Ethiopian language In-depth

ሥር ለሰደደው የፖለቲካ ችግራችን መታከሚያ መድሐኒት ምን ይሆን?

‹‹በእያንዳንዱ ቀውስ መሐል ታላቅ ዕድል አለ›› አልበርት አይንስተይን

ቪድ-19 በቻይና መገኘቱ ይፋ ከተደረገበት ከሦስት ወራት በኋላ የዓለም ጤና ድርጅት በሽታው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡ በሽታው በኢትዮጵያ እስከ ግንቦት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 261 ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን፣ የአምስት ሰዎችን ሕይወት ደግሞ ቀጥፏል፡፡ በኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስ የፈጠረው የጤና ችግር ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሒደትንም ጭምር ነው ያዛባው፡፡ ከተሞች ከፊል ዝግ በመደረጋቸው ሳቢያ ማኅበራዊ ግንኙነቶችና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ እየተጎዱ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና ኮሮና ከዚህ አሉታዊ ጎን በተጨማሪ አዎንታዊ ሊባል የሚችል አጋጣሚ ለሃገሪቱ አምጥቷል፡፡ የሰዎች ትኩረት እጅግ ከፍተኛ በሆነ ስሜታዊነት ከታጀበው የምርጫ ዙሪያ የፖለቲካ አታካራ ሁሉንም ሊያግባባ ወደሚችል የማኅበረሰባዊ ጤና እንዲዞር አድርጓል፡፡

ወረርሽኙ ከሁሉም ቀዳሚ አጀንዳ በመሆን አገራዊ ክርክሮችን ሙሉ በሙሉ ከሆነ ፖለቲካዊ ይዘታቸው ወደ ማኅበረ-ፖለቲካ ዘውግ እንዲቀየሩ ያደረገ ሲሆን፣ ተቃራኒ የፖለቲካ አስተሳሰብ የያዙ የተለያዩ የሃገሪቱ ቡድኖች በአንድ እንዲቆሙ አድርጓል። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በጋራ ጉዳይ ላይ ውይይት ሲያደርጉ መመልከት እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡ ምን አልባትም ይኼንን መሰል በቅርብ የታየ ብቸኛ ጉልህ ክስተት በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት በማውገዝ ከሁሉም አቅጣጫ የተንጸባረቀው ተመሳሳይ አቋም ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም፡፡

ሌላው የኮሮና ውረርሽኝ በሃገሪቱ ላይ ያመጣው ተጽኖ በዚህ አመት ሊደረግ የነበረውን ሃገራዊ ምርጫ እንዲሰረዝ ማድረጉ ነው። የዝግጅት ሥራዎችን ለመሥራት አዳጋች ነው በማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊደረግ የታሰበውን አገራዊ ምርጫ አራዝሟል፡፡ እንግዲህ ይህ የሆነው ቀድሞውንም የፖለቲካ መተማመንና ጠንካራ ዲሞክራሲያዊ ባህል ባለመኖሩ እንዲሁም የልሒቃን ድርድርና ውይይት በበቂ ሁኔታ ባለመካሔዱ ምርጫ ለማድረግ በሚያስችል ጊዜ ላይ አንገኝም የሚል ሐሳብ እየተስተጋባ ባለበት ወቅት ነው ፡፡ ከዚህ አንጻር ሲቃኝ ምርጫው መደረጉ ጥቅሙ የበዛ ላይሆን ይችል ነበር ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ረገድ ሲታይ የወረርሽኙ መከሰት ምርጫው እንዳይደረግ እንቅፋት መሆኑ ለሃገሪቱ ያልተጠበቀ ሲሳይ አምጥቷል ማለት ይቻላል።

እየደበዘዘ የመጣው ተስፋ?

በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ መላ ኢትዮጵያ በተስፋና ከራስ በመነጨ ከልክ ያለፈ ደስታ ተጥለቅልቆ ነበር፡፡ ከእርሳቸው ወደ ሥልጣን መምጣት አስቀድሞ አገሪቱ ከእርስ በርስ ጦርነት አፋፍ ደርሳ ነበር፡፡ ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የበሰበሰውን የኢሕአዴግ ሥርዓት ለመበጣጠስ በወሰዱት ድፍረት የተሞላበት ዕርምጃ እርሳቸውን በተግባርም ሆነ በመንፈስ እንደ መሲህና ኢትዮጵያዊ ሙሴ በሚመለከቱ ኢትዮጵያውን ልብና አዕምሮ ውስጥ ተስፋን መዝራት ችለዋል፡፡ ብዙ ሰዎች በተለምዶ ወጀብ የበዛበትን የፖለቲካ ምህዳራችንን ያስተካክሉልናል፣ የተከፋፈለችውንም አገር አንድ ያደርጓታል፣ ተቋማትን ያጠነክራሉ፣ እንዲሁም የተዛባውን ኢኮኖሚ መስመር ያስይዛሉ ብለው እምነት እንዲጥሉባቸው አድርገው ነበር፡፡ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ማግስት ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንን የብዙዎች ተስፋና እምነት በሚመጥን መልኩ የጋራ ታሪክን፣ መልካም ማኅበራዊ ዕሴቶችን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያውያንን የጋራ ዕጣ ፈንታ በማጉላት አንድነትን ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ በስደት የነበሩ ቡድኖችን ወደ አገር ቤት ጋብዘዋል፣ በርካት የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ አድርገዋል፣ በሐይማኖት ተቋማት ውስጥ የነበሩ ክፍፍሎችም እንዲቀሩ ረድተዋል፡፡ በሙስናና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይተቹ የነበሩ ከፍተኛ የደኅንነት ተቋማት ሹመኞችን ከማባረር በተጨማሪ የደኅንነትና የፍትሕ ተቋማትን ለማሻሻል ወይም እንደ አዲስ ለማቋቋም በማሰብ የተለያዩ አማካሪ ቡድኖችን አዋቅረዋል፡፡

እነዚህ ፈጣን እርምጃዎች ግን ሁሉንም ያስደሰቱ ስላልነበሩ ከሥልጣንና ጥቅማ ጥቅም ፈቀቅ ከተደረጉ የቀድሞ የኢሕአዴግ አኩራፊ ባለሥልጣናት ጨምሮ ከተለያዩ አቅጣጫዎችና ቡድኖች ተቃውሞዎችን ማስተናገዱ አልቀረም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃዎች አገራዊ ለውጡን እነርሱ ላይዘውሩት እንደሚችሉ ሥጋት ከገባቸው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባላት ከሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወገኖች ሳይቀር ጠንካራ ተቃውሞ አስከትለዋል፡፡

በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን በጣም አስገራሚ የነበረው ነገር ቢኖር በአገሪቱ ውስጥ ያሉት የተለያዩ ፖለቲካዊ ቡድኖችም ሆነ አመራሮች አገሪቱ ከገባችበት ለውጥ ጋር ራሳቸውን ለማጣጣም ያልቻሉ፣ ለአገራዊው ለውጥ የሚመጥን በቂ ዝግጅት ያልነበራቸው ሆነው መታየታቸው ነው፡፡

በእርግጥ ዐቢይ ራሳቸው አንዳንድ ጊዜ በዕቅድ የሚመሩ አይመስሉም ነበር፡፡ አስተዳደራቸው የረጋ አልነበረም፡፡ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ በየቀኑ በሚታዩ የለውጥ እርምጃዎች መካከል ለራሳቸው የሚሆን መንገድ ለማበጀት ዝግጅቱ አልነበራቸውም፡፡ ከዚህ ባለፈ ግልጽ የሆኑ የሚና ግጭቶችም ይስተዋሉ ነበር፡፡ ባለሥልጣናት እንደ ተቃዋሚ ይቃጣቸው የነበረ ሲሆን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በበኩላቸው ከአስተዳዳሪው ፓርቲ ጋር ያላቸውን የርዕዮተ ዓለም ልዩነት በግልፅ ለማስቀመጥ ሲቸገሩ ይታዩ ነበር፡፡

ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ፣ ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር በሆኑ በጥቂት ወራት ውስጥ በርዕዮተ-ዓለም፣ በመሬትና በሥልጣን ምክንያት የተፈጠሩ የቆዩ አገራዊ ቅራኔዎች የብሔርና የሐይማኖት ግጭቶችን በመንተራስ ወዲያው መገለጥ መጀመራቸው ነበር፡፡ የተፈረካከሰው የደኅንነት ተቋምና ድሮ እጅግ የተማከለ የነበረው የፓርቲ ሥርዓት መንኮታኮት ክፍተትን ፈጠረ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በብሔር ማንነት የተዋቀሩ ክልሎች የሚያደርጉት የትጥቅ ፉክክር ጉልህ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በግጭት የተነሳ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በቅርቡ የግጭቶች ብዛትና መጠን ቢቀንስም፣ ዛሬም በብሔርተኝነት የሚቃኘው የፖለቲካ ሽኩቻ አደገኛ፣ አገሪቱም ጸጥታና ሰላም የማያስተማምን ነው።

በለውጡ ማግስት ደስታን ፈጥረው የነበሩ ጉዳዮች በአሁኑ ሰዓት በጥርጣሬ የተተኩ ሲሆን፣ በወደፊት የዴሞክራሲ ሽግግር ተስፋ ላይ ጥላ አጥልተዋል ፡፡ ዛሬ ላይ ከሕግ የበላይነት መስፈን፣ ከባለሥልጣናት ሰፊ ተቀባይት መኖር፣ ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ መረጋገጥ፣ ዜጎች በሕዝብ ተቋማት ላይ ባላቸው እምነት እንዲሁም በለውጥ ሒደቱ የባለቤት ስሜት መኖርና በመሳሰሉ መስፈርቶች ከተለኩ፣ አገራዊ ለውጦቹ መዋቅራዊና ስር ነቀል ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ እርግጥ መሰረታዊ መዋቅራዊ ለውጦች ጊዜ ይወስዳሉ፣ ትዕግስትና ምቹ የፖለቲካ ከባቢንም ይሻሉ፡፡ ይሁንና በዴሞክራሲ፣ በሰላምና በአካታች ልማት መስመር ላይ ለመቆየት ሲባል ያለንበት ቀውስ የሚጠይቀውን ትኩረት በተገቢው ልክ መስጠት ጊዜ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች

አገሪቱ እያለፈችበት ባለው ዘርፈ ብዙ ለውጥ ውስጥ እስካሁን ድረስ ትኩረት እያሻው ተገቢው ትኩረት የተነፈገው አንድ ነገር ሕገ መንግሥቱ ነው። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች በቂ ሕዝባዊ ድጋፍ የለውም፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች ጥቂቶቹ የክልሎች አወቃቀር፣ ቋንቋ፣ የአናሳ መብትና ያለተገደበ የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብቶች የሚሉት ናቸው፡፡ ነገር ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከሁለት ዓመታት በኋላም እነዚህ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ግልጽ ውይይትን ይሻሉ፡፡ ስለዚህም ቅድሚያ ተሰጥቶት ሕገ መንግሥቱ  አለመዳሰሱ እስካሁን የተደረጉ ለውጦች ይዘት በሙሉ የገጽ ቅብ ናቸው ለማለት አንድ ማሳያ ነው፡፡

መንግሥት በምርጫ ያገኘው ሕዝባዊ ተቀባይነት እንደሌለውና የጉዳዩን ኢ-ተገማችነት በምክንያትነት በመጥቀስ እንዲህ ላሉ አስቸጋሪ ጉዳዮች መፍትሔ ለመስጠት ጊዜው አሁን እንዳልሆነ ተናግሯል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶች እንደሚሉትም እነዚህ ምክንያቶች ጊዜ ለመግዛት ከሚደረግ ከቀደመው ጊዜ የኢሕአዲግ ስልት ብዙም የተለዩ ሰበቦች አይደሉም። መንግሥት ውስጡን በማደራጀትና ውስጣዊ ውህደት በመፍጠር ወደ አምባገነንነቱ ለመመለስ እየተፍጨረጨረ ይሆናል የሚልም ስጋት አላቸው፡፡

በእርግጥም ትርጉም ያለው ለውጥ ከተፈለገ መጀመር የነበረበት የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቅሬታዎች ሁሉ ምንጭ የሆኑ መሠረታዊ ችግሮችን በመቅረፍ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ የሕጎች ሁሉ ምንጭ የሆነውን ሕገ መንግሥት እንዳለ በመተው የምርጫና ሌሎች ሕጎችን ለማሻሻል ቅድሚያ መስጠት ጋሪውን ከፈረሱ ማስቀደም ነው፡፡

ከዚህ በዘለለ፣ እንደኛ አገር የማንነት ብዝሃነት ያላቸው የሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ የልሒቃን ድርድር ማለትም በፖለቲካው ተሳታፊ የሆኑ ፖለቲከኞች የሚያደርጉት የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል ድርድር፣ ብዙን ጊዜ የሚመጣው ከምርጫ አስቀድሞ እንጂ ከምርጫ በኋላ አይደለም፡፡ በድርድሩ የሚሳተፉ በሙሉ ደግሞ የግድ የሚመረጡ ቡድኖች መሆን አይጠበቅባቸውም፡፡ ለተሳትፎ ሕዝባዊ ተቀባይነትን ማግኘት ብቻ በቂ ሲሆን፣ ይሔ ደግሞ በኢትዮጵያም ሊሠራ የማይችልበት ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህም እንደ ሕገ መንግሥት ያሉ ወሳኝ ጉዳዮችን ላለመንካት የሚደረግ ጥረት ጠንካራ መሠረት ላይ የቆመ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ሰዎች መንግሥት የበሽታውን ምልክቶች ከመፋለም ይልቅ በሽታውን ለማከም ያለውን ቁርጠኝነት እንዲሁም ከፍተኛ ጭቆናና አምባገነናዊነት ከነገሰበት ያለፈው ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ የተፋታ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያለውን ፍላጎት በጥርጣሬ የሚመለከቱት፡፡

የፈረሱና የጋሪው መምታታት

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አካታች የአገርና የዴሞክራሲ ግንባታን በተመለከተ እየተሸረሸረ የመጣውን ተስፋ ወደ ቀደመ ስፍራው ለመመለስ የሚያስችል ወርቃማ ዕድል ይዞ መጥቷል፡፡ ልሒቃኑ እስካሁን ካልነበረውና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ አስፈላጊ ግብዓት ከሆነው መግባባት ላይ እንዲደርሱ የሚያስችል ጊዜ ሰጥቷቸዋል፡፡ ይሔ ሊባክን የማይገባው ዕድል ነው፡፡ ይህ ዕድል ቀጣይ ትውልዶች የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መሥራች አባቶቻቸውን እያመሰገኑ ቀድተው ሊጠጡባቸው የሚችሉባቸው የነጻነት፣ የእድገትና የለውጥ ተስፋ ምንጮችን ለመፍጠር የሚያስችል አጋጣሚ ነው፡፡

ይህ ሁሉ ሊሆን የሚችለው ግን ሁላችንም ስንተባበር፣ ግልጽ ግለ-ሂስ ስናደርግ፣ ላለፉ መልካምና ክፉ ጊዜያቶቻችን እውቅና ስንሰጥ እንዲሁም ጥልቅ የሆኑ የጋራ ዕሴቶቻችንን በመጠቀም በእኩልነት፣ በአገር ወዳድነት፣ በጠንካራ የሥራ ባሕልና በሕግ የበላይነት ምሰሶነት የቆመ አገር ስንገነባ ነው፡፡

ሥነ ምግባራዊ አካሄድ

ፕሬዚዳንት ኦባማ በአንድ ወቅት ‹‹የዘመኑ ፖለቲካ በሞራላዊ ሕግ የማይገዛ በጎ ማኅብረሰባዊ እሴቶችን የሚሸረሽር ጨዋታ ሆኗል›› ሲሉ ጽፈዋል፡፡ በእውነቱ ከሆነ ይህ ንግግር ከኢትዮጵያ በላይ ገሃድ የሆነበት ሌላ ቦታ ያለ አይመስለኝም፡፡ ፖለቲካችን ተራቾችን፣ ዋሾዎችንና ጽንፈኞችን ያበረታታል፡፡ የተጠቂነት መንፈስን፣ የሌላውን ማንነት ማጠልሸት እንዲሁም አድመኝነትን ይሸልማል፡፡ ጥበብን፣ ለዘብተኝነትን አልያም ሃቅን እምብዛም አያበረታታም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በዩንቨርስቲዎችበቤተ እምነቶችበሌሎች ቦታዎች በታየው የመንጋ ፍትሕ የሚታየው የአጠቃላይ የማኅበረሰባችን የሞራል ዝቅጠት መኖር ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።

እውነታው ግን በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ አካታች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መቅረጽና መተግበር ከርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች በላይ በሚሻገር ሥነ-ምግባር የተቃኘ ፖለቲካን ይፈልጋል፡፡ ለአብነት ያህል እኛ ኢትዮጵያውያን  ለክብር ትልቅ ቦታ አለን፡፡ ይህ የግለሰብም ሆነ የጋራ ባህል ዘረመላችን አካል የሆነና በረዥም ታሪካችን ውስጥ ብዙ መሰዋትነት የከፈልንበት ዕሴት ነው፡፡ መከበር የበርካታ ኢትዮጵያውያን ፍላጎት ሲሆን፣ የአገራዊ ኩራታችን መሠረት የሆነ የጸና ዐለት ነው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ይህ ስሜታዊ ፍላጎት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከሚገባው በላይ ቦታ ተሰጥቶት ይታያል፡፡ በዚህም አነስተኛ የሚባሉ አለመግባባቶችና የፖለቲካ ክርክሮች (ግጭቶች) እንኳ ብዙን ጊዜ አንዱ ወገን እንደተናቀና ክብር እንዳልተሰጠው ወይንም እንደተጠላ እንዲሰማው የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ይህ ማለት ግንኙነታችን እርስ በርስ ከመከባበር የተፋታ ነው፡፡ በዚህ ያልተገመተ የጤና ቀውስ ጊዜ ሳይቀር ወረርሽኙን እንዴት እንከላከለው በሚለው ጉዳይ ላይ እንኳን ሥልጡንነት አይታይም፤ ቢያንስ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንደሚታየው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ሥነ ምግባር የጎደለው ፖለቲካችን፣ ፖለቲከኞቻችን የግለሰብ ጸቦችን የማኅበረሰብ፤ የግል ችግሮችን የአገር አጀንዳ በነጻነት የሚያደርጉበት ሁኔታ እንዲፈጠር አስችሏል፡፡ ወደፊት መሔድ ካለብን ግን ሥነ ምግባር የለሽ ፖለቲካን በመተው ኢትዮጵያውያን በፍቅር ከያዟቸውና ለረዥም ጊዜ ከቆዩ እንደ መቻቻል፣ መከባበርና የጋራ መግባባት ያሉ ማኅበራዊ ዕሴቶች በወጡ የሞራል መርሆዎችን በፖለቲካችን ውስጥ ማካተት ይገባናል፡፡ ለዚህም ማኅበረሰባዊ የባሕልና የአመለካከት ለውጥ መፍጠር እንዲሁም ተጨባጭ ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅብናል፡፡ የዚህ ሁሉ ጥምርታ የምንፈልገውን ዓይነት ማኅበረሰብና የምንፈልጋትን አገር የሚፈጥርልን ይሆናል፡፡

ለድርድር በማይቀርቡ ጉዳዮች ላይ መደራደር

በብዙ አገሮች ለድርድር ክፍት የሆኑ የተወሰኑ ጉዳዮች ያሉ ሲሆን፣ የተወሰኑ ደግሞ ለድርድር የማይቀርቡ ጉዳዮች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን የአገሪቱን ቀጣይ ህልውና ጨምሮ ለክርክር የማይዳርግ ጉዳይ የለም፡፡ የዚህ አገራዊ ጉዳዮች አለመኖር ፖለካውን ሥርዓት አልባ፣ ልሒቃዊ ብሎም ከዕለት ተዕለት ችግሮቻቸው ጋር ለሚታገሉ የተቀሩት የሕብረተሰብ ክፍሎች የመከራ ምንጭ አድርጎታል፡፡ ከዚህ አሳዛኝ መንገድ የተለየ አዲስ አካሔድ መንገድ መቀየስ ከነበረብን ብዙ ዘግይተናል፡፡ ጥሩን ከመጥፎ የሚለይና ለድርድር የማይቀርብና የሚቀርብ ጉዳይን የሚገነዘብ አገር አቀፍ መታደስና ንቃት ያስፈልገናል፡፡

ለመነሻ ለምሳሌ ሦስት ጉዳዮችን ማለትም የአገር አንድነት (ላዊነት)የብሔር: ቋንቋ ወይንም የሐይማኖት ማንነት ጥበቃየሕግ የበላይነት ለድርድር የማይቀርቡ አገራዊ ጉዳዮች ናቸው ብለን መለየት እንችላለን።  እነዚህን ግቦች ለማሳካት የምንሔድበትን መንገድ መደራደር እንችላለን፤ ነገር ግን በነዚህ ጉዳዮች መሠረታዊነትና መከበር ላይ ግን ድርድር አያስፈልገንም፡፡ ለምሳሌ ዴሞክራሲ በሥርዓት አልበኝነት ላይ አይገነባም፡፡ በሕግ የበላይነት ከለላ ውስጥ የሚገነባ ሥርዓት ነው እንጂ ከዛ ውጭ አይሆንም፡፡ ስለዚህም በሕግ የበላይነት መርህ ላይ ከተስማማን አሁን እየተለመደ እንደመጣው ሁሉ ልዩነቶችን በአመጽና በጉልበት ለመፍታት ከሚፈልግ ማንኛውም ሰው በተቃራኒው ለመቆም የሞራል ግዴታ ይኖርብናል ማለት ነው። በተመሳሳይ ሁሉም ሰው የአገሪቱን አንድነት፣ የቡድኖችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት፣ ቋንቋቸውን ለማበልጸግና ባህላቸውን ለማጎልበት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚጎዳ ማንኛውም ተግባር ውስጥ ላለመሳተፍ መታቀብ ይኖርበታል፡፡

ምርጫ ሁሉን ችግር ፈቺ አይደለም

በዚህ የመታደስ ጥረታችን ውስጥ ሌላው ልንገነዘበው የሚገባን ነገር የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች ምንም ያህል ፍትሐዊና ነጻ የሆነ ምርጫ ቢደረግ በምርጫ ብቻ የሚፈቱ አለመሆናቸውን ነው። ምርጫ ለችግሮቻችን መፍትሄ አንዱ ቢሆንም፣ የአገሪቱ ችግሮች እጅግ ውስብስብና መርዛማ በመሆናቸው ሳቢያ አሸናፊው ሁሉንም በሚጠቀልልበት የምርጫ ሥርዓት የሚፈቱ አይደሉም፡፡ ምንም እንኳን ብዙ ፖለቲከኞቻችን ምርጫ ተመራጭ የፉክክር ሜዳቸው እንደሆነ ቢናገሩም፣ ሥር ለሰደዱ ችግሮቻችን መፍትሔ ግን አይሆንም፡፡ ደግሞም ዴሞክራሲ በጨዋታው ሕግ ዙሪያ በወሳኝ የፖለቲካው ተጫዋቾች መካከል መግባባትን መፍጠር፣ ለምርጫ አስፈላጊ የሆኑ ነጻና ገለልተኛ ተቋማትን መገንባት፣ እንዲሁም የማኅበረሰቡን የፖለቲካ ንቃተ ሕሊና ማጎልበትን ይጠይቃል፡፡ በአሁኑ ሰዓት  ከእነዚህ ሁሉ አንዱም በኢትዮጵያ አይገኝም፡፡

ምርጫውን የማራዘም ውሳኔ ከመተላለፉ አስቀድሞ እንኳን፣ ሒደቱ ከዴሞክራሲያዊ ሽግግር ይልቅ ወደ ባሰ ቀውስ ሊያመሩ የሚችሉ ችግሮች እየገጠሙት ነበር፡፡ መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎች ምንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍል ለማሸነፍ ብቻ የተዘጋጁ ይመስሉ ነበር፡፡ ማንንም ተመልካች በሚረብሽ መልኩ የተወሰኑቱ ስለማሸነፋቸው እርግጠኞች ነበሩ፡፡ የዴሞክራሲ ወሳኝ አካል የሆነውን ሽንፈትን በጸጋ የመቀበልን መርህ ለማክበር ዝግጁ  አይመስሉም ነበር፡፡

ከዚህ ባለፈም፣ ሒደቱ በተቃዋሚዎች የመንገላታት ቅሬታዎች ይበልጡኑ የጠለሸ ነበር፡፡ እንደ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ያሉ ፓርቲዎችም የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት ከጥያቄ ውስጥ ከትተዋል፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ሕዝቡ ለመምረጥ ምንም ዓይነት ተነሳሽነትን የማያሳይ መሆኑ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለምርጫ ያላቸው ፍላጎት እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ የብዙዎች ስጋት የነበረው ሒደቱ ወደ ባሰ የፀጥታና ደኅንነት ቀውስ አልያም እንደ ዩጎዝላቪያ መሰል የእርስ በርስ ጦርነት የሚያመራ ይሆናል የሚል ነው፡፡ በአጠቃላይ፣ ምርጫውን ለማራዘም ከተላለፈው ውሳኔ አስቀድሞ የነበረው ነገር ሁሉ የሚያመላክተው ዴሞክራሲያዊ ሽግግሩን መስመር የሚያስት ብጥብጥ እንደሚከሰት ነው፡፡

ምርጫው እንዲጠቅመን የምንፈልግ ከሆነ ግን፣ አስቀድመን ምርጫ አገራዊ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የሚጫወተውን አነስተኛ ሚና መቀበል ይኖርብናል፡፡ ምርጫ ከልሒቃን ድርድር በኋላ ካልመጣና ከዚህ በሚገኙ ስምምነቶች በመነጩ ሕጎች ተቃኝቶ በገለልተኛ ተቋማት ካልተመራ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመምራት ይልቅ ራሱ የህልውና ሥጋት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከምርጫ በፊት ቆም ብሎ መተማመንን መፍጠር፣ ቅን ድርድሮችን ማድረግና በድርድር አማካይነት በመንግሥት አስተዳደር ቅርጽ፣ በሥልጣንና በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ላይ ከስምምነት በመድረስ ያስፈልጋል፡፡ ይህ በምንም መልኩ ቀላል አይደለም፤ ነገር ግን ጠንካራ አገር ለመፍጠር በሚደረግ ሒደት ውስጥ ሊዘለል የማይችል ሒደት ነው፡፡

ነባራዊ እውነታን ያማከለ ፖለቲካ

የበርካታ ኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት የኑሮ ትግሎች ከጋራ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡ ከጫና ነጻ ሆነው ሐይማኖታዊና ባሕላዊ ነጻነታቸውን ለመጠቀም ካላቸው ፍላጎት በዘለለ፣ ሰዎች የተሻለ ጤና፣ ትምህርት፣ መንገድ፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ ቤት፣ ምግብ እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ይሻሉ፡፡ ይሁንና ፖለቲካችን ከእነዚህ ማኅበራዊ ፍላጎቶች ውስጥ የትኞቹንም አያንጸባርቅም፡፡ ፖለቲከኞቻችንም እነኝህ መሠረታዊ ችግሮችን ነባራዊ እውነታን ባገናዘቡ ፖሊሲዎች ከመፍታት ይልቅ ክርክሮችን ማሸነፍ ላይ ያተኩራሉ፡፡ አሁን ምርጫ የሁሉ ነገር ማዕከል በሆነበት ወቅት እንኳ አገራዊ ስር ሰደድ ችግሮቹን ለመፍታት ያግዛሉ የሚባሉ የፖሊሲ አማራጮች ላይ የሚደረጉ ክርክሮች አይታዩም፡፡ ስለዚህ ፖለቲካችን የኢትዮጵያውያንን ሕይወት በሚያንጸባርቅ መልኩ መቃኘት የሚያስፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ይህም ሲባል፣ የኢኮኖሚ ችግሮችን ብቻ ሳይሆን በማኅበረሰቡ ውስጥ በጥልቀት የሰረጉትንና እንደ ፆታዊ መድሎ፣ አድልዎ፣ ሙስናና የተዛባ ብሔር ተኮርነት የመሳሰሉ ማኅበራዊና ባሕላዊ ችግሮችን መቅረፍን ያጠቃልላል፡፡

ለዚህም ፖለቲከኞቻችን ቀላሉን መንገድ ከመከተልና በሰፊው መግቢያ ከመትመም ፍላጎትና ተፈጥሯዊ ዝንባሌ ራሳቸውን መቆጠብ መቻል አለባቸው፡፡ ጤናማ ፖለቲካ አስቸጋሪውን መንገድ መከተልና በጠባቡ መንገድ መግባትን ይጠይቃል፡፡ ሲጀመር ወደ ፍትሕ፣ እኩልነትና ብልጽግና የሚያመራ አቋራጭ መንገድ የለም፡፡ በመከፋፈል፣ በማግለልና በጥላቻ ላይ የሚያብብ ፖለቲካ ምንም ብቃት የማይጠይቅና አርቆ መመልከት የማይችል ነው፡፡ ያለፈው ታሪካችን እንዳሳየን ሁሉ አንድ ቡድን ሀብትና ሥልጣንን ተቆጣጥሮ ጎረቤቱ በባዶ ሆድ እያደረ ለሁሉም ሰላምና ብልጽግናን ማረጋገጥ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ በከፋፋይና በጥላቻ ፖለቲካ መጋለብ እንዲሁም በአንዱ ህልውና ላይ አንድን ቡድን እንዲጠቀም ለማድረግ መሞከር ጥበብ ያልታከለበት ተራ ሥራ ከመሆኑም በላይ ቆይቶም ቢሆን እጠቅመዋለሁ ብለን ላሰብነው ለራስ ቡድን ጠላትን የሚያፈራ አጥፊ መንገድ ነው፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ፣ ረጅሙንና ጠመዝማዛውን መንገድ መከተል ለዘላቂ ለውጥ ጥልቅ ፍላጎት መኖሩን ያመላክታል፡፡ ይህም ማለት ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለነጻነት ባለን ፍቅር፣ ለድርድር ብልሐትን በመላበስና ሰጥቶ ለመቀበል ዝግጁ በመሆን፣ በትዕግሥተኛነት እንዲሁም ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮችን በጥልቅ መገንዘብ በመቻል ተደጋጋሚ ችግሮችን መፍታት ማለት ነው፡፡ ይህ የጥላቻና የአመጽ ሳይሆን የፍቅርና የሰላም ቋንቋን መናገር፣ ድልድይ እንጂ ግድግዳን አለመገንባት፣ የክፍፍልና የልዩነት ሳይሆን የአንድነትና የኅብረት ዘር መዝራትን፣ አዳዲስ የማኅበራዊ ትስስሮችን መፍጠር አልያም ያሉንን ማጠናከር፣ እንዲሁም ከሁሉም በላይ ትሕትናና ርህራሄን ማጎልበት ይጠይቃል፡፡ ረጅሙን መንገድና ጠባቡ መግቢያን መከተል ሁሉን አውቃለው የሚል ግብዝነትን ማስወገድን ይሻል፡፡ እውነታዎቻችንና ትርክቶቻችንንም ደጋግመን እንድንመዝን፣ እውቀታችንን በቀጣይነት እንድናጎለብትና የራሳችንን ጥያቄ ፍትሐዊነት መስበክን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሰዎች ጥያቄዎች ፍትሐዊነት መረዳትንና ሃዘኔታን እንድናሳይ ድፍረት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡

የማስመሰል መተሳሰብ ይብቃ

ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ ራሳቸውን ለሌላው አዛኝ ወይም አሳቢ (empathetic) አድርገው ይገነዘባሉ፡፡ በእርጥም መደበኛው የተራው የማኅበረሰቡ የቀን ተቀን ሕይወት  ይህንን እውነታ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ይሁንና፣ ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት፣ ፖለቲካችን ሥር የሰደደ የመተሳሰብ እጦት በሽታ ገጥሞታል፡፡ ይህም ለአካታችነትና ለአገር ግንባታ ወሳኝ የሆነው መቻቻልን ማምጣት አዳጋች እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ለዚህ የመተዛዘን እጦት ዋና ምክንያቶች የእውነትና የእውቀት ፍጹም ባለቤትነት አለኝ የሚል እሳቤና ሌላኛው ወገን ሐሳብ እንዳለው ወይንም የስሜት መጎዳት ትኩረትና ተቀባይነት እንደሚገባው ለማመን እምቢተኛ መሆን ናቸው፡፡ የዚህ ዋነኛ ማሳያ በተደጋጋሚ የሚታየው የአማራናኦሮሞ ልሒቃን የታሪክ ትርክቶች ውዝግብ ሲሆን፣ ምን ያህል መተሳሰብ የጎደለው ንትርክ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡

መተሳሰብ ወይም መተዛዘን (empathy) ስንል ስለ ምክንያታዊነትና እውነታ አይደለም፡፡ ይልቁንስ መሠረቱ ምንም ሆነ ምን ለሌሎች የስሜት መጎዳት ተገቢውን ትኩረት መስጠትና ሕመሙን መጋራት ማለት ነው፡፡ ከሰንደቅ ዓላማ እስከ ጀግኖቿና ታሪካዊ ትርክቷ ውዝግብ በሚነሳባት አገር፣ መተሳሰብ ከሐቀኝነት ጋር ሲቆራኝ ቁስሎችን ያክማል፣ ክፍተቶችን ይደፍናል፣ ብሎም ማኅበረሰባዊ ስንጥቆችን ማኅበረሰባዊ ልዩነቶችን ተሻግሮ ያስታርቃል፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ግን፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ልሒቃኖቻችን የእነርሱ ታሪክ አከራካሪ ያልሆነ እውነታን የተሸከመ እንደሆነ እንዲሁም ታሪካዊ ትርክቶቻቸው ህጸጽ የማይገኝባቸው እንደሆኑ ሲናገሩ የሚደመጡ ሲሆን፣ ይህ ስለድሮው እንከን የለሽ መልካም ጊዜ እያነሱ የሚናገሩ ኢትዮጵያኒስቶችን፣ የመለስ ዜናዊ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥትን የሚያቀነቅኑ የሕወሓት ሰዎች አልያም ታሪካዊ ጭቆናን በማጉላት ላይ የተጠመዱ ሌሎች የብሔር ፖለቲከኞችን ሁሉ ይመለከታል፡፡ ሃዘኔታ ጎድሏቸው መተሳሰብ ሳይኖራቸውና በአዋቂነት ትምክህት ተዘፍቀው ራሳቸውን የእውነት መፍለቂያ ምንጭና የእውቀት ጳጳሳት እንደሆኑ የእኛ የሚሉትን ቡድን ለማሳመን ሲታትሩ ይታያሉ፡፡ እውቀትን ሆን ተብሎ በተመረጡና ለእነርሱ ብቻ የማይካድ እውነትን በተሸከሙ ምንጮች ብቻ ለማስረገጥ ይጥራሉ፡፡

እነርሱ የሳቱት ጉዳይ ቢኖር ግን፣ ፖለቲካ በእውነታ ብቻ የማይመራ ዓለም መሆኑን ነው፡፡ እውነታዎች ምንም ያህል ትክክል ቢሆኑ ብቻቸውን ፖለቲካዊ ውዝግቦቻችንን ሊያረግቡ አይችሉም፡፡ ይልቁን ችግሮቻችንን ለመፍታት መተሳሰብ ያለውን ተምሳሌታዊ ዕሴትና ጉዳትን የማከም ኃይል መረዳት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ከሌሎች አቻ ዜጎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት መተሳሰብን ከግንዛቤ መክተት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ርትዕ ያላቸውን እውነታዎች ብቻ በመተግበር ብቻ ሳይሆን፣ በስሜት ረገድም ትክክል የሆኑትንም ጭምር ማድረግ ነው፡፡ ከስሜት ረገድ ትክክል የሆነ ሁሉ በርትዕ እውነታ አለው ማለት እንዳልሆነ እንዲሁም በርትዕ እውነት የሆነም በስሜት ትክክል እንደማይሆን እሙን ነው፡፡

የሰጥቶ መቀበል ፖለቲካ

በዚህ የምንም ነገር እርግጠኝነት ላይ ክርክር በሚነሳበት ዘመን የኛ ፖለቲካ የድጋፍ አልያም የተቃውሞ፤ ይህ አልያም ያ ወደሚሉ እኑስ አማራጮች ወርዷል፡፡ ትክክልና ስህተት ለሚል መከፋፈል ለማይገጥሙ የሕይወታችን ገጽታዎች እውቅናን የማይሰጥ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የግለሰብ አመለካከቶችን እንኳን ይህና ያ ብሎ ለሁለት መክፈል አዳጋች መሆኑን መገንዘብ አልቻለም፡፡ የገሃዱ ዓለም ሁለት አማራጮችን ብቻ አይደለም የሚያቀርብልን፡፡ ሁሉም አይወደድም ሁሉም አይጠላም፤ ሁሉም ነገር አይቆጠብም፤ ሁሉም ነገር አይጣልም፡፡ በጥላቻና በፍቅር፣ ትኩረት በመስጠትና ትኩረት በመንፈግ መካከል ግድ የለሽነት አለ፤ በመወለድና በመሞትም መካከል ሕይወት አለ፡፡ በፖለቲካም እንዲሁ እኛ ትክክልና ስህተት፣ ልክና የተዛባ፣ አግባብና አግባብ ያልሆነ ብለን በምናስባቸው መካከል ሁሌም ሦስተኛ የሚሆኑ በርካታ አማራጮች ይገኛሉ፡፡ ጤናማ ፖለቲካ የሚባልም ለሦስተኛ መንገድና  አማራጭ ቦታ የሚሰጥ ነው።

በኢትዮጵያ ግን ብዙ ጊዜ ፖለቲካ በፌዴራሊስቶችና (በብሔርተኛ ኃይሎች) እና በአሐዳውያንና (በኢትዮጵያዊያኒስት)  ቡድኖች ብቻ የሚደረግ ፍልሚያ ተደርጎ ነው የሚታሰበው፡፡ ይህ ፍልሚያ ማንንም  በሚያሳስት መልኩ አገሪቱ ያሏት ብቸኛ አስተዳደራዊ አማራጮች የብሔር ፌዴራሊዝም ወይንም አሐዳዊ መንግሥት እንደሆኑ አስመስሏል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ጠንካራ ደጋፊዎች ያሏቸው ሲሆን፣ የየደጋፊዎቻቸውን ስስ ብልቶች በመነካካት አንዳቸው በአንዳቸው ላይ የሞራል የበላይነትን ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት የራሳቸውን ቡድን በማስደሰት ደረጃ ስኬት ሲያቀዳጃቸው ይታያል፡፡ በተቃራኒው የትኛውም ወገን ግን እምብዛም ከእራሱ አይነኬ አቋም ውጭ መመልከት አይሻም፡፡ በመሆኑም ፌደራሊስቶችም ሆኑ ኢትዮጵያኒስቶች ከራሳቸው ቡድን የተሻገረ ቅቡልነት የጎደላቸው ሦስተኛ አማራጮችን የማይመለከቱ ግትር ቡድኖች ሆነው ይታያሉ፡፡

ይሁንና፣ ከዕሴቶቻችን፣ ታሪካችንና የጋራ ዕጣ ፈንታችን ተቀምረው ሊዋቀሩ የሚችሉ አማራጮች ግን አሉን፡፡ ይህም አንድ ቀላል እውነታን በመቀበል ይጀምራል – ኢትዮጵያ የፌዴራሊስቶች ወይንም የአሐዳውያን አገር ብቻ ሳትሆን የፌዴራሊስቶችም የአሐዳውያንም አገር ነች፡፡ ሦስተኛው አማራጭ ይህንን እውነታ የሚቀበል ለኢትዮጵያኒስቶች ወይም ለፌደራሊስቶች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚመጥን ፖለቲካ ማራመድን ይጠይቃል። በተጨማሪም ሦስተኛው አማራጭ የኢትዮጵያን ችግሮች የተለዩና ሊፈቱ የማይችሉ አድርጎ ከማሰብ መቆጠብን ይሻል፡፡ ኢትዮጵያ የብሔር፣ የባህል፣ የቋንቋና የሐይማኖት ብዝሀነት ያላቸው ቡድኖች የሚኖሩባት ያልታረቁ የባህል ቁርሾዎች ያሉባት፣ ወይንም የአገር ግንባታ ሒደት ሂደቷ ያላለቀ ብቸኛ አገር አይደለችም፡፡ እንዲህ ያሉ አገሮች በዓለማችን ሞልተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ፣ <እያንዳንዱ በር የቁልፍ መክፈቻ ቀዳዳ አለው> እንደሚባለው ሁሉ ምንም ያህል ከባድ ቢመስልም በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ከሆንንና በመተባበር ከፈለግናቸው ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔዎች አሉ፡፡ የአሜሪካ ሴነተር ኮኒ ብሩከር እንዳሉት፣ ‹‹የተባበረችና አንድ የሆነች አገር ዘላቂ ትግል ነች፡፡ የጋራ ጥረትና የግለሰብ መስዋዕትነት ያስፈልጋታል፡፡›› ኢትዮጵያም ከዚህ የተለየች አይደለችም፡፡ በርግጥ ወረርሽኙን ለመከላከልና በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሳየነው የኅብረት ድምጽ ያሳዩን የጋራ የሆኑ ጉዳዮቻችንን ለመፍታት ያለንን ብቃት ነው፡፡ እናም፣ ‹ከሚያራርቁን ልዩነቶቻችን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች ይበዛሉ፡፡›

ስለዚህ፣ ያለንበትን ሁኔታ አዙረን በመመልከት ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም መስማማት ላይ መድረስ የሚገባን ሲሆን፣ ይህ ማለት ከሁለት ሥርዓቶች አንዱን ብቻ እንደመምረጥ ቀላል እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የብሔር ፌደራሊዝም ወይም አሐዳዊ የሚባል ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ለኢትዮጵያውያን የሚስማማ፤ ለተቃራኒ ፍላጎቶች ሚዛናዊ የሆነና ጽንፎችን የሚያለዝብ አማራጭ ያስፈልገናል፡፡

አንድ ምሳሌ ብናነሳ ሰዊትዘርላንድ የ26 ራስ ገዝ አስተዳደሮች ኮንፌዴሬሽን ናት፡፡ አራት ክፍሎች (ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያንና ሮማኒያ) ያሏት ብትሆንም፣ ክልሎቿ ግን የግድ ቋንቋን መሠረት ያደረገ መዋቅር የላቸውም፡፡ ይህ የሆነው ለግጭቶች እንደ ምክንያት የሚነሳውን ተደራራቢ ማንነትና ግዛቴ ነው ማለትን ለማስቀረት ነው፡፡ ሥርዓቱ የተበጀው የራስን ዕድል በራስ መወሰንን ለማስጠበቅ እንዲሁም የግዛታዊ ብሔርተኝነትን አደጋ ለመቀነስ ነው፡፡ የቡድኖችን ማንነት የማስከበርና ራስን በራስ የማስተዳደር እንዲሁም የአገርን ህልውና የሚገዳደር ብሔርተኝነትን የመከላከል ሥራን አጣጥሞ ይዟል።

በኢትዮጵያ ‹ሦስተኛው መንገድ› የኛ ብቻ የሆኑ ልዩ ባህርያቶቻችንን በሚያስተናግድ መልኩ ተስተካክሎ በዚህ መልኩ ሊበጅ ይችላል፡፡

አንድ እጅ ለብቻው አያጨበጭብም

‹አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም› እንደሚባለው ሁሉ፣ ምንም ያህል ብልህና በልምድ የተካኑ ግለሰቦች አልያም የተደራጁና ጠንካራ ቡድኖች ቢሆኑ፣ የኛ ችግሮች እጅግ ውስብስብ ከመሆናቸው የተነሳ በማንም ሰው ወይም ቡድን በተናጠል የሚፈቱ አይደሉም፡፡ ይልቁን አገራዊ ፈተናዎቻችን በግለሰቦችና በቡድኖች መካከል ትብብርን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ወደዱም ጠሉም፣ አገሪቱን መምራት የሚሹ ከሆነ የብሄር ፖለቲከኞችም ሆኑ የኢትዮጵያ ብሔርተኞች አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር የግድ በትብብር መሥራት ይጠበቅባቸዋል ፡፡

ከራሳቸው ደጋፊዎች ድምጽ በመሰብሰብ ጠባብ የድምጽ የበላይነትን ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ ይህችን ብዝሃነት ያለባትን አገር ለመምራት አያስችልም፡፡ ሁለቱም ጽንፍ ከቆሙ መራጮቻቸው በተሻገረ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ በጠቅላላው እንደ አገር ጠቀሜታ ያለው ብቻ ሳይሆን፣ ለፖለቲከኞቹም የረዥም ጊዜ ፍላጎቶች ወሳኝ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያ ከሰመጠች፣ የትኛውም አካሏ ሊንሳፈፍ አይችልምና፡፡

ለማጠቃለል ያህል  ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና መጓዝ ከጀመረች ከሁለት ዓመታት በኋላ፣ በወደፊት አቅጣጫችን ላይ ግልጽነት የለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ታላቅ የሆነ ለውጥን እንዳመጡ ጥርጥር የለውም፡፡ የወሰዷቸው የጀግንነት ዕርምጃዎች ከአምባገነናዊ ቀምበር የተወሰነ እፎይታን አስገኝተዋል፡፡ ይህ አስደሳችና ሊደነቅ የሚገባው ስኬት ነው፡፡

በሌላ ወገን ዜጎች በተቋማት ገለልተኝነት ላይ ካላቸው አመኔታ፣ አምባገነናዊነት ተመልሶ እንደማይመጣ ከለላ ከማግኘት፣ ከሕግ የበላይነት መከበር፣ ከዜጎች ፍትሐዊ ተሳታፊነት፣ በብሔር ምክንያት የሚደርስ መገለል መቀነስ፣ እንዲሁም የልሒቃን መግባባት ከመሳሰሉ ተጨባጭ መለኪያዎች አንጻር ለውጡን ከለካን፣ ውጤቱ እምብዛም ሚዛን የሚደፋ ነው ለማለት ሙሉ በሙሉ አያስደፍርም ፡፡ ወጥነት የሌለው፣ የቀጨጨ ዴሞክራሲያዊ ልምምድና ያለመተማመን ባህል ለዚህ አሳዛኝ እውነት አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አሁን ብሔራዊ ምርጫዎች የተራዘሙ ሲሆን፣ አገሪቱ አይታና ደርሳበት ከማታውቀው የሕገ መንግሥት ቀውስ እየገባች ትገኛለች፡፡ ይሁን እንጂ የምርጫው መራዘም ይዞ የመጣው ቀውስ ብቻ አይደለም፤ ወደ ኋላ መለስ ብለን የመጣንበትን መንገድ ለመገምገምና ወደ ዴሞክራሲ የምናደርገውን ጉዞ እንዲሁም እጅግ የዘገየውንና አካታች አገር የመፍጠር ፕሮጀክት ሒደት ለማቃናት ዕድልንም ይዞልን መጥቷል ፡፡

ካሁን በኋላ ኢትዮጵያ የአንድ ግለሰብ አገዛዝን፣ አምባገነናዊ ሥርዓትን፣ አልያም ጥቂቶችን ብቻ በመጥቀም በርካቶችን የሚያገል አድሏዊ ሥርዓትን ለመቀበል ትዕግሥቱም ጫንቃውም የላትም፡፡ እነዚህን ሁሉ ከበቂው በላይ አስተናግዳለች፡፡ ካለፈው ጊዜ አካሔድ ሙሉ በሙሉ በመቀየር እንደ ለጋስነት፣ መቻቻልና ባልንጀራን መውደድ፣ ብሎም እንደ አድዋ ድል ባሉ ታሪኮቻችን እንደታየው ሁሉ ለጋራ ዕጣ ፈንታ መታገል ከመሳሰሉ ዕሴቶቻችን የተቀዳ አዲስ ሥርዓት መገንባት መጀመር በእጅጉ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ አገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትን የተራበች ሲሆን፣ ዴሞክራሲም ይገባታል፡፡ ለዚህ ሁሉ፣ ፖለቲካውን ማቃናት ያስፈልገናል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከአሁኑ የተሻለ ምቹ ጊዜ መቼውንም አይኖርም፡፡

መነሻ የሚሆነው ከሕገ መንግሥቱ የሚመነጩ ብሔራዊ ጥያቄዎችን ለመፍታት በጋራ መቀመጥ ሲሆን፣ ይህም ግብ ባለው የልሒቃን ድርድር መከናወን አለበት፡፡ ወረርሽኙንና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በሚደረጉ ጥረቶች ተቃዋሚዎችን በማሳተፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳዩት ጅምር አበረታች ነው፡፡ ይህ መደበኛ ሆኖ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ብቻ ከመሆን ባለፈ ጥቅም ላይ መዋል አለበት፡፡ ጊዜውን በመዋጀት ድፍረት አሰባስቦ ከባድ ጉዳዮችን ማንሳትና መፍትሔ ለማበጀት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን፣ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ለብቻቸው ያለሌሎቹ ተሳትፎና ትብብር ውስብስብ የሆኑ ችግሮቻችንን ለመፍታት ይቅርና ይህንን ሽግግር እውን ለማድረግ እንኳን እንደማይቻላቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡

Follow us on Twitter @EthiopiaInsight and join our Telegram channel here

Editor: William Davison

Query or correction? Email us

Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished. 

We need your support to analyze news from across Ethiopia

Please help fund Ethiopia Insight’s coverage

Become a patron at Patreon!

About the author

Zola Moges

Zola has a Ph.D. in international law and works in the fields of human rights, conflict analysis, and peacebuilding in post-conflict societies. Contact him at zelju2000@gmail.com

2 Comments

Leave a Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.