Elections 2021 Ethiopian language In-depth

ብልጽግና ፓርቲ እያንጸባረቀ ቢሆንም የአምባገነንነት ጥላሸት ግን አሁንም አለ

የህጎች መሻሻል እንዳለ ሆኖ ገዢው ፓርቲ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ተጽእኖ ተቃዋሚዎቹ ላይ ደግሞ እንቅፋት ለመፍጠር የተለመዱ ስልቶችን ተጠቅሟል።

This is an Amharic language translation of the EIEP article EIEP: While Prosperity Party shines, authoritarian stain remains

ግንቦት 15 በቤንሻንጉል-ጉሙዝ ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ ውስጥ ያለ አንድ የመካከለኛ ደረጃ የተቃዋሚ አመራር ራሱን ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ አገኘው። በአዲስ አበባ ሶስት ወራትን በስደት ካሳለፈ በኋላ አሶሳ ከተማ ወደ ሚገኙት ቤተሰቦቹ በማምራት ላይ ነበር። ወደ ከተማዋ ሲመለስ ስራ የማይኖረው ሲሆን ከአሶሳ ዩኒቨርስቲ የሚያገኘውም ደሞዝ ለወራት ያህል አልተከፈለውም ነበር።

ቢያንስ ግን እስር ላይ አልነበረም፥ ይህም በርካታ ሰዎች የታደሉት ነገር አይደለም።

ከቀናት በፊት የተወሰኑ ከእሱ ጋር አንድ አይነት ፓርቲ ውስጥ የነበሩ አባላት ከእስር እንደተለቀቁ ሰምቶ ነበር። ያለ ፍርድ ሂደት የታሰሩት ባልደረቦቹ የሆኑት የቤንሻንጉል-ጉሙዝ ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ አባላት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጣልቃ እንዲገባ ለወራት ከወተወቱ በኋላ የስፍራው የምርጫ ቦርድ ተወካዮች ከገዢው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸውን መኮንንኖች በአስሮች የሚቆጠሩ እስር ላይ የነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ ክስ እንዲመሰርቱ ወይም ከእስር እንዲለቋቸው አሳመኗቸው።

ሆኖም ግን በርካቶች በፍርድ ቤት ቀርበው መከራከር ባለመቻላቸው በስቃይ ላይ ቆይተዋል። “በቀላሉ በቁጥጥር ስር እንውላለን ከዛም በአግባቡ ክስ ሳይመሰረትብን ለወራት በእስር እንቆያለን” በማለት የቤንሻንጉል-ጉሙዝ ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ  ፖለቲከኛ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግሯል። በአሶሳ ከተማ አንድ አቃቤ ህግ ከኢትዮጵያ ኢንሳይት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ባለፉት ስድስት ወራት ቁጥራቸው ያልታወቀ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ ከቤንሻንጉል-ጉሙዝ ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ  በተጨማሪ ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ውስጥ የሚገኙ አባላት ይገኙበታል። አቃቤ ህጉ የክልል የህግ አስፈጻሚ (አስከባሪ) መኮንኖች የፓርቲ ወኪሎችንና ደጋፊዎቻቸውን በክልሉ ግጭቶችን እያባባሳችሁ ነው በሚል ውንጀላ በቁጥጥር ስር ማዋላቸው የተለመደ ነው ብለዋል።

ከክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ክንፍ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባላቸው የስፍራው ባለስልጣናት የሚፈጸሙት እነዚህ ጨቋኝ ስልቶች ከምርጫው አስቀድሞ በነበሩት ጊዜያት በቤንሻንጉል-ጉሙዝ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲዳከሙ አርገዋል። በርካታ ተቃዋሚ አባላት ልክ የቤንሻንጉል-ጉሙዝ ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ  አባል እንደሆነው ግለሰብ ከመከሰስ ይሻላል በማለት ተሰደዋል። በብልጽግና ፓርቲ ተቋማዊ ክብደት የተነሳ የሚፈጠረው አቅም የማጣት ስሜት አስፈሪ ነው። እንደ ቤንሻንጉል-ጉሙዝ ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ ፖለቲከኛ ከሆነ “የፍትህ ተቋማት ራሳቸው የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ማሽን አካል ሆነዋል”።

ነገሮችን የሚያባብሰው ደግሞ በቤንሻንጉል-ጉሙዝ እየተካሄደ ስለነበረው ነገር የግንዛቤ እጥረት መኖሩ ነው። ጋዜጠኞች በማይሄዱበትና ችግሮቹን አብዛኞች በጥልቀት በማይረዱበት በዚህ ክልል፤በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ሌሎች ስፍራዎች የፖለቲካ ሴራ በድንገት ነው የሚፈጠረው።

ከብልጽግና ፓርቲ ቀድሞ የነበረው ፓርቲ (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)) የሚከተለውን ስልት ለየሚያውቁ ሰዎች የብልጽግና ፓርቲ የቁጥጥር ዘዴዎች ከቀድሞው ስርዓት ጋር ተመሳሳይ በመሆናቸው ሊገመቱ የሚችሉ ናቸው።

ከ1987 ዓ.ም እስከ  2011 ዓ.ም በምርጫ ተመርጦ መንግስት ሆኖ በመራበት ረዥም የአገዛዝ ዘመናት ኢህአዴግና (እስኪከስም ድረስ) ባለስልጣኖቹ የመጫወቻ ሜዳው ወደ ገዢው ፓርቲ እንዲያጋድል ለማድረግ ሁሉንም አይነት ጨቋኝ ስልቶች ተጠቅመዋል፤ ከነዚህም ውስጥ የመንግስትን ሀብቶች ለፓርቲ ጥቅም ማዋልና ፖለቲካዊ የሆነ የፍትሕ ስርዓትን ተጠቅሞ ተቃዋሚዎችን ወንጀለኛ ማድረግ ይገኙበታል።

አሁን በ2013 ዓ.ም፤ ልክ ቀደም ሲል ኢህአዴግ የበላይ እንደነበረባቸው አስርት አመታት ከምርጫ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ ያፈጠጡ ችግሮች በመላው አገሪቱ ታይተዋል። የመንግስትና የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ደካማ በሆኑባቸው፣ ዝቅተኛ የመገናኛ ብዙኃን ተደራሽነት ባሉባቸው፣የደኅንነት ስጋቶች ከፍተኛ በሆኑባቸውና ሁነቶችን የመቆጣጠሪያ ችሎታ አስቸጋሪ በሆኑባቸው ስፍራዎች በተለይ ሙስናና ጭቆና ጠንካራ ናቸው።

ሰፊና በርካታ ስፍራዎችን የሚያካልል ጭቆና

                    ጋምቤላ

እንደ ቤኒሻንጉል ሁሉ ሌላ ችላ በተባለው ክልል ጋምቤላ ለምሳሌ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አምባገነን የነበረው ፓርቲ መንግስት ይጠቅምባቸው ከነበሩ ስልቶች በርካቶቹን ተጠቅሟል።

በየካቲት ወር በተጀመረው የቅስቀሳ ወቅት የወረዳ ባለስልጣናት የቀበሌ አመራሮችን በቀበሌያቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅስቀሳ እንዲያካሂዱ ከፈቀዱ ከስራ ገበታቸው እንደሚያባርሯቸው አስፈራርተዋቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፍቃድ ደብዳቤ ከወረዳ ባለስልጣናት እያላቸው እንኳን በነፃነት ቅስቀሳ ለማድረግ አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር። በጎግ ወረዳ የታታ ቀበሌ ሊቀመንበር ለብልጽግና ፓርቲ ያለው ታማኝነት በቂ አይደለም በሚል ምክንያት ከኃላፊነቱ ተነስቷል።

የተቃዋሚ ክንፎች በአመራር ጉድለቶች የተነሳ የበለጠ ተቆርጠዋል፤ለምሳሌ ለተቃዋሚዎች ቅስቀሳ የሚውል የመንግስት ገንዘብ ዘግይቶ ሲሆን የመጣው እንደዛም ሆኖ በቂ አልነበረም። በምርጫ ቀን በኢታንግ ወረዳ እንደተደረገው፤የአንዳንድ ፓርቲ ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያዎች እንዲወጡ ተነግሯቸው ነበር። ይህን የተቃወሙ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትም አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል እንዲሁም ሁለት የምርጫ ታዛቢዎች በአካባቢ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ዋና የመጓጓዣ መንገድ የሆኑት ሞተር ሳይክሎችም በተለይም በአቦቦ እንዳይሰሩ ታግደው ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የመንግስት መኪናዎች ምርጫ በመካሄድ ላይ እያለ ከአንድ የምርጫ ጣቢያ ወደ ሌላ ሲመላለሱ ነበር።

ፕሮፓጋንዳም ተጽእኖ ፈጥሮ ነበር። የብልጽግና ፓርቲ ባለስልጣናት ደገኞች ወደ ሚበዙባቸው የጋምቤላ ክፍሎች ባመሩ ወቅት የክልል ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ፀረ-ደገኞችና “ጠባብ ብሔርተኞች” ናቸው በማለት የወነጀሉ ሲሆን እነዚህም ኢህአዴግ የብሔራዊ ልማትና የክልል ነፃነትን በኣንድ ጋር ለመደገፍ ይጥር በነበረ ወቅት በፓርቲው መዝገበ ቃላት ውስጥ የነበሩ ቃላቶች ናቸው።

በተመሳሳይ ሁኔታም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ራሳቸው በክልሉ ውስጥ ቅስቀሳ በሚያደርጉ ወቅት ብልጽግናን ውድቅ ለማድረግ ተመሳሳይ የሚታወቁ ውንጀላዎችን ተጠቅመዋል። ገዢው ፓርቲን በሙስናና ከገንዘብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ማን አለብኝነት የተጠናወተው ነው በማለት የወነጀሉ ሲሆን ፓርቲው ቀደም ሲል በኢህአዴግ ጊዜ ያደርግ እንደነበረው ሁሉንም የፌደራል ፖሊሲዎች ያለጥያቄ እየተቀበለ ነው ሲሉም አክለዋል። መሰል ከተቃዋሚዎች የሚሰነዘሩ ውንጀላዎች አዲስ ፖሊሲና የላቀ ግልጽነት በማምጣት ረገድ አማራጭ ያላቀረቡ በመሆናቸው ጠንካራ ተጽእኖ አልነበራቸውም።

ብልጽግና ተቃዋሚዎች ክልሉን ለመምራት ብቁ አይደሉም በማለት የሚያቀርባቸው ውንጀላዎች አግባብነት ያላቸው አስተያየቶች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፤ ነገር ግን የበለጠ ስም የሚያጠፉ ውንጀላዎቻቸው አግባብነት ያላቸው አይደሉም።

በጋምቤላ ቅስቀሳ በሚያደርጉ ወቅት የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት የጋምቤላ ህዝቦች ነፃ አወጪ ንቅናቄ እና ኢዜማ አባላትን ደገኞችን የማይወዱ አማጺያን ናቸው በማለት ወንጅለዋቸው ነበር። በተጨማሪም ኢዜማ አገሪቱን ወደ አንድ ወጥ ስርዓት ለመመለስ ይፈልጋል በሚል ተወንጅሏል (እውነታው ግን ፓርቲው ከብሔር ነፃ የሆነ ፌደራሊዝምን እንደ አማራጭ የሚያቀርብ መሆኑ ነው)። የብልጽግና ካድሬዎች ኢዜማ ካሸነፈ ፓርቲው ጋምቤላን በሌላ ክልል ውስጥ በማድረግ (ቀደም ሲል የኢሊባቡር አካል እንደነበረችው ማለት ነው)ወደ ዞን ደረጃ እንድትወርድ ያደርጋል ብለው ነበር።

በኢህአዴግ ጊዜ የተሰደዱትንና የታሰሩትን ከዛም በአብይ ጊዜ ከእስር የተፈቱትን የቀድሞውን የጋምቤላ ክልል ፕሬዝደንት የነበሩትን አቶ ኦኬሎን በመጥፎ መልኩ በማውሳት የብልጽግና መሪዎች የጋምቤላ ተቃዋሚዎች ችግሮች ሲፈጠሩ ሸሽተው ይሄዱ ነበር ብለዋል።

እንደዚህ አይነት መልዕክቶች እንዲሁም የበለጠ የሚረብሹ መልዕክቶች በብልጽግና የማኅበራዊ ድረ-ገጽ መለያዎች (አካውንቶች) ተሰራጭተዋል። ልክ ኢህአዴግ ግንቦት 7ትን (ከኢዜማ አሁን ያለውን ስያሜ ከመያዙ በፊት ቀድሞ የነበረ ነው)፣ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ብሔራዊ ግንባርን (ኦብነግ) እና የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባርን (ኦነግ) በ2003 ዓ.ም ሽብርተኛ ድርጅት ብሎ እንደሰየማቸው፤ ብልጽግናም በዚህ ዓመት “ሽብርተኛ” የሚለውን ቃል ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት ተጠቅሞበታል። ሚያዝያ 28 የብልጽግና የበላይነት የሚታይበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትግራይ ህዝቦች ነፃ አውጪ ግንባርን (ትህነግ) እና “ኦነግ ሸኔ”ን ሽብርተኛ ብሎ ሰይሟል።

የብልጽግናን ከባድ ተጠራጣሪነት ከሁሉ በላቀ ሁኔታ የሚያሳየው የጋምቤላ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ለማድረግ የሚሰሩ የትህነግ ተባባሪዎች ናቸው በሚል መወንጀሉ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታም በጋምቤላ የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ እጩዎች ሆን ብለው፤ ተቃዋሚዎች ካሸነፉ የተቃዋሚ ደጋፊዎችን መሬት፣ስራ እንዳያገኙ እናደርጋለን ወይም በሌላ መንገድ ህይወታቸውን አስቸጋሪ እናደርገዋለን በማለት ለመራጮች ተናግረዋል።

እውነትም ብልጽግና በከፍተኛ ሁኔታ ካሸነፈ በኋላም ቢሆን፤ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የተያያዙ ሰዎች ከስራቸው እየተባረሩ ነው። በጆር ወረዳ ለየጋምቤላ ህዝቦች ነፃ አወጪ ንቅናቄ የተወዳደረ አንድ እጩ አሁን ስራ የለውም፤ይህም የሆነው በፖለቲካ እንቅስቃሴዬ ምክንያት ነው ይላል። በጆር ወረዳ የሚገኙ የደህንነት፣የግንኙነት እንዲሁም የታጣቂዎች ኃላፊዎችም ጭምር ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።

ምንም እንኳን ብልጽግና በአጠቃላይ የምክር ቤት መቀመጫዎችን ያሸነፈ ቢሆንም በጋምቤላ አቦቦ ወረዳ (የጋምቤላ ህዝቦች ነፃ አወጪ ንቅናቄ ጥሩ ድምጽ ባገኘባቸው ስፍራዎች) መራጮች ብልጽግናን ባለመምረጣቸው እንደተቆጩ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግረዋል። የጋምቤላ ህዝቦች ነፃ አወጪ ንቅናቄ ባሸነፈባቸው ቀበሌዎች ውጤት ከተገለጸ በኋላ ገዢው ፓርቲን የሚወክል የወረዳ መሪ ለነዋሪዎቹ “ከአሁን በኋላ አምቡላንስ ስትፈለጉ ለኛ ሳይሆን ለጋምቤላ ህዝቦች ነፃ አወጪ ንቅናቄ ደውሉ” ማለቱ ተነግሯል። የኢህአዴግ የመቆጣጠሪያ መንገድም የአገልግሎት አቅርቦትን ፖለቲካዊ ማድረግ ላይ የተመረኮዘ ነበር።

                    ደ/ብ/ብ/ህ/ክ (ደቡብ)

እንደ ዳውሮ ዞን ባሉ የመንገድ እጥረቶች ዋና ችግሮች በሆኑባቸው የደ/ብ/ብ/ህ/ክ ክፍሎች ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ  አነስተኛ እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው። በክልሉ ደቡብ ምዕራብ የሚገኙ ነዋሪዎች፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጽህፈት ቤቶች ቀጥተኛ ከሆነ ጭቆና ጀምሮ ስውር በሆኑ ማስፈራሪያዎችና በነፃነት ቅስቀሳ ለማድረግ ባለመቻል የተነሳ መዘጋታቸውን ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግረዋል።

ለገዢው ፓርቲ የተደላደለ የመጫወቻ ስፍራ በመኖሩ ምክንያት ለታይታ የሚቀርቡ የመንግስት ልገሳዎች ከፖሊሲ ክርክሮች ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሆነዋል። ከምርጫው በፊት በነበሩት ወራት በደቡብ የሚገኙ ባለስልጣናት ልክ በአገሪቱ ሌሎች ስፍራዎች እንደሚደረገው አዲስ የመሰረተ ልማት እቅዶች እንዲጀመሩ ያደረጉ ሲሆን ይህንን ያደረጉትም ብልጽግና ፓርቲን የሰዎች ህይወት ላይ ለውጥ ከሚያመጣ ልማት ጋር ለማያያዝ ነው።

ብልጽግና ክልል ስለመሆን ጥያቄ ያለውን አቋም በግልጽ በማሳወቅ ህዝብን ከማሳመን ይልቅ ህዝብን ስለልማት ማሳመን የሚቀለው ይመስላል ይህም በመላው ደ/ብ/ብ/ህ/ክ የሚገኙ በርካታ ዜጎች በአብይ አገዛዝ ስር አንኳር አሳሳቢ ጉዳይ ብለው የሚገልጹት ጉዳይ ነው። ብልጽግና አሁን ካሉት ላይ ተጨማሪ ክልሎችን የመፍጠር ሁኔታን ይደግፋል እንዲሁም ይቃወማል።

በጉዳዩ ላይ ቢያንስ አንድ የቅድመ ምርጫ ፖሊሲ ያወጣ ሲሆን የደቡብ ምዕራብ ሪፈረንደም ተካሂዷል። ነገር ግን ይህ እራሱ ከላይ ወደ ታች የሚመጣ መፍትሔን በማስተዋወቁ ምክንያት በተወሰነ መልኩ ከኢህአዴግ ተግባር ጋር የሚመሳሰል ነው። የአካባቢ (የስፍራው) ባለስልጣናት በስተመጨረሻ እያንዳንዶቹ ዞኖች የየራሳቸውን ክልል የመመስረት ፍላጎትን ከሚያሳድዱ ይልቅ በርካታ ዞኖችን ያቀፈ አንድ ክልል የመኖሩን ጉዳይ የደገፉ ሲሆን ይህም ቢያንስ ብልጽግና የኢህአዴግን ያህል ግትር እንዳልሆነ የሚያሳይ ስምምነት ነው።

ሂደቱ ግን ምርጫ ቦርድ መቋቋም ከሚችለው በላይ ነበር ይህም ውሳኔውን ወደ መስከረም ወር እንዲዛወር አርቆ በመግፋት የአካካቢው ተወካዮችን አሳዝኖ ነበር። ይህ በምርጫ ቦርድ የብቃት ማነስ የተፈጠረ ሊሆን ይችላል ነገር ግን በከፊል ይህ የሆነ  በቴፒ አካባቢ በሸካና መዥንገር ቡድኖች መካከል የፖለቲካ ስልጣን ለማግኘት የነበረ ሥር የሰደደ (ለረዥም ጊዜያት የቆየ) ግጭት በመኖሩ የተነሳ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በወላይታ ዞን የነበሩ ክልል የመሆን ጥያቄዎች ተገድበዋል። በወላይታ የክልል ጥያቄ ዘመቻ አራማጆች በስተመጨረሻ የሲዳማ ሪፈረንደም እንዲካሄድ በፈቀዱ ባለስልጣናት ዘንድ መድልዎ የሚያደርግ መስፈርት ብቻ ሳይሆን ህይወት እስከማሳጣት የሚደርስ ጭቆናም ጭምር ስለመኖሩ ቅሬታ አቅርበዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት (የቱሳ ፓርቲ፣የወላይታ ብሔራዊ እንቅስቃሴና የወላይታ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባርን ጨምሮ) በአካባቢ ባለስልጣኖችና ከገዢው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ባላቸው ግለሰቦች በመላው የምርጫው ጊዜ ትንኮሳ እንደደረሰባቸው የጠቆሙ ሲሆን የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄና የወላይታ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሰኔ 5 ባወጡት የጋራ ዘገባ ሰባት አባላቶቻቸው እንዲሁም እነሱን ደግፈው ሙዚቃ ያቀናበሩ ሁለት ሙዚቀኞች እንደታሰሩ፣ሁለት የፓርቲ እጩዎች ባልታወቀ ምክንያት ከስራቸው እንደተባረሩ፣ወጣት ደጋፊዎች እንደተደበደቡና በፖሊስ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ እንዲሁም የተወሰኑ የፓርቲ አባላት የሲቪል አገልግሎት ደሞዛቸውን እንደተከለከሉ አትተዋል።

ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ጋዜጠኞች ተደራሽ በሆኑ ዞኖች ውስጥ የነበሩ ፖለቲካዎች ይህን የሚመስሉ ነበሩ። ነገር ግን ክልሉ በብዝሃነቱና ያላደገ በመሆኑ የሚታወቅ ነው። ሌሎች ስፍራዎች ምን ተፈጥሮ ሊሆን እንደሚችል የምርጫ ታዛቢዎች መገመት ይችላሉ።

                  ሲዳማ

በሲዳማ (የኢትዮጵያ አዲሷ ክልል) ተፎካካሪዎችን ለማጥፋት ብልጽግና የተጠቀመው ዘዴ ጥልቅ ፍተሻ ያስፈልገዋል። በኢህአዴግ ምርጫ ወቅት ከምርጫው ቀድሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይደመሰሱ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ብልጽግናም የተወሰኑ ፓርቲዎች አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ አስገድዷል።

ባይዳከም ኖሮ በክልሉ የብልጽግና ዋና ተፎካካሪ፤ረዥም ጊዜያትን ያስቆጠረውና ለክልል ነፃነት ለዓመታት የታገለው የሲዳማ ነፃ አውጪ ንቅናቄ ይሆን ነበር። የቀድሞ የሲዳማ ነፃ አውጪ ንቅናቄ አባል ፓርቲው ከምስረታው ጀምሮ ስራው በመንግስት ሲሰናከል የቆየ መሆኑን ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግረዋል።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የክልል ባለስልጣናት የሲዳማ ነፃ አውጪ ንቅናቄ አባላት፤ ጽህፈት ቤት እንዲሁም የመሰብሰቢያ ስፍራዎች እንዳይከራዩ አግደው የነበረ ሲሆን የፓርቲውን እንቅስቃሴ ይሰልሉ (ይከታተሉ) እንዲሁም ፓርቲውን ለማዳከም የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። ከዚያ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ፓርቲው ከብልጽግና ጋር ለመዋሀድ ፈረመ።

ይህ ውህደት የኢህአዴግን መክሰም ተከትሎ (እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ከኢትዮጵያ ፤ የትግራይ፣ኦሮሚያ፣አማራና ደ/ብ/ብ/ህ ክልሎች አራት አባላት ኅብረቶችና፤ ከቤንሻንጉል-ጉሙዝ፣ጋምቤላ፣አፋርና ሀረሪ ክልሎች አምስት ሳተላይት ፓርቲዎች የነበሩበት ነው) የተካሄደ የቅርብ ጊዜ ውህደት ነው። አሁን ከትግራይ በስተቀር በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ፓርቲዎች በአብይ ብልጽግና ፓርቲ ስር አንድ እንዲሆኑ ተደርገዋል።

የብልጽግና አባል ለመሆን በመስማማት የሲዳማ ነፃ አውጪ ንቅናቄ ያጋጥመው የነበረውን እንግልት ያስቆመ ሲሆን የቀድሞ የሲዳማ ነፃ አውጪ ንቅናቄ አባላቶች ግን የሲዳማ ነፃ አውጪ ንቅናቄn ማብቃት ይቃወማሉ፤ ውህደቱም በጉቦ፣ውሸትና ማስፈራሪያ የመጣ ነው ይላሉ።

ተጨማሪ መጥፎ ምሳሌዎችን በሲዳማ ማየት ይቻላል። ምንም እንኳን ብልጽግና ከምርጫ ቀደም ብሎ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ እንቅስቃሴ እንዲደረግ ከፈቀደበት አንዱ ዘርፍ ጋዜጠኝነት እንደሆነ በተደጋጋሚ ቢጠቀስም፤ ፓርቲው መገናኛ ብዙኃንን እንደ ድሮው ወደ መጨቆኑ መመለሱ የኢህአዴግ የቀድሞ ልማዶች ቶሎ እንደማይከስሙ ተጨማሪ ማሳያ ነው።

የሲዳማ መገናኛ ብዙኃን ግንኙነት(የሲዳማ ሚዲያ ኔትወርክ) መስራች አባል የሆነው ጌታሁን ዳጉዬ ወደ አንድ ዓመት ገደማ ያህል (ከ2011 ዓ.ም-2012 ዓ.ም) በእስር ነው ያሳለፈው። ለሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ ከታገሉና (ምንም እንኳን የአብይ ፖሊሲዎች ሃሳብን በነፃነትን መግለጽ ቢያበረታቱም) ለክልል ጥያቄው በመታገሉ ምክንያት ከታሰሩ 150 ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው።

“በክልል የመሆን ጥያቄው ሂደት በአጠቃላይ ላለፉት የተወሰኑ ዓመታት ከኛ ጋር ሲገናኙ የነበሩ ባለስልጣናት እራሳቸው አመጽ በመቀስቀስ በሚል ክስ እስር ቤት ወርውረውናል’’ ብሏል ጌታሁን ዳጉዬ በሚያዝያ ወር ለኢትዮጵያ ኢንሳይት በሰጠው ቃለምልልስ።

ከእስር ከተፈታ በኋላ ጌታሁንና ምክትሉ በሚድያ ኔትወርኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ወደ ስራ ኃላፊነታቸው እንዳይመለሱ ተከልክለዋል። በመጀመሪያ ውሳኔውን ሞግተው የነበረ ሲሆን ከዛ ግን ከኤስ ኤም ኤን ቦርድ “የሚድያ ኃላፊዎች ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው አይችልም’’ በሚል ምክንያት የተነሳ ወደ ኃላፊነታቸው መመለስ እንደማይችሉ የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሳቸው።

ኤስ ኤም ኤን ማኅበረሰቡን በማንቀሳቀስና በክልሉ ተገቢ የሆኑ ጉዳዮችን በማስተዋወቅ ኃይለኛ መሳሪያ ነበር። ኤስ ኤም ኤን ከመመስረቱ በፊት የክልሉ የመገናኛ ብዙኃን የሲዳማ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት  በሳምንት ሁለት ሰዓታትን ብቻ ነበር የሚመድበው። እንደ ጌታሁን ከሆነ የክልሉ የመገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ እንደሚገኙ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን “መንግስት ለመዳሰስ የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች ብቻ እንዲያስተላልፉ የተቃኙ ነበሩ።’’

በሌላ መልኩ ኤስ ኤም ኤን በማኅበረሰቦች የሚደጎምና በዚህም የተነሳ ከመንግስት ተጽዕኖ ነፃ የሆነ ነው። ቢሆንም ጌታሁን ይህ ኔትወርክ “ወደ ጎን ገሸሽ እየተደረገ ነው’’ ያለ ሲሆን መስራቾቹ አቅመ ቢስ በመደረጋቸው ምክንያት ኤስ ኤም ኤን በርካታ የገንዘብ ድጋፉን በማጣቱ የተነሳ መንግስት እንደሚወርሰው እንደሚያምን ገልጿል።

                  በሁሉም ስፍራ

ይህ አይነት ሁኔታ በነበረበት ገዢው ፓርቲ በሰኔ 14 የመጀመሪያው ዙር ምርጫ በፌደራል ምክር ቤት ከሚገኙ 425 መቀመጫዎች 410 ሩን ያሸነፈ ሲሆን በክልልና ከተማ ምክር ቤት ከሚገኙ መቀመጫዎች ደግሞ ወደ 98 በመቶ የሚሆኑ መቀመጫዎችን ማለትም ከ1,664 መቀመጫዎች ውስጥ 1,625 መቀመጫዎችን አሸንፏል።

ከአብን አምስት ፣ከኢዜማ አራት፣ ከጌድዮ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሁለት እና ከግል ዕጩዎች ደግሞ አራት ዕጩዎች ብልጽግና ፓርቲን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀላቀሉ ሲሆን ነገር ግን አዲሱ የምክር ቤት አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሆነው ዳንኤል ክብረት ምን ያህል ‘ገለልተኛ’ እንደሆነ መጠየቅ ምክንያታዊ ነገር ይመስላል።

አንድም ተቃዋሚ ዕጩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካልተወከለበት 2002 ዓ.ም ጋር ወይም አንድ ተቃዋሚ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ብቻ ካገለገለበት 2007 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር በአሁኑ ምርጫ 15 የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መግባታቸው በጣም ጥሩ ይመስላል። ይህ ቁጥር ከማንኛውም ያደገ ዲሞክራሲ ጋር ሲነጻጸር እንዲሁም ለማሸነፍ ጥቅም ላይ የዋሉ ዘዴዎች ግምት ውስጥ ገብተው ሲታይ ግን በጣም መጥፎ ነው። ፉክክር ያለበት እውነተኛ ምርጫ እንደሚኖር ጠ/ሚ አብይ ቃል ከገቡት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ እውነትም በጣም መጥፎ ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ነገሮች የበለጠ በተቀየሩ ቁጥር የበለጠ ተመሳሳይ እየሆኑ ነው የሚመጡት።

የተወሰኑ የምርጫ ታዛቢዎች ዲሞክራሲን በተግባር የሚያሳይ አድርገው በመመልከት በምርጫ ጣቢያዎች በነበሩ ረዥም ሰልፎች ቢደነቁም እውነታው ግን ብልጽግና (የኢህአዴግ ዳግም ውልደት) በመላው አገሪቱ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ዕጩዎችን በዘዴ ማሳነሱና (ማኮሰሱና) ማግለሉ ነው።

የኢትዮጵያ ፌስ ቡክ

ድሮ ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ ስልቶችን ጨምሮ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የገዢው ፓርቲ የበላይነቱን የሚያሳይበት አንዱ መሳሪያ ነበር። በአገር ውስጥ 6 ሚሊየን ተጠቃሚዎች ያሉት በመሆኑ ፌስ ቡክ በተለይ ከምርጫው ቀደም ብሎ በነበሩት ጊዜያት መረጃንና ዜናን ለማጋራት እጅግ ጠቃሚ ነበር።

የማኅበራዊ ትስስር ገጽ አብዛኛውን ጊዜ የገንዘብ ሀብት፣ተቋማዊ አቅምና በስፋት በመጓዝ በተለያዩ ወረዳዎች ያሉ መራጮችን ለመቀስቀስ የሰው ኃይል ለሌላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠቃሚ መሳሪያ ነበር። ነገር ግን የትኞቹም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፌስ ቡክን ኃይል የብልጽግናን ያህል ለመጠቀም አልቻሉም።

የብልጽግና ይፋ የማኅበራዊ ትስስር መለያ (አካውንት) በኢትዮጵያ እስከአሁን ካሉት የፓርቲ መለያ ገጾች እጅግ ከፍተኛ ተከታዮች ያሉት ገጽ ነው፤ 3.5 ሚሊየን ተከታዮችን በመያዝ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገጽ በአገሪቱ ካሉ የፖለቲካ ገጾች እጅግ ተመራጩ ነው። ኢዜማ ከብልጽግና ፓርቲ ቀጥሎ በፌስቡክ ከፍተኛ ተከታዮች  ማፍራት የቻለ ብቸኛው ፓርቲ ነበር።

ፌስቡክን ከመራጮች ጋር መገናኛ ዋና መድረክ አርጎ ሲጠቀም የነበረው ምርጫ ቦርድ እራሱ ከፌስቡክ ጋር በጋራ በመስራት መለያዎችን (አካውንቶች) የማረጋገጥ፣ የጥላቻ ንግግሮችን መቀነስና ከምርጫ ቀደም ብሎ በነበሩ ጊዜያት ሀሰተኛ መረጃን የመፈተሽ ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። ድርጅቱ የአብን፣ኢዜማ፣ኦነግ፣ኦፌኮ፣ነፃነትና እኩልነት፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲሁም የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ተወካዮች ያጋሯቸውን የማኅበራዊ ትስስር ልጥፎች በመጠቆም አመጽ ለመቀስቀስ የጥላቻ ንግግርን ተጠቅመዋል ይህንን በማድረጋቸውም የምርጫ መመሪያዎችን ጥሰዋል በማለት ፓርቲዎቹን ወቅሷል።

በመጋቢት 2012 እና 2013 ዓ.ም ፌስቡክ ከኢትዮጵያ መለያዎች (አካውንቶች) በአጠቃላይ 87,000 የጥላቻ ንግግሮችን አስወግዷል

ከምርጫ በፊት በነበሩት ወራት የምርጫ ታዛቢዎች የማኅበራዊ ትስስር መድረኮችንም የተከታተሉ ሲሆን ይህም በፖለቲካ ፓርቲዎችና እጩዎች፣በህዝብና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት፣በሲቪል ማኅበራትና ተጽእኖ ፈጣሪዎች የሚተዳደሩ (የቴሌግራም ቻናሎች፣ የትዊተር መለያዎች (አካውንቶች)ና የፌስቡክ ገጾችን ያካትታል። የ IRI እና የ NDI ተመራማሪዎች በርካታ ተመራጭ መለያዎች (አካውንቶች) ያልተረጋገጡ መሆናቸውንና በተደጋጋሚም ሀሰተኛ መረጃ ያሰራጩ እንደነበር ለማወቅ ችለዋል። እንደ ድርጅቶቹ የምርጫ ዘገባ ከሆነ በማኅበራዊ ትስስር ያለው እንቅስቃሴ “መራጮች የፓርቲ የምርጫ ምልክቶችን የሚለዩበትን ሁኔታ ያወሳሰበ ሲሆን ይህም ሀሰተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመኖራቸው ምክንያት የተፈጠረ ነው።’’

ከምርጫው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ሬውተርስ ፌስቡክ ሰፊ “ትስስር (ኔትወርክ)’’ ያላቸውን ሀሰተኛ መለያዎች (አካውንቶች) እንደዘጋ ዘግቦ የነበረ ሲሆን ይህ “የተቀናጀው ተገቢ ያልሆነ ባህሪ’’ የፌስቡክን የአጠቃቀም ደንብ የሚጻረር ነበር።

እንደፌስቡክ ከሆነ ይህ ትስስር (ኔትወርክ) በ2012ና በ2013 ዓ.ም እንቅስቃሴውን ያፋጠነ ሲሆን መለያዎች (አካውንቶች) በቀዳሚነት ስለአገር ውስጥ ፖለቲካዎች በአማርኛ ይለጥፉ እንዲሁም በዋናነት ከብልጽግናና ከአብይ ጋር የተያያዙ ዜናዎችን ያጋሩ ነበር፤ ዜናዎቹም የመንግስት የልማት እቅዶችን የሚያጎሉና ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም ምስል የሚያንጸባርቁ ነበሩ።

መለያዎች (አካውንቶች) የተቃዋሚዎችን እንቅስቃሴና መሪዎቻቸውን የሚቃወሙ(አብዛኛውን ጊዜ ይህ “ሽብርተኛ’’ ድርጅቶች ተደርገው የተፈረጁትን ኦነግንና ትህነግን የሚያካትት ነው) ሂሳዊ ሐተታዎችንም ይለጥፉ ነበር። ግንቦትና ሰኔ የነበሩ ልጥፎች አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የጣለችው ማዕቀብ ላይ በአሉታዊ መልኩ አስተያየት የሰጡ ሲሆኑ በተጨማሪም #ኢትዮጵያትቅደም #ኢትዮጵያአሸንፋለች የሚሉ ሃሽ ታግ (መለያ ሀረጎች) ጎልተው እንዲታዩ ያደረጉ ነበር።

ወደ 1.1 ሚሊየን የሚሆኑ ተጠቃሚዎች የትስስሮቹን (ኔትወርኮች) አንድ ወይም ሁለት ገጾች ይከተሉ የነበረ ሲሆን 766,000 ተጠቃሚዎች ደግሞ የትስስሮቹን (ኔትወርኮች) አንድ ወይም ከአንድ በላይ ቡድኖች ተቀላቅለዋል። በሁሉም መለያዎች (አካውንቶች) ለማስታወቂያ የወጣው ገንዘብ ከ 6,000 ዶላር አይበልጥም።

በቅስቀሳው በሙሉ በርካታ የሶስተኛ ወገን የፓርቲ ገጾች ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ብልጽግና ፓርቲን የሚያስተዋውቁ የፌስቡክ ማስታወቂያዎችን ያስኬዱ ነበር። ለግብይት ይከፈል የነበረው በአሜሪካ ዶላር የነበረ ሲሆን አንዳንድ አካውንቶችም በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ይታመናል። የምርጫ ገምጋሚዎች ከሰኔ ምርጫ በኋላ የተወሰኑ ማስታወቂያ ያስኬዱ የነበሩ ገጾች መጥፋታቸውን የጠቀሱ ሲሆን ይህም ገጾቹ ትክክለኛ ስላለመሆናቸው የበለጠ ጥርጣሬ የሚፈጥር ነው።

ፌስ ቡክ በምርመራው በርካታ አካውንቶች ቀጥታ ከመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ጋር እንደሚያያዙ አውቋል።

ኢንሳ የኢትዮጵያን ብሔራዊ የደኅንነት ፍላጎቶች የሚያስጠብቅ የሳይበር አቅምን ለመገንባት በማለም በኢህአዴግ ጊዜ የተመሰረተ ሲሆን ኤጀንሲው ቴሌ ኮምዩኒኬሽንን እና ኢንተርኔትን ይቆጣጠራል እንዲሁም “የመንግስትን እርምጃዎችን” ለመደገፍ ከፍተኛ መጠን ያለው የተጠቃሚዎችን መረጃ ያሰባስባል። በ1999ና በ2002 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር ከዛም ተጠባባቂ ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።

በነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም በአብይ የኢንሳ ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ሹመቴ ግዛው “ብሔራዊ አንድነትንና ሰላምን” የሚሰብኩ እንዲሁም ፥የኢትዮጵያን እውነታ የሚያሰራጩ መለያዎች (አካውንቶች) ናቸው ያሏቸውን መለያዎች (አካውንቶች) ፌስቡክ በመዝጋቱ ተችተውታል።

ዳይሬክተሩ ፌስቡክ፣ትዊተርና ዋትስ አፕን የሚተካ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ስለመፍጠር መታቀዱን አሳውቀዋል። ምንም እንኳን ኤጀንሲው ሌሎች የማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን ለመዝጋት እንዳላቀደ ቢናገርም ሹመቴ “ቴክኖሎጂው አገር ውስጥ ያለውን አቅም በመጠቀም የሚሰራበት ምክንያት ግልጽ ነው፤ ለምን ይመስላችኋል ቻይና WeChat ን የምትጠቀመው?’’ ሲሉ ተናግረዋል።

WeChat በቻይና ከሚገኙ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችና የመልዕክት መላላኪያ አፕ ትልቁ ሲሆን የቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ የዜጎቹን እንቅስቃሴዎች የሚከታተልበት ቁልፍ መሳሪያ ተደርጎ ይታሰባል።

በህግና በጦርነት ውስጥ ሁሉም ነገር “ልክ” ነው

እነዚህ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ምርጫው የቅርብ ጊዜ የህግ ማሻሻያዎች በመሬት ላይ ካሉ እውነታዎች ጋር የተፋጠጡበት ምርጫ በሚል መጠቃለል ይችላል። የተወሰኑ ማሻሻያዎች ቢኖሩም፣ ያገረሹ የቀድሞ የፖለቲካ ስልቶች ተንሰራፍተው ነበር።

ታሪኩን ከመገናኛ ብዙኃን ምልከታም አኳያ መናገር ይቻላል፤ ለምሳሌ፤ የተለያዩ ህጎች ተከታትለው መቀየራቸውን በማድነቅ የመገናኛ ብዙሃን ከዘገቡ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ተለመደው የፖለቲካ ዘገባን ወደ መስራት ነበር የተመለሱት።

በ 2009 ዓ.ም በኢህአዴግ ጨቋኝ አገዛዝ ስር ወደ ሶስት አስርት ዓመታት ካሳለፈች በኋላ ኢትዮጵያ ለፕሬስ ነፃነት እጅግ መጥፎ ከሆኑት የዓለም አገራት ውስጥ አንዷ በመሆን አሳፋሪ ስም ያተረፈች ሲሆን ግልጽ የሆነ ትርጓሜ ያልተሰጠው ነገር ግን ሁሉን አቀፍ የሆነው የፀረ-ሽብር ህግና ገደብ የሚጥሉ የሚዲያ መመሪያዎች በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመታሰራቸውን ጉዳይ ምክንያታዊ የሚል ሽፋን ሰጡት። የእነዚህ ህጎችና መመሪያዎች ተጠቂዎችም ከጋዜጠኞች እስከ ማኅበረሰብ አንቂ ብሎገሮች ይደርሳሉ።

በሪፓርተርስ ሳንስ ፍሮንቲየርስ (አር ኤስ ኤፍ) በፕሬስ ነፃነት ጠቋሚ ዝርዝር ላይ ከተጠቀሱ 180 አገራት ኢትዮጵያ 150ኛ ደረጃ ላይ በመሆን አነስተኛ ደረጃን ይዛ የነበር ሲሆን በ2011 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሽግግር አመራር ከመጣ ከአንድ አመት በኋላ ኢትዮጵያ በዝርዝሩ 40 ደረጃዎች ከፍ ብላለች።

የዛ ዓመት ግንቦት ወር የዩኔስኮ ዓመታዊ የዓለም ፕሬስ ነፃነት በአዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት የተከበረበት አንዱ ምክንያት ይህ ማሻሻያ ነበር። የዓመቱ መሪ ቃልም ‘በፕሬስና ዲሞክራሲ መካከል ያለው ግንኙነት’ ነበር፤ንግግር አቅራቢዎችም በምርጫ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን ያላቸው ሚናን የሚያጎሉ ንግግሮች እንዲያቀርቡ ተጋብዘው ነበር። ይህም የኢትዮጵያ የመጀመሪያ “ነፃና ፍትሐዊ’’ ለሚሆነው ምርጫ (በጊዜው ግንቦት 2012 ዓ.ም ነበር የታቀደው)ቅድመ ዝግጅት የሚሆን ተገቢ ፕሮግራም ነበር። በተጨማሪም የአብይ መንግስት ጠቃሚ ማሻሻያዎችን በማድረጉም ይህ ፕሮግራም ተገቢ ነበር።

ጠ/ሚ አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በመጀመሪያ ዓመቱ 250 ድረ-ገጾች ከእገዳ ነፃ ወጥተዋል፣በአስሮች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች ከእስር ተለቀዋል፣በሺህዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ምህረት ተደረጎላቸዋል እንዲሁም በደርዘን የሚቆጠሩ የተቃዋሚ መሪዎች ወደ አገሪቱ ተመልሰው እንዲገቡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። በተጨማሪም አዲሱ አመራር የፖለቲካ ተቃውሞን ለማጨለም ያለመውን የኢትዮጵያን አወዛጋቢ የፀረ-ሽብር ህግ እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች (ሲ ኤስ ኦ) በመብት ጉዳዮች ላይ እንዳይሰሩ የሚገድቡትን ህጎች እንዲሻሻሉ አድርጓል።

ምርጫው በእርግጥ እንደታቀደው ሳይካሄድ ለሶስት ጊዜ የተራዘመ ሲሆን ይህም በኢድስ መልክ የተዋቀረው ምርጫ ቦርድ ዝግጅት እንዲያደርግ የበለጠ ጊዜ ሰጥቶታል፤ በተጨማሪም በሃሳብ ደረጃ ለዲሞክራሲ የበለጠ ምቹ የሆነ ሁኔታ እንዲፈጥር አስችሎታል። ለማሻሻያዎችም የበለጠ ጊዜ ሰጥቷል።

በዚህ ዓመት በየካቲት ወር በሌላ እመርታ ባሳየ እርምጃ የአብይ ምክር ቤት የስም ማጥፋት ወንጀል ሆኖ እንዳይወሰድ የሚያደርግ ህግን ጨምሮ ሌሎች ለውጦችን የሚያካትት የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ አወጣ። አዲሶቹ ህጎች የኢትዮጵያ የብሮድካስቲንግ ባለስልጣንንም እንደገና ቅርጽ አስያዙት፤ ባለስልጣኑ ለመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶችን ፍቃድ የሚሰጥና የሚሰርዝ ሲሆን በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን ተጽዕኖ እንዲሁም ጣልቃ ገብነት እንዳይኖርባቸው ጥበቃ እንዲሰጥ ኃላፊነት የተሰጠው ነው።

በአዲስ መልክ የተመዘገበው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን (ኢ ኤም ኤ) ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት በሌላቸው ገለልተኛ የቦርድ ኃላፊዎች እንደገና የተዋቀረ ሲሆን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ከነበረው የቀድሞ የብሮድካስቲንግ ባለስልጣን በተለየ መልኩ የኢ ኤም ኤ ቦርድ ተጠያቂነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።

ባለፉት ጊዜያት ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሃን ስራ ለማስተጓጎል የተቋቋሙ የፍቃድ አሰጣጥ ዘዴዎችም ተሻሽለዋል፥ ይህም የበለጠ ቁጥር ያላቸው የመገናኛ ብዙሃኖች ምዝገባ በማካሄድ ዜናዎችን እንዲዘግቡ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ ነው።

ሆኖም በርካቶች በማሻሻያዎቹ ላይ ያሉ አሳሳቢ ውስንነቶችን ጠቁመዋል። ኅብረት ለምስራቅና ደቡብ አፍሪካ (CIPESA) የመልካም አስተዳደር ፖሊሲዎች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ድርጅት ሲሆን በርካታ የማሻሻያዎቹ አንቀጾች በአተረጓጎማቸው ድፍን ያሉ በመሆናቸው ተችቷል። ከነዚህም ውስጥ ከጥላቻ ንግግሮችና ሀሰተኛ መረጃ ከማሰራጨት ጋር የተያያዙ ህጎች ይገኙበታል። እናም በተግባር ኢ ኤም ኤ አሁንም የፈለገውን የመወሰን ሰፊ ስልጣን እና የዘፈቀደ ውሳኔ ለማሳለፍ ሰፊ ቦታ አለው።

የመገናኛ ብዙሃን ህጎች የህግ ውስንነቶች እንዳሉባቸው የተረጋገጠው በምርጫው መዘግየት ወቅት ሁለት ታሪካዊ ሁነቶች በተከሰቱ ጊዜ ነው። አንዱ ሁነት በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም የሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በህዳር ወር 2013 ዓ.ም የትግራይ ጦርነት መከሰት ነው።

ያለፈው ዓመት በአገሪቱ ጋዜጠኞችን በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር የማዋልና ጋዜጠኞች ላይ ጥቃት የማድረስ ሁኔታዎች ጨምረው ታይተዋል። በርካቶች ጭቆናው የተጀመረው በሃጫሉ (ተወዳጅ የኦሮሞ ሙዚቀኛ ነው) መገደል ጊዜ ነው ይላሉ፤ይህን ተከትሎም ለሶስት ሳምንታት የመገናኛ ብዙሃኖች ተቋርጠዋል፣ በተጨማሪም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል እንዲሁም በአስሮች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞችና በርካታ የመገናኛ ብዙሃኖች ተዘግተዋል። ከተዘጉ የመገናኛ ብዙሃኖች መካከል የሃጫሉን የቀብር ስነስርዓት በቀጥታ በማስተላለፍ አመጽ ቀስቅሷል በማለት መንግስት ተጠያቂ ያደረገው የኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ (OMN) ይገኝበታል።

ባለፈው ሐምሌ ወር በሺህዎች የሚቆጠሩ የአሮሞ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና የማኅበረሰብ አንቂዎች የሃጫሉን ሞት ተከትሎ በተፈጠረው የሰው ህይወትን በቀጠፈው አመጽ ምክንያት በቁጥጥር ስር ውለዋል። በዚህም የተነሳ በዚህ አመት፤በክልሉ ለገዢው ብልጽግና ከባድ ተፎካካሪዎች የነበሩ ሁለቱ ፓርቲዎች የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ባጋጠማቸው ጭቆና የተነሳ የምርጫ ውድድሩ ፍትሀዊ አይደለም በማለት ከምርጫው እራሳቸውን አግልለዋል።

ለረዥም ጊዜያት ተቃዋሚ ለነበሩ ሰዎች ደግሞ የአሁኑ ምርጫ ቀደም ሲል ከተደረጉ ምርጫዎች ጋር አንድ አይነት ነበር ይህም ለኢትዮጵያ አዲስ የዲሞክራሲ ወጋገን ነው ወይም ብልጽግና ከኢህአዴግ የተለየ ነው የሚሉ አባባሎች መዘባበቻ እንዲሆኑ ያደረገ ነው። በሰኔ ወር ምርጫ ከተካሄደ ከሁለት ቀናት በኋላ የኦፌኮ መሪ መራራ ጉዲና “ነፃና አካታች ያልሆነ ምርጫ ዲሞክራሲን ማምጣት አይችልም’’ ሲሉ ትዊት አድርገዋል።

በ 2012 ዓ.ም መጨረሻ ትህነግ የብልጽግናን ጥምረት ለመቀላቀል አሻፈረኝ ማለቱን ተከትሎ ትግራይ ክልል የራሱን ምርጫ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም ያካሄደ ቢሆንም የፌደራል መንግስት ግን ምርጫውን ህገ ወጥ ብሎ በየነው። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይል በአማራ ክልላዊ ኃይሎችና በኤርትራ ብሔራዊ ኃይሎች እርዳታ ትህነግን ከስልጣን ለማስወገድ ጣልቃ ገቡ። መጀመሪያ “ህግ የማስከበር እርምጃ’’ በማለት የተጠራው አሁን ከክልሉ ጋር የተከፈተው ሙሉ ለሙሉ ጦርነት የፕሬስ ነፃነት ወደ ኋላ እንዲመለስ (ለረዥም ጊዜ የነበረ የግንኙነት (ኮምዩኒኬሽንስ መቋረጥን ያካትታል) ያደረገ ምክንያት ነው።

ለምሳሌ ሪፓርተር ሉሲ ካሳ የትግራይ ጦርነት ላይ ዘገባ መስራቷን ተከትሎ በቤቷ በታጣቂዎች ጥቃት ስለደረሰባት አገሪቷን ለቃ የተሰደደች ሲሆን ያየሰው ሽመልስ በመጋቢት ወር ከሌሎች በርካታ የኢትዮ-ፎረምና የአውሎ የመገናኛ ብዙኃን አባላት ጋር በጋራ በሽብር ክስ በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል በኢህአዴግ ጊዜ ታስሮ የነበረ ተቃዋሚና የአብይ ደጋፊ የሆነው ዮናታን ተስፋዬ ሲሆን ከተሾመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ህትመቱ የትህነግን አጀንዳን የሚያራምድ ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ ነው የሚሰራው በሚል አዲስ ስታንዳድርድ መጽሔትን አሳደደው። አዲስ ስታንዳርድ የትግራይ ህዝባዊ ተቃውሞ ንቅናቄን ምህጻረ ቃል በመተንተኑ የኢትዮጵያ መንግስት “ሽብርተኛ ድርጅት’’ ብሎ የፈረጀውን ቡድን በመደገፍ ተወንጅሎ የነበረ ሲሆን ይግባኝ ካለ በኋላ ግን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የቅጣት እርምጃ ተቀልብሷል።

ዋና ዋና ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃኖች ኢንተርሴፕትሬውተርስና ቢቢሲን ጨምሮ በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ መንግስት ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨቱ ምክንያት ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው ገልጸው ነበር። በነሐሴ ወር ለምሳሌ የትግራይ ኃይሎች ወደ አፋር ክልል ከገቡ በኋላ የአካባቢው ባለስልጣናት ከቢቢሲ ጋዜጠኞች ጋር ሀሰተኛ ቃለምልልስ አዘጋጅተው እንደነበር የቢቢሲ ጋዜጠኞች ማስረጃ አቅርበዋል። ማስረጃው በተጨማሪም የመንግስት ደጋፊ የሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር መለያዎች (አካውንቶች) ስለጥቃቶችና የሟቾች ቁጥር ሀሰተኛ መረጃ ማባዛታቸውን ያሳያል።

ሁለት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በ 2013 ዓ.ም በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል። የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ አርአያ በጥር ወር መቀሌ ውስጥ የተገደለ ሲሆን በወለጋ ዞን የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ጋዜጠኛ ሲሳይ ፊዳ ደግሞ በግንቦት ወር ተገድሏል።

የሰኔ 14ቱን ምርጫ ተከትሎ በነበሩት ቀናት በደርዘን የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ውለው በይፋ ክስ ሳይመሰረትባቸው ታስረው የቆዩ ሲሆን ሃጫሉ በተገደለ በማግስቱ በቁጥጥር ስር የዋለው የኦ ኤም ኤን ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳ አሁንም በእስር ላይ ይገኛል።

የህዝብ ችሎት

“ውይይት የሁሉ ችግሮች መፍትሔ ነው፤ እንዳለመታደል ሆኖ ገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ተቃውሞን የሚያስተናግድበት መንገድ በፊት የነበረውን ስርዓት፣ዘዴ በመጠቀም ነው’’  በማለት የቤንሻንጉል-ጉሙዝ ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ  ፖለቲከኛ በቦሌ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ ኢንሳይት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ተናግሯል።

በቤንሻንጉል-ጉሙዝ ልክ እንደ ጋምቤላ ከፍተኛ የአካባቢ የብልጽግና ፓርቲ ባለስልጣናት በቤንሻንጉል-ጉሙዝ ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ  እና በቤንሻነጉል ጉሙዝ ህዘቦች ዴሞክራሲያሳዊ ፓረቲ የሚገኙ ያሰሯቸውን ከፍተኛ የተቃዋሚ መሪዎች ከትህነግ ጋር ግንኙነት በመፍጠር በክልሉ ግጭትን ለማስፋፋት ተልዕኮ ያላቸው ናቸው በማለት ወንጅለዋል። ይህ ውንጀላ በመንግስት መገናኛ ብዙሃንም የተረጋገጠና ይህን ተከትሎም ትርክቱ ባላፉት ወራት በማኅበራዊ ትስስሮች በመሰራጨት ሲባዛ የነበረ ነው።

ተጨባጭ መረጃ ስላልተገኘ ውንጀላዎቹ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ አልቻሉም። በህዝብ አስተያየት ፍርድ ቤት ግን ማኅበራቱ አንድ ስፍራ ላይ ተገትረው ቀርተዋል። በሁለቱም ፓርቲዎች በኩል ያሉ መሪዎች የስም ማጥፋት ክስ ሊመሰርቱ እንቅስቃሴ ቢያድርጉም ህግ ግን ከጎናቸው እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

የሃሳብ ልውውጦችና ጤናማ ክርክር ዲሞክራሲ እየተተገበረ እንደሆነ የሚያሳዩ ወሳኝ ምልክቶች ሲሆኑ ነጻ፣ታማኝና መድልዎ የሌለባቸው የመገናኛ ብዙሃን የሃሳብና የመረጃ ልውውጦች ሚዛናዊና ትክክለኛ እንደሆኑ በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት በአብይ አገዛዝ እየቆየ ቀንሷል ስለሚሉ በቅርብ ጊዜ እየተሰሙ ስላሉ አስተያየቶች ቢልለኔ ስዩም “ፍጹም የሆነ ሁኔታ የለም፤ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ በማደግ ላይ ያለ ዲሞክራሲ ወደ ኋላ እየተመለሰ ነው ሊባል አይችልም’’ በማለት ምላሽ ሰጥታለች

በኢትዮጵያ ያለው ዲሞክራሲ እውነትም በማደግ ላይ ያለ ያለና ፍጹም ያልሆነ ነው።

እነዚህ ምርጫዎች እንዳረጋገጡት ጠቃሚ ጥረቶች የተጀመሩ ቢሆንም ጉልህ ማሻሻያዎች ግና ገና እውን አልሆኑም። አገሪቷ ወደ ኋላ ትመለስ አትመለስ የሚለውን ጉዳይ፤ አስፈላጊ ነው ብሎ ያሰበውን ማንኛውንም መንገድ ተጠቅሞ የፖለቲካ ስልጣን በድጋሚ የያዘው ገዢ ፓርቲ የሚመልሰው ነገር ነው።

ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች የተነሳ የ2013 ዓ.ም ምርጫ ጥቅም ላይ ሳይውል ያመለጠ መልካም አጋጣሚ ነው። ኢትዮጵያ የእውነት ያስፈልጋት የነበረው ስልጣን የማጋራት ሙከራ እንጂ በተወሰነ መንገድ የተሻሻለ የኢህአዴግ የፓርቲ-መንግስት (party-state) እንዲሁም ከገጠር ይልቅ በአብረቅራቂ የከተማ ልማት ላይ ያተኮሩ ብሔራዊ ፖሊሲዎች አይደሉም። እውነተኛ ብዝሃነትና የድህነት ቅነሳን ለማፋጠን ምንም አይነት አዲስ ነገር ባለማድረጉ የተነሳ የምርጫው ሂደት የኢትዮጵያውያንን ህይወት ለማሻሻል ያበረከተው አስተዋጽኦ እጅግ አነስተኛ ነው።

Query or correction? Email us

Follow Ethiopia Insight

ይህ ጽሁፍ ምርጫ 2013ን በሚመለከት ዘለግ ያሉ ጽሁፎችን ከመላው ኢትዮጵያ በተከታታይ የምናቀርብበት የ “Ethiopia Insight Election Project (EIEP)” ክፍል ነው።

ዋና ምስል: የብልጽግና ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ፥ ግንቦት 21፣2013፥ ፋና።

Join our Telegram channel

Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished.

We need your support to analyze news from across Ethiopia
Please help fund Ethiopia Insight’s coverage
Become a patron at Patreon!

About the author

Ethiopia Insight

Leave a Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.