲከበርም አድርጓል ለማለት ያስደፍራል።
በኢህአዴግ ዘመን የፖለቲካ እስረኛ የነበረውና ከኢህአዴግ የተወለደው ህገ መንግስት ላይ ማሻሻያን የሚጠይቀው በፍቃዱ ሃይሉ ፤ ‹‹ምርጫው ነፃ፣ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ሊታይ የሚችል አይደለም ። ነገር ግን ሂደቱ ለወደፊት የዲሞክራሲ እንቅስቃሴዎች ጥሩ ትምህርት ሆኖ ያለፈ ነው። የምርጫ ቦድር የሚበረታቱ ጥረቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ እንዲሁም ህዝቡ ለሰላም ያሳየው ፍላጎትና ምርጫ ለመምረጥ የወጡ ሰዎች ቁጥር ያሳያሉ›› ይላል።
ከነዚህ ሁነቶች የተወሰኑት በዋና ከተማዋ የተስተዋሉም ነበሩ።
ኢትዮጵያ ኢንሳይት በአዲስ አበባ በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ የምርጫ ስፍራዎችን በቃኘበት ወቅት በትልልቅ የምርጫ ክልሎችና በየወረዳው በነበሩ ጣቢያዎች ውስጥ ወጣቶች የምርጫ ጣቢያ ሃላፊዎች ሆነው በትጋት ሲሰሩ ተመልክቷል። በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያ ደግሞ እነዚሁ ወጣት ሃላፊዎች በታችኛው የአስተዳደር እርከን ላይ ከሚገኙ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና አባላት ጋር ሲከራከሩና ከጣቢያው ለቀው እንዲሄዱላቸው ሲጠይቋቸው መመልከት ችሏል።
ሌላው በዚህ አመት ምርጫ ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ ከነበራቸው ባለድርሻዎች የሚጠቀሱት ደግሞ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ነበሩ። በዋናነት ከ1997 ዓ.ም አጠቃላይ የምርጫ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ነበራቸው። ነገር ግን በ2001 ዓ.ም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅና ለዚሁ አዋጅ ማስፈፀሚያ ህጎች ከወጡ ለአመታት እንቅስቃሴዎቻቸው እንዲዳከም ሆኗል።
የዚህ አመቱ ምርጫ በችግር ውስጥም ሆነው ለአመታት ለሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ትንሳዔን የሚያመለክት ነው ሊባል የሚችል ሲሆን አዲስ ለሆኑ አንዳንድ ድርጅቶችም የመጀመሪያ ምዕራፍን ያመለክታል።
በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም አዲስ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ህግ ተሻሽሎ የፀደቀ ሲሆን ይህም የዲሞክራሲ ተቋማቶችን ለማጠናከርና የመብት ተከራካሪዎችን ወሳኝ ስራ ለመደገፍ ከተደረጉ የማሻሻያ ሂደቶች አንዱ ነው። ይህ ደግሞ ለ11 አመታት በስራ ላይ የነበረውንና ‹አፋኝ› ተብሎ የሚነሳውን አዋጅ በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሻለ ነበር። የቀድሞው አዋጅ መብት ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች 90 በመቶ የገንዘብ አቅምን ከአገር ውስጥ እንዲያሰባስቡ ከማድረግ ጀምሮ በመብትና ዴሞክራሲ ዙሪያ የሚሰሯቸውን ስራዎች ያለአግባብ በመተርጎም እንቅስቃሴዎቻቸውን ለመቀልበስ የታለሙ መመሪያዎች ስራ ላይ ያዋለ ነበር።
ከምርጫው በኋላ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የማጠቃለያ ሪፖርት እንደሚያሳየው 46 ሃገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአጠቃላይ 44,560 ታዛቢዎችን አሰማርተዋል። የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶቹ በሂደቱ በሙሉ በደንብ ተሳትፎ ለማድረግ የቻለ ህብረት ፈጥረዋል። ስራቸው ግን ችግር የሌለበት አልነበረም።
‹‹የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች በዚህኛው ምርጫ የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት ሞክረዋል። በምርጫው ከነበራቸው ቁጥርና ፍላጎት አኳያ ከዚህም የተሻለ መስራት ይችሉ የነበር ቢሆንም በአጠቃላይ የሚያበረታታ ተሳትፎ ነበራቸው። በተለይ ፤ ምንም እንኳን ዘግይቶ የጀመረ ቢሆንም፤ በስነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ላይ የነበራቸው ሚና ላይ ጠንክረው ሊሰሩ ይችሉ ነበር። ነገር ግን የፈንድ እጥረት ነበር። የፈንድ ጉዳይ በቀላሉ እራሳቸው ባሰቡበት መንገድ የሚሄድ አልነበረም›› ይላል በህግ ማሻሻያዎች አማካሪ ጉባዔ ውስጥ አዲሱን የሲቪል ማኅበራት ህግ የሚያረቀው ጥናት ቡድን ሊቀመንበር የነበረው ደበበ ሃይለገብርኤል።
‹‹የዓለም አቀፍ ለጋሾች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ለመደገፍ ያሳዩት ፍላጎት አነስተኛ ነበር። በተለይም እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ ተቋማትን በደገፉበት ልክ ሲታይ ለሲቪል ማህበራት ድርጅቶች የተደረገው እጥረት ነበረበት። ይህ ደግሞ እስከታች የገጠር አደረጃጀቶች ወርደው መስራት የነበረባቸውን ስራ ገድቧል›› ሲል ደበበ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት አስረድቷል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጀቶች የነበራቸው ብቸኛ የገንዘብ ምንጭ የተገኘው መቀመጫውን በሃገረ አሜሪካ ካደረገው አለም አቀፉ የሪፓብሊካን ተቋም (IRI) ነበር። እንደ ደበበ ሃሳብ የገንዘብ ድጋፎች በፍትሀዊ መንገድ በመሬት ላይ ለሚገኙ ተዋናዮች ከአንድ ቋት ተሰብስቦ (basket fund) ቢሰራጭ ይጠቅም ነበር ይላል። ይህ አሰራር በ1997 ምርጫ የተሞከረ ሲሆን በዚህኛው ምርጫ ግን በበለጠ ሁኔታ እውን ሊሆኑ ይችሉ ነበር።
የምርጫ ታዛቢዎች በምርጫ ጣቢያዎች ተከስተዋል ካሏቸው ህፀፆች አንዱ ፆታን መሰረት ያደረጉ ትንኮሳዎች እንደሆኑ የተጠቀሰ ቢሆንም በርካቶች የሴቶች ተሳትፎ አጥጋቢ አለመሆኑንም አላሰመሩበትም።
የመጫወቻ ሜዳው ልዩነት ፣ ጠባቡ የፖለቲካ ምህዳር
የሰኔ 14ቱ አጠቃላይ ምርጫ በርግጥም ሰላማዊ ነበር። የምርጫው ሰላማዊነት ትርክት ግን ሃገሪቱ የገባችበትን ትልቅ ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ብሎም በዴሞክራሲያዊ ስርአት ወደኋላ የማፈግፈጓን ሁኔታ ሊሸፍን አይገባም። ምርጫው ብቻውን የሃገሪቱን አስፈሪ የደህንነት ስጋቶች ለመታገል እምብዛም እንዳልሰራ ያስጠነቀቁ ታዛቢዎች ይህንኑ ይጋራሉ።
የሃገሪቱን መሰረታዊ፣ሥር የሰደዱና የበዙ ከባድ ልዩነቶችን ለመፍታት የሚያስችሉና ትርጉም ያላቸው ውይይቶች ባልተደረጉበት ሁኔታ የተካሄደው ይህ ምርጫ ለአዲስ መንግስት ስልጣን የሚሰጥ ይሆናል። ነገር ግን ይህ አዲስ መንግስት የስራ ዘመኑን እጅግ ውስብስብ በሆኑ ችግሮች የታሰረች ሃገርን በማስተዳደር የሚገፋ ይሆናል።
‹‹ይህ ምርጫ የአገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች የሚፈታ አይደለም›› ይላል በፍቃዱ።
የምርጫ ቦርድ ጭምር በተደጋጋሚ ስጋቱን ከገለፀበት ጉዳይ አንዱ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብና ካለፉት አመታት እምብዛም ያለመቀየሩ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አሁንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በገዢው ፓርቲ ትንኮሳ ይደርስባቸዋል፣ ፅህፈት ቤቶቻቸው ይዘጋሉ፣ አባሎቻቸው ይታሰራሉ ብሎም ተቋማት ለገዢው ፓርቲ በሚመች መልኩ ይጠመዘዛሉ።
ከምርጫው ቀደም ብሎ በነበሩ ጊዜያት የነበሩት ስጋቶች ከደህንነት ጋር የተያያዙ ነበሩ። ቦርዱ ከፌደራል ተቋማት በተለይም ግጭት ያለባቸውን አካባቢውች ከመለየት አንስቶ አጠቃላይ የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮችን በተመለከተ ‹‹ተገቢውን መረጃ እያገኘን አይደለም›› በማለት በሰብሳቢዋ በኩል ቅሬታ ሲያቀርብ ተደምጧል።
በህዝብ ቁጥር ብዛት ቀዳሚ በሆነችው የኦሮሚያ ክልል ደግሞ ከደህንነትና ለምርጫው አይነተኛ ተፎካካሪዎች ናቸው የተባሉ ፓርቲዎችን ከማፈን ጋር የተያያዙ ሁነቶች በተለየ ሁኔታ የሚነሱና ውስብስብም ነበሩ። ቀደም ሲል በኢህአዴግ ዘመን ‹‹ሽብርተኛ›› ተብለው የተፈረጁ የተቃዋሚ ቡድኖችና ድርጅቶች በጠ/ሚር አብይ አስተዳደር ወደሃገር ቤት ተመልሰው እንዲገቡ ተደርጎ ነበር። በገቡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ምን አይነት የፖለቲካ መሰረት መገንባት ይችሉ እንደሆነ ለማየትና የማህበራዊ መሰረታቸውን ለማጠናከር በሰላማዊ መንገድ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲሞክሩ ነበር።
ለኦሮሞ ህዝብ ድምፅ በመሆን የሚታወቁት አንደነ ጀዋር መሃመድ ያሉ እውቅ የማኅበረሰብ አንቂዎች ወደ ፓርቲ ፖለቲካው መግባታቸውን ጤናማ የፉክክር ዴሞክራሲ ሂደት ምእራፍን ሊከፍት እንደሚችል የሚያመለክቱ ሁነቶች ነበሩ። ጀዋር ቀደምት የፖለቲካ ምሁር በሆኑት መራራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) የሚመራውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀላቀለ። በመቀጠልም ኦፌኮ ከኦሮሞ ብሔርተኛ ፓርቲዎች ታሪካዊ መሰረት ካለውና በኦሮሚያ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ አለው ተብሎ ከሚታመነው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ጋር የፖለቲካ ህብረት መሰረተ።
በሂደቱ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ስለምዝገባ ሂደቱና በፍትሀዊ መንገድ መሳተፍ ስላለመቻላቸው በርካታ ቅሬታዎችን እያነሱ የቀጠሉ ቢሆንም ዜጎች የእውነት አማራጭ የሚኖራቸውና በውጤቱም ላይ ተጽእኖ ማሳረፍ የሚችሉበት ፤ ኢትዮጵያም እስከአሁን አድርጋው የማታውቀው አይነት ምርጫ ለማድረግ እያመራች እንደነበር በበርካቶች ዘንድ የተፈጠረ አንድምታ ነበር።
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ግን ሁሉንም ነገር ቀየረ።
ተወዳጁ የኦሮሚኛ ሙዚቃ አቀንቃኝና እውቅ የመብት ተሟጋች የሆነው ሀጫሉ ሁንዴሳ ቦንሳ በርካቶች ሴራ አለበት ብለው በሚያምኑት ሁኔታ በዛች ቀን ምሽት በግፍ ተገደለ። ጀዋርና የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበርና እውቁ ፖለቲከኛ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች የተቃዋሚ መሪዎች እስከ አሁንም ድረስ ለሚገኙበት እስር ተዳረጉ። ዘግየት ብሎ ኦፌኮ ሙሉ ለሙሉ ከምርጫው እራሱን አገለለ ፤ ኦነግም እንዲሁ፤ በመላው ኦሮሚያ የሚገኙ አባላቶቻቸውም ለሰላማዊ ሂደት ያላቸው ተስፋ ጨለመ።
የፖለቲካው ምህዳር እየጠበበ ሲመጣ በኦነግ መሪዎች መካከል የነበረው ክፍፍል እየሰፋ እንዲመጣ ሆነ። ይህ ውስጣዊ ሽኩቻ ሁልጊዜም ችግር ይፈጥር የነበረና የመፈራረስ ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረግ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት እንዲመሰረት ያደረገ ነው።
የምርጫ ቦርድም ግጭት ውስጥ የነበሩትን የአንድ ድርጅት ሁለት ቡድኖች ህጋዊነት ለመዳኘት ተገዶ ነበር። በስተመጨረሻም የእርስበርስ ሽኩቻዎቹ ላይ ከምርጫ ቦርዱ ጋር የነበሩ ጉዳዮችና በይበልጥም ከገዢው ፓርቲ በነበረው ሃይለኛ ጫና ኦነግን ከምርጫው እንዲወጣ አስገደዱት፤ ኦሮሚያም ገዢው ፓርቲን የእውነት የሚፎካከር ፓርቲ እንዳይኖራት ሆና ቀረች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ በሌሎች ክልሎች የሚገኙ በርካታ መራጮችና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በፌዴራልና ክልል ምክር ቤቶች ውስጥ መቀመጫ የሚያገኙበት እድል እደሚኖር ተስፋ አድርገው ቆይተው ነበር። ነገር ግን የሰኔው ምርጫና ሂደቱ በምርጫው ለመወዳደር ፍቃደኛ ለሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀር ተስፋ በሚያስቆርጥ ውጤት ተጠቃሏል።
እንደ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ያሉ ፓርቲዎች በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኙና በከተማ ልሂቃን ዘንድ ከፍ ያለ ተቀባይነት እንዳላቸው ይታመን ነበር። የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ደግሞ በአማራ ክልልና በሃገሪቱ ሌሎች ክፍሎች በሚኖሩ በአማራ ተወላጆች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ነበረው። በዚህም የተነሳ ድምጽ በማግኘት መቀመጫዎችን ለመያዝ ጠንካራ አቋም ላይ ያሉ ይመስል ነበር። በአዲስ አበባ ደግሞ ኢዜማን ጨምሮ የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ እንዲሁም የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በከፊል ተከታዮችን ማፍራት ችለው ነበር።
በተለይ አብን ከተመሰረተበት 2010 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ያለው ተቀባይነት ፤ ይልቁንም በአማራ ወጣቶች ዘንድ ፤ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን ፓርቲው ለአማራ ህዝብና የግዛት አንድነት እየጨመሩ የመጡ ስጋቶች ናቸው የሚላቸውን ጉዳዮች ለመቀልበስ በመታገልና ለአማራ ብሄርተኝነት በመሟገት አዲስ ትውልድ እንዲነሳ ያደረገ ነው።
ከምርጫ በፊት በነበሩት ጊዜያት በአማራ ክልል የተመረጡ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በክልሉ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት የፈጠሩ ነበሩ። ይህን ተከትለው በተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች ላይ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ በቀጥተኛ ጥፋተኛ ተደርጓል። መንግስትን በመቃወም ይሰሙ የነበሩ መፈክሮችም በዚሁ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ እንዳለ ይጠቁሙ ነበር።
ምንም እንኳን ለመፎካከር አቅምና ተቀባይነት የነበረው ቢመስልም አብን በአማራ የክልል ምክር ቤት 13 መቀመጫዎችን ብቻ ነው ማሸነፍ የቻለው። ገዢው የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ከ294 መቀመጫዎች 128ቱን መቀመጫዎች ይዟል። የተቀሩት የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ጳጉሜ 1 2013 በአምስት ወረዳዎች በድጋሚ በሚደረገው ምርጫ ለፉክክር የሚቀርቡ ናቸው።
አብን ለክልሉ ለተመደቡት 138 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች አምስት እጩዎቹን ብቻ መላክ ሲችል እስከ አሁን ድረስ የአማራ ብልጽግና እጩዎች 114 መቀመጫዎችን አሸንፈዋል። አብን ለምርጫ ቦርድ አመራሮች ጥረት እውቅና የሰጠ ቢሆንም ምርጫው ጉልህ ስህተቶች የነበሩበት ነው በማለት ሞግቷል።
በአዲስ አበባም አብን ውጤቱ ላይ ተጽእኖ እንደሚፈጥር ከፍተኛ ተስፋ ነበረው። ለዚህም በመዲናይቱ ከእስክንድር ነጋ ባልደራስ ፓርቲ ጋር ቅንጅት በመፍጠር ጭምርም እንዲሰራ አድርጎታል። ሆኖም ብልጽግና በከተማዋ ምክር ቤት ያሉትን 138 መቀመጫዎችን በሙሉ፣ በምክር ቤት ደግሞ ከአንዱ በስተቀር 22 መቀመጫዎችን በማግኘት በከፍተኛ ሁኔታ አሸንፎ በከተማዋ መንበር የበላይነቱን አስቀጠሏል።
አዲስ አበባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 23 መቀመጫዎች ያሏት ሲሆን አንዱን መቀመጫ የግል ተወዳዳሪ የሆነው ዳንኤል ክብረት (ኢትዮጵያዊነትን በሚያቀነቅኑ ንግግሮቹና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባለው ጥብቅ ግንኙነት የሚታወቅ የኦርቶዶክስ ዲያቆን ነው) አሸንፏል።
ሐምሌ 23 ቀን ባልደራስ የአዲስ አበባን ውጤት እንደማይቀበል የገለፀ ሲሆን ድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ ጠይቆ ጉዳዩንም ወደ ፍርድ ቤት እንወሰደው ይፋ አርጓል። ፓርቲው በምርጫ ሂደቱ ላይ አካሄድኩኝ ባለው ‹‹ሳይንሳዊ ጥናት›› ግኝት መሰረት ምርጫው በብልጽግና ፓርቲ ‹‹ተጠልፏል›› ሲል ተሟግቷል። ፓርቲው የብልጽግና ባለስልጣናት በምርጫ ጣቢያዎች ቅስቀሳ አድርገዋል በማለት የወነጀለ ሲሆን የድምጽ ማጭበርበርም ተካሂዷል ብሏል። ከህዝብ የተመረጡ ታዛቢዎች በምርጫው ላይ አልተገኙም ሲልም ቅሬታ አቅርቧል።
‹‹የምርጫው ውጤት የገዢው ፓርቲ አባላት ሆን ብለው ሂደቱን ለማበላሸት እንደሰሩ ያሳያል ነው›› ያለው ባልደራስ። የባልደራስ መሪ እስክንድር፤ እሱና ሌሎች በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ የፓርቲ አባላቶችን ከምርጫ በማገድ ኢብምቦ ያሳለፈውን ውሳኔ በተሳካ ሁኔታ በመሞገት በሰኔው ምርጫ ከእስር ቤት ሆኖ ለመወዳደር ችሏል።
የቀድሞ የኢኮኖሚ ፕሮፌሰር፣ በአንድ ወቅት የትጥቅ ትግል የመረጡት አማፂ እንዲሁም ከባድ ፉክክር በነበረበት በ1997ቱ ምርጫ በሚታወቀው ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የሚመራው ኢዜማ በከተማ ልማት፣ ምጣኔ ሀብት እና ሌሎች መሰል ዘርፎች ላይ በአጠቃላይ ተጨባጭ ፖሊሲ እንዳለው ይታሰባል ። ነገር ግን በፌደራል መንግስት በዘንድሮው ምርጫ አራት መቀመጫ ብቻ ነው ማግኘት የቻለው፤ብርሃኑ እራሱ ተሸንፏል። ፓርቲው በደቡብ ክልል ምክር ቤት 10 መቀመጫዎችንም አሸንፏል።
ኢዜማ ምርጫው ከተካሄደ ከአጭር ጊዜ በኋላ በ68 ወረዳዎች ተፈጥረዋል ያላቸውን ስህተቶች (ሀሰተኛ የምርጫ ወረቀቶች፣የመራጮች የምዝገባ ሰነድ መጥፋትና የድምጽና የመረጃ ጥቅንር ስህተቶችን ይጨምራል) ጠቅሶ ለምርጫ ቦርድ ቅሬታ ያቀረበ ሲሆን በ28 ወረዳዎች፤ሁሉም በደቡብ ክልል ነው የሚገኙት። በእነኚሁ የምርጫ ክልልሎች ምርጫው እንዲደገም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቧል።
ኢዜማ አብን እና ሌሎች ከምርጫው ቀድም ብሎ በነበሩት ጊዜያት አባላቶቻቸው በመንግስት እየታሰሩና አካላዊ ጥቃትም እየደረሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የተወሰኑት የተቃዋሚ ስጋቶች የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ጥምረት ለምርጫ ባወጣው ሪፖርትም ላይም በተመሳሳይ ተጠቅሰዋል። ጥምረቱ በምርጫው ዕለት 3,000 ያህል ታዛቢዎችን ማሰማራቱንም ገልጿል።
በአፋር የሚንቀሳቀሱ አምስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ ከእውቅናችን ውጪ ‹‹ምርጫው ሰላማዊ ፣ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ነበር›› በሚልና የአፋር ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቋም ነው በሚል በአፋር ብልፅግና ፓርቲ የወጣን መግለጫ አጥብቀው ተቃውመዋል። በሃሰት ባወጣው በዚህ መግለጫ የአፋር ብልጽግና ፓርቲ ‹‹እውነትን ፣ ፍትህንና ዲሞክራሲን ለመቅበር ሞክሯል›› በማለት በክልሉ የተካሄደው ፍትሀዊ ያልሆነው ምርጫ እንዲደገምም ጥሪ አቅርበዋል።
በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ በሪፖርተር አማርኛ ጋዜጣ በወጣ ዘገባ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከምርጫው ጋር በተያያዙ 74 ክሶች ወደ ፍርድ ቤቶች መቅረባቸውን አስታውቋል። እነዚህም ከምርጫው በፊት የተከሰቱ 57 ክስተቶችን፣4 በምርጫ ዕለት የተከሰቱ እና 13 በድህረ-ምርጫ የተከሰቱ ሁነቶችን ያካትታሉ። ከነዚህ ውስጥ 22 ክስተቶች በወንጀል ክስ የቀረቡ ሲሆኑ ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማስታወቂያ ፖስተሮችችን መቅደድ፣በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ቅስቀሳ ማድረግና መሳሪያ መታጠቅን የመሰሉትን ይጨምራሉ። ቀሪዎቹ ደግሞ በፍትሃ ብሄር ህግ ተጠቃለዋል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ታዛቢዎች የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ውጤት ቆጠራ ከተጠናቀቀ በኋላ ውጤት መለጠፍ ቢኖርባቸውም ይህን እንዳላደረጉ ያስታወቁ ሲሆን ሌላው ስጋት ደግሞ በምርጫ ወረቀቶች ላይ የተፈጠሩት ስህተቶች የምርጫውን ውጤት ሊቀይሩ ይችላሉ የሚለው ነው። የምርጫ ሰነዶችና ውጤት ጋር ተያይዘው የመጡ ልዩነቶችን ያነሱም አሉ።
‹‹በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች (ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 20 በመቶ ክልሎች) የነበሩ ተቀባይነት የሌላቸው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ቁጥር መጠን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፤ አንዳንዶቹ አሃዞችም አሸናፊ እጩ ለማሸነፍ ከሚያስፈልገው ቁጥር የሚበልጡ ነበሩ›› በማለት አንድ አለም አቀፍ ታዛቢ ከኢትዮጵያ ኢንሳይት ጋር ባደረጉት ውይይት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት ግብዣ መሰረት ውስን የምርጫ መታዘብ ስራ ያካሄዱት ሁለቱ የአሜሪካን መንግስታዊ ያልሆኑት ድርጅቶ ፤ የአለም አቀፉ ሪፐብሊካን ተቋም (IRI) እና ብሔራዊ የዲሞክራሲ ተቋም (NDI) በጋራ ባሳተሙት ባለ 36-ገፅ ሪፖርት ፤ ካለፉት ምርጫዎች ሲነፅር፤ በዚህኛው ምርጫ ወሳኝ ተቋማዊ ለውጦችንና ህጋዊ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አወድሰዋል። ሪፖርቱ ቀጥሎ ምርጫውን በቅስቀሳና ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ፣ የፀጥታና ደህንነት ሁኔታዎች፣ የምርጫ ክልሎች ልየታ እና አከላለል፣ በመራጮች ምዝገባና የምርጫ ሰነዶችን በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ‹‹ቁልፍ መስፈርቶችን ያላሟላ ነበር›› ሲል አትቷል።
የማያራምዱ እርምጃዎች
በምርጫው ሂደት በታዩና ከላይ በተዳሰሱት አያሌ ምክንያቶችና በሃገሪቱ ባለው ዋልታ ረገጥ የፖለቲካ ልዩነት አንዳንድ ባለሞያዎች ምርጫውን ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ መጥፎ ምልክት አሳይቶ እንዳለፈ እንዲያነሱ አድርጓል።
ከእነዚህ አንዱ ምርጫው የተካሄደው እኩል ባልሆነ የመጫወቻ ሜዳ ላይና ፍርሃትና ሀሰተኛ መረጃዎች ባየሉበት ጊዜ ነው በማለት ባለፈው ሐምሌ ወር የሞገቱት መብራቱ ቀለቻ (ዶ/ር) ናቸው። በዚሁ የኢትዮጵያ ኢንሳይት ገፅ ላይ ሰፋፊና ጥልቅ ትንተናዎችን ሲያቀርቡ የሚታወቁት መብራቱ ፣ በለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የፅሁፎች መድረክ ላይ ላወጡት ፅሁፍ ‹‹የኢትዮጵያ ምርጫ ከድምፅ መስጠት በፊት ለጠቅላይ ሚንስትሩ የተደረገ የንግስ ሲመት ነው ›› የሚል ርዕስ ነበር የሰጡት።
መብራቱ በሙግታቸው ፣ በገዢው ፓርቲ ጫና በኦሮሚያ ክልል ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መገፋታቸው፣ ህወሃትን ከስልጣን በማውረድ ከፉክክር ውጭ ለማድረግ በማሰብ ከትግራይ ጋር ጦርነት መከፈቱን ብሎም ለውይይት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን እንደማሳያ ይጠቅሳሉ።
‹‹የሽግግሩና የዚህ ምርጫ አካሄድ ለአምባገነን አገዛዝ ማንሰራራት መሰረት በሚጥል የተመሰቃቀለና ከባድ ፖለቲካዊ መንገድ እንደነበር ያረጋገጠ ነው›› ይላሉ መብራቱ። ‹‹ምርጫው በመጥፎ ሁኔታ ከማለፉም ባሻገር በሃገሪቱ የጋራ የወደፊት ርዕይ የመፍጠር ዕድል ላይ መጥፎ ጥላ አጥልቶ ያለፈ ነበር ››በማለት በፅሁፉቸው አክለዋል።
እንደ መብራቱ ምልከታ ፣ ምርጫው አሁን ያለውን የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት አወቃቀር በአግባቡ እንዳይከብር ወይም እንዲቀለበስ ሊያደርግ ይችላል። ምንም እንኳን በምርጫው ድምፅ ማግኘት ባይችሉ ፣ የአማራ ብሔርተኞችንና ከተለያዩ ብሔሮች የተቀላቀሉ የከተማ ልሂቃንን ጨምሮ የብሔር ፌደራሊዝም ቢወገድ ወይም በከፍተኛ ሁኔታ ቢዳከም ደስ የሚሰኙ ሰዎች በእርግጥም አሉ በማለት ያመለክታል ይኸው የመብራቱ ፅሁፍ።
በርግጥ ሃሳቡ ትክክል ይመስላል። ኢትዮጵያ ምንም ቢሆን ብዝሃነት ያለባት ሃገር ናት። ይህ ደግሞ በቋንቋ፣ባህልና ልማድ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካና ስለመንግስት አወቃቀር ባሉ ፍላጎቶችና አመለካከቶች የሚገለፅ ነው። ኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነች አንድ አይነት ሃሳብ ለማንፀባረቅ ሲባል ብቻ ልዩነቶች እንዲታፈኑ ማድረግ የዲሞክራሲ መርሆዎችን ብቻ ሳይሆን የበርካታ ኢትዮጵያውያኖችን ፍቃድም ይፃረራል።
በምርጫው (ምንም እንኳን በአጠቃላይ ፍትሃዊ ነበር ለማለት ባያስደፍርም) ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል። ኢትዮጵያውያኖች ለመምረጥ በሚችሉባቸው ስፍራዎች ለምርጫ የወጡባቸውና በአንድነት የቆሙባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት አንዲሰፍን ያላቸው መሻት ትልቁ ነው።
እዚህ ላይ ግን ሊሰመርበት የሚያሻው የብልጽግና ፓርቲን መምረጥ የፓርቲውን ፖለቲካ ያለቅድመ ሁኔታ እንደመቀበል ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ነው። የብልጽግና ዋና ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩና በብሔር ፖለቲካ የተደራጁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ባለመወዳደራቸው ብሎም የፖለቲካ ምህዳሩ እኩል በሆነ የጨዋታ ሜዳ ላይ ባለማረፉ የዚህ አመቱ ምርጫው በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ በትክክል ያሸነፈበት አድርጎ ለመወሰድ አዳጋች ያደርገዋል።
Query or correction? Email us
Follow Ethiopia Insight
ይህ ጽሁፍ ምርጫ 2013ን በሚመለከት ዘለግ ያሉ ጽሁፎችን ከመላው ኢትዮጵያ በተከታታይ የምናቀርብበት የ “Ethiopia Insight Election Project (EIEP)” ክፍል ነው።
ዋና ምስል: ወ/ሪት ብርትኳን ሚደቅሳ የምርጫ ወጤት ማሳወቅያ ዝግጅት ላይ፥ ሃምሌ 3፣ 2014።
Join our Telegram channel
Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished.
Leave a Comment