In-depth

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዋሻ በሩቅ የምትታየው የተስፋ ጮራ

ለጥቃት ሰለባዎች ከወገንተኝነት የጸዳ የተቆርቋሪነት ስሜት ማሳየት፣ በልሂቃን መካከል የሚደረግ ውይይትና በማሕበረሰብ ደረጃ ጥልቅ የሆነ ራስን የመፈተሽ እርምጃ ኢትዮጵያን ሊታደጋት ይችላል፡፡

ኢትዮጵያ አዲስ አመት ለወትሮው ተስፋ የሚሰነቅበት  ቢሆንም ባለፈው ወር ግን የጭለማ ደመና አጥልቶበት ተስተውሏል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን መጪው ዘመን ለአገራቸው ይዞት የሚመጣው ሁኔታ ለፍርሃት ዳርጓቸዋል፤ በእርግጥም ደግሞ በቅርቡ የተከናወኑት ክስተቶች ይህ ስጋታቸው ምክንያታዊ እንደሆነ በተጨባጭ አሳይተዋል፡፡

ይህም ‹‹ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚያደርገን ምክንያት ይኖር ይሆን?›› ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ እኔ በበኩሌ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን አስቀድመን የልዩነቶቻችንን ሸለቆ የሚያሻግር ውይይት ለማድረግ የሚያስችል መላ ልንፈልግ ይገባል፡፡

በሰኔ 29 ከኢትዮጵያ ከዋክብት አንዱ የሆነውና ቀልብ በሚገዙየኦሮምኛ ዘፈኖቹ የሚታወቀው ሃጫሉ ሁንዴሳ በጥይት ተመትቶ ህይወቱ አለፈ፡፡ በዚህም በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጥልቅ ሃዘን ያደረባቸው ቢሆንም ይህን ተከትሎ የተፈጠረው ግን ከሞቱ የከፋ አሳዛኝ ክስተት ነበር፡፡ ከሞቱ ጥቂት ሰአታት በኋላ በኦሮሚያና በመዲናይቱ አዲስ አበባ ተቃውሞ ተነሳ፡፡ ወዲያው ተቃውሞው ወደ ሁከት ተቀይሮ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከመቶ ሃምሳ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ቀጠፈ፡፡

ስለክስተቱ አሁንም የማይታወቁ ነገሮች ቢኖሩም ግልጽ የሆኑ እውነታዎች ግን አሉ፡፡ አንደኛ፣ ምንም እንኳ ይፋ የተደረጉ መረጃዎች ከሰለባዎቹ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች እንደሆኑ ቢገልጹም ሁከቱ አብዛኛውን ጊዜ ያነጣጠረው የአማራ ብሔር ተወላጆች እና አጋሮቻቸው እንደሆኑ በሚታሰቡ(ለምሳሌ አማራ ያልሆኑ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች) ላይ ነበር፡፡ ሁለተኛ፣ ምንም እንኳን የሃጫሉ ግድያ ለሰላም መደፍረሱ መነሻ ቢሆንም የተወሰኑ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ኦሮሚያ ውስጥ በሚኖሩ  አማሮች ላይ የያዙት ስር የሰደደ ቅሬታ ለሁከቱ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡

ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፣ መንግስት በጃዋር መሐመድ ጉዳይ ላይ ያሳየው  ዝርክርክነት እየጋለ የመጣው ቅሬታ ወደ ጥቅምት 2012   ሁከት እንዲለወጥ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ የሂደቱን ፈለግ ወደኋላ በመመለስ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከደርግ ወደ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የመንግስት ስልጣን ሽግግር በተደረገበት ወቅት በተፈጠረው የደህንነትመዋቅር ክፍተት እንደ በደኖና ኣርባ ጉጉ ባሉ የኦሮሚያ ቀጠናዎች በሚኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ከማስቻሉ ጋር ልናቆራኘው እንችላለን፡፡

የሚያሳዝነው በኦሮሞ ተቃዋሚዎች ዘንድ በቅርቡ በተከሰቱ የፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ የመረረ ቅሬታ የሚስተዋል በመሆኑ ይህን የመሰለ ሁከት ከመቀስቀስ አንጻር የሃጫሉ ሞት የመጨረሻው ክስተት አለመሆኑ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ በኦሮሚያ የሚኖሩ አናሳ ብሔረሰቦች የሕይወት ዋስትናቸው አስተማማኝ አይደለም፡፡

ምንም እንኳን ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት ኦሮሚያን የብሔር ግጭቶች ማዕከል የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ደግሞ ከሌሎች በተለየ የሁከቱ ግንባር ቀደም ተዋንያን የሆኑ መስሎ እንዲታይ ያደረገ ቢሆንም ችግሩ ከዚያ በእጅጉ የተስፋፋ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን መውጣትና የፖለቲካ አውዱ ነጻ መሆን ልጓም ያልተበጀለት ብሔረተኝነት እንዲሰፍን መንገድ ከፍቷል፡፡ ይህም ከደሕንነት መዋቅሩ አንጻራዊ ድክመትጋር ተጣምሮ ላለፉት ሁለት አመታት በመላ ሃገሪቱ የብሔር ግጭቶች እንዲከሰቱ ምክንያት ሆኗል፡፡

በተለይም ከጥር እስከ ጥቅምት 2012 በነበሩት ወቅቶች በአማራ ክልል አናሳ ብሔረሰብ በሆኑት ቅማንቶች ላይ የተፈፀመ ጥቃት( እንደ አማራ አክቲቪስቶች ደግሞ በቅማንት ሚሊሻዎች የተፈጸመ ትንኮሳ) የተስተዋለበት በዚህም ሰበብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበትና ሺዎች የተፈናቀሉበት ጊዜ ነበር፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝም በቁጥር አናሳ የሆኑት የአማራየኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የጥቃት ኡደት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ በመተከል ዞን በተነሳና ለሳምንታት በቆየ ጥቃት እንኳን በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አልፏል (እንደ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ዘገባ ከ160 በላይ የአማራ ብሔር ተወላጆች በጥቃቱ ተገድለዋል)፡፡ በአማራ ክልል በሚኖሩ የጉሙዝ ብሔር ተወላጆች ላይም የደረሰው የጅምላ ጭፍጨፋም ሌላው  አሰቃቂ የሆኑ የብሔር ግጭቶች እየተስፋፉ ለመምጣታቸው ማሳያ ነው፡፡

መጥፎ ትርክቶች

ምናልባት እያጣናቸው ካሉት የንጹሐን ሰዎች ሕይወት እና እያሳለፍነው ካለው የሕሊና ቁስልም በላይ ይበልጡን አሳዛኝ የሆነው ነገር የተለያዩ የፖለቲካ ጎራዎችና አጋፋሪዎቻቸው የሆኑት የመገናኛ ብዙሃን ክስተቱን እያቀረቡበት ያለበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህም ልዩነቶች እየሰፉና ግጭቶችም እየተባባሱ እንደሚሄዱ አመላካች በመሆኑ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡

ለምሳሌ የኦሮሞ ብሔረተኞችና እንደ ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ.ኤም.ኤን) ያሉ የነሱን ሐሳብ የሚያንጸባርቁ ሚዲያዎች የሃጫሉን ሞት ተከትሎ በብሔር ግጭት ውስጥ የተሰማሩ የኦሮሞ ወጣቶችን ለማውገዝ አንዳችም ሙከራ አላደረጉም፡፡ በተመሳሳይ በጥቅምት 2012 የኦሮሞ ነውጠኞች ኦሮሞ ያልሆኑ ወገኖችን በገደሉበት ወቅት በአመዛኙ ዝምታን መርጠዋል፡፡

ሌላ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በመስከረም 2011 የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የግንቦት ሰባት አመራሮች ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ተከትሎ በተጠራው የድጋፍ ሰልፍ ወቅት የተከሰተው በአስርት የሚቆጠሩ ነፍሳትን የቀጠፈው የቡራዩ ጭፍጨፋ ነው፡፡ በወቅቱ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ የኦሮሞ ብሔረተኞች ጥቃቶቹን ከመኮነንና ድርጊቱን የፈጸሙትን የኦሮሞ ወጣቶች ከማውገዝ ይልቅ ጣታቸውን ወደ ሌላ መጠቆምና የፈጠራ ትርክቶች ላይ ተጠምደው ነበር፡፡ ለምሳሌ ጃዋር መሐመድ አንዳችም መረጃ ሳያቀርብ ግጭቱ ‹‹የፌዴራል ስርአቱን ለመናድ›› የተጠነሰሰ ሴራ ውጤት እንደሆነ ገልጾ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨመሪም ኦ.ኤም.ኤን ላይ ባደረገው ቃለ ምልልስ በመንግስት ሚዲያዎች ከቀረበው ወገንተኝነት ከተስተዋለበት ዘገባ በተቃራኒ በመዲናይቱ አዲስ አበባ 43 የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መገደላቸውንና ይህም የጥቃቱ ሰለባዎች ኦሮሞዎች መሆናቸውን እንደሚያሳይ ገልጾ ነበር፡፡ ነገር ግን ለዚህ ገለጻ ደጋፊ የሚሆን አንዳችም ማስረጃ ያላቀረበ ሲሆን ይህም ገለጻው ሐሰት ነው ያሰኛል፡፡

የኢትዮጵያዊነት ጎራ አቀንቃኞችና የሚዲያ ተቋማቶቻቸውም ከዚህ ችግር ነጻ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ የጥቅምት 2012ን ጭፍጨፋ ያቀረቡበትን ሁኔታ እንውሰድ፡፡ በዚህ ጎራ በሚካተቱ በርካታ ሰዎች እይታ በግጭቱ ለተገደሉት 86 ሰዎች ነፍስ መጥፋት ተጠያቂው ጃዋር ነው፡፡ ይሁን እንጂ የውጪ ፓስፖርት ያላቸው የሚዲያ ባለቤቶች ግጭት እየቀሰቀሱ እንደሆነና መንግስትም በነሱ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ፓርላማ ላይ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፤ ይህ ደግሞ ጃዋርን አስመልክቶ የተነገረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ከአንድ ቀን በኋላ የፖሊስ አባላት በወቅቱ የሚዲያ አክቲቪስት የነበረውን የጃዋርን መኖርያ በሌሊት ከበው ጠባቂዎቹ ጥለውት እንዲሄዱ ሲያስገድዱ ነበር፡፡

ጃዋር ይህን ስጋቱንና ለግጭት መነሻ የሆነውን ክስተት በፌስቡክ ድረ ገጽ ለተከታዮቹ አካፍሏል፡፡ በእርግጥ ይሄንን ተከትሎ የከፋ ግጭት ተከስቷል፣ ነገር ግን ጃዋር ይህንን ሁኔታ በፌስቡክ መለጠፍ አልነበረበትም ብሎ መሞገት ራሱን የመከላከልም ሆነ ሐሳቡን የመግለጽ መብት የለውም እንደማለት ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ላይ ጃዋር ደጋፊዎቹ ከሁከት እንዲታቀቡ ጥሪ በማቅረብ ሁኔታው እንዲረጋጋ መማጸኑ ሊታወስ ይገባል፡፡ በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልልን በውክልና በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ያሉት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ፖሊሶች ወደ ጃዋር መኖሪያ መሄዳቸው ስሕተት መሆኑንና ክስተቱም ምርመራ እንደሚደረግበት፣ መንግስትም የጃዋርን ደህንነት እንደሚያረጋግጥ ገልፀው  ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያዊነት ጎራ አቀንቃኝ ከሆኑ ሰዎች በርካቶቹ አጀንዳቸውን ለማራመድ እንዲመቻቸው ጃዋርን በተናጠል ተጠያቂ ማድረግን መረጡ፡፡ በእውነት ለጥቃቱ ሰለባዎች ቢቆረቆሩና ለፍትሕ ቁርጠኛ ቢሆኑ ኖሮ የፖለቲካ ነጥብ ከማስቆጠር ይልቅ ከመንግስት ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ይጠይቁ ነበር፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያዊነት ጎራ ተከታዮች “አሁን በኢትዮጵያ የተስፋፋው የብሔር ግጭት የሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ስርአቱ ተጠያቂ ነው” የሚለውን ትርክት አለማቋረጥ የማቀንቀን አዝማሚያ ይታይባቸዋል፡፡ ብሔር ተኮር ወንጀሎችም በተፈጸሙ  ቁጥርም  ወንጀሎቹን  ይህን ሙግት ለማቅረብ ይጠቀሙባቸዋል፡፡

ምንም እንኳ የሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም አንዳንድ ጠባያት ለግጭቶች አስተዋጽኦ ማበርከታቸው አጠራጣሪ ባይሆንም ስርአቱን አሁን እየተከሰተ ላለው ሁኔታ ብቸኛ ተጠያቂ ማድረግ በአግባቡ ሁኔታውን እንድንረዳ አያስችለንም፡፡ አንደኛ፣ የብሔር ፌደራሊዝሙ የፓርቲና የመንግስት አሰራር አምባገነናዊ በነበረባቸው የኢሕአዴግ አመታት በስራ ላይ  የነበረ ቢሆንም በነዚያ ጊዜያት እንደአሁኑ አይነት መጠነ ሰፊና አስከፊ የብሔር ግጭቶች  እምብዛም አይከሰቱም ነበር፡፡

ሁለተኛ፣ ብሔርን መሰረት ያደረገ የፌደራል ስርአት በማይተገበርባቸው የአፍሪካ አገሮች አሰቃቂ የብሔር ግጭቶች በብዛት ይከሰታሉ፡፡ለምሳሌ በአንጻራዊነት የተሻለ ዲሞክራሲ አላት በምትባለው ኬንያ ባለፉት አስር አመታት የብሔር ግጭት ለሺዎች ሞትና መፈናቀል መንስኤ ሲሆን ይህን መሰል ግጭት የመከሰት እድሉ አሁንም ከፍ ያለ ነው፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያዊነት ጎራ አቀንቃኞች  የብሔር ፌደራሊዝምን ማስወገድ እንዴት አድርጎ የብሔር ግጭትን እንደሚያጠፋ ሊነግሩን ይገባል፡፡

በተመሳሳይ በዚሁ የርዕዮተ ዓለም ጎራ ሲገለጽ የሚደመጠው ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝሙ ብሔረተኝነትን ወልዷል የሚለው ትርክት ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ቢያንስ እንኳን ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ማብቂያና ከዋልልኝ መኮንን የ1969 ታዋቂ ጽሑፍ አንስቶ ብሔረተኝነት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማጠንጠኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡

እንደውም በተቃራኒው (ምናልባትም የሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም በጎ አስተዋጽኦ ተደርጎ ሊወሰድ በሚችል ሁኔታ) በደርግና በኃይለ ሥላሴ ዘመን ከነበረው ጋር ሲነጻጸር  ብሔርተኝነት አሁን ቀንሷል፡፡ በቅርብ አስርት አመታት የመገንጠል አላማን ገፍተው የሚያራምዱ ብሔረተኛ የነጻ አውጪ ግንባሮች አልተስተዋሉም፡፡ በደርግ ዘመነ መንግስት ማብቂያ እንደ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የአፋር ነጻነት ግንባር፣ ምእራብ ሶማሌ ነጻነት ግንባርና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ያሉ ሕዝባዊ ድጋፍ የነበራቸው በርካታ ቡድኖች መገንጠልን አንግበው ይፋለሙ ነበር፡፡

ምናልባት እነዚህ ቡድኖች የመገንጠል እንቅስቃሴያቸውን ወደ ማርገብ የደረሱት የራስን እድል በራስ የመወሰንና የመገንጠል መብቶች በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 39 ሕጋዊ እውቅና ስለተሰጣቸው ነው የሚለው መከራከሪያ ምክንያታዊ ነው፡፡ ለመገንጠል ለሚደረጉ ንቅናቄዎች ሕዝቡ  የነበረው ድጋፍም የቀነሰ ይመስላል፡፡ የዚህ ምክንያቱ የፌዴራል ስርአቱ (ቢያንስ በወረቀት ላይ) ብሔሮች ከአገሪቱ መገንጠል ሳይኖርባቸው ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ክብርና እውቅያ እንዲጎናፀፉ እንዲሁም ራስን በራስ የማስተዳደር  መብት እንዲኖራቸው ወዘተ ስላስቻለ ነው የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡

ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያዊነት ጎራ ያሉ ወዳጆቻችን ሊገነዘቡ የሚገባቸው የክልሎችን የብሔር መሰረት በመናድ የፌዴራል አወቃቀሩ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማድረግና ሕገ መንግስቱ ለቡድን መብቶች የሚሰጠውን ትኩረት ቀንሶ የግለሰብ መብቶችን ለማረጋገጥ በሚል አካባቢያዊ ፌደራሊዝምን ለመተግበር የሚደረጉ ጥረቶች ለእርስ በርስ ጦርነት ሊዳርጉ የሚችሉ መሆኑን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ከዚህ  እጣ ፈንታ  ቢያመልጥ እንኳን የፌዴራል አወቃቀሩን ማፍረስ ደርግን ለውድቀት የዳረጉ ብሔርን መሰረት ያደረጉ የሽምቅ ውጊያዎች እንዲያንሰራሩ ሊያደርግ ይችላል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያዊነት አራማጅ ወዳጆቻችን ለዲሞክራሲ ቁርጠኛ እንደሆኑ የሚገልጹ እንደመሆናቸው መጠን የአብዝሓው ድጋፍ እንዳላቸው ሳያረጋግጡ የፌዴራል አወቃቀሩን ለመለወጥ ከመሞከር በመቆጠብ ይህንን አቋማቸውን በተግባር ሊያሳዩ ይገባል፡፡ የአካታች ዲሞክራሲ መሰረታዊ መገለጫ ይህን የመሰሉ ጉዳዮችን የመወሰን መብት ድምጻቸው ከፍ ብሎ ለሚደመጡ ከተማ ቀመስ ልሂቃን ብቻ የሚተው አለመሆኑ ነው፤ እናም የኢትዮጵያዊነት ርዕዮት አራማጆች ዓላማቸውን ለማሳካት ሰፊው ሕዝብ ሓሳባቸውን እንዲደግፍ ሊጥሩ ይገባል፡፡ የሲዳማ  ሕዝበ ውሳኔን ውጤት፣ ደቡብ ውስጥ እየጠነከረ የመጣውን ክልልነት የማግኘት ፍላጎት፣ በትግራይ ያለው ሁኔታ እንዲሁም የብሔር ፌደራሊዝም በሕዝቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ለመለካት በቅርቡ የተካሄደውን ጥናት ስንመለከት ግን አራማጆቹ በሚመኙት መጠን የኢትዮጵያዊነት ርዕዮት በበርካታ ሕዝብ ዘንድ ድጋፍ ላይኖረው ይችላል፡፡

በኢትዮጵያዊነት ጎራ ውስጥ ያሉ ወገኖች የብሔር ግጭት ሰለባ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን በእውነት የሚቆረቆሩ ከሆነ(ደግሞም እንደማስበው በርካቶች በርግጥም ይቆረቆራሉ) መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ ተቀዳሚ ሐላፊነቱን እንዲወጣ መጠየቅ አለባቸው፡፡ የችግሩ ብቸኛ ተጠያቂ ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም እንደሆነ አድርገው ከማቅረብ ይልቅ ‹የደህንነት መዋቅሩ ለምን ውጤታማ እንዳልሆነና› ለምን የአብይ መንግስት የሕዝብን ደህንነት ማረጋገጥ በተደጋጋሚ እንደተሳነው መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ለችግሩ ተጠያቂ ወደ መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ እያደረግነው ነው የተባለው ጉዞ ነውን? ችግሩ የዜጎችን የነጻነት መብት በማረጋገጥና ስርአትን በማስፈን መካከል ያለውን ትክክለኛ ምጣኔ (ሚዛን) የማግኘት ፍልስፍናዊ እንቆቅልሽ ውጤት ነውን? ወይስ የመንግስት ኃላፊነት ለመወጣት ያለመቻል ግልጽ ድክመት ነው?

የኢትዮጵያዊነት ጎራ ውስጥ ያሉ ወገኖች ሙግታቸውን በሚያቀርቡበትና ከሚጠየፉት የፌደራሊዝም ስርአት ኢትዮጵያን ለመታደግ እቅድ በሚያወጡበት ሂደት ውስጥ ሆነውም ቢሆን እንኳን እኒህን ጥያቄዎች ሊያነሱና በጥልቀት ሊመረምሩ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ከዚህም በላይ ለኢትዮጵያውያን ደህንነትና የሰብአዊ መብት መከበር በሚያደርጉት ትግል ከአድልዎ ሊጠበቁ ይገባል፡፡ የኦሮሞ ብሔረተኞች የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በአናሳ ማሕበረሰቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃትና የሰለባዎቹን መከራ አይተው እንዳላዩ እንደሚያልፉት ሁሉ አንዳንድ የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ አራማጆችም የአንዳንዶችን ጉዳት አይተው እንዳላዩ ያልፋሉ፡፡

በነሱ አመለካከት የጸረ ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም አጀንዳቸውን ለማቀንቀን ስለሚጠቅሙ (የአብይ ደጋፊ ለሆኑ ኢትዮጵያኒስቶች ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኖረውን ድጋፍ ለማጠናከር ሊረዱ ስለሚችሉ) በኦሮሚያ ያሉ የግጭት ሰለባዎች ትኩረት የሚገባቸው እና ዋጋ ያላቸው ሰለባዎች ናቸው፡፡

በአንጻሩ የኢትዮጵያ መንግስት የኃይል እርምጃ ሰለባ የሆኑ ሰዎች አጀንዳቸውን ለማራመድ ስለማይረዱ በነሱ አይን ዋጋ ቢስ ናቸው፡፡ ለምሳሌ መንግስት በባለቤትነት የሚያስተዳድራቸው የሚዲያ ተቋማትና እንደ ኢሳት ያሉ ታዋቂ የኢትዮጵያዊነት ርዕዮት አራማጅ ሚድያዎች በኦሮሞ ነጻነት ጦር ላይ የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ በሚል ስም በንጹሐን ኦሮሞዎች ላይ የተወሰደውን የማሰቃየት፣ ከፍርድ ውጪ የመግደልና በዘፈቀደ የማሰር አካሄድ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ስለጉዳዩ ዝርዝር ሪፖርት ከቀረበ በኋላ እንኳን በአመዛኙ በዝምታ አልፈውታል፡፡ ይኸው ዝምታ በነሐሴ የመንግስት ባለስልጣናት በወላይታ ተቃውሞ ባካሄዱ ሰዎች ላይ ገደብ ያለፈ ኃይል በተጠቀሙበት ወቅትም በድጋሚ ተስተውሏል፡፡

እንደ አምነስቲ ያሉ አለም አቀፍ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ሲመረኮዝና በህወሓት የሚመራው መንግስት ሲያደርሳቸው የነበሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የምዕራባውያን መንግስታት በሚያወግዙበት ወቅት ጽኑ ድጋፉን ሲሰጥ የነበረው ይኸው ጎራ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ አንድ መቶ ሰማንያ ዲግሪ በመዞር ከነዚህ ወገኖች የሚወጡ መግለጫዎችንና ሪፖርቶችን ማመን እንደማይገባን መሞገት መጀመሩ ምጸትን ያጭራል፡፡ አንዳንዶች እንዳውም በሚያሳዝን ሁኔታ እነዚህ ወገኖች ኢትዮጵያን የመጉዳት ድብቅ ሴራ አላቸው እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡

በዋሻው መጨረሻ የብርሃን ጮራ ይኖር ይሆን?

በከፍተኛ ሁኔታ  ጽንፍ የያዙ ልሂቃን አጀንዳቸውን ባገኙት አጋጣሚ ለማራመድ ጥረት ማድረጋቸው፣ ዜጎቹን ከጥቃት መታደግ የተሳነው ማዕከላዊ መንግስት አሁን ደግሞ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑ፣ እንዲሁም ደግሞ የእርስ በርስ መገዳደል እየተለመደ መምጣቱ ‹‹በርግጥ ተስፋ የምናደርገው አንዳች ነገር ይኖር ይሆን?›› ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡

ለዚህ መልሱ አዎ በርግጥም ብዙ ተስፋ እንድናደርግ የሚያደርጉን ነገሮች አሉ የሚል ነው፡፡ በጨለማው ዋሻ መጨረሻ በርግጥም የብርሃን ጮራ አለ፡፡ ነገር ግን ብርሃኑ እየደመቀና እየሰፋ የሚሄደው ሁላችንም የድርሻችንን ስንወጣ ብቻ ነው፡፡

አንደኛ፣ አስቀድሞ እንደተጠቆመው መንግስት የዜጎችን ሕይወት የመጠበቅ ተቀዳሚ ሐላፊነቱን እንዲወጣ መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ይህን ማድረግ የተሳነው መንግስት የከሰረ መንግስት ነው፡፡ ይህን በማድረግ ሂደት ግን (የኖአም ቾምስኪን አገላለጽ ልዋስና) ሰለባዎችን  ‹‹ዋጋ ያላቸው እና ዋጋ የሌላቸው ተጠቂዎች›› ብለን ደረጃ ወደ ማውጣት አስቀያሚ ሁኔታ  ውስጥ እንዳንገባ የቻልነውን ልናደርግ ይገባል፡፡

ሁለተኛ፣ የሐይል እርምጃ በሚወስድና  የሕግ የበላይነትን ለማስፈን በሚጥር መንግስት መካከል ጉልህ ልዩነት ያለ መሆኑን ልንረዳ ይገባናል፡፡ ስለሆነም መንግስት የሰው ሕይወትን ለመጠበቅ በሚል ሰበብ (ሕገ ወጥ) የሐይል እርምጃ ላይ እንዳይጠመድ ዜጎች መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ወለጋ ባሉ ኦሮሞዎችም ላይ ይሁን ሶዶ ባሉ ወላይታዎች ላይ የሚወሰድን የኃይል እርምጃ ሁላችንም ልንቃወመው ይገባል፡፡

በተጨማሪም የወንጀል መከላከልና ፍትህ ስርአቱ ከወገንተኝነት የጸዳ እንዲሆን ተጽእኖ የማናደርግ ከሆነ መንግስት የሕግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ የምናደርገው ጥረት ትርጉም አልባ እንደሚሆን መገንዘብ አለብን፡፡ በቅርቡ የተወሰደውን ታዋቂ ፖለቲከኞችን ጨምሮ የ10,000 ሰዎችን በጅምላ የማሰር እርምጃን ተከትሎ የፍትሕ ስርአቱ እየተፈተነ ነው፡፡ የፍትሕ ስርአቱ ከወገንተኝነት ነጻ መሆኑ እጅግ ወሳኝ ሲሆን ይህን ለማረጋገጥ የምናደርገው ተጽእኖም ሚዛኑን የጠበቀ ሊሆን ይገባል፤ ፍርድ ቤቶች የእስክንድርን ክስ በተመለከተ ፍትሐዊ እንዲሆኑ የምንጠይቅ ከሆነ መንግስት በጃዋር ክስ ላይ እጁን ሲያስገባ አይተን እንዳላየን ልናልፍ አይገባም፤ በተቃራኒውም እንዲሁ፡፡ እንዲህ ካደረግን እየጣርን ያለነው ፍትህ እንዲሰፍን ሳይሆን የፖለቲካ አጀንዳችንን ለማራመድ  ነው፡፡

መንግስት ፍርድ ቤቶችን ዓላማውን ለማራመድ አሁንም ሊጠቀምባቸው እንደሚችል የሚያመላክቱ አሳሳቢ ሁኔታዎች አሉ፡፡

ለምሳሌ፣ በምርመራ ሂደቱ መጀመሪያ አካባቢ ባለስልጣናት ምንም መረጃ ሳይኖራቸው የሃጫሉን ግድያ ህወሓትና ኦነግ ሸኔ በጋራ እንዳቀነባበሩት ሲገልጹ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድም ‹‹ደም በማፍሰስ የተነጠቀውን ሥልጣን መልሶ ለማግኘት የሚፈልግ የፖለቲካ ቡድን ግድያውን አቀነባብሮታል›› በማለት ይህን  እይታ ደግፈው  ተናግረዋል (ይህን ሲሉ ስለ ህወሓት እያውሩ እንደሆነ ግልጽ ነው)፡፡ ግብጽ እጇ ሊኖርበት እንደሚችልም አክለው ጠቁመዋል፡፡ የፌደራል አቃቢ ህግ ጃዋር ግብጽ ውስጥ አሸባሪ ቡድን አሰልጥኗል የሚል ክስ እያቀረበ መሆኑ ሁኔታውን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበትና በጥልቀት በመከታተል የሚታወቀው ሬኔ ለፎርት እንደገለጸው ይህ በጃዋር ላይ የቀረበው ክስ ጨርሶ የማይመስል ሲሆን በርሱ ላይ የቀረቡትን ክሶች አመኔታ እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው፡፡ በተመሳሳይ በእስክንድር ነጋ ላይ ከቀረቡት ክሶች መካከል በአማራ ክልል የሽብር ቡድን በማደራጀት የአዲስ አበባ የቀድሞ ከንቲባ ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎችን ለመግደል አቅዶ ተንቀሳቅሷል የሚል ያለበት ሲሆን እነዚህ ውንጀላዎች ኢተአማኒ ከመሆናቸው የተነሳ ስለ ፍትሕ ስርአቱ እንድንሰጋ ሊያደርጉን ይገባል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ሕገ ወጥ መሳርያ በመያዝ ክስ ጉዳዩ እየታየ የሚገኘው ሌላኛው ታዋቂ ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌውን መንግስት የያዘበት ሁኔታም አሳሳቢ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የፍትሕ ስርአቱን ለማዛነፍ የሚደረጉ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በመፋለም ረገድ ከወገንተኝነት የጸዳ አቋም ይዘን ለመገኘት ልንጥር ይገባናል፡፡

በተጨማሪም እጅግ የዘገየው ብሔራዊ ውይይት መደረግ አለበት፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ያሉት ሁለቱ ዋነኛ የርዕዮተ አለም ጎራ አራማጆች (ማለትም ኢትዮጵያዊነትና የብሔር ፌደራሊዝም) ጥልቅ ውይይት ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ይህ እንዲሆን ግን ሁለቱም በውስጣቸው ያሉ መሰነጣጠቆችን (ስብራቶችን) ሊጠግኑ ይገባል፣ የአብይ መንግስትም ውይይቱን ለማካሄድ ሙሉ ለሙሉ ቁርጠኝነት ሊያሳይ ይገባል፡፡ ተመራጭ የሚሆነው በዚህ ሂደት አብይ ወደ የትኛውም ወገን ሳያደላ የመሪ አደራዳሪነትን ሚና ቢጫወትነው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያዊነት ጎራ ውስጥ ባሉ አንዳንድ ወገኖች ዘንድ አብይ ተጽእኖ ፈጣሪ አጋር ተደርጎ የሚታይ በመሆኑ ይህ የመሆኑን ነገር አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ በዚህ ሂደት ቢያንስ መሰረታዊ መግባባት ላይ መድረስ ካልተቻለ ብዝሓዊ ዲሞክራሲን ለመተግበር የሚካሄድ ጥረት አደገኛ ይሆናል፡፡ በርግጥም የአገር አቀፍ የውይይት መድረክ መዘጋጀት አስፈላጊነቱ እጅግ አንገብጋቢ የመሆኑ ነገር ግልጽ ከመሆኑ የተነሳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ በመስቀል በአል ወቅት ሁሉን ያሳተፈ ጥልቅ ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም ይህ ወቅት ራሳችንን የምንመለከትበት ሊሆን ይገባል፡፡ የሌላውን ወገን ሐሳብም የምናደምጥበት ወቅት ሊሆን ይገባል፡፡ በጥልቅ የምናምናቸውን ሐሳቦች የምንፈትሽበትም ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡ የሃያ አመት የአዲስ አበባ ተወላጅና ከአማራ ብሔር የተገኘሁ እንደመሆኔ ስለ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንና ስለ ገናናው ታሪካችን ያለኝን አመለካከት የማይጋሩ ወገኖች በሚያሳዩት ቁጣና ምሬት ላይ ፊቴን ማዞር ለኔ ቀላል ነው፡፡ነገር ግን ራሴን ስጋፈጥና በውስጤ የያዝኳቸውን እሳቤዎች ስፈትሽ ቢያንስ የተወሰነው ቁጣቸው ተገቢ እንደሆነ ልረዳ እችላለሁ፡፡

እነሱ የኔን ቋንቋ የሚናገሩ ቢሆንም  እኔ ግን ከቋንቋቸው የአንዲቷን ቃል ትርጉም አለማወቄን እረዳለሁ፤ እኔም ሆንኩ የሚቀርቡኝ ሰዎች ለልጆቻችን የኦሮሞ ወይም የሲዳማ ስም ፈጽመን እንደማናወጣ እረዳለሁ፤ ከነሱ በርካቶቹ ግን እኔ በማውቃቸው ስያሜዎች ይጠራሉ፤ እነሱ የኔ ጀግኖች ያላቸውን ታሪክ በስፋት እንደሚያውቁና እኔ ግን ስለነሱ ጀግኖች የማውቀው ነገር እንደሌለ እረዳለሁ፤ የፊልም፣ የሙዚቃና የፋሽን ኢንዱስትሪው ገንነው  የሚታዩት ለኔ (ባሕል) ቅርብ የሆኑ ፊቶች፣ ስሞች፣ አስተሳሰቦችና ትርክቶች እንደሆኑ እረዳለሁ፤ ስለ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሳስብ በምናቤ የሚመጣልኝ ስእል አንድ ሶማሌን ወይም አኝዋክን እንደማይመስል እረዳለሁ፡፡ ማለቂያ የሌላቸው ግንዛቤዎች!

የተቆጡና የተማረሩ ወገኖች ደግሞ ሊገነዘቡ የሚገባቸው ይህ ችግር እንደ ብሔር ፌደራሊዝም ወይም የትምህርት ፖሊሲ ባሉ ተቋማዊ በሆኑ እርምጃዎች  ሊፈታ አለመቻሉን ነው፡፡ መፍትሔው ለብሶታቸን አይናቸውን ጋርደዋል ብለው ከሚያስቧቸው ወገኖች ጋር ንቁ ግንኙነት መፍጠርን ይጠይቃል፡፡ የሁለትዮሽ መተማመን፣ የቤተሰብነት መንፈስ፣ ልቦችን (በፍቅር) የማሸነፍና ጥልቅ ማሰላሰልን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ፍሬያማ እንዲሆን ደግሞ ልባቸውን ለመርታት የሚፈልጓቸው ወገኖች የሚሰማቸውን ስቃይ መጋራት ግድ ይላል፡፡ ‹‹የራሳቸው ወገን›› አባል በሆኑ ሰዎች የሚፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችንም ለማውገዝ ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል፡፡

ይህን ማድረግ ከቻልን መጪው ዘመን የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ ከማድረግ የሚያግደን አንዳችም ምክንያት አይኖርም፡፡ ይህን ማድረግ አለመቻል ግን ኢትዮጵያን ለውድቀት መዳረግ ነው፡፡ ስለሆነም መንግስትና አንጃ የፈጠሩ የፖለቲካ ልሂቃን በብሄራዊ ውይይት ውስጥ በሚሳተፉበት ወቅት እኛም የራሳችንን ውይይት ልናደርግ ይገባል፡፡ በቁጥር ትንሽ ሆነን ውይይት ማድረግ፣ በቤተሰብ ውስጥ መወያየት፣ በማሕበራዊ ሚዲያ መወያየት፣ ከራስ ጋር መወያየት– የሚጎረብጡንን ውይይቶች ለማካሄድ መዘጋጀት ይገባናል፡፡

ሁላችንም በህብረት ከቆምን በዋሻው መጨረሻ ላይ የምናገኘው የብርሃን ጮራ እኛው እንሆናለን፡፡

 ጥያቄ ወይም እርማት? ኢሜል ይላኩልን

ዋና ፎቶ: አንድነት ፓርክ; 26 ጃንዋሪ 2020; ዊሊያም ዴቪሰን

በ Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 ዓለም አቀፍ ፈቃድ ስር የታተመ ፡፡ እንደገና ካተሙ  የኢትዮጵያ ኢንሳይትን  ስም ጠቅሰው ይህንን ገጽ ያገናኙ ፡፡

ከመላ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዜናዎችን ለማቅረብ ድጋፍዎን እንፈልጋለን
እባክዎን የኢትዮጵያ ኢንሳይትን ዘጋቢ ይርዱ
Become a patron at Patreon!

About the author

Emmanuel Yirdaw

Emmanuel is an undergraduate philosophy student at the University of Nevada, Las Vegas. Born and raised in Ethiopia, he moved to the U.S. as a high school student in 2015. Follow him on Twitter @EmmanuelYirdaw

2 Comments

  • This atrticle has given an balanced view of the situation in the empire. Who was the instigator of the crisis involved in the Hachalu’s death? He is accountable for all the messes.
    What was the ratio of death by ethnic groups? I also didn’t understand your views of the government’s stand on Jawar. Did Jawar ever spoke against Amhara or any other ethnic groups in Ethiopia? Give me an evidence or proof the hater.

Leave a Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.