Elections 2021 Ethiopian language In-depth

ማግለልና እንግልት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ

ብልሹ አስተዳደር የክልሉ ሕገ መንግስት ነባር ናቸው በሚላቸውና በሀገር ደረጃ በታሪክ የበላይነት ነበራቸው ተብለው በሚታሰቡ ወገኖች መካከል ግጭት እንዲፋፋም አድርጓል፡፡

በሚያዝያ 11፣ 2011 በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን ባለችው ዳንጉር ወረዳ በአንድ የታክሲ ሹፌርና በተሳፋሪ መካከል በአስር ብር የታሪፍ ጭማሪ ምክንያትነት የተነሳ ጠብ ለመፍታት አንድ የፌዴራል ፖሊስ ተጠርቶ ነበር፡፡

በጉዞ ክፍያ አለመስማማት በተፈጠረው እሰጥ አገባ ፖሊሱ ተሳፋሪውን ተኩሶ ገድሎታል፡፡

የዳንጉር ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ጉሞዞች ደግሞ አጸፋ ለመመለስ በአዪቺካ ቀበሌ የሚኖሩ አራት የአማራ ብሔር ተወላጆችን ገድለዋል፡፡

ይህን ተከትሎ የአካባቢው የአማራ ተወላጆች በዞኑ በሚገኙ ከተሞች እና ከመተከል ውጪ ባሉ አጎራባች አካባቢዎች ላይ ተመሳሳይ የኃይል እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡

በሚያዚያ 30 የአማራ ክልል ልዩ ሀይሎች በአማራ ክልል በጃዊ ወረዳ ባሉ ሁለት ቀበሌዎች የሚኖሩ የጉሙዝ ብሔር ተወላጆችን የጨፈጨፉ ሲሆን ከዚያም በሰኔ 24 ከድንበሩ በወዲያ ባለው ዳንጉር ወረዳ በሚገኘው ዲልባንጂ ቀበሌ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ ፈጽመዋል፡፡

በዛው ሰሞን በዱንጉር ማንቡክ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ወጣቶች በጉሙዝ ነዋሪዎች ላይ ጅምላዊ ግድያ ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል፡፡

ብዙዎች የፓርላማ አባልና በማሕበራዊ ሚዲያ መልዕክቶችን በመለጠፍ የሚታወቀውን አቶ ጋዎ ጃኒያን ለተከሰተው ችግር ተጠያቂ አደረጉ፡፡ ይህን ተከትሎ ልጁ ላይ በአድመኞች ጥቃት የተፈጸመበት ሲሆን ወደ ሆስፒታል በመወሰድ ላይ ሳለ ህይወቱ አልፏል፡፡

በአማራ እና በተመሳሳይ የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ በበቁት በአገው ተወላጆች መካከል የጋራ ጥምረት ተመሰረተ፡፡ የሽናሻ ሕዝብ ምንም እንኳ በግጭቱ ከየትኛውም ወገን ጎን ያልተሰለፈ ቢሆንም የግድያ እና መፈናቀል ሰለባ ሆኗል፡፡

የዳንጉር ነዋሪዎች ዛሬ ላይ መለስ ብለው በ2011 የሆኑትን እኒህን ክስተቶች ሲያስታውሱ፣ ብዙዎቹ ከሁለት አመት በኋላ እንኳ የጥቃቱ ፈጻሚዎች ለፍርድ አለመቅረባቸው እና አንዳንዶቹ ጭራሹኑ በወንጀል ያለመጠየቅ መብት እስከማረጋገጥ መብቃታቸው እንዳሳዘናቸው ያወሳሉ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ባለፈው ሁለት አመት ከመንፈቅ በተከሰቱ ግጭቶች በሚያሳዝን ሁኔታ መቶዎች፣ ብሎም ሺዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ታሪኩ እጅግ አሳዛኝና ውስብስብ ነው፡- በብሔር የተቃኘና በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ  ግጭት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ መፈናቀል፣ መገለል የሚያስከትላቸው ስነ-ልቦናዊ ተጽእኖዎች፣ ብልሹ አስተዳደር፣ ደካማ የኢንቨስትመንት አተገባበርና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ታሪክ ላይ ለሚታየው የተቃረነ ትርክት የዘመናችን ትውልድ የሚሰጠው (የተዛባ) ምላሽ ይንጸባረቅበታል፡፡

ታሪኩ የትኛውንም በክልሉ የሚገኝ ወረዳ ማዕከል ሊያደርግ ይችላል፤ መነሻውን በየትኛውም ዘመን ላይ ሊያደርግና በክልሉ ካሉት በርካታ ብሔረሰቦች መካከል የአንዳቸውን እይታ መነሻ በማድረግ ሊተረክም ይችላል፡፡

ሁኔታው ኢትዮጵያ በወቅቱ የገጠሟት በርካታ ተግዳሮቶች ተንጸባርቀውበታል፡፡ ከነዚህ መካከል ውህዳዊ የሆነ አገራዊ እይታ ዳግም ማንሰራራት፣ ብሄረተኝነት የግጭት መንስኤ ወደመሆን ማደግ፣ በኑሮ ደረጃ አለመመጣጠን የሚያስከትለው የኢኮኖሚና የገቢ ምንጮች መመናመን፣ በሚፈጠረው ድክመት ለመጠቀም የሚሹ ጎረቤት አገሮችን ጨምሮ ኃያላን የፖለቲካ ተዋናዮች የፈጠሩት ስጋት፣ እኒህ ሁሉ እርስ በርሳቸው ተጠላልፈው የከፋ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥረው ይታያሉ፡፡

ሁኔታውን የበለጠ አስከፊ የሚያደርገው፣ እነዚህ ተግዳሮቶች በኢትዮጵያ ከመሀሉ ክፍል ርቀው ከሚገኙትና ዝቅተኛ ትኩረት ከሚሰጣቸው የዳር አገር ክልሎች ዋነኛ ተጠቃሽ በሆነው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸው ነው፤ ይህን ተከትሎም በአመዛኙ ሳይዘገቡ የሚያልፉ እጅግ አሰቃቂ መከራዎች  የሚደርሱበት ስፍራ ሊሆን በቅቷል ፡፡

ኢትዮጵያውያን፣ በተለይ ደግሞ በስልጣን ላይ ያሉቱ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እየደረሰ ላለው ስቃይ ምላሽ ለመስጠት ብሎም እዚህ የደረሰው ውድመት በተቀረው የአገሪቱ ክፍል እንዳይከሰት ለማድረግ ቁርጠኛ ሰላም የማስፈን እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለው ሊደመድሙ ይችላሉ፡፡

በገዛ ቤት ባይተዋርነት

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በክልላዊ ህገ መንግስቱ ላይ እንደተቀመጠው በውስጡ አምስት ነባር ብሔረሰቦችን አካቶ ይዟል፡፡ በርታ (ቤኒሻንጉል ተብለውም ይጠራሉ) እና ጉሙዝ ሕዝቦች በጋራ ከሞላ ጎደል ከክልሉ የሕዝብ ብዛት ግማሽ ያህሉን ይይዛሉ፡፡

ሌሎቹ ሶስቱ ነባር ብሔረሰቦች ሽናሻ፣ ኮሞና ማኦ ናቸው፡፡ የፌደራል አወቃቀር ከመምጣቱ አስቀድሞ ቀጠናው አማራ ብሔር አብላጫውን ቁጥር በያዘበት በጎጃም ክፍለ ሐገር ስር ይተዳደር የነበረ ሲሆን፣ በስተ ደቡብ ያለው የክልሉ ክፍል ደግሞ ኦሮሞ ብሔር የሚበዛበት የወለጋ ክፍለ ሐገር አስተዳደር አካል ነበር፡፡

በክልሉ የሚስተዋለው ቁልፉና ሁሉን አቀፉ ችግር ራሳቸውን በታሪክ የመገለል ሰለባዎች እንደነበሩ አድርገው የሚመለከቱት ጉሙዝና በርታዎች በአንድ ወገን፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ ኢፍትሐዊ አካሄዶችን ለማረም በሚል የተተገበሩት እርምጃዎች ራሳቸው አድሎአዊ ናቸው ብሎ የሚያምንና የአማራ ተወላጆች በብዛት የሚገኙበት ወገን ደግሞ በሌላኛው በኩል በመሆን እያካሄዱት ያሉት የፖለቲካ ትግል ነው፡፡

የአማራ ብሔረተኞች ህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት) በእቅድ ጸረ አማራ አድርጎ የቀረጸው እንደሆነ የሚያስቡትን የብሔር ፌደራሊዝም ስርአት ለአስርት አመታት ሲታገሉ ከቆዩ በኋላ በቅርብ አመታት የበላይነቱን የያዙ ሲሆን የጉሙዝ ሚሊሻዎችም ይህን በመቃወም የሐይልና አብዛኛውን ጊዜም ጅምላዊ የሆነ የአጸፋ እርምጃ እየወሰዱ ነው፡፡

ይህ ደግሞ የአማራ ተጽእኖ ፈጣሪነትን ይበልጡን ያነሳሳ ሲሆን ይህን ተከትሎም የተሳለጠና የማያቋርጥ የግጭት አዙሪት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

‹‹ነባር›› ሕዝቦቹ በተናጠል ይሁን በሕብረት በአገሪቱ ብሔራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተጽእኖ በእጅጉ አናሳ ነው፡፡ በየጊዜው የሚያካሂዱት ፍልሰት ከቀያቸው ያልራቀ ሲሆን በፌዴራል መንግስቱ ዘንድ ያላቸው ውክልናም የለም ሊባል የሚችል አይነት ነው፡፡ ባጭሩ የተጽእኖ ቀጠናቸው ከሞላ ጎደል በሚኖሩባቸውና ለዘመናት ህልውናቸውን አስጠብቀው በቆዩባቸው አካባቢዎች ላይ ብቻ የተገደበ ነው፡፡

አብረዋቸው ደግሞ ከፍ ያለ የሕዝብ ብዛት ያላቸው የአማራና ኦሮሞ ተወላጆች የሚኖሩ ሲሆን የሁለቱ ብሔሮች ነዋሪዎች ድምር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካሉት ነባር ማሕበረሰቦች የሕዝብ ብዛት ጋር ከሞላ ጎደል ይመጣጠናል፡፡ እኒህ ሁለት ብሔሮች በሚኖሩባቸው ክልሎች ሁሉ ኃያላን ናቸው፤ ይህም በአገሪቱ መንግስት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ከመካከላቸው የተወሰኑት ለክፍለ ዘመናት በቦታው ኖረዋል፡፡ የተወሰኑት በደርግ መንግስት ዘመን በኢትዮጵያ በተደረገው የሰፈራ ፕሮግራም ወቅት የመጡ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ መሬትና ሕዝብ በብዛት ያልሰፈረበት አካባቢ ፍለጋ በስደተኝነት በቅርቡ የመጡ ናቸው፡፡

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ ነባርና ነባር ያልሆኑ ተብለው በሚጠሩት ማሕበረሰቦች መካከል ያለው ግንኙነት የተወሳሰበ ከሆነ ረጅም ዘመን አስቆጥሯል፡፡ ክልሉ በሕገ መንግስት ከመመስረቱ በፊት አንስቶ በመሬት በሀብት እና በሥልጣን ባለመብትነት ዙሪያ አለመስማማቶች በሰፊው ይንጸባረቁ ነበር፡፡ በ2019 (እ.አ.አ) መቋጫ  አካባቢ የብልጽግና ፓርቲ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ እኒህ አለመስማማቶች የለየላቸው ግጭቶች በመሆን ተገልጠዋል፡፡

መተከልና ካማሺ ዞኖች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግጭት ቀጠናዎች በመሆን ደም መፋሰስ በብዛት የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ሆነዋል፤ አሶሳ ዞንም ቢሆን መጠነኛ አለመረጋጋት ተስተውሎበታል፡፡ ከሁሉም የከፋው ግጭት የተቀሰቀሰው በታህሳስ ወር 2012 መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በምትገኝ በቁጂ በተባለች ትንሽ ቀበሌ ውስጥ ነበር፡፡ በግጭቱ ህጻናትና እርጉዞችን ጨምሮ 207 ዜጎች ተጨፍጭፈዋል፡፡ ከሰለባዎቹ አብዛኞቹ ሺናሻዎች እንደነበሩና ገዳዮቹም ጉሙዝ ሚሊሻዎች እንደሆኑ ተዘግቧል፡፡ በ2010 አጋማሽ ካማሺ ውስጥ በአብዛኛው በኦሮሞና ጉሙዝ ተወላጆች መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት የተቀሰቀሰ ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ አልፎ አልፎ ክስተቱ ቀጥሏል፡፡

ወደ ጳጉሜ 1 በተላለፈው ምርጫ ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ለመዘገብ አሶሳ ዞን ወደምትገኘው ባምባሲ ወረዳ ተጉዤ ነበር፤ በግንቦትና ሰኔም የግጭት መንስኤዎችን፣ የደረሰውን ጉዳት መጠን፣ በመጪው ምርጫ የሚኖረው ተጽእኖ እና ስልጣን የሚረከበው መንግስት ሊያጤናቸው የሚገቡ መፍትሔዎች ላይ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎችን አነጋግሬያለሁ፡፡

እኒህ አካባቢዎች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ካሉት ሌሎች ስፍራዎች በተለየ ግጭት በከፍተኛ ሁኔታ የሚስተዋልባቸው አይደሉም፤ ነገር ግን እዚህም ተመሳሳይ አለመስማማቶች በተለያዩ መንገዶች ራሳቸውን ሲገልጡ ይስተዋላል፤ ከነዚህም መካከል ሰዎች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው ከተሞች በማሕበረሰቦች መካከል የሚፈጠር ውጥረት፣ እንደባምባሲ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች አነስተኛ መጠን ያላቸው ግጭቶች፣ እንዲሁም በርቀት በሚገኙ እንደ መተከልና ካማሺ ባሉ አካባቢዎች እልቂቶች መከሰት የተወሰኑት ናቸው፡፡

ነባር ማሕበረሰቦች እና የመብት ጥያቄዎች

ኢትዮጵያ መንገዱን የሳተው የለውጥ ሂደት፣ በትግራይ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የደረሰባት ፖለቲካዊ መገለል፣ የኢኮኖሚ መሳሳብ ያሳደረው ጫና ከብዷት በምትንገዳገድበትና የብሔር ፖለቲካ ያስከተለው መጠነ ሰፊ ግጭት በተፋፋመበት በዚህ ወቅት በውስጧ ካሉት ክልሎች የቤኒሻንጉል ጉሙዝን ያህል ውጥረት የነገሰበትና በአግባቡ ያልተረዳነው ክልል የለም፡፡

አሁን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብለን የምንጠራው አካባቢ በይፋ የኢትዮጵያ አካል የሆነው አጼ ምኒልክ በወቅቱ ሱዳንን ታስተዳድር ከነበረችው ታላቋ ብሪታንያ ጋር ያደረጉት የ1902 ናይል ተኮር ስምምነት አካል በመሆን ነበር፡፡

በ1987ቱ ሕገ መንግስት ከተመሰረተ ወዲህ በክልሉ ማን ባለ መብት ነው የሚለው ጥያቄ ሲያወዛግብ ቆይቷል፡፡ በ1996 የጸደቀው ኋላ በ2002 የተሻሻለው የክልሉ ሕገ መንግስት ታዋቂ በሆነው የመግቢያ ክፍል እንዲህ ሲል ይጀምራል ‹‹እኛ የክልሉ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች …››

ነገር ግን ከሌሎች የክልል ሕገ መንግስቶች በተለየ መልኩ የቤኒሻንጉሉ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ምንም እንኳ በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች እውቅና ቢሰጣቸውም፣ የክልሉ ባለቤቶች ግን የበርታ፣ ጉሙዝ፣ ሺናሻ፣ ማኦና ኮሞ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው››፡፡ ሕገ መንግስቱ እኒህን አምስት ማሕበረሰቦች በክልሉ ‹‹ነባር›› እንደሆኑ ያስቀምጣል፡፡

አምስቱ ነባር ማሕበረሰቦች ብሔርን መሰረት ባደረጉ አካባቢያዊ አስተዳደሮችና በነባሮች በሚመራው የክልል መንግስት በሚመቻቹ ኢ-መደበኛ አካሄዶች አማካኝነት በዋነኝነት ጥቅማ ጥቅሞችን ያገኛሉ፡፡

የነባር ብሔረሰቦች ልሂቃን በቀያቸው ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን ይተገብራሉ፤ ይህም ነባር ካልሆኑ ማሕበረሰቦች ይህ ነው የሚባል ተቃውሞ በሌለበት በክልሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የበላይነትን በመውሰዳቸው ጭምር ይገለጻል፡፡ እኒህ ልሂቃን ነባር ያልሆኑ ሕዝቦች በአካባቢያቸው ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የበላይነቱን ለመውሰድ የሚያደርጉትን ጥረት ተቀባይነት እንዳያገኝ ይከላከላሉ፤ በተጨማሪም ነባር ያልሆኑ ሕዝቦች በአካባቢያቸው መኖራቸውና መስፈር መቀጠላቸው ስጋት እንደፈጠረባቸውም ያነሳሉ፡፡

በሌላ በኩል ነባር ያልሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ባገኙት ውክልና እንዲሁም ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን በማስጠበቁ ረገድ ባለው ሁኔታ ደስተኞች አለመሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በክልሉ መንግስት ተመጣጣኝ ውክልና መኖር አለበት የሚል ሀሳብ ያነሳሉ፤ በማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ቢያንስ ከነባር ብሔረሰቦች ጋር ተቀራራቢ በሆነ መልኩ መስተናገድ እንዳለባቸው ይጠይቃሉ፡፡ ብዙዎች በክልሉ ካሉ አካባቢዎች ጋር ያላቸውን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ቁርኝነት በማንሳት ነባሮች በክልሉ የተለየ መብት አላቸው የሚለውን ሐሳብ እንኳ ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡

የአማራዎች፣ ሺናሻዎች እና በክልሉ የሚገኙ ሌሎች ዜጎች ላይ እልቂት እንዲከሰት ካደረገ የአጸፋ ጥቃት ጋር እኒህ ቅሬታዎችም አብረው አሉ፡፡ ይህን ተከትሎም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርና ከሕዳር 2020 ወዲህ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የሆኑት ደመቀ መኮንን ጥቅምት ላይ ወደ ክልሉ ተጉዘው የአማራ ሲቪሎች የማሕበረሰብ መከላከያ ሀይል በመሆን እንዲሰለጥኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ምንም እንኳ በአማራ ሲቪሎች ላይ ግድያዎች መፈጸማቸው የአማራ ፖለቲከኞችን ማሳሰቡ ተገቢ ቢሆንም እንዲህ አይነት አካሄዶች ከግጭቶቹ በስተጀርባ ያሉትን ታሪካዊ ውጥረቶች ያባብሳሉ የሚለው ሙግት ሚዛን ይደፋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከቅርብ አመታት ወዲህ ትግራዊያን የነበራቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት በማጣታቸው የተለቀቁ ቦታዎችን በግብርና ላይ የተሰማሩ ተሰሚነት ያላቸው የአማራ ተወላጅ ኢንቨስተሮች ሊጠቀሙባቸው እንደሆነ ይታመናል፡፡ የሁለት ተቀናቃኝ የፖለቲካ እሳቤዎች የፍልሚያ ቀጠና ከመሆን በተጨማሪ በአንጻራዊነት ያልለማው የክልሉ መሬትም ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቷል፡፡

በፖለቲካው አውድ ሶስት አስርት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ በቆየው የብሔር ፌደራሊዝም አገዛዝ ስር የተቀናቃኞች እይታዎች የተለያየ መልክ ይዘዋል፡፡

በ2018 (እ.አ.አ) አዲሱ አስተዳደር ለረጅም ጊዜ የቆዩ የፖለቲካ ቅሬታዎች በነጻነት የሚደመጡበትን እድል እንደሚያመቻች ቃል በመግባት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያሉት መከፋፈሎች አፋጣኝ ትኩረት እሚያሻቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ የፖለቲካ መሪዎችና የክልሉ ነዋሪዎች አዲሱ ‹የተሀድሶ› መንግስት በማያዳግም ሁኔታ መፍትሔ ይሰጣቸዋል ብለው በማሰብ ረጅም እድሜ ያስቆጠሩትን ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በሽግግሩ መንግስት ዘመን በነበረው ቆይታ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ላለው ግጭት ተገቢ ምላሽ በመስጠቱ ረገድ ከሞላ ጎደል ስኬታማ አልነበረም፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ተገቢ ያልሆኑ መንገዶችን በመጠቀም ክርክሮችን እስከማፈን ደርሰው ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎች የዚህ መንስኤ የፓርቲው የመደመር ርዕዮት ትርጓሜ እንደሆነ ያስባሉ፡፡

ሰዎች ሁሉ ለጥንካሬና ለጋራ ጥቅም ሲሉ ሕብረት መፍጠር አለባቸው የሚለውን ሐሳብ የሚያቀነቅነው የአቢይ የመደመር ፍልስፍና አገረ-መንግስትን ሁሉ ወደ አንድ የሚቀልጥበት ማሰሮ  አድርጎ ያቀርባል፡፡ ሐሳቡ መልካም ቢሆንም  ውሁድነትን በሚያራምዱ የአብላጫ ሀይሎች ህልውናቸው አደጋ ውስጥ ገብቷል የሚል ስጋት በክልሉ ባሉ ኣናሳ ሕዝቦች ዘንድ ዳግም እንዲያንሰራራ አደርጎታል፡፡ በዚያኛው ወገን ያሉ ሕዝቦች የአንድነትን ጽንሰ ሐሳብ ለነሱ በሚመች መልኩ በማዞር የአንድ ብሔር የበላይነት የሚንጸባረቅበት አገዛዝን ለማስተጋባት እየተጠቀሙበት ያሉ ይመስላል፡፡

የብልጽግና አመራር መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት በአግባቡ ምላሽ ባለመስጠታቸው ስር የሰደዱ ቅራኔዎች በፈጠሩት ጫና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለቀውስ ተዳርጓል፤ ይህ ሁኔታ በተለይ በመተከል ዞን በግልጽ ይስተዋላል፡፡

የመተከሉ ማዕበል

መተከል ላለፉት አስር አመታት በግንባታ ላይ የሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚገኝበት ቀጠና ነው፡፡ እንደ ወርቅ፣ ለም መሬት እና ውሃ ያሉ ተፈጥሯዊ ሀብቶች በብዛት ይገኙበታል፡፡ ብዛት ያለው ሕዝብም ይኖርበታል፡፡  የተለያዩ ብሔረሰቦች ተቀላቅለው በመካከላቸው ከፍ ያለ ግጭት ሳይቀሰቀስና ጠንካራ በሆነ ማሕበራዊ፣ ሀይማኖታዊና የጋብቻ ትስስር ተጋምደው  ለበርካታ ክፍለ ዘመናት ለመኖር ችለዋል፡፡

ነዋሪነታቸው መተከል የሆኑ የአይን ምስክሮች እንደሚሉት ለመጀመሪያ ጊዜ ግጭት የተከሰተው በሚያዝያ 2019 (እ.አ.አ) ነው፡፡ በግጭቱ መጀመሪያ ወቅት ውጊያ ይደረግ የነበረው በጉሙዝና አማራ መካከል ነበር፡፡ ግጭቱ በገጠራማ አካባቢዎች በሚኖሩና በግብርና በሚተዳደሩ ማሕበረሰቦች መካከል ይከሰት የነበረ ሲሆን በሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ትልልቅ ከተሞች በአንጻራዊነት ሰላም የሰፈነባቸው ነበሩ፡፡ ግጭቶቹ ታቅደው የሚከወኑ አልነበሩም፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎችም በአመዛኙ ይጠቀሙ የነበረው እንደቀስትና ጩቤ ያሉ በቅርብ ርቀት ፍልሚያ ጊዜ የሚያገለግሉ መሳርያዎችን ነበር፡፡

ነባርና ነባር ባልሆኑ ሕዝቦች መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሄደው በመሬት ይገባኛል የተነሳው አለመግባባት በ2019 (እ.አ.አ) ከፍተኛ ውጥረት ያለበት ትእይንት እንዲከሰት አድርጓል፡፡ በግንቦት ወር ከኢትዮጵያ ኢንሳይት ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉ የነባር ብሔረሰብ ልሂቃን እያደገ ያለውን የአማራ ብሔረተኝነት ማእከል በማድረግ የሚቀርቡ እየከረሩ የመጡ ‹የመተከል ዞን የአማራ ታሪካዊ ግዛት አካል ነው› የሚሉ በአማራ ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸው – በተለይም በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ – የሚንጸባረቁ አቋሞች ዋነኛ የስጋታቸው ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በ2019 (እ.አ.አ) መጨረሻ አካባቢ የብልጽግና ፓርቲ መመስረቱን ተከትሎ በርካታ የሕብረ ብሔራዊ ሥርአቱ ደጋፊዎች ብልጽግናን የአሃዳዊነት ርዕዮት አራማጅ አድርገው ማቅረባቸው ለሁኔታው ሌላ ቁመና ጨምሮለታል፡፡

በአናሳዎች መብት መከበር ተገቢነት ዙሪያ በተዘጋጀ ወርክሾፕ ላይ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሀላፊ የሆኑት አቶ ብርሃኑ አየሁ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹የመተከል ግጭት መንስኤ ምን እንደሆነ የትኛውንም የጉሙዝ ብሔር ልሂቅ ወይም አላፊ አግዳሚ ብትጠይቁ የአማራ ልሂቃን መተከልን የታሪካዊ ግዛታቸው አካል እያሉ እንደሆነ ይነግሯችኋል፡፡ ወደ ግጭት የገቡበት ምክንያት ይሄ ቡድን እነሱን ከማፈናቀሉ በፊት ለቀያቸውን ዘብ ለመቆም ነው››፡፡

ኢትዮጵያ ኢንሳይት ባደረገው ቃለ መጠይቅ ወቅት አንድ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ደጋፊ ይህንን የብርሃኑን ገለጸ አጠናክሯል፡፡ እንደሱ አባባል በመተከል የአማራ የበላይነትን የሚያቀነቅን ርዕዮት በአብን መድረኮች በግልጽ ተንጸባርቋል፡፡ የአብን አመራር በታሪክ የጎጃም ግዛት አካል የነበረው ይህ ዞን ወደ አማራ ክልል እንዲጠቃለል ጥያቄ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡

መተከልና አንዳንድ የትግራይና ኦሮሚያ ግዛቶች ባለቤትነታቸው የአማራ መሆኑን በገለጹባቸው በክልሉ በተካሄዱ የተለያዩ ትዕይንተ ሕዝቦች ወቅት አንግበዋቸው በነበሩ ምልክቶችና መፈክሮች ይሄ አቋማቸው በግልጽ ይታይ ነበር፡፡

በ2018 (እ.አ.አ) በመተከል በጉምዝ ህዝቦች ላይ የአማራ ታጣቂዎች ፈጽመውታል በተባለ ጭፍጨፋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ በሌላኛው ወገንም እንዲሁ የአማራ ብሄር ተወላጅ ነዋሪዎች ለግድያና በጉልበት ለመፈናቀል መዳረጋቸውን ተከትሎ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንደተከናወነ ነዋሪዎቹ ይገልጹ ነበር፡፡

በሚያዚያ ወር ላይ በፖሊስ የተፈጸመው የጉሙዝ መንገደኛ ግድያ እና ይህን ተከትሎ የተፈጠረው ብጥብጥና ግጭት በ2019 (እ.አ.አ) ውጥረቱ ምን ያህል ተባብሶ እንደነበር አመላካች ነው፡፡ በተጨማሪም ክስተቱ ማናለብኝነት የተለመደ እውነታ በሆነበት ክልል የሕግና የተጠያቂነት ጥግ እስከምን ድረስ እንደሆነ ያሳየ ነበር፡፡

የውሃ አገልግሎት ሰራተኛ የሆነ የሽናሻ ብሔር ተወላጅ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት በሰጠው ቃል በብሔሩ ምክንያት ሰኔ 17፣ 2019 (እ.አ.አ) ላይ የአገው ወጣቶች ቡድን ጥቃት አድርሰውበት እንደነበር ተናግሯል፡፡ ጥቃት ፈጻሚዎቹ እሱን በሚደበድቡበት ወቅር እየፎከሩና እየሸለሉ እንደነበርም ገልጿል፡፡ ሆስፒታል ሄዶ በርካታ ቦታዎች ላይ ለደረሰበት የአጥንት ስብራትና የጥርሶች መውለቅ የሕክምና እርዳታ እያገኘ በነበረበት ወቅትም ቤቱ ሊዘረፍ ችሏል፡፡

‹‹በሕይወት በመትረፌ ፈጣሪን አመሰግናለሁ፤ ነገር ግን በዞኑ ለሚመለከተው አካል የደረሰብኝን ሪፖርት ባደርግም አንድም ግለሰብ በሕግ ፊት አለመቅረቡ እጅግ አሳዛኝ ነው›› በማለት አክሏል፡፡

እየተባባሰ የመጣው ግጭት

የግጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መባባስ ፍትህ የመስፈን እድሉ የመነመነ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ አለመረጋጋት በመተከል በሰፊው የተዳረሰ ሲሆን አንዳችም የመቆም ምልክት እያሳየ አይደለም፡፡ ነሐሴ 2020 አካባቢ ግጭቱ ተፋፍሞ ይበልጥ የተደራጀ ደም መፋሰስ እና ሰፊ ቀጠና መሸፈን ወደሚስተዋልበት አዲስ ምእራፍ ሊሸጋገር በቃ፡፡

አንድ ማንነቱ እንዲገለጽ ያልፈለገ በዳንጉር ወረዳ የሚኖር የፖሊስ አባል ሚያዝያ 25 ዕለት ለኢትዮጵያ ኢንሳይት በሰጠው ቃለ ምልልስ በቀጠናው የተፈጸመው አሳዛኝ ክስተት መቋጫ እንደሌለው አመላክቷል፡፡ በሁሉም የመተከል ወረዳ ሁኔታው ተለውጧል፡፡ ግጭቱ በፊት ባልተደራጁና በቅርብ ርቀት ጥቅም ላይ የሚውሉ መሳርያዎችን በሚጠቀሙ የሲቪል ቡድኖች ይፈጸም የነበረ ሲሆን አሁን ግን በተለይ በጉሙዞች ወገን በተደራጀ፣ ከፍተኛ አቅም ባለውና ከሱዳን ጋር ድንበር የሚሻገር ትስስር በፈጠረ አማጺ ሚሊሻ የሚከናወን ሆኗል፡፡

በመተከል ያለው የጉሙዝ አማጺ ቡድን መሪ እንደሆነ የሚነገርለት ሻቫ የተባለው ግለሰብ ስለሱ ያለው መረጃ አነስተኛ ቢሆንም የጉባ ወረዳ ተወላጅ እንደሆነ ግን ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እጅ የገባ ሰነድ እንደሚያመለክተው የጉሙዝ አማጽያን የጋንታ መሪዎች አላቸው፤ ሰነዱ እስከ መቶ የሚደርሱ አባላትን እንዲመሩ የተሾሙ ሰዎችን ስም ዝርዝር የያዘ ሲሆን መሪዎቹ በተመደቡባቸው ወረዳዎች ያሉ አማጽያንን የማደራጀት ሀላፊነትም ተሰጥቷቸዋል፡፡

በ2019 (እ.አ.አ) ጥቃቱ አነጣጥሮ የነበረው በአማራ ህዝብ ላይ ሲሆን በአመዛኙ የመከላከል ባሕርይ ነበረው፤ አሁን ግን የተደራጁ የጉሙዝ ሚሊሻዎች ‹ቀይ› በመባል በሚታወቁና ቀላ ያለ ቆዳ ባላቸው የመተከል ነዋሪዎች ሁሉ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየሰነዘሩ ነው፡፡

ይህን ተከትሎም ነባር የሆኑ የሽናሻ ማህበረሰቦች በግላጭ ዳግም ለአስከፊ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡ አንዳንድ ስፍራዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት የጅምላዊ ባሕርይ አለው፡፡

በመተከል ባሉ ወረዳዎች የሚሰሩ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ኢንሳይት እንደገለጹት የአማጽያን ቡድኖች ጥቂት ጉሞዞች ብቻ የሚኖሩበትን የፓዊ ወረዳን ጨምሮ በዞኑ ባሉ ወረዳዎች ሁሉ ሰርገው በመግባት ጥቃት ፈጽመዋል፡፡ የክልሉ ብልጽግና መር መንግስት ሊያስተዳድራቸው ያልቻላቸውን የመተከል ገጠራማ አካባቢዎችንም በቁጥጥራቸው ስር ለማስገባት ችለዋል፡፡

አሁን ላይ የአማጽያኑ ሚሊሻዎች በከተሞች የሚኖር ሕዝብን በማፈናቀል ተግባር ላይ የተሰማሩ ሲሆን ይህም ከፍ ያለ ችግር አስከትሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአማራ ክልል ጓንጓ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ጥቃት ለማድረስ ሞክረዋል፡፡

ከመተከል የተፈናቀሉ ሰዎች በ ጓንጓ ወረዳ፥ ታህሳስ 13፣ 2013፥ የጓንጓ ወረዳ ግንኙነት።

አማጽያኑ ጦርነት በሚያካሂዱበት ወቅት ያልተነገረለት መከራ መተከል በሚገኝ የጉሙዝ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ነው፡፡

ሀሰን እንዲራስ የተባለ በጉባ ወረዳ በግብርና ተሰማርቶ የነበረ ኋላ ግን በግጭቱ ምክንያት አካባቢውን ለመልቀቅ የተገደደ አንድ ኢንቨስተር ለኢትዮጵያ ኢንሳይት እንደገለጸው ንጹሁ የጉሙዝ ሕዝብ በሁለት ወገን ማለትም በአንድ ወገን አማጽያኑ፣ በሌላኛ ወገን በደረሰባቸው ጥቃት በቁጣ ከተነሳሱ ሌሎች ማሕበረሰቦች የሚደርስ ጥቃት ሰለባ ነው፡፡

አማጽያኑ የጉሙዝ ሲቪሎችን የሰው ጋሻ በማድረግ የሚጠቀሙባቸው ሲሆን ታጥቀው ወደ ጦርነቱ እንዲቀላቀሉም ያስገድዷቸዋል፡፡ ሰላም እንዲወርድ ጥሪ የሚያቀርቡ ወይም ጦርነቱን የሚቃወሙ የጉሙዝ ማሕበረሰብ አባላት ኑሯቸው የሚፈርስበት፣ ንብረታቸው የሚዘረፍበትና የሚገደሉበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡

ሀሰን ለግጭቱ መፍትሔ ለመፈለግ ወደ አማጽያኑ የሄዱ የአገር ሽማግሌዎች የደረሰባቸውን አካፍሎናል፡፡ አንተነህ ሻዊን ጨምሮ የመሪነት ሚና የነበራቸው የአገር ሽማግሌዎች ተገድለዋል፤ አንተነህ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ ባቀረበበት በዚያው ቀን ነበር በጥይት ተመትቶ የተገደለው፡፡

የጉሙዝ ወጣቶችም ቤተሰቦቻቸው ሳይፈቅዱ በአማጸያኑ እየታገቱ የአጭር ጊዜ ስልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ መረጃ ለመንግስት የሚያቀብሉ እንዲሁም ልጆቻቸው የአማጽያኑን ሀይል እንዲቀላቀሉ ፈቃደኛ ያልሆኑ የአካባቢው መሪዎችና ሲቪሎች ተገድለዋል፡፡

በተመሳሳይ ጊዜ የጉሙዝ ሲቪሎች የአማጽያኑን እንቅስቃሴ ለመግታት የአማራ ብሔር ተወላጆችና ቀይ ቆዳ ያላቸው ሌሎች ሰለባዎችን በማካተት በቡድን ተደራጅተው በሚንቀሳቀሱ ሀይሎች የከፋ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡

በዳንጉር ወረዳ አዪ ፓፑዋ፣ ጊጺ፣ ኪተልዬ እና አዲስ ሰፈር አጠገብ የሚኖሩ የጉሙዝ ነዋሪዎች ቤትና ንብረታቸው ሙሉ ለሙሉ እንደቃጠለ የአይን እማኞች ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ገልጸዋል፡፡ እነሱም ህይወታቸውን ለማዳን ቀያቸውን ጥለው ወደ ጫካዎች ለመሸሽና ከባድ ዝናብና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመጋፈጥ ተገደዋል፡፡

በአብዛኛው ጉሙዞች የሚኖሩባቸው ሰፋፊ አካባቢዎች እስካሁን መንግስታዊ አገልግሎቶች እያገኙ አይደለም፤ ተፈናቃዮችም ከመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች አንድም ድጋፍ አላገኙም፡፡ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ከተሞች የሚመጡ አንዳንድ የጉሙዝ ተወላጆችም ለጅምላ ጥቃትና ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡

ለምሳሌ ሚያዚያ 4 ላይ አንድ የጉሙዝ ተወላጅ የባንክ አገልግሎት ለማግኘት የአማራ ክልል ድንበር ተሻግሮ ቻግኒ ከተማ በመጣበት ወቅት በመንግስት ሀላፊዎች ፊት ተቀጥቅጦ ተገድሏል፡፡

ከፍርሀት የተነሳ በርካታ የጉሙዝ ተወላጆች በህመም ተይዘውና አስቸኳይ እርዳታ እያስፈለጋቸው እንኳ በጫካዎች ይሸሸጋሉ፡፡

ክፉ ጎረቤቶች

አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ የጉሙዝ አማጽያን ከአካባቢው አመራር የመከላከያን እንቅስቃሴ ጨምሮ የሎጂስቲክና የመረጃ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች የክልሉ ፖሊስና ልዩ ሀይል አባላት እንደታገቱና መሳሪያቸውንም በሀይል እንደቀሟቸው በመግለጽ አማጽያኑን እንደተቀላቀሉና መሳሪያቸውንም ለነሱ እንዳስረከቡ ይነገራል፡፡

ኢትዮጵያ ኢንሳይት ያነጋገራቸው አንድ አስተያየት ሰጪ እንደገለጹት መጀመሪያ ላይ በአማራና በጉሙዝ ሕዝቦች መካከል የተከሰተውን የመሬት አለመግባባት እንደ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀሙ በፈለጉ የህወሐት አባላት የአመራር ድጋፍ ለአማጽያኑ ይሰጥ ነበር፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት ህወሐት በተለይ ከሱዳን እና ግብጽ ጋር ቁርኝት ያላቸው አማጽያንን ፈጥሯል፡፡

አማጽያኑ ከህወሐት ጋር አላቸው የተባለው ግንኙነት መላ ምታዊ ቢሆንም ከሱዳን ጋር ያላቸው ቁርኝት ግን በገሀድ የሚታይ ነው፡፡ ከባድ ፍልሚያ በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች የጉሙዝ ሚሊሻዎች በሱዳን ድንበር በኩል ወደ አገሪቱ ሲገቡ ታይተዋል፡፡ አማጽያኑ ከሱዳን ስልጠና፣ የቴክኒክ እርዳታና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኙ የአይን እማኞች ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ገልጸዋል፡፡

ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ከባድ መሳርያ የውጪ ሀይል ጣልቃ ገብነት እንዳለ መጠነኛ ማስረጃ በመሆን ያገለግላል፡፡ አማጽያኑ ትልልቅ መኪኖችን ማውደም የሚችሉ በሮኬት የሚወነጨፉ ፈንጂዎች (አር ፒ ጂ) እና መሰል ከባድ መሳርያዎች ይዘው ታይተዋል፡፡

የላቀ የጦርነት ታክቲኮችን በመተግበር በሚያደርጉት የማጥቃት እርምጃ በቂ ትጥቅ የሌላቸውን የመከላከያ ሀይላት እንዲያፈገፍጉ አድርገዋል፡፡ አንጻራዊ በሆነ ሁኔታ ድሃና ኋላ ቀር በሆነ ክልል በሚደረገው አማጺያን መር ግጭት እየተተገበረ ያለው የረቀቀ ስትራቴጂና እየደረሰ ያለው የውድመት ደረጃ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

አወዛጋቢው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሊት ከመከናወኑ በፊት የውጪ ሀይላት ግጭቱ ውስጥ ተሳትፈው ሊሆን ይችላል የሚለው እሳቤ የኢትዮጵያ መንግስት ሊቆጣጠረው ያልቻለው ድንበር ተሸጋሪ ጦርነት እንደሚቀሰቀስ አመላካች ሆኗል፡፡

በጉሙዝ አማጽያን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው አንድ ቁልፍ ስትራቴጂ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተሸከርካሪዎች በዋናው መንገድ ወደ ግድቡ ቀጠና እንዳይሄዱ ማገድ ነው፡፡

የግንባታ እቃዎች ወደ ግድቡ ቀጠና የሚጓጓዙት ከወታደራዊ አጃቢዎች ጋር እንደሆነ መተከል ያሉ የፖሊስ መኮንኖች ለኢትዮጵያ ኢንሳይት አረጋግጠዋል፡፡ አማጽያኑ በሹፌሮቹና መከላከያ ሰራዊት ላይ ተኩስ በመክፈት እንዲሁም መንገዱን በመዝጋት ቁሳቆሶች ወደ ግድቡ እንዳይጓጓዙ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡

ለምሳሌ ሚያዚያ 17 ከግድቡ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ማንጎ መንደር አካባቢ ለህዳሴ ግድቡ ቁሳቁሶች እያጓጓዘ በነበረ ኮንቮይ ላይ በደረሰ ጥቃት አስር ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ከአራት ቀናት በኋላ በጉባና በሕዳሴ ግድብ መካከል ባለው ኦሪሼድ ቀበሌ አማጽያኑ 18 ሲቪሎችን እና ስድስት የልዩ ፖሊስ አባላትን ገድለዋል፡፡

ቃለ መጠይቅ ሰጪዎቹ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት እንደገለጹት ምንም እንኳን በግጭት ቀጠናዎቹ የኮማንድ ፖስት የተቋቋመና በከፍተኛ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ የተጎበኙ ቢሆንም በመተከል በቅርቡ ሰላም የሚሰፍንበት ሁኔታ የመነመነ ነው፡፡ የመንግስት ሰራዊት በአማጽያኑ ላይ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ ፍቃደኛ አይደለም፡፡ ለዚህ በከፊልም ቢሆን ምክንያቱ አማጽያኑ ሲቪሎችን እንደከለላ በመጠቀም ኋላ ላይ የጉሙዝ ሕዝብ ሲገደል ‹‹ብሔር ተኮር ዘር ማጥፋት›› ፈጽመዋል  ስለሚሉ ሲቪሎችን በመግደል ተጠያቂ መሆን ካለመፈለግ የመነጨ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ውጤታማ የአጸፋ እርምጃ ባለመወሰዱ ቅሬታ ያደረባቸውና ይህን ተከትሎ የአገር መከላከያን ጥለው የወጡ አንዳንድ የሰራዊቱ አባላት አሉ፡፡ ይህን ተከትሎ ሲቪሎች ራሳቸውን እንዲከላከሉ ተትተዋል፡፡

አማጽያኑ በመተከል ዞን በስድስት ወረዳዎች (ጉባ፣ ዳንጉር፣ ማንዱራ፣ ድባጤ፣ ቡለን እና ወንበራ) ያሉ የመንግስት ጽሕፈት ቤቶችን በተሳካ ሁኔታ ከተቆጣጠሩ በኋላ ከመንግስት ጋር በተደረገ ድርድር የተሳተፉ የአማጽያኑ ተወካዮች በዞኑ ከጉሙዝ ሚሊሻ ጋር አስተዳደራዊ የስልጣን ክፍፍል እንንደረግና ለሚሊሻ አባላቱ መሬት እንዲሁም ስራና የገንዘብ ድጋፍ እንዲሰጥ የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበው ነበር፡፡

እኒህ የተዘረዘሩ ግቦች በአማጽያኑ ዘንድ የተራዘመ ጦርነት ለማካሄድ ፍቃደኝነት መኖሩን ያመለክታሉ፡፡

በርግጥም ድርድሮቹ እንደተጠናቀቁ የጉሙዝ አማጽያን በዳንጉር ወረዳ የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት አስታባባሪ የሆኑትን ሌተናንት ጀነራል አስራት ደኔሮን ይዘው ወስደዋል፡፡ ሌተናንት ጀነራሉ ሰላም ለማምጣት ያደርገው በነበረው ጥረት ታዋቂ የነበረ ሲሆን እንደውም በርካቶች ለአማጽያኑ ከተገቢው በላይ አዘኔታ ያሳያል በማለት ይወቅሱታል፡፡

የሽምቅ ውጊያው ወደ ካማሺ ዞን እና ሌሎች እንደሰዳል፣ አጋሎ ሜጢ እና ያሶ ወረዳዎች ያሉ ጉሞዞች ወደሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሊዛመት ችሏል፡፡

ግጭቱ በክልሉ ዋና ከተማ በአሶሳ ሳይቀር እየተካሄደ ነው፤ ነገር ግን እስካሁን እምብዛም የደም አፋሳሽነት ጠባይ አልተስተዋለበትም፡፡

የሚቃረኑ ፍላጎቶች

በአሶሳ ዞን በሥልጣን፣ መሬትና ሀብታት ዙሪያ ብርቱ የመገፋፋትና መሳሳብ ሽኩቻ ውስጥ የገቡት በዋነኝነት ነባሮቹ በርታዎች እንዲሁም የአማራና ኦሮሞ ሰፋሪዎች ናቸው፡፡

ከሰባቱ የአሶሳ ወረዳዎች ከሱዳን ጋር በሚዋሰኑት በአራቱ ማለትም ሆሞሻ፣ መንጌ፣ ሸርቆሌና ኩሙርክ ከፍተኛ ውጥረት አለ፡፡ እኒህ አካባቢዎች ለምና በማዕድን የበለጸጉ ናቸው፤ እናም በነባሮችና ነባር ባልሆኑት ነዋሪዎች መካከል በመሬት ባለቤትነትና በሀብታት የተነሱ አለመስማማቶች በቅርቡ ወደ ጽኑ ደም መፋሰስ የማምራት ስጋት ተደቅኗል፡፡

ባምባሲ ላይ የግጭቱን ጎርፍ ያቀቡት በሮች ተከፍተዋል፡፡

እንደሌላው የክልሉ አካባቢ ሁሉ በበርታዎች የሚመሩ በአሶሳ ያሉ የነባር ብሄረሰቦች ልሂቃንም በአማራና ኦሮሞ ሰፋሪዎች እንዲሁም እንደሚባለው በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጭምር እየተከናወነ ባለው የመሬት ተስፋፊነት ዙሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ የመጣውን ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ ተጽእኖ ባላቸው በአማራና ኦሮሞ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት እንዳይወሰድባቸው ይፈራሉ፤ በተጨማሪም እኒህ ነባር ያልሆኑ ማሕበረሰቦች የራሳቸውን ሰፋፊ የክልል መንግስታት ይዘው ሲያበቁ ወደ ሌሎች ግዛት የሚያደርጉት መስፋፋት ተገቢነት ዙሪያ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡

ስጋታቸው ከሕልውና ስጋት ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በሰኔ ወር የአሶሳ ከተማ መሪዎች እንደገለጹልን ከሆነ የባሕል መክሰም አደጋ ተደቅኗል፡፡ አንድ የብልጽግና ፓርቲ አመራር ነባሩ ሕዝብ በተለይ ደግሞ በርታዎች ይበልጥ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ቡድኖች በሚያሳድሩት ጫና የህልውናቸውን መሰረት በቅርብ አመታት ውስጥ የማጣት አደጋ እንደገጠማቸው በሰኔ 8 2021 ለኢትዮጵያ ኢሳይት ግልጿል፡፡ የመሬትና የገንዘብ ዝርፊያ እየተካሄደ መሆኑን በማብራራት ይህም የፖለቲካ ስልጣኑን በአማራና ኦሮሞ እጅ እንዲገባ በማድረግ በክልሉ ያሉ ዝቅተኛ ስልጣን ያላቸውን ቡድኖች ማንበርከክና መጨቆን እንደሚያስችላቸው ይናገራል፡፡

ይህ ፖለቲከኛ እንዲህ ሚዛኑን የሳተ አገዛዝ ሊያስከትለው የሚችለውን ጦስ በቁጭት ሆኖ ገልጿል፡፡ በርታዎች እንደሌሎች በክልሉ የሚገኙ ነባር ማሕበረሰቦች ሁሉ ተጽእኗቸው በቀያቸው ባለ መሬትና ማሕበረሰብ ላይ ብቻ የተገደበ መሆኑንና በሌሎች አካባቢዎች ምንም ተጽእኖ እንደማይፈጥሩ ያስረዳል፡፡ እዚህም ያላቸውን መብት ካጡ ይፋዊ መገለል ቅቡል ወደ ነበረበት የታሪክ ዘመን የመመለስ እጣ ይገጥማቸዋል፡፡

በሌላ በኩል በአሶሳ ያሉ ነባር ያልሆኑ ሕዝቦች በተለይም ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ የአማራ ተወላጆች እንደተገለሉና እንደሁለተኛ ዜጋ እንደሚታዩ ያስባሉ፡፡ ብዙዎች አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ደስተኞች አይደሉም፤ ምንም እንኳ በተገቢው መልኩ ኑሯቸውን የሚመሩና የሚጠበቅባቸውን ክፍያ ሁሉ በወቅቱ የሚከፍሉ ቢሆንም ስርአቱ አናሳ ያልሆኑት ማሕበረሰቦች በሚኖሩባቸው ክልሎች ፍትሐዊ አስተዋጽኦ ከማበርከት እንዲገለሉ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ፡፡ የሆቴልና የምግብ ቤቶች ባለቤት የሆነ አንድ ማንነቱ እንዳይገለጽ የጠየቀ የአማራ ተወላጅ በሰኔ 4 ለኢትዮጵያ ኢንሳይት በሰጠው ቃለ መጠይቅ ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቋል፡፡

የአብን ደጋፊ መሆኑን በኩራት የሚገልጸው ይህ ግለሰብ የአማራ ተወላጆች የክልሉ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች እንደሆኑ በአጽንኦት ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ እንደሱ አባባል ዝቅተኛ ግብር የሚከፍሉት የአናሳ ብሔረሰብ ተወላጆች የተሻለ የመሬትና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማጥቅሞች ያገኛሉ፡፡ የአማራ ሕዝብ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በሚመራባቸው አካባቢዎች መሬት በኪራይ ለመጠቀም መገደዱ ቅሬታ ፈጥሮበታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የሆቴል ቤቱ ባለቤት ነባር ሕዝቦችን ከፍ ለማድረግ የሚሰጠው አወንታዊ እርምጃ (አፈርማቲቭ አክሽን) ብቃት ያላቸውን የአማራ ነዋሪዎች ከተጠቃሚነት የሚያስቀር አድሎአዊ አሰራር እንደሆነ ይሞግታል፡፡ በሲቪል ሰርቪስ ሴክተር ለነባር ሕዝቦች ቅድሚያ የመስጠት ሂደት የስራ መደቦች ልምድ ለሌላቸው ሰዎች እንዲሰጥና ይህም ከሚጠበቀው በታች እንዲሰሩ ያደርጋል፡፡

በአራት ወረዳዎች – ማለትም በሆሞሻ፣ መንጌ፣ ሸርቆሌ እና ኩርሙክ – መሬት ለበርታ ሕዝብ ተጠብቆ ይያዝላቸዋል፡፡ ሌሎች ግን በአጭር ጊዜ ክራይ መሬት የማግኘት እድል እንኳ ይነፈጋሉ፡፡

ለሰባት አመታት በሆሞሻ መሬት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ይሰራ የነበረ አንድ ባለሙያ ‹‹ከአካባቢው አመራር ጋር ልዩ ግንኙነት ካላቸው ወይም ገንዘብ (በጉቦ መልክ) ካልከፈሉ በቀር በርታ ላልሆኑ ሰዎች ለእርሻ፣ ለመኖሪያም ሆነ ለኢንቨስትመንት መሬት አይሰጥም›› በማለት ለኢትጵያ ኢንሳይት ገልጿል፡፡

በርታዎች በባሕል የበላይነት ባላቸው ሕዝቦች እንዳይዋጡ ለመከላከል የተደረገ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹ሰፋሪዎች ገፍተው ያስወጡናል … ይህ ታሪክ እዚህ እንዳይከሰት አዲስ መጤዎች በቋሚነት እንዳይኖሩ መግታት አለብን››፡፡

በአሶሳ ያሉ በርካቶች የነባሮችን መብት ለማስከበር የተቀመጡ መርሆዎች ተገቢ መሆናቸውን ቢስማሙም፣ ነዋሪዎች የግልጽነት አሰራር ባለመኖሩና የነባሮች መሬት ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ አካሄዶች ሲተገበሩ ህጋዊ ማዕቀፍ የሌላቸው መሆኑ እንዳሳሰባቸው ይናገራሉ፡፡

ለምሳሌ አንድ የመንጌ ወረዳ ነዋሪ የሆነ መምህር ሰኔ 12 ከኢትዮጵያ ኢንሳይት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የወረዳ አስተዳዳሪዎች የአካባቢው ማሕበረሰብ አባላት የሰሯቸውን ቤቶች ሲያፈርሱ እንዳየ ገልጿል፡፡ የአስተዳደር ሀላፊዎች በበኩላቸው ቤቶቹ በድብቅ ነባር ላልሆኑ ሰዎች የተሸጡ እንደሆኑና እንዲህ አይነት አሰራር ደግሞ መስተዳደሩ እንደሚከለክል ይናገራሉ፡፡

መምህሩ፣ እንደ ሌሎች አስተየየት ሰጪዎች ሁሉ በአካባቢው አስተዳዳሪዎች በር ተዘግቶ በሚፈጸሙ አሰራሮች ደስተኛ እንዳልሆነ አመልክቷል፡፡

አንዳንዶች ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ጋር ሲነጻጸሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የገጠር ወረዳዎች በኢኮኖሚ እንዳያድጉ ይህን የመሰሉ አሰራሮች ማነቆ እንደሆኑባቸው ያምናሉ፡፡ ትንንሽ ከተማዎች መሰረተ ልማትና መሰረታዊ አገልግሎት የማግኘት ምቹ አጋጣሚዎች የላቸውም፤ ይህም በግሉ ሴክተር ለኢንቨስትመንት ተፈላጊ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ከነዋሪዎቻቸው ግብር ቢሰበስቡም በዚህ አነስተኛ የገቢ ምንጭ ከአመት በጀታቸው ሩቡን እንኳ መሸፈን አይችሉም፡፡

አንድ በአሶሳ ከተማ የሚኖር ጠበቃ በግንቦት ወር ለኢትዮጵያ ኢንሳይት እንደገለጸው አስቀድሞ በዘፈቀደ ይፈጸሙ ለነበሩ የመሬት ሕግጋት ሕጋዊ ማዕቀፍ ለመስጠት እንዲቻል ማሻሻያ የተደረገበት የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር ሰነድ ተዘጋጅቷል፡፡ ለምሳሌ ያህል የተሻሻሉት ሕግጋት በነዋሪዎች መካከል የመሬት ኪራይ ስምምነቶች እንዳይፈጸሙ በግልጽ ይከለክላሉ፡፡ እንዲህ አይነት ስምምነቶችን ማድረግ መሬቱን መውረስን ጨምሮ ሌሎች የቅጣት እርምጃዎች መንግስት እንዲወስድባቸው ሊያደርግ ይችላል፡፡

እንዲህ ግልጽ ሕግጋት ቢቀመጡም እንኳ አሁንም በመሬት መልሶ መያዝ ዙሪያ በአሶሳ አስተዳደር አካላት መካከል  ውዝግቦች ተነስተው ነበር፡፡ ለገጠርና ከተማ መሬቶች የተዘጋጁት የማካካሻ አሰራሮች አርስ በርስ የሚጋጩ መሆናቸው እንዳሳሰባቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ እዚህም ላይ የብሔር ጉዳይ የትኩረት ነጥብ ሆኖ ተነስቷል፤ የዚህ ምክንያቱ ለሕዝብ ፍላጎት በሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ስም የከተማና ነዋሪዎችና የገጠር ገበሬዎች በጉልበት ከመሬታቸው እንዲነሱና ወደሌላ እንዲዛወሩ ስለተደረጉ ነበር፡፡

በ2007 የአሶሳ ስቴድየም በአሶሳ ከተማ መሀል የተገነባበት ሁኔታ ለዚህ አዝማሚያ አንድ ምሳሌ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጀመር የከተማ ልማት ቢሮ ሀላፊዎች በቀጠናው የቤትና ንብረት ባለቤቶች የሆኑት በአብዛኛው የበርታ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡና መሬታቸውን ለኮንትራክተሩ ማለትም ጋድ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/ግ/ማ እንዲያስረክቡ ታዘዙ፡፡ ከስፍራው እንዲለቁ የተደረጉት ነዋሪዎች ከገንዘብ ካሳ በተጨማሪ የሚሰፍሩበት ተመጣጣኝ  የከተማ መሬት ተሰጣቸው፡፡

የተወሰኑ የአማራ ነዋሪዎች መንግስት ሆን ብሎ በርታዎችን – በስቴድዮሙ ቀጠና ቤት የነበራቸው የመንግስት ሀላፊዎች ከመካከላቸው ነበሩ – ለመጥቀም ያደረገው እንደሆነ ይከሳሉ፡፡ ማንነቱ እንዳይገለጽ የጠየቀ አንድ በአሶሳ የሚኖር የአብን ደጋፊ የአማራ አክቲቪስት ሰኔ 9 በሰጠው ቃለ መጠይቅ ከሞላ ጎደል ሁሉም የበርታ ብሔረሰብ ተወላጅ ለሆኑት የንብረት ባለቤቶች መንግስት ለመሬቱ ከሚገባው በላይ ተመን በማውጣት የተጋነነ ካሳ እንደከፈለ ይገልጻል፡፡

ከአንድ አመት በኋላ መንግስት የአሶሳ ዩኒቨርስቲን በሚያሰራበት ወቅት የነበረው ሁኔታ ከላይ ከተጠቀሰው ጋር ያለውን ልዩነት ለማሳየት በምሳሌነት መቅረብ ይችላል፡፡ ከአሶሳ ከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ ባለው የገጠር መንደር ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአማራ ሰፋሪዎች ተሰባስበው ይኖሩበት ነበር፡፡ መሬታቸው በ2008 ተጀምሮ በመካሄድ ላይ ላለው ለዩኒቨርስቲውና ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት እንዲውል ተከፋፈለ፡፡

የቀድሞ የአምባ 8 ቀበሌ አስተዳዳሪ ከኢትዮጵያ ኢንሳይት ጋር በሰኔ ባደረገው ቃለ መጠይቅ ላይ ‹‹መንግስት የአሶሳ ዩኒቨርስቲ ግንባታ ፕሮጀክት ሲያስቀጥል መሬታቸው ለተወሰደባቸው ነዋሪዎች ማካካሻ የሚሆን መሬት በከተማ እንደሚሰጣቸውና ባጡት እርሻ መሬትና መተዳደሪያ ምትክ የገንዘብ ካሳ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶ ነበር›› ይላል፡፡

ይሁን እንጂ ነዋሪዎችን የማስወጣቱ ተግባር ሲጠናቀቅ ‹‹መንግስት የገባውን ቃል ማጠፍም ብቻ ሳይሆን ቃል መግባቱንም ነው የካደው›› ይላል የአምባ 8ቱ አስተዳዳሪ፡፡ በመቀጠልም ‹‹(የገንዘብ) ካሳውን እና ሌሎች ነገሮችን ስንመለከት፣ ጥቅማ ጥቅሞች ሙሉ ለሙሉ እንዳይሰጡ ተከልክሏል›› በማለት ያብራራል፡፡

በአሶሳ ከተማ ላለው ስቴዲየም ከተደረገው የካሳና ልውጥ ቦታ የመስጠት መርሃ ግብር ጋር ሲነጻጸር የአምባ 8ቱ ሂደት ይበልጡን ውስብስብ ነበር፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የገጠርና የከተማ መሬቶችን ለመመዘን የሚቀመጡት መለኪያዎች የተለያዩ ስለሆኑና አምባ 8 የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ስልጣን ስላልሆነም ጭምር ነው፡፡

400 ሄክታር መሬት የተወሰደ ቢሆንም 200 ሄክታር መሬት ብቻ ነበር በምትክነት የተሰጠው፡፡ ምንም እንኳ አብዛኞቹ የተፈናቀሉት ገበሬዎች በምትክነት የተሰጣቸውን የከተማ መሬት የሚመርጡ ቢሆንም በርካቶች ከግብርና የሚያገኙትን ስራና የገቢ ምንጭ እንደማጣታቸው ለካሳነት መሬት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ተሰምቷቸዋል፡፡

የተወሰደው መሬት በአመዛኙ ሰው የማይኖርበት በደን የተሸፈነና ለእንስሳት ግጦሽ የሚውል መሬትን የሚያጠቃልል መሆኑ የካሳውን ጉዳይ ውስብስብ አድርጎታል፡፡ የመሬት አስተዳደር አዋጅ እንደሚለው ካሳ የሚከፈለው ለቤቶችና እንደ ፍራ ፍሬ ያሉ ምርቶችን ለሚሰጡ ዛፎች ብቻ ነው፡፡

ቢሆንም የተፈናቀሉት ገበሬዎች እንደተጭበረበሩ ስለተሰማቸው ለፍርድ ቤት አቤት አሉ፡፡ እንደአስተዳዳሪው አባባል ‹‹ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት ቢየቀርቡም መንግስት ጠበቃቸውን (በለጠ አባተን) ለ14 ቀናት በእስር ቤት እንዲቆይ በማድረጉ ሕዝቡ ተማሮ ክሱን ለመተው በቃ››፡፡

ሁለቱ ነዋሪዎች እንዲነሱ የተደረጉባቸው ክስተቶች ለንጽጽር ቀርበው በሚታዩበት ወቅት ለነባር ሕዝቦች የበለጠ ቦታ የሚሰጥ መድሎአዊ አስተዳደር ለመኖሩ መረጃ እንደሚሆን አንዳንዶች ያምናሉ፡፡ መድሎ አልባ ሊሆን በሚገባው ስርአት ለረጅም ጊዜ አብረው የኖሩ ነባር ያልሆኑ ነዋሪዎች በደረሰባቸው ኪሳራ ከፍተኛ ቅሬታ እንዲሰማቸው ሆኗል፡፡

በአሶሳ የሚስተዋለው በመኖሪያ ቤቶችና መሬት ባለቤትነት ዙሪያ የሚስተዋለው ውዝግብ በዚህ አያበቃም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን የፌዴራል መንግስት በመኖሪያ ቤት ግንባታ ማሕበር ለመሰረቱ ሲቪል ሰርቫንት ሙያተኞች መሬት የማደል ፖሊሲ እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ ይህን ፖሊሲ ለማስኬድ የተሞከረው የሲቪል ሰርቫንት ሙያተኞች በተለይ ደግሞ መምህራን ያጋጠማቸውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ነበር፡፡

ይህን ስትራቴጂ ተከትሎ አሶሳ ከተማን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ላሉ የሲቪል ሙያተኞች ማሕበራት መሬት ተከፋፍሏል፡፡ ይሁን እንጂ የክልሉ እና አሶሳ ከተማ አስተዳደር ካቢኔዎች በአሶሳ ለተመሰረተው የመምህራን ማህበር መሬት ላለመስጠት ወሰኑ፡፡ ከዚህ ማሕበር አባላት መካከል አብዛኛዎቹ በዩኒቨርስቲ ደረጃ ያሉ ሌክቸረሮች ሲሆኑ በርካቶቹም ነባር ያልሆነ ብሔር ተወለጆች ናቸው፡፡

የማህበሩ መሪ ከኢትዮጵያ ኢንሳይት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ እንደገለጸው ከመምህራን ተደጋጋሚ ቅሬታ ከቀረበላቸው በኋላ እሱና ሌሎች አባላት ለምን መምህራን የመኖሪያ ቤት ለማግኘት ማሕበራት እንዳይመሰርቱ እንደተከለከሉና ባሉት የመኖሪያ ቤት ማህበራት የታቀፉት መምህራንም ቤቶች ለምን እንዳልተሰጣቸው ለመጠየቅ ወደ አሶሳ ከንቲባ እና መዘጋጃ ጽህፈት ቤት ሄደው ነበር፡፡

እንዲህ ይላል፡- ‹‹ጽሕፈት ቤቱ መልስ ሊሰጠን አልቻለም፤ በጥቅሉ የመንግስትን መመሪያ እንደተከተሉ ነገሩን፡፡ መምህራንን የሚከለክለውን መመሪያ እንዲያሳዩን ደጋግመን ብንጠይቃቸውም ሰነዱን ሊያቅርቡልን ግን አልቻሉም፡፡ በክልል መንግስቱም ተመሳሳይ ምላሽ ነው የተሰጠን፤ ጉዳዩም እስካሁን መፍትሔ አላገኘም››፡፡

በአሶሳ ያሉ የዩኒቨርስቲ መምህራን ክልከላ እንደተደረገባቸው ያስባሉ፤ ቃል የተገባላቸው የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚነትን የሚከለክለው መመሪያ ሕጋዊ በመሆኑ ላይም ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ውሳኔው አከራካሪ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት እንዲያቀርቡም ሆነ ራሳቸውን እንዲከላከሉ እድል እንኳ አልተሰጣቸውም፤ ሀላፊዎች እነሱን ባስተናገዱበት መንገድም ፍጹም ደስተኞች አይደሉም፡፡

በአሶሳ ከተማ በመኖሪያ ቤት ዙሪያ የሚነሱ ውዝግቦች አነስተኛ ፋይዳ ያላቸው ይመስላሉ ነገር ግን በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ በማሕበረሰቦች መካከል ያለው ውጥረት ተባብሶ ይገኛል፡፡ በባምባሲ ወረዳ የተከሰተው ግጭት የተቆሰቆሰው በተሳሳተ መልኩ በተፈጸሙ ነዋሪዎችን የማዛወር መርሃ ግብራት ምክንያትነት ነው፡፡ ይህም ከበስተጀርባ ያሉ ጉዳዮች መፍትሔ ሳይበጅላቸው ከተተዉ ብርቱ ደም መፋሰስ በቀላሉ ሊዛመት እንደሚችል እንደ ማንቂያ ደወል ሊያገለግል ይገባል፡፡

የአናሳዎች መብት

በአሶሳ ዞን ያለው ባምባሲ ወረዳ በውስጡ ቢያንስ 38 ቀበሌዎች አሉት፡፡ በወረዳው መልሶ ማወቀር ስራ እየተከናወነ ስለሆነ ያሉት ቀበሌዎች ስንት መሆናቸው ግልጽ አይደለም፡፡ ነባር ብሔረሰቦች፣ በተለይም በርታዎች ነባር ካልሆኑት በዋነኝነት ከአማራዎች ጋር በጋራ የሚኖሩባቸው ቀበሌዎች ያሉ ሲሆን በአንዳንዶቹ ቀበሌዎች ደግሞ አንደኛው ወይም ሌላኛው ወገን በብዛት ይገኛሉ፡፡

ለብዙ ምእተ አመታት በቦታው ከኖሩት ነባር የበርታ ማሕበረሰብ በተቃራኒ አብዛኞቹ በባምባሲ የሚኖሩት አማሮች ከበርካታ ኦሮሞዎች ጋር በስፍራው መኖር የጀመሩት በ1980ዎቹ ደርግ የሰፈራ ፕሮግራም በተገበረበት ወቅት ነበር፡፡ በርታዎች ሰፋሪዎቹን ተቀብለዋቸው ለረጅም ዘመናት በአንጻራዊ ሰላም አብረው ኖረዋል፡፡

ኢህአዴግ የብሔር ፌደራሊዝምን በአገሪቱ ከተገበረ በኋላ በባምባሲ ነዋሪ የሆኑ ነባር በርታዎች በክልሉ እንዳሉት ሌሎች አናሳዎች ራሳቸውን እንዲያስተዳደሩ ልዩ መብት ተሰጣቸው፡፡

ይህም እኩል አስተዋጽኦ እያደረጉ ሳለ ጥቅማ ጥቅሞችን እኩል ባለመካፈላቸው በባምባሲ በሚኖረው ነባር ባልሆነው ማሕበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ የተበዳይነት ስሜት እንዲፈጠር አደረገ፡፡ በብዙ መልኩ ሲገመገም ይህ አስተሳሰብ የተጋነነ ነበር፡፡ በተጨባጭ ሲታይ በአመዛኙ በአሶሳ የሚኖረው ነባር ያልሆነ ሕዝብ በኢንቨስትመንት፣ በአገልግሎት፣ በንግድና ግብርና ሴክተር ሳይቀር የበላይነት ነበረው፡፡ እሳቤው እውነተኛም ይሁን ምናባዊ፣ በሁኔታው የመከፋት ስሜት ተፈጠረ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የባምባሲ ወረዳ ነዋሪዎች በወረዳው በሰፈነው ብልሹ አስተዳደር ተከፍተው ነበር፡፡

በግንቦትና ሰኔ ወር ከኢትዮጵያ ኢንሳይት ጋር ቃለ ምልልስ ያካሄዱ የባምባሲ ወረዳ አምባ 48 ቀበሌ ሀላፊዎች እንዳገለጹት በፍጥነት ቁጥራቸው እየበዛ የመጡ ወጣቶች የስራ እድል በተለይም የግብርና ስራ እንዲሰጣቸው በቀበሌ መስተዳደሩ ላይ የሚያሳድሩት ጫና ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ሄዷል፡፡ ለስሞታቸው ምላሽ ለመስጠት በአካባቢያቸው የመሬት ክፍፍል እንዲደረግ የሚጠቁ ደብዳቤዎችን የቀበሌው አስተዳዳሪዎች ወደ ወረዳ መስተዳደር ለአራት አመታት በተደጋጋሚ ሲጽፉ ቆይተዋል፡፡

የወረዳ መስተዳደሩ ከቀበሌ የደረሱትን ደብዳቤዎች ወደ ጎን በማለት በሰኔ 2020 አማሮች ወደሚበዙበት የጀማጼ ቀበሌ ኢንቨስት ለማድረግ ለመጡ በአመዛኙ የበርታ ብሔር ተወላጅ ለሆኑ ነዋሪዎች መሬት አድሏል፡፡

ይህ ውሳኔ የተተገበረው በአካባቢው ነዋሪዎችና ሀላፊዎች መካከል ምንም አይነት ምክክርም ሆነ ስምምነት ባልተደረገበት ሁኔተ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግረዋል፡፡

በወረዳ አስተዳደሩ እርምጃና ውሳኔ የተከፉ የአማራ ወጣቶች በቡድን ሆነው አዲስ መጤዎቹ በተከሏቸው መዋቅሮች ላይ እሳት ለቀውበታል፡፡ የክልሉ ልዩ ሀይል ዘግይቶ የደረሰ ሲሆን በተቃውሞው ውስጥ መሳተፋቸውን የሚያሳይ መረጃ በሌለበት በጅምላ ወጣቶችን በማሰር የአጸፋ እርምጃ ወስዷል፡፡ ቀጥሎ በተከሰቱት ግጭቶችም በቁጣ ገንፍሎ በወጣው ሕዝብ ላይ ተኩስ በመክፈት ሶስት ሰዎችን ገድለዋል፡፡

የሀይል እርምጃው ሕዝቡ ልዩ ሀይሉን ተቃውሞ እንዳይወጣ አደረገው፤ ከዚያ ይልቅ ሲቪሎች እርስ በርስ ግጭት ውስጥ ገቡ፡፡

በቀጣይ ቀናት የአማራና በርታ ማሕበረሰቦች አባላት የሆኑ 9 ሰዎች ሲገደሉ 81 የአማራ ተወላጆች ደግሞ ታሰሩ፡፡ ከታሰሩት መካከል የቀበሌው ሊቀ መንበርና ሌሎች ሀላፊዎች እንዲሁም በግጭቱ ወቅት በአካባቢው ያልነበሩ የማሕበረሰቡ አባላት ይገኙበታል፡፡ ከአርባ በላይ ሰዎች አሁንም አለምንም ማስረጃ እንደታሰሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህ መራራ ፍልሚያ የተነሳ በማሕበረሰቡ ውስጥ የነበረው ግንኙነት ቆርፍዷል፡፡

በርግጥ በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላማዊ በነበረ አካባቢ በማሕበረሰቦች መካከል እንዲህ ግጭት ሊስፋፋ የበቃው ለምንድን እንደሆነ ለመተንተን የሚሞክሩ ተፎካካሪ እይታዎች አሉ፡፡

ኢትዮጵያ ኢንሳይት መረጃ የሰጡ የአማራ ተወላጆች የወረዳ አስተዳደሩ ሌሎችን ያገለለ ድጋፍ  ለነባር ማሕበረሰብ አባላት ያደርጉና ራሳቸውንም ይጠቅሙ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

አንድ በባምባሲ የሚኖር የብልጽግና ፓርቲ ደጋፊ የሆነ የበርታ ተወላጅ በወጣቶች ዘንድ የነበረውን ያለመረጋጋት በመጠቀም ቅሬታዎችን የሚያባብስ የተጎጂነት ርዕዮት የአብን አመራር እንዳስፋፉ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት አስረድቷል፡፡ እንደሱ አባባል ከሆነ የአብን ፓርቲ አባላት አማራ ባልሆኑት ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ አበረታተዋል፤ በነባር ብሔረሰብ ተወላጆች በሚመራው አስተዳደር ላይ ያላቸው ቅሬታ እንዲባባስ አድርገዋል፤ እናም ‹ሀላፊነት የጎደላቸው› እና ‹የወጣቱን ትውልድ በተሳሳተ አቅጣጫ መርተውታል›፡፡

በሁለቱም ወገኖች ባሉ መሪዎች አነሳሽነት በባምባሲ የተከሰተው ግድያና ውድመት በሌሎች የዞኑ አካባቢዎችም ተመሳሳይ ችግርና መከፋፈል ገንፍሎ ከዚህ ጋር የሚነጻጸር ደም መፋሰስ ሊከሰት እንደሚችል የማንቂያ ደወል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

የምርጫው መራዘም

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የግጭቶች መባባስን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመተከል እና ካማሺ ዞኖችም ሆነ በአሶሳ ዞን ባለው ኦዳ ቡልዲግሉ ወረዳ በደህንነት እጦት ምክንያት ምርጫው እንደማይካሄድ አስታውቋል፡፡

የክልሉ ምርጫ ጳጉሜ 1 መተላለፉን ተከትሎ ሁለቱ ዞኖችና ወረዳው የሚሳተፉበት ሁኔታ ይኑር አይኑር በቀጣይ የሚታይ ይሆናል፤ አሁን ያለው ሁኔታ ግን በቅርቡ ሰላም የሚሰፍንበት አዝማሚያ መኖሩን አጠያያቂ አድርጎታል፡፡

አሶሳ ዞን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምክር ቤት ካሉት 100 መቀመጫዎች መካከል 42ቱን በመያዝ የክልሉ ትልቁ የምርጫ ቀጠና እንደሆነ የክልሉ ሕገ መንግስት ይደነግጋል፡፡ በቆዳ ስፋት የሚበልጡት ነገር ግን ሕዝብ በብዛት ያልሰፈረባቸው መተከልና ካማሺ ዞኖች በድምሩ ከግማሽ በጥቂት ብቻ ከፍ የሚለው ቀሪ መቀመጫ (33 እና 20) ይደርሳቸዋል፡፡ የመጨረሻዎቹ 4 ወንበሮች በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ የተያዙ ናቸው፡፡

በመተከልና ካማሺ ሰላም ለማስፈን ትኩረት አድርጎ መስራት የክልል መንግስት ለማዋቀር ጭምር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከነሱ የሚገኘው ወንበር ባልተሟላበት ሁኔታ በመስከረም 6 ምርጫ የሚደረግ ከሆነ ከጠቅላላ ምርጫ ቀጠናዎች በምርጫው የሚሳተፉት ከግማሽ ያነሱ ነው የሚሆኑት፡፡

በተመሳሳይ አሶሳ ባሁኑ ሰአት በክልሉ ስራውን ያላስተጓጎለ ብቸኛ ዞን እንደመሆኑ እዚህም ግጭት እንዲቀንስ መንቀሳቀስ በዚያው ልክ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ስለሆነም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ውጥረት ለማርገብ መፍትሔ የማፈላለጉ ጥረት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አብረው በሚኖሩ ነባርና ነባር ያልሆኑ ሕዝቦች መካከል የተፈጠሩ ውጥረቶች የአመራሮች የትኩረት ቀጠናዎች መሆን አለባቸው፤ በማሕበረሰቦች መካከል የሚፈጠረውን ግጭት የሚያባብሰው መሰረታዊ ችግር በባለቤትነት መብት ሕጋዊነት ዙሪያ የሚነሱ ተቀናቃኝ ስጋቶች መሆናቸውንም ግምት ውስጥ ሊያስገቡ ይገባል፡፡

በሰኔ ከኢትዮጵያ ኢንሳይት ጋር ውይይት ያደረገ በአሶሳ የሚኖር አንድ የብልጽግና አመራር ያቀረበው የመፍትሔ ሀሳብ በመሬትና ማዕድናት ላይ የተደራጀ የቁጥጥር ስርአት በአስተዳደር ደረጃ ሊዋቀር ይገባዋል የሚል ነበር፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ክፍፍል ስርአታትም በግልጽ ሊቀመጡ ይገባል፣ በሀብት አጠቃቀም ዙሪያ የሚነሱ እሰጥ አገባዎችም ፍትሐዊ፣ ሕጋዊና ይፋዊ በሆነ መንገድ እንዲዳኙ ለማስቻል መደበኛ የመሬት ባለቤትነት ፖሊሲዎች በሕግ መደንገግ ይኖርባቸዋል፡፡

ፖለቲከኞችና መሪዎች ይበልጥ ቁጥብነትና አርቆ አሳቢነት ሊለማመዱ ይገባል፡፡ የአድመኝነት አስተሳሰብን ሲያፋፍሙና ብሔር ተኮር ግጭቶችን ጽንፍ እንዲይዙ ሲያደርጉ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መገንዘብ አለባቸው፡፡ በነባር ብሔረሰብ መር መስተዳድሮች ስር ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ የብልጽግናና የአብን አመራሮች ለነዋሪዎች የመሬትና የመኖሪያ ቤት፣ የህግ ከለላና ደህንነት እንዲሁም የስራ እድል የማግኘት ፍላጎት ተገቢ ምላሽ መስጠት የሚያስችል መፍትሔ ለማፈላለግ በጋራ ሊሰሩ ይገባል፡፡

መሪዎች የሚነሱ ሐሜቶችና መላ ምቶችን ለማስቀረት በፖሊሲዎቻቸው ዙሪያ ይበልጥ ግልጸኛ አሰራር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ውይይት ሳይደረግና ማብራርያ ሳይሰጥ እርምጃዎች ስለሚወሰዱ ይህ አካሄድ ብዙዎች የራሳቸውን ድምዳሜ እንዲይዙ ምክንያት ሆኗል፡፡

በክልሉ በሁለቱም ወገን ጥላቻና ግድ የለሽነት በሰፊው የሚስተዋል እንደመሆኑ ሚዛናዊነት በጎደለበት፣ ግልጽ አሰራር በሌለበትና ሕግን ያልተከተለ አካሄድ በብዛት በሚኖርበት ሁኔታ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ክፍፍሎች መባባሳቸው ሊያስገርም አይገባም፡፡

ነባርና ነባር ያልሆኑ ነዋሪዎችን ፍላጎት ሚዛናዊ ምላሽ መስጠት ፈታኝ ነገር ግን እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነው፡፡

በመካከላቸው አለመስማማት የሚስተዋልባቸው ማሕበረሰቦች ፍላጎታቸውን በአግባቡ ለመመርመርና ለመረዳት እንዲችሉ ፖለቲከኞች በሲቪል ማሕበረሰቡ ውስጥ ካሉ ድርጅቶች፣ የጎጥ አለቆችና አክቲቪስቶች ጋር አብረው መስራት አለባቸው፡፡ በሕብረተሰቡ መካከል የሚነሱ መለያየቶችን በእርቅ መፍታትና ሰላምን መልሶ ለመገንባት ሊሰሩ ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር ሁሉን አቀፍ ውይይት ማካሄድ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

ነባር ማሕበረሰቦች ራስን የማስተዳደር ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን እንዲተገብሩ የሚያስችል ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ የክልሉ ነባር ያልሆኑ ነዋሪዎች የማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻቸውን በበቂ ሁኔታ እንዲያሳኩ የሚፈቅድ መፍትሔ ለሁለቱም ወገኖች ጠቃሚ ነው፡፡

Query or correction? Email us

Follow Ethiopia Insight

ይህ ጽሁፍ ምርጫ 2013ን በሚመለከት ዘለግ ያሉ ጽሁፎችን ከመላው ኢትዮጵያ በተከታታይ የምናቀርብበት የ “Ethiopia Insight Election Project (EIEP)” ክፍል ነው።

ዋና ምስል: ከመተከል ዞን የተፈናቀሉ ዜጎች በቻግኒ፣ አማራ ክልል፥ 2013፥ ቢቢሲ።

Join our Telegram channel

Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished.

We need your support to analyze news from across Ethiopia
Please help fund Ethiopia Insight’s coverage
Become a patron at Patreon!

About the author

Mistir Sew

This is a generic byline for all anonymous authors. The anonymity could be because they fear repercussions, as they are not authorized by their employers to express their views publicly, or for other reasons.

Leave a Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.