Elections 2021 Ethiopian language In-depth

የኢትዮጵያ ሴቶች የተቀዳጁት የከፍታ ጉዞ በ ጾተኛ ማነቆዎች እየተገደበ ነው

ምንም እንኳን ፈር ቀዳጅ ፖሊሲዎችና ተራማጅ ህጎች ቢኖሩም የተለመዱ እንቅፋቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሴቶች ፍትሀዊ ውክልና እንዳይኖራቸው ያደርጋሉ

የኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙ ሚኒስትሮች የስራ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቃል ሲገቡ በዓለም ዙሪያ ርዕሰ ዜና ሆኖ ነበር። በድጋሚ በተዋቀረው 20 አባላትን በያዘው ካቢኔ 10 ሴት ሚኒስትሮች ሲሾሙ በአንዲት ጀምበር አገሪቷ በስልጣን ላይ ያሉ ወንዶችና ሴቶችን ቁጥር እኩል ለማድረግ በመቻሏ በአህጉሩ ፆታ በማጣጠን (እኩልነት) መሪ ሆነች። ይህም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ከወሰዳቸው በርካታ ማሻሻያዎች አንዱ ሲሆን ሴቶች እንደዚህ ባለ ከፍተኛ የሚኒስትር ደረጃ እኩል መቀመጫ ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን በፊት በሴቶች ተይዘው የማያውቁ የኃላፊነት ስፍራ መያዛቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በአገር ውስጥ አድናቆት የተቸረው ጉዳይ ነበር። ከዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው የአገሪቱ የመጀመሪያ የሰላም ሚኒስቴር ሙፈሪያት ከሚልና የመከላከያ ሚኒስቴር አይሻ መሀመድ ሹመት ነው። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የአገሪቷ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዝደንት በመሆን ሌላ ክብረ-ወሰን ሰበሩ።

ከ30 አመታት ገደማ በፊት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አገሪቷን ሲቆጣጠር ምንም እንኳን ሴቶች የፓርቲውን 30 በመቶ የሚይዙ ቢሆንም በሚኒስትር ደረጃ የሚገኝ የስራ መደብ ላይ ከዛ ቀደም አንዲት ሴት ብቻ ነበረች የነበረችው። ከዛን ጊዜ ጀምሮ የሴቶች ውክልና በፍጥነት በመጨመር በ1987 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ከነበረው 13 የምክር ቤት መቀመጫ አሁን ወደ 210 ሴት አባላት አድጓል።

በ2011 ዓ.ም የተደረገው የሚኒስትሮች ሹመት ከፍተኛ አድናቆት ተችሮት የነበረ ቢሆንም ካቢኔው ይህን የፆታ እኩልነት በፍጥነት አጣው። ከተሾሙ አመት ሳይሞላቸው አይሻ በለማ መገርሳ ተተኩ፤ ሌሎች ሶስት ሴት ሚኒስትሮችም በቀጣይ ሁለት አመታት ከቦታቸው ወደ ሌላ ቦታ የተዛወሩ ሲሆን ለዚህም ምክንያት ነው የተባለው ከማሻሻያ ሂደቶች ጋር የተያየዙ ሁኔታዎች ወይም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተፈጠሩ አለመግባባቶች ናቸው።

በአይሻ መሾም የደስታ-መግለጫዎች እንደነበሩ ሁሉ ከፍተኛ ትችቶችም ነበሩ። “ሴት እዚህ የስራ ኃላፊነት ላይ በመቀመጧ ሰዎች የሰጡት ምላሽ አስደንጋጭ ነበር” በማለት የኢትዮጵያ ሴቶች የህግ ባለሞያ ማኅበር ዋና ኃላፊ የሆነችው ሌንሳ ቢየና ተናግራለች። “አገሪቷ የተወረረች ነበር የሚመስለው’” ስትልም ታክላለች።

አይሻ በመሾማቸው ዙሪያ ያለው ይህ አመለካከት ኢትዮጵያውያን ሴቶች በፖለቲካው ዘርፍ አቅማቸው እንዳይጎለብት የሚያደርጉ እንቅፋቶች ምሳሌ ሲሆን እክሎቹም የተወሰኑት በአብዛኛው መንገድ እስከአሁን ድረስ ያልተቀየሩ እና ሴቶችን በባህላዊ ሚናዎች ውስጥ የሚያስቀምጡ ጥንታዊ የማኅበረሰብ ልማዶች ናቸው።

የአይሻ ከሌሎች ሴት የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ከቦታቸው ወደ ሌላ ቦታ መዛወር በኢትዮጵያ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና የአቅም ማጎልበት ላይ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ያለውን ሌላ ጋሬጣ ያመለክታል፥ ይህም ጋሬጣ ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያረጋግጡ ተቋማዊና ህጋዊ ማዕቀፎች እጥረት ነው። ሴቶች በስልጣን ላይ በሌሉበት ሁኔታ የሴቶች ሚና እና ተጽዕኖ ስልጣን በያዙ ሰዎች በጎ ፍቃድ ላይ ይመረኮዛል።

የህይወት ወይም ሞት ፖለቲካ

በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም አገሪቷ ለ28 አመታት የቆየውን ብሔራዊ የሴቶች ፖሊሲ የኢትዮ አውስትራሊያ ምርምር ኢንስቲትዩት በሆነው ኢንክሉዶቬት እርዳታ አማካኝነት መከለስ ጀመረች። ፖሊሲው በመጀመሪያ የተቀረጸው የሴቶችን መብት በኢኮኖሚ፣ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ ተቋማዊ ለማድረግና በነዚህ ዘርፎች ውስጥ የሴቶችን መብት ወደ ፊት ለማራመድ በማለም ሲሆን ማሻሻያው ፖሊሲው ዓላማውን እንዳሳካና ካሳካም ምን ያህል እንደሆነ ለማየት ታስቦ የተደረገ ነበር።

ከበርካታ ችግሮች መሃል 68 ወረዳዎች በጋራ የጠቀሱት አንድ ችግር የደኅንነት እጥረት ነው። ለዚህም በየጋምቤላ ህዝቦች ነፃ አውጪ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ውስጥ የሴቶች ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ እንደሆነችው ክዋት ኦጅዋቶ ያሉ ሴቶች ምስክር ናቸው።

ኢህአዴግ በሽምቅ ውጊያ በ1983 ዓ.ም ድል ሲቀዳጅ በርካታ ወታደሮች ከጦርነት ወደ ቤታቸው ተመለሱ። በጊዜው የአንድ ልጅ እናትና የ23 አመት ወጣት የነበረችው ክዋት የኢህአዴግ መስራችና መሪ ከሆነው የትግራይ ህዝቦች ነፃ አውጪ ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) ጋር በማበር ጦርነቱን ለመቀላቀል ሄደው የነበሩትን እነዚህን ተመላሽ ወታደሮች ለመመዝገብ በጋምቤላ በሚገኝ አንድ ካምፕ ተመልምላ ነበር። በጋምቤላ ተወልዳ ያደገችው ክዋት ልጇን ከአራት አመታት በፊት በ19 አመቷ በመውለዷ የተነሳ ትምህርቷን እንድታቋርጥ ተገዳ የነበረ ሲሆን በወታደሮች ካምፕ የነበረው የመጀመሪያ የክፍያ ስራዋ ዋና ከተማዋ ውስጥ ለሚደረግ የፖለቲካ ስልጠና እንድትመረጥ አደረጋት። ዋና ከተማዋ ባለቤቷ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እየተማረ የሚሰራባት ከተማ ነበረች።

‘’ሌሎች እንደኔ ያሉ ሁለት ሴቶች ነበሩ። በጊዜው የሁላችንም ባለቤቶች አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይማሩ ነበር’’ ትላለች።

የስልጠና ስፍራቸው ከደረሱ በኋላ ሌሎቹ ሁለት ሴቶች በባለቤቶቻቸው ትዕዛዝ ምክንያት ወደ ጋምቤላ ተመለሱ። የክዋትም ባለቤት ክዋት ለስልጠና ወደ ዋና ከተማዋ ለመምጣት በመወሰኗ ደስተኛ አልነበረም።

“ወደ አዲስ አበባ የመጣሽው ሴተኛ አዳሪ ለመሆን ነው’’ በማለት ወነጀለኝ። “የሚማረው እኛን ቤተሰቦቹን ለመንከባከብ እንደሆነ ተናገረ፤ ነገር ግን እኔም መማር እንደምፈልግና በልጅነቴ ባልወልድ እሱ የደረሰበት ደረጃ እደርስ እንደነበር ነገርኩት” ትላለች።

የክዋት እምቢተኝነት የዛን ዕለት ማታ ውድ ዋጋ አስከፈላት፤ ባለቤቷ የሆቴሉ ሰራተኞች ጣልቃ ገብተው ድብደባውን ከማስቆማቸው በፊት ደም በደም እስክትሆን ድረስ ደበደባት።

“የጋምቤላ ወንዶች ሴቶች ፖለቲካ ውስጥ ሲገቡ ደስ አይላቸውም። ነገር ግን ማንም ሰው እጣ ፈንታዬን እንዲወሰን ለማድረግ አልፈቅድም ነበር፤ ለዓላማዬ ለመሞት ተዘጋጅቼ ነበር” ትላለች።

ባለቤቷን በነጋታው ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ከሰሰች ፤ በኢህአዴግ ያላት ተሳትፎም ከፍተኛ የሴቶች ጥቃት ባለበት አገር ላይ እምብዛም የማይገኝ ጥበቃ እንድታገኝ አስቻላት። ባለቤቷ የትምህርት እድሉን እንዲሁም ስራውን ሲያጣ ክዋት ደግሞ በአላማዋ በመቀጠል የሶስት ወር ስልጠና አጠናቀቀች።

ክዋት በኢህአዴግ ውስጥ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ያገለገለች፤ እዛም ለመድረስ መስዋዕትነት የከፈለች ቢሆንም የፖለቲካ ተሳትፎዋ ተስፋ እንድትቆርጥ ነው ያደረጋት። የወሰደቻቸው በርካታ ስልጠናዎች ለውይይት ከሚቀርቡበት የስልጠና ክፍል ውጭ ተግባር ላይ አይውሉም ነበር። የኢህአዴግ አገዛዝ ጋምቤላ በፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ረገድ እንድትገለል በማድረጉ እንዲሁም በአኝዋ ክልል የጭካኔ እርምጃ በመውሰዱ ይታወሳል።

እራሷ አኝዋ የሆነችው ክዋት ዘግየት ብሎ ኢህአዴግን በመልቀቅ የጋምቤላ ህዝቦች ነፃ አውጪ እንቅስቃሴን (ለሁለት ከመከፈሉ በፊት) በመቀላቀል ከሌሎች የፓርቲው አባላት ጋር በመሆን በስደት በኤርትራ ለአንድ አመት ከኖረች በኋላ የአብይን መምጣትና በርካታ የተሰደዱ ፓርቲዎች ጋ እርቅ የማውረድ ጥረቶችን ተከትሎ ከሌሎች የፓርቲው አባላት ጋር በመሆን በ2011 ዓ.ም ወደ አገሯ ተመለሰች

ለክልሏ ምክር ቤት እጩ ሆና የተወዳደረችው የ42 አመቷ ክዋት በጋምቤላ ፖለቲካ ውስጥ አነስተኛ ቁጥርን ከሚይዙት ሴቶች ውስጥ አንዷ ናት። አንድ በሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር እና በዩኤን ዉመን በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም የተካሄደ ናሙና ጥናት እንደሚያመለክተው በክልሉ መንግስት በአጠቃላይ 21 በመቶ ሴቶች ብቻ ናቸው በአመራር ስፍራ ላይ የሚገኙት። ይህ በሶማሌ ወደ 11 በመቶ በአፋር ክልል ደግሞ ወደ 7 በመቶ ዝቅ ይላል።

‘’እኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ሴቶች አልተማሩም። የራሳቸውን መብት አያውቁም ስለዚህ ለመብታቸው ሊታገሉ አይችሉም’’ ትላለች ክዋት።

ነገር ግን አንደኛ ክፍልን ከሚጀምሩ ልጃገረዶች ውስጥ ግማሽ ያህል የሚሆኑት አምስተኛ ክፍል ሳይደርጉ በሚያቋርጡባት ኢትዮጵያ ትምህርት ከባድ ትግል የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። አምስተኛ ክፍል ከሚደርሱት ልጃገረዶችም ውስጥ 75 በመቶ ያህሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከማጠናቀቃቸው በፊት በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ያቋርጣሉ፤ ከነዚህም ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ያለዕድሜ ጋብቻ  ነው።

 ታሪካና ህግ

ክዋት መጀመሪያ ወደ ፖለቲካ በገባች ጊዜ አከባቢ የተቀረጸው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ፖሊሲ በጊዜው መቀረጹ ጠቃሚ ነበር። በሽግግር መንግስት ወቅትና ከአገሪቷ የ1987 ዓ.ም ህገ መንግስት ቀደም ሲል የተቀረጸው ይህ ፖሊሲ በአገሪቱ ለሴቶች መብት መንገድ የጠረገ ነበር።

ኢትዮጵያ የCEDAW ን ስምምነት ከዚህ ፖሊሲ ቀድማ የፈረመች ስትሆን ከዛን ጊዜም ጀምሮ የሴቶችን መብቶች የሚያስጠብቁ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እና ብሔራዊ ህጎችን አጽድቃለች። ከነዚህም ውስጥ በቅርብ ጊዜ የወጣው የ2007 ዓ.ም ዘላቂ የልማት ግቦች ይጠቀሳል። ነገር ግን ክዋት እንደወሰደቻቸው በርካታ ስልጠናዎች ፖሊሲዎቹና ይህን ተከትለው የሚመጡ የህግ መሳሪዎች በወረቀት ላይ ብቻ ተወስነው ቀርተዋል።

“ኢትዮጵያ ሁል ጊዜም ጥሩ ፖሊሲዎች አሏት። ችግሩ ትግበራ ነው። ትግበራው ጠንካራ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችን ልምድ ይፈልጋል ይህ ደግሞ እኛ የለንም።” ስትል የፌሚኒስት ኔትወርክ የሆነው በ2006 ዓ.ም የተመሰረተው ሴታዊት መስራች ስኅን ተፈራ ትናገራለች።

ሴታዊት ልክ በአገሪቷ ለሴቶች መብት እንደሚሟገቱ እንደ የኢትዮጵያ ሴቶች የህግ ባለሞያ ማህበር እና የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ኔትወርክ ያሉ ድርጅቶች አጋዥ ዘገባዎችን (ሪፖርቶችን) በመጻፍ የተሳተፈ ሲሆን እነዚህ ዘገባዎች መንግስት ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን በመተግበር ያለውን አፈጻጸም በተለይም ለCEDAW ያለውን ቁርጠኝነት የሚገመግሙ ናቸው።

በየካቲት ወር 2011 ዓ.ም ሴታዊት ለኮሚቴው ባቀረበው ዘገባ የተለያዩ ክፍተቶችን ጠቁሟል፤ክፍተቶቹም በፆታዊ ጥቃት ላይ የሚያተኩሩ ህጎች አለመኖራቸውንና የተለያዩ ጉዳዮችን ከግምት የሚያስገባ ሴቶች በራሳቸው መንገድ የፖለቲካ ተዋናዮች እንደሆኑ የሚረዳ አስተሳሰብ አለመኖርን ያካትታሉ።

“ይህ በተለይም ፆታዊ ጥቃትን በሚያካትቱ ጉዳዮች ላይ ሰውን ለማሳመን ተደጋግሞ ጥቅም ላይ የሚውል ነገር ነው። ሰዎች ሀዘኔታን ለማግኘት ሴቶችን የአንድ ሰው ልጅ፣ እህት ወይም ሚስት በማድረግ ይስላሉ፤ ሰው መሆናቸው ብቻ ግን በቂ ሊሆን ይገባው ነበር” ትላለች ስኅን።

ህብረተሰብ ሴቶች አቅማቸው በመጎልበቱ ያለጥርጥር ያተርፋል ነገር ግን ሴቶች በተፈጥሮ ያላቸውን ዋጋና መብት ከወንዶች ቀጥሎ በሁለተኝነት ደረጃ የሚያስቀምጥ ትርክት ጎዶሎ ነው። ሴቶች በኢትዮጵያ የቤተሰብ ዋና ተንከባካቢ እንደመሆናቸው ፖለቲካዊ መብታቸውን የመጠቀማቸው ሁኔታ ወንዶች በቤት ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ቢወጡ እንደሚያድግ ልብ ማለት ጠቃሚ ነው።

የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ከሚያቀርቡት አጋዥ ዘገባ በተጨማሪ የእነዚህን ስምምነቶች ትግበራ ለማረጋገጥ መደረግ የሚችል ነገር እምብዛም የለም፣ ምክንያቱም ይህን ለማድረግ ሁሉም አገር በቀል አማራጮች ተሟጠው ጥቅም ላይ መዋል ይኖርባቸዋል። እነዚህን የማረጋገጥ ጥረቶች ረዥም፣አድካሚ እንዲሁም በአብዛኛው የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ላይ የሚወድቅ ነው፤ እነዚህ የሲቪል ማኅበራት ደግሞ ለረዥም ጊዜያት ሲታፈኑ የነበሩ ናቸው።

የውጭ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ለምሳሌ ከአስር በመቶ በላይ የገንዘብ ድጎማቸውን ከውጭ የሚያገኙ ከሆነ ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዙ ጉዳዮችና የሴቶች መብት ላይ እንዳይሳተፉ በ2001 ዓ.ም የወጣ ህግ አግዶ የነበረ ሲሆን ህጉ በ2011 ዓ.ም ተሻሽሎ እነዚህን ገደቦች አንስቷል። ነገር ግን ለአስር አመት የቆየው እገዳ አሁን የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችን ከጊዜው ጋር ለመሄድ ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉ እያስገደዳቸው ይገኛል።

ተግባራዊ እርምጃ

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ አንዱ ቀደም ሲል ተሰዳ የነበረችውን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መሪ  ብርቱካን ሚደቅሳን የተሻሻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊ አድርጎ መሾም ሲሆን ይህም ስልጣን በኢትዮጵያዊት ሴት ሲያዝ የመጀመሪያው ነው።

አዲሱ የምርጫ ህግ ቀደም ሲል የምርጫ ሂደቶችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ ሂደቶችንና የፓርቲ ህጎችን የሚያስተዳድሩ ሶስት ህጎችን በማዋሀድ አንድ ያደረገ ነው። ይህም ምንም እንኳን የአገሪቷን የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ለማጠናከር ታልሞ የተደረገ ቢሆንም ረቂቁ ለምክክር ሲቀርብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስጋቶቻቸውን በመጥቀስ 13 ድንጋጌዎች እንዲሰረዙ ጠይቀዋል። ከነዚህ ድንጋጌዎች ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና የምርጫ እጩዎች ላይ እንዲሁም በምርጫ ሂደቱ ውስጥ የሚሳተፉ እንደ የምርጫ ጣቢያ ሰራተኞች ያሉት ላይ ጭምር የተሻለ የፆታ መመጣጠንን ለማምጣት የታለሙ ድንጋጌዎች ነበሩ።

“ረቂቁ በሚዘጋጅ ጊዜ በርካታ ስለፆታ የሚሰነዘሩ ጥቆማዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞ የተነሳ ተሰናክለዋል። መድረስ የሚጠበቅባቸው [የጾታ ማመጣጠን ቁጥር] ተግባራዊ መሆን የማይችል ነው።’’ ሲል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆነው ጌታቸው አሰፋ ይናገራል።

ይህ ቢሆንም እንኳ ህጉ የምርጫ ቦርድ የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉትን ጥረት እንዲከታተል ያስችለዋል። ቀደም ካሉት ህጎች የሚለየው ሴቶችን አባላቸው፣አመራራቸው እና እጩዎቻቸው አድርገው ለሚያካትቱ ፓርቲዎች ማበረታቻ መስጠቱ ነው በማለት ጌታቸው ይገልጻል።

በረቂቁ ውስጥ ያለ አንድ አስቸጋሪ ድንጋጌ ሴት እጩ ከወንድ እጩ እኩል ውጤት ካመጣች አሸናፊ ትሆናለች የሚለው ነው።ይህ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማበረታታት የታቀደ አወንታዊ እርምጃ ቢሆንም ድንጋጌው ኢ-ህገ መንግስታዊ ተደርጎ ታይቷል። ይህም የሆነበት ምክንያት አንድ እጩ እንዲያሸንፍ 50 በመቶ ሲደመር 1 ድምጽ ስለሚያስፈልገው ነው፤ ዘግይቶም ድንጋጌው እንዲወገድ ተደርጓል። ነገር ግን የሴቶች መብቶች ተሟጋቾች ህገ መንግስቱ ለሴቶች ድጋፍ የማግኘት መብት (affirmative action) እንደሚሰጥና ይህም ፖለቲካን ጨምሮ በሁሉም ዘርፍ መንጸባረቅ እንዳለበት ያምናሉ።

የከፍተኛ ትምህርት ህጉ ለሴቶች ድጋፍ ለማድረግ የተለየ የመግቢያ መስፈርት ያስቀመጠበት ድንጋጌ አለ። በተመሳሳይ ሁኔታም የስራ ህጉ ለሴቶች በምልመላና በስራ እድገት ላይ እንዲሁም በትምህርትና በስልጠና እድሎች ላይ ልዩ ድጋፍ የማግኘት መብት ያቀዳጃል። ነገር ግን ለሴቶች የሚደረጉ የድጋፍ እርምጃዎችን በተመለከት ብሔራዊ ፖሊሲ ባለመኖሩ ህገ መንግስታዊ መመሪያው በወጥነት መተግበር ይቀረዋል።

ሴቶችን ማጥመጃ

ዩጋንዳና ሩዋንዳን ጨምሮ ለሴቶች ተሳትፎ አስገዳጅ ኮታን የሚያስቀምጡ በርካታ አገራት አሉ። ነገር ግን ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የህግ መሰረት ባይኖራቸውም በአሁኑ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአባላቶችና የአመራር ቡድኖቻቸው እራሳቸው ያመጡትን የፆታ ኮታ ሲያስተዋውቁ ነበር፤ ተግባራዊነቱ በፓርቲዎቹ ፍቃደኛነት ላይ ይመረኮዛል።

ሚያዝያ 29፣ 2013 ዓ.ም በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት መሃል በመዲናዋ ከሚገኙ እንቅስቃሴ ከሚበዛባቸው ጎዳናዎች ውስጥ የሚገኙት ወደ ጋቦን ጎዳና የሚያመሩት ጎዳናዎች ተዘግተው ፤ ለብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርግ ሰው በበርካታ ሴቶች ተከቦ በድምጽ ማጉያ ይጮሃል። መልዕክቱ ግልጽ ነበር፡ ” ለብልጽግና የሚሰጥ ድምጽ ለሴቶች የሚሰጥ ድምጽ ነው’’ የሚል ነበር።

ብልጽግና በምርጫው 43 ሴት እጩዎችን በማቅረብ (ይህ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ካቀረበው የሴት እጩዎች ከፍተኛው ነው) አስገራሚ የፆታ መመጣጠን መፍጠር ችሏል። ነገር ግን ይህ ሴቶች ተሳታፊዎች ፓርቲውን ከልብ ፈልገው ከመቀላቀላቸው ይልቅ በሌሎች ምክንያቶች የመጣ ሊሆን ይችላል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህ የሆነው የገዢው ፓርቲና መንግስት አሁንም ድረስ ሊለዩ ባለመቻላቸው ነው ይላሉ።

አንድ ጥቅም ላይ የሚውል መጠምዛዣ መንገድ የፕሮዳክትቪ ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ነው። መጀመሪያ በ 1997 ዓ.ም ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያለባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ የተጀመረው ይህ እቅድ ከተወሰኑ እንደ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ ከሆነ ሴቶችን ለማጥመድ ጥቅም ላይ ይውል ነበር።

መጀመሪያ ከተደጎመው 450 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም በቅርቡ በአገሪቱ 11 ከተሞች ከተተገበረው የፕሮግራሙ አይነት ጀምሮ ይህን ፕሮግራም ወደ ተፈለገው አቅጣጫ ለመጠምዘዝ የተጋለጠ የሚያደርገው ነገር ተጠቃሚዎች የሚመረጡበት መንገድ ነው። ውሳኔዎች በቀበሌ ደረጃ የሚወሰኑ ሲሆን ዝርዝር መረጃ ባለመኖሩ የተነሳ በሚገባ አላማቸው ላይ ያተኮሩ አይደሉም ፤ ዝርዝር መረጃ አለመኖሩም የባለስልጣኖች የግል ግምገማ ላይ እንዲመረኮዙ የሚያደርግ ነው።

ሴት የብልጽግና ፓርቲ ደጋፊዎች አዲስ አበባ በተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ፥ ሰኔ 7፣ 2013፥ የአዲስ አበባ የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ።

የዓለም ባንክ ከግማሽ ሚሊየን ህዝብ በላይ ለመርዳት ከ738 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አብዛኛውን በመስጠት ለፕሮግራሙ መጀመር በግንቦት ወር 2012 ዓ.ም ይሁንታውን ገልጿል። አንዳንድ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ፕሮግራሙ በገዢው ፓርቲ የሴቶችን ድምጽ ለመጠምዘዝ ጥቅም ላይ ውሏል፥ ይህ የሴቶችን ድምጽ ለመጠምዘዝ ጥቅም ላይ ከሚውሉ በርካታ መንገዶች አንዱ ነው ይላሉ።

“መንግስት ምርጫ ሲቀርብ ሴቶችን እንደ ማበረታቻ ብቻ መጠቀሙን ማቆም አለበት’’ በማለት የኢዜማ የሴቶች ተወካይ የሆነችው ገነት ለኢትዮጵያ ኢንሳይት ተናግራለች።

ነገር ግን የፆታ ኢ-እኩልነት ጭራሽ እየጨመረ በሚገኝባት አገር (ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የፆታ ክፍተት ጠቋሚ ላይ ባለፈው አመት 15 ደረጃዎችን በመቀነስ ከ156 አገራት 97ኛ ሆናለች)፤የኢኮኖሚ ነፃነትን መፈለግ ሴቶች ፖለቲካን እንዲቀላቀሉ ወይም ጥቅም ለሰጣቸው እንዲመርጡ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

የምርጫ ቦርዱ ፓርቲዎችን በመጀመሪያ በመዘገበበት ወቅት (ቁጥራቸው በጊዜው 105 ነበር) ሴቶች ከመስራች አባላት ውስጥ ከአንድ አምስተኛ ያነሰውን ስፍራ ይይዙ ነበር። በአንድ በኩል የአሁኑ ምርጫ ብዝሃነት ያለው የበርካታ ፓርቲዎች ስርዓት እንደሚፈጥር ተስፋ የነበረ ቢሆንም በርካታ ፓርቲዎች ቢመረጡ እንኳን የሴቶች ቁጥር ውክልና አነስተኛ እንደሚሆን ስጋት ፈጥሯል።

በእርግጥም እንደ ዓለም አቀፍ ሪፓብሊካን ተቋምና ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ተቋም የምርጫ ዘገባ ከሆነ የሴት እጩዎች ቁጥር በ 2007 ዓ.ም 29 በመቶ የነበረ ሲሆን በ2013 ዓ.ም ይህ ቁጥር ወደ 21 በመቶ ወርዷል። ይህም በደኅንነት ስጋትና የገንዘብ አቅም ማነስ እንዲሁም ስለሥርዓተ- ፆታ የተሳሳቱ አመለካከቶች በመኖራቸው የመጣ ነው ይላል። በአጠቃላይ በዚህ አመት 1,982 ሴት እጩዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 16 በመቶ የሚሆኑት እጩዎች ለፌደራል ምክር ቤት 22 በመቶው ደግሞ ለክልል ምክር ቤት የተመዘገቡ ናቸው።

ዘገባው “ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ የሚገኙ ሴቶች የበለጠ ማስፈራሪያና በቅስቀሳ ወቅትም በደኅንነት ኃይሎች እንዲሁም በገዢው ፓርቲ ጣልቃ ገብነት ያጋጥማቸዋል” በማለት ጠቅሷል። ሌላ ባለፈው አመት የተካሄደ የቅርብ ጊዜ ግምገማ ሴቶች ሆን ብለው በፖለቲካ ለመሳተፍ ፈልገው ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚቀላቀሉት በፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ እንደ ስኬት ተደርጎ የሚቆጠረውን ኮታ ለማሟላት በፖለቲካ ፓርቲዎች ስለሚመለመሉ እንደሆነ ይጠቁማል።

ፕሬዘዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ በምርጫ ጣብያ፥ ሰኔ 14፣ 2013፥ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ

አልማዝ ሰቦቃ በኦሮሚያ ባሌ ዞን የሚገኘው የጎባ ወረዳ የምክር ቤት ተወካይ ስትሆን ኢህአዴግን ተቀላቀይ የሚል ጥያቄን ለአመታት ስትሸሽ ኖራለች። “አንድ ጊዜ እንዲያውም እንዲተዉኝ ስል ብቻ የቅርብ ቤተሰቤ ታሟል ብዬ ነበር። በጊዜው ፖለቲካ ጥሩ ምርጫ አልነበረም’’ ብላለች። ይህ የሆነው ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም ስልጣን እንደያዘ ሲሆን አልማዝም ችግር ነው የሚያመጣው በሚል ፍራቻ ከመቀላቀል ተቆጠበች።

አልማዝ አብዛኛውን የስራ ዘመኗን መምህር በመሆን አሳልፋለች። ኢህአዴግን ተቀላቀይ የሚለው ጥያቄ የመጣው በ20 አመቷ ከሮቤ የመምህራን ኮሌጅ ከተመረቀች ከአመት በኋላ ሲሆን ኢህአዴግን ከመቀላቀል ይልቅ የመምህርነት ስራዋን መቀጠልንና ሁለት ልጆቿን ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ መረጠች።

በ1997 ዓ.ም ባለቤቷ በድንገት በሞት ከተለየ ከአንድ አመት በኋላ አልማዝ በስተመጨረሻ ፓርቲውን ለመቀላቀል ወሰነች። ይህንንም ያደረገችበት ወሳኙ ምክንያት ማኅበረሰቧን እንደምታገለግል በመረዳቷ ነበር። ከዛን ጊዜ ጀምሮ አልማዝ ለብቻዋ እናትነትን፣ የፓርቲ ፖለቲካን እንዲሁም የዲግሪ ትምህርቷን እየተማረች መስራትን በአንድ ላይ ስታስኬድ ቆይታለች።

አልማዝ በትምህርት ላይ ያላት ልምድ በአካባቢዋ ባለው የትምህርት ቢሮ የመጀመሪያዋ የሆነውን የመሪነት የስራ ኃላፊነት እንድታገኝ አስቻላት ከዛም የወረዳው ጉባኤ አፈ ጉባኤ መሆንን ጨምሮ ተጨማሪ የስራ ኃላፊነቶችንም ልታገኝ ችላለች። ከአስር አመታት የፖለቲካ ተሳትፎ በኋላ እጩ በመሆን የተመረጠች ሲሆን በ2007 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫም በምክር ቤት መቀመጫ ማግኘት ችላለች።

“በርካታ ችግሮችን አሳልፌያለሁ። በራስ ችሎታ ማመንና የራስ መተማመን እንዲኖር ማድረግ ከባድ ነው፥ ግን ከሌሎች ሰዎች በተሻለ ሁኔታ መስራት እንደምንችል ሁሉ እንረዳለን’” ትላለች።

የብቸኝነት ጉዞ

ሴት የምክር ቤት አባላት ከጨመረው ቁጥራቸው ጋር የሚመጣጠን ሚና (የስራ ኃላፊነት) ግን ገና አልያዙም። ይህ በበርካታ ምክንያቶች የሚመጣ ሲሆን ከነዚህም ምክንያቶች ውስጥ ሴቶች ለፓርቲያቸው ቁርጠኛ (ታማኝ) አለመሆናቸው፣ የልምድ ማነስ እንዲሁም በቤት ውስጥ ዋና የቤተሰብ ተንከባካቢ መሆናቸው ይገኙበታል።

“በሌሎች የፓርቲ አባላት ለምን ስጋቶቻችንን እንዳነሳን የተጠየቅንበት ጊዜያቶች አሉ። ጥያቄዎቹ እንዲጠየቁ ይፈለግ የነበረው ወንዶቹ ለማቅረብ በሚፈልጉበት መንገድ ብቻ ነበር’’ ትላለች አልማዝ።

ስንዱ ገብሩ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት የምክር ቤት ተመራጭ ሆና በመመረጥ ታሪክ ከሰራች ወደ ሰባ አመታት ገደማ አልፏል። በዛኔና በአሁኑ ጊዜ መሃል የሴቶች ቁጥር በፍጥነት አድጓል። ሴቶች የመጀመሪያ ሴት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ከመሆን ጀምሮ ሌሎች በርካታ ለሴቶች የመጀመሪያ የሆኑ ነገሮችን አሳክተዋል።

እየጨመሩ ያሉት ቁጥሮች ግን ኢትዮጵያውያን ሴቶች የሚጋፈጡትን እውነታ ያሳብቃሉ። ይህም እውነታ ሴቶች በወንዶች ብቻ የተያዙ ስፍራዎችን ማለፍ የሚጠበቅባቸው መሆኑ ሲሆን ይህም ድምጻቸውን ለማሰማት የሚያስፈልግ የህይወት ክህሎት ነው። እነዚህ ወንዶች ብቻ የሚገኙባቸው ስፍራዎች ወንዶች ከሴቶች ጋር የሚጋሯቸው የጋራ ተሞክሮዎች እምብዛም የማይገኙባቸው ናቸው።

መአዛ አሸናፊ፣ የመጀመርያዋ ሴት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ጉባኤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ግንኙነትን ለማሳለጥ የተመሰረተ ሲሆን በቅርቡ እንደተሾመችው የጉባኤው ጠቅላይ ጸሀፊ ራሄል ባፌ ከሆነ በዚህ የምርጫ ወቅት የጉባኤው ተግባራት በከፊሉ በፓርቲዎች መካከል የጋራ መግባባትን መፍጠርና ለሴት አባላት የፖለቲካ ስልጠና መስጠት ነበር።

“ከፍተኛ ልምድ ካካበቱ ሴት ፖለቲከኞች ጋር ውይይት በማድረግ እንዲመጡና እንዲሳተፉ፤ ለተሳታፊዎቹ ልምዳቸውን እንዲያጋሩ ጠይቀናል” ብላለች። ግን እዚህ ራሱ ከፓርቲዎች እውነተኛ ቁርጠኝነት አልነበረም። ይህ ክስተት ራሄል ለረዥም ጊዜ ፖለቲከኛ የነበረች እንደመሆኗ ራሷ ያስተዋለችው ነገር ነው። የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ አባል ሆና መሳተፍ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከእሷ ውጪ ሴቶች በሌሉባቸው ክፍሎች ተቀምጣለች እንዲሁም ተናግራለች።

‘’ማንም ከኔ ጋር ተመሳሳይ የህይወት ተሞክሮ የማይጋራ መሆኑ በመጀመሪያ ከባድ ነበር፤ ግን ለመድኩት’’ ትላለች።

አሁን ከሁለት አስርት አመታት ገደማ በኋላ ከ50 በላይ አባላት ያሉት ጉባኤ ኃላፊ ሆናም ሁኔታው በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው።

“ሴት ተወካዮች የሚገኙት እጅግ በጣም አልፎ አልፎ ነው፤ ሲገኙም አንድ ሰው በመውጣቱ ምክንያት ያንን ሰው በመተካት ነው የሚገኙት” ብላለች።

ዘመናዊ ጋሬጣዎች

በሴቶች የፖለቲካ ጉዞ ላይ ላዩን ያለ እመርታን የሚያሳዩ ቁጥሮች ራሳቸው የፌደራልና ክልላዊ ልዩነቶችን ያሳያሉ። በፌደራል ደረጃ የሚገኘው 20 ሚኒስትሮችን የሚይዘው ካቢኔ የፆታ ቁጥሩ ለመመጣጠን የተቃረበ ሲሆን ይህ መጠን ወደ ክልል ካቢኔዎች ሲመጣ በግማሽ ቀንሶ እናገኘዋለን። በተባበሩት መንግስታትና በመንግስት በጋራ እንደወጣ ዘገባ ከሆነ የዞን ካቢኔዎች ላይ ይህ የፆታ መመጣጠን (እኩልነት) ከዚህም በባሰ ደረጃ በመውረድ 18 በመቶ ላይ ይገኛል።

በዝቅተኛ አስተዳደር ደረጃዎች ላይ የሴቶች ተሳትፎ ህብረተሰቡ አባታዊ ስርዓት ያለው ከመሆኑና ከዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ የሚመጣ ነው። ነገር ግን ይህ በዋና ከተማ የሚገኙ ፣ ወጣት፣ የተማሩና የከተማ የፖለቲካ ልሂቃን በመሆናቸው ከሌሎች ሰዎች እንዲበልጡ የሚያስችል እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ በሚያገኙ ሴቶችም ዘንድ የሚስተዋል ነው።

አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማን የምትወክለው የኢዜማ እጩ የሆነችው ናርዶስ ስለሺ በሮትራክት ክለብ ለአስር አመታት አባልና መሪ በመሆን የቀሰመችው ልምድ በፖለቲካው ውስጥ መንገዷን እንድታገኝ አስፈላጊውን መሳሪያ ሰጥቷታል። ናርዶስ በሮትራክት ክለብ በነበራት የዘጠኝ አመታት ቆይታ እጅግ በጣም በጥሩ ሁኔታ በመስራት፤የካንትሪ ክለብ ጸሀፊ ከዛም ኬንያ፣ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳንን የሚያካትተው የዲስትሪክት ሮትራክ ክለብ ፕሬዝደንት እስከመሆን ደርሳለች።

የ28 አመቷ ወጣት በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከነበረችበት ክለብ ጋር በመሆን የተማሪዎች ምገባ ላይ ሰርታለች፤ ይህም የከተማይቷ የቀድሞ ከንቲባ ታከል ኡማ የትምህርት ቤት ምገባን ከከተማይቷ ትልቅ እቅዶች ውስጥ አንዱ በማድረግ በ2012 ዓ.ም ከማስጀመሩ በፊት ነበር።

“በክለብ ውስጥ እንሰራባቸው የነበሩ በርካታ ጉዳዮች የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ በፖለቲካዊ ደረጃ ሊፈቱ የሚችሉ እንደሆኑ ተገነዘብኩ’’ ትላለች ፓርቲውን ለመቀላቀል ያነሳሳትን ምክንያት ስትገልጽ። ኢዜማን መቀላቀሏ በርካቶችን ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነበር። በርካታ ጓደኞቿ ከፖለቲካ ተሳትፎዋ ምን ይገኝ እንደሆነ ይጠይቁ ነበር። ቤተሰቦቿ ምንም እንኳን ሃሳባቸው ተከፋፍሎ የነበረ ቢሆንም ጣልቃ አልገቡም።

ኢዜማ የሴት አባላት ቁጥሩን 30 በመቶ ማድረስ የቻለ ሲሆን ከ19 መሪዎቹ ውስጥ 6ቱ ሴቶች ናቸው። ፓርቲው 2,000 እጩዎች ያሉትና በብሔራዊ ደረጃ የተወዳደረ ሲሆን ከነዚህ እጩዎች ውስጥ 180 ሴቶች ናቸው።

ናርዶስ ከአመት ባነሰ ጊዜ የፓርቲው እጩ መሆን የቻለች ቢሆንም ይህ መሆን የቻለው ግን ከከፍተኛ ትግል በኋላ ነው። “ከበርካታ ሰዎች እኔ በእድሜ አንሳለሁ፣ በዚህም የተነሳ የእውነት እየተወዳደርኩ እንደሆነ ማመን ከብዷቸው ነበር’’ ትላለች።

ናርዶስ በስብሰባ ጊዜ ወንዶቹ ሴቶቹ ቡና እንዲያፈሉ ይጠብቁ ስለነበረበት ጊዜ ስትናገር “ቡና ከማፍላት በዚህ ስብሰባ በመሳተፍ ለናንተ የበለጠ እጠቅማለሁ” ለማለት ተገድጄ ብላለች። “ቡድኑን የመምራት እድል ነበረኝ እናም ችሎታዬን ለማሳየት ተጠቀምኩት” ብላለች።

አባላቱ ምርጫ አደረጉ፥ በመጨረሻም ምርጫውን በማሸነፍ ናርዶስ ለፌደራል ምክር ቤት እጩ ሆነች። ከተማረና ከሚያበረታታ ቤተሰብ የተገኘች ቢሆንም የእኩልነት መልዕክት የራሷን ቤት ጨምሮ ገና የብዙዎችን ቤት ማንኳኳት እንዳለበት ካለፈው ምርጫ መረዳት ችላለች።

አንዲት እናት አንጦጦ አከባቢ ድምጽ ስትሰጥ፥ ሰኔ 11፣ 2012፥ አሶሽየትድ ፕሬስ።

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት እናቷ በመታመሟ ሁለት ስራ እየሰራች የቤተሰቡ ገቢ እንዳይጓደል ማድረግ፣ እናቷን መንከባከብ  በተጨማሪም የቤተሰቡን ምግብ ማብሰል ነበረባት። ‘’አባቴና ወንድሜ ከጊዜው ጋር የሚራመዱ ናቸው፤ በእኩልነት ያምናሉ ይደግፉኛልም። ግን ችግሩ ለራሳቸው ምግብ ለማዘጋጀት ወደ ኩሽና አይገቡም ስለዚህ ያ ኃላፊነት እኔ ላይ ይወድቃል’’ ብላለች።

ይህ ሁሉ መስዋዕትነቷ ግን ለምርጫ እጩ ሆና በተመረጠች ጊዜ ችሎታዋና ቁርጠኝነቷ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ነው ያደረገው። “እዚህ መሆን እንደሌለብኝ አይነት አቀባበል ነበር የገጠመኝ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠብቁት ቁርጠኝነት ከስራ ያለክፍያ እረፍት እስከመውሰድ ድረስ ይደርሳል እኔ ግን ከስራዬ እረፍት ለመውሰድ አልችልም” ብላለች።

ሴቶች ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ውድድሩ ወደ ሚጀመርበት መስመር እንዲቃረቡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገኝ የገንዘብ ድጋፍና የእነዚህ ተቋማት የገንዘብ አቅም (ጥንካሬ) እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው።

እንደ ናርዶስ ያሉ ሴቶች ታሪካዊ ሸክሞች የሚጋረጡባቸው ሲሆን በተጨማሪም እድል እንዲሰጣቸው እራሳቸውን ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።

ይህ በቦርዱ በአጠቃላይ የሚገኙ ሴቶች፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት እንዲሁም በመንግስት ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በሙሉ የሚያጋጥማቸው ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ሴቶች እንዲሰባሰቡ ይህ መንስዔ ሆኖ ጥቅም ላይ የመዋሉ ጉዳይ ገና ቢሆንም ሁሉም ግን የሚኖሩት ህይወት ነው።

“ሴቶች እቤት ሲሄዱ ቤተሰቦቻቸውን ይንከባከባሉ ወንዶች ግን እቤት ሲሄዱ ጉግል በማድረግ የበለጠ ነገር ይማራሉ። ለዚህም ነው በአገሪቷ በሴቶች የፖለቲካ አቅም ሰፊ ክፍተት የምናየው” በማለት የብልጽግና የሴቶች ሊግ ኃላፊ የሆነችው መስከረም ተናግራለች።

መስቀለኛ መንገድ?

በቅርቡ የኢትዮጵያ የህግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር በምርጫ ወቅት ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በሚል በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የምርጫ መገምገሚያ ጀምሯል።

አሁን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት የሆኑትና ይህንንም የኃላፊነት ስፍራ ለመያዘ የመጀመሪያ ሴት የሆኑት መዓዛ አሸናፊ ከሌሎች ጋር በመሆን በጋራ የመሰረቱት የኢትዮጵያ የህግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ባለፉት ጊዜያት ሴቶችን ወክሎ በመስራቱ ኢላማ ተደርጓል፥ በተጨማሪም በሴቶች መብት ጉዳይ መንግስትን በመተቸቱ የተነሳ ስራው ሁሉ እንዲቋረጥ ተደርጎ ነበር።

በቅርብ መተግበር የጀመረው የማኅበሩ ፕሮጀክት እንደ የፖለቲካ እጩ ሆኖ መወዳደር፣በምርጫ ስፍራዎች መስራት ወይም መምረጥ የመሳሰሉ የሴቶች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር የሚያሰቡ ድርጊቶችን ይከታተላል። ይህ ለመምረጥ ሰልፍ ይዘው በሚጠብቁ ጊዜ የሚጎነተሉና ትንኮሳ ሚደርስባቸውን ሴቶች እንዲሁም አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት እንዲሁም የስነልቦና ኢኮኖሚያዊ ጥቃትን ያካትታል።

“ምርጫዎችን ባለፉት ጊዜያት ስንከታተል ነበር (ለምሳሌ ፍትሐዊነትን በመገምገም)፤ነገር ግን ሥርዓተ-ፆታ ላይና የሴቶች ተሞክሮ ላይ አተኩረን አናውቅም” ብላለች የኢትዮጵያ የህግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ኃላፊ የሆነችው ሌንሳ።

ሴት እጩዎች በምርጫ ቅስቀሳ ላይ የሚያጋጥማቸው ስም ማጥፋት፣ ማስፈራራትና የቃላት ጥቃት እምብዛም ከማይታይ ነገር ግን ሴቶች በምርጫ ወቅት ከሚያጋጥማቸው ዋነኛ የስነልቦና ጥቃት ውስጥ የሚመደብ ሲሆን የኢኮኖሚ ጥቃት ደግሞ እንደ ፕሮዳክቲቭ ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ያሉትን ድምጽ ለማግኘት እንደ ወጥመድ መጠቀም ነው።

በመጀመሪያ ዘገባው ድርጅቱ ሴቶችን ማስፈራራት ከምርጫው ቀደም ብሎ በነበሩት ጊዜያት 350 ታዛቢዎች ከጠቆሙት የህግ ጥሰቶች መካከል እጅግ ከፍተኛ ድርሻውን የሚይዝ እንደሆነ ከነዚህም ውስጥ 41ዱ ክስ እንደተመሰረተባቸው ዘግቧል።

በአንድ የአዲስ አበባ ምርጫ ጣብያ ሴቶች ድምጽ ለመስጠት በሰልፍ ላይ፥ ሰኔ 14፣ 2013፥ አዣንዝ ፍራንስ ፕሬስ

“ሰዎች ይህ የሥርዓተ-ፆታ ምልከታ የማይረባ እንደሆነ ነው የሚያስቡት። ሴቶች በዚህ የሚጎዱ አይመስላቸውም ምክንያቱም በፖለቲካ ምክንያት የወንዶችን ያህል ለእስር ስለማይዳረጉ ነው፥ ነገር ግን ከብዙ ጎጂ ተግባራት መካከል ጥቂቱን ብቻ ነው ግልጽ ማረግ የቻልነው’’ ብላለች ሌንሳ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጫ የመረጠችው የ26 አመቷ ሳራ ተስፋዬ በዚሁ ምክንያት ነው ድምጿን ሳትሰጥ የተመለሰችው። የምርጫ ቦርዱ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ዘግይቶ መጀመሩን ተከትሎና በከፊልም የመራጮችን ረዥም ሰልፎች ለማስተናገድ በማሰብ የአገልግሎት ሰዓቶቹን አራዝሞ ነበር።

‘’እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት ድረስ ተሰልፌ ነበር። ወደ ቤት የሚሸኙኝ የተወሰኑ የሰፈር ጓደኞች ነበሩኝ ግን ከዛ በላይ መቆየት አልቻልኩም’’ ብላለች ሳራ።

የኢትዮጵያ የህግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ዘገባ በ1990ዎቹ አጋማሽ ገደማ ከተካሄዱት የቀድሞ ጥናቶች ጋር በሚያስደነግጥ መልኩ ይመሳሰላል።

“ቁጥሮቹ ተቀይረዋል ግን ጉዳዮቹ በአብዛኛው ተመሳሳይ ሆነው ቆይተዋል’’ ብላለች ሌንሳ። አክላም “ይህ ጥናት ፆታዊ ትንኮሳ ላይ ግልጽ ህግ እንዲኖር መሰረታዊ የሆነ መረጃ ለማቅረብ የታለመ ነው’’ ብላለች።

እንደ የኢትዮጵያ የህግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ከሆነ ማንኛውም የሴቶችን መብት የሚጻረር ነገር ለምሳሌ በጫካ መሃል የሚገኝ የምርጫ ጣቢያ፣ሴቶች በቤት ውስጥ ያለባቸውን ኃላፊነትን ባላገናዘብ ሁኔታ በግድ የለሽነት የሚታቀዱ የስብሰባ ሰዓቶች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ጉዳይ ቁም ነገር እድርገው እንዲወስዱ አስገዳጅ ድንጋጌዎች ያለመኖራቸው ጉዳይ የጥቃት መገለጫ ነው።

‘’ምንም አይነት ውለታ እየጠየቅን አይደለም። ይህ መብታችን ነው-በግልጽ የተጻፈ ነው’’ ብላለች ሌንሳ።

Query or correction? Email us

Follow Ethiopia Insight

ይህ ጽሁፍ ምርጫ 2013ን በሚመለከት ዘለግ ያሉ ጽሁፎችን ከመላው ኢትዮጵያ በተከታታይ የምናቀርብበት የ “Ethiopia Insight Election Project (EIEP)” ክፍል ነው።

ዋና ምስል: ፎርብስ መጽሄት በ2020 (እ.ኤ.አ) ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአለም ካሉ ከፍተኛ አቅም ካላቸው (powerful) ሴቶች መሃከል ናቸው ማለቱን ተከትሎ ሴት የመንግስት ባለስልጣናት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅን እንኳን ደስ አለዎት እያሉ፥ ከመአዛ አሸናፊ የትዊተር አካውንት የተወሰደ።

Join our Telegram channel

Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished.

We need your support to analyze news from across Ethiopia
Please help fund Ethiopia Insight’s coverage
Become a patron at Patreon!

About the author

Maya Misikir

Maya is a freelance journalist based in Addis Abeba, Ethiopia. While writing is her chosen way of self-expression, playing rugby comes as a close second.

2 Comments

  • All achievement is applauded, however I dare the Ethio women to stand up for PEACE in the midst of war. Sad to see they are following the usual male war mongering…..

  • I am not sure you should be copying the West and complaining just for the sake of complaining which is what I think you are doing. Ethiopia’s evolutionary change is better than the fake revolutions the West have undergone. Women are not free in the West, I don’t care what you think you see. When you go even skin deep, White woman are prisoners of expectations of who they can marry, and love. Black lives are valued at a far lower level than others. No Western woman has the freedoms and privileges that an Ethiopian woman has, and Ethiopian woman are slowly and surely gaining ground. Go the slow and steady route.

Leave a Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.