Elections 2021 Ethiopian language In-depth

ግድ የለሽነት የሚንጸባረቅበት የማዕከላዊ መንግስት አቋም በጋምቤላ ማሕበረሰቦች ዘንድ የተፈጠረውን የጦፈ ፉክክር ይበልጥ ያፋፍማል

አኝዋሃ እና በኑዌር መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ልማት ሥራዎች የሚሳለጡበት መንገድ ሊመቻች ይገባል።

በጋምቤላ የሚገኙ አኝዋዎች ኦኩራ ብለው የሚጠሩት አሳ አለ። ጣዕም የለውምና ለመብላት በርከት ያለ ጨው ያስፈለገዋል። በዚህም ምክንያት ዋጋው ርካሽ ነው።

በፑግኒዶ ከተማ ባለው ገበያ አንድ እድሜያቸው የገፋ የትምባሆ ሻጭ “የአንድ አኝዋሃ ህይወት ዋጋው የኦኩራ አሳን ያህል የረከሰ ነው” ብለውኝ ነበር፤ አነጋገራቸው የማያሻማ እውነታ እየገለጹ እንዳሉ አይነት ነበር፡፡ ይህ የሆነው በየካቲት ወር በአንድ ሞቃታማ ዕለት በአኝዋሃ ዞን የሚገኘውንና በጋምቤላ ከሚገኙ ካምፖች ረጅሙን እድሜ ያስቆጠረውን የስደተኛ ካምፕ ለመጎብኘት እያመራሁ በነበረበት ወቅት ነበር።

እኔም የጋምቤላ አኝዋሃ ተወላጅ እንደመሆኔ፤ እንዲህ አይነት ተስፋ መቁረጥ የሚታይባቸው አመለካከቶች በማሕበረሰቡ ዘንድ ሲንጸባረቁ መስማት ለኔ እንግዳ አይደለም፤ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ማኅበረሰቡ ለረዥም ዘመናት የከባቢያዊ መፈናቀልና ብሔራዊ መገለል ሰለባ ሆኖ መቆየቱ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉ ገለጻዎች አብይ አህመድ ስልጣን ላይ ሲወጣ ማሕበረሰቡ የነበረው ተስፋ ገና በሶስት ዓመቱ ከስሞ ዳግም ወደ ተስፋ መቁረጥ እንደተመለሰ ያሳያሉ።

አብዛኛው የጋምቤላ የፖለቲካ መደብ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) መፍረስን በደስታ ነበር የተቀበለው። በኢህአዴግ ጊዜ ለአራቱ አባል ክልሎች ዋና ትኩረት ይሰጥ የነበረ ሲሆን ጋምቤላ ግን ከገዢ ፓርቲያቸው ከኢህአዴግ ጋር ከአጋርነት ያላለፈ ግንኙነት ከነበራቸው ክልሎች መካከል አንዱ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣን ላይ ከወጡ ከአንድ ወር በኋላ ማለትም በግንቦት ወር 2010 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን የምዕራቡን ክልል  በጎበኙበት ወቅት የጋምቤላ ሕዝብ  በስተመጨረሻ ተገቢውን እውቅና እንደሚያገኝና ፤ ችግሮቹም በብሔራዊ ደረጃ ክብደት እንደሚሰጠው አስበው ነበር። የጋምቤላ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴንና ሌሎች ሰባት የክልል ገዢ ፓርቲዎችን በማዋሃድ በ2011 ዓ.ም የብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት ደግሞ ይህ ተስፋ ጨመረ።

ከሶስት አመት በኋላ ግን ያ የተገባው ቃል ታጥፏል፣ ጋምቤላም ከፍ ባለ ውዝግብ  በተጠመዱት ኃያላን  ተዋናዮች አይን  ቀዳሚ ትኩረት የማይሰጣት ክልል ተደርጋ በመቆጠሯ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማድረግ የነበራት ተስፋ ከስሟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መፍትሔ ሳይበጅላቸው ተቀምጠዋል።

በአንፃራዊነት የተትረፈረፈ መሬትና ውኃ ባለበት በዚህ ሸለቋማ ክልል አንደኛው ስር የሰደደው ጉዳይ ውስብስብና ጥንቃቄ የሚፈልገው የስደተኞች ጉዳይ ነው። ምንም እንኳ በጋምቤላ ለሚገኙ ስደተኞች በአገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠ ቢሆንም፤ የፖሊሲ ውሳኔዎች የሚወሰኑት ከማኅበረሰቡ ጋር በቂ ምክክር ሳይደረግና ማኅበረሰቡ በበቂ ሁኔታ ይሁንታውን ሳይሰጥ ነው።

የጋምቤላ ክልል የህዝብ ቁጥር በአንፃሩ አነስተኛ ቢሆንም በጋራ ለመኖር ከባድ ለሆነባቸውና የክልሉ ሁለት አበይት ማኅበረሰቦች ለሆኑት አኝዋሃና ኑዌር ሕዝቦች ግን እውቅና፣ስልጣንና ሌሎች ዕድሎችን የማግኘት አጋጣሚዎች ውስን ናቸው የሚለው እሳቤ እርስ በእርስ ፍትጊያ ውስጥ እንዲገቡና አንዱ እንዲጠቀም ሌላው ተጎጂ መሆንን የሚጠይቅ ሁኔታ ይፈጥራል።

ምርጫ በደረሰበት በዚህ ወቅት፤ በክልሉ ያሉ ውሳኔ ሰጪዎች ለሁሉም ማኅበረሰቦች ዕድሎችን መጨመር የሚችሉበት ሁኔታዎች ላይ በማተኮር በሁለቱም ወገን ያለ የመወነጃጀል አዙሪትን ማስቆም አለባቸው። በመጨረሻም የአካባቢው ነዋሪዎች በአኝዋሃና በኑዌር መካከል ረዥም ጊዜ ላስቆጠሩ የውጥረት መንስዔዎች መፍትሔ ቀርፀው መተግበር አለባቸው።

ገንዘብ ማሳደድ

በደቡብ ሱዳን ድንበር ወሳኝ ስፍራ ላይ የምትገኘው ጋምቤላ በኢትዮጵያ ከሚኖሩ 900,000 ከሚጠጉ ስደተኞች መካከል ግማሽ የሚደርሱትን ያህል ታስተናግዳለች። የኢትዮጵያ ፓርላማ በጥር 1996 ዓ.ም ያወጣውን የስደተኞች አዋጅ  በጥር ወር 2011 ዓ.ም አሻሽሏል፤ ይህም በአለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት እንዲቸረው አድርጓል።

አዲሱ ህግ 193 የተባበሩት መንግስታት አባል አገራት እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 ያጸደቁትን የኒውዮርክ የስደተኞች እና ተፈናቃዮች አዋጅ ባገናዘበ መልኩ ስደተኞችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ከሚመደበው ከፍተኛ ገንዘብ ተጠቃሚ ለመሆን ታቅዶ የተዘጋጀ ነው። በተለይም ከቀኝ ክንፍ ብሔርተኞች  በሚደርስባቸው የፖለቲካ ጫና የተነሳ የስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄዎችን ለመቀነስ በሚያስቡ የአውሮፓ አገራት ዘንድ ሐሳቡ ክፍ ያለ ዋጋ እንደሚሰጠው እሙን ነው።

ይህ ኃሳብ በጸደቀ ወቅት አውሮፓ “ዓለም አቀፍ የስደተኛ ቀውስ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ጫና እየተጋፈጠች በነበረበት ጊዜ በመሆኑ ለጋሾች ስደተኞችን አገራቸው አቅራቢያ ለማስፈር  አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገቡ። የዚህ ቀውስ መንስኤ ከፊሉ በሶሪያና ሊቢያ የተከሰተው ጦርነት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በአውሮፓና በአውሮፓ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች በነበሩት አገራት መካከል ሰፊ የኑሮ ደረጃ ልዩነት መፈጠሩ ነው፡፡

ከካምፕ ውጪ አወቃቀር ፤ በተሰኘውና ለኤርትራውያን ስደተኞች ታስቦ በተዘጋጀው አሰራር ላይ በመመርኮዝ ሁሉም በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች በአገሪቱ የትኛውም ስፍራ እንዲሰፍሩ፣ የስራ ፍቃድ እንዲያገኙ፣በመንግስት ተቋማት የትምህርት እድል ማግኘት እንዲችሉ፣ውልደት፣ጋብቻና ሞትን ማስመዝገብ እንዲችሉና የተወሰነ የመሬትና ገንዘብ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢያንስ በወረቀት ደረጃ ተፈቅዷል ።

በአዲሱ ህግ ላይ የነበረው የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ከቀዘቀዘ በኋላ ለ100,000 ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራሉ ተብለው ለታሰቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እርዳታ ተመድቦ የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 30 በመቶ የሚሆነው ለስደተኞች ተደራሽ እንደሚደረግ ቃል ተገብቶ ነበር።

በሰኔ 2010 ዓ.ም የዓለም ባንክ ኢኮኖሚክ ኦፖርቹኒቲስ ፕሮግራም በተሰኘው መርኃ ግብሩ አማካይነት ለኢትዮጵያውያኖችና ለስደተኞች ስራ የመፍጠር ሙከራዎችን ለመደገፍ 202 ሚሊየን ዶላር ቃል ገብቷል። እንግሊዝም ለተመሳሳይ አላማ 80 ሚሊየን ፓውንድ ቃል ገብታለች። የአውሮፓ ህብረት 50 ሚሊየን ሲለግስ፤ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ደግሞ 200 ሚሊየን ፓውንድ ብድር ሰጥቷል። ለኢትዮጵያ መንግስት፤ ወደ አንድ ሚሊየን ገደማ የሚጠጉ ስደተኞችን ወደማኅበረሰቡ ለማቀላቀል ቃል መግባት ማለት በአንፃራዊነት እንደአስፈላጊነቱ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ ነገር ነው። እውነታው ግን በኢንዱስትሪያል ፓርኮች የሚሰሩ ስደተኞች መጠን ከ30 ፐርሰንት ይልቅ ለ 0 ይቀርብ መሆኑ ነው፤  በተጨማሪም መንግስት ምንም እንኳ አዲሱን የፌደራል አዋጅ ለመተግበር የሚያስፈልገውን ድጋፍ  የተረከበ ቢሆንም በተለይም በክልልና በአካባቢ ደረጃ ወደ ትግበራ የሚመሩ ፖሊሲዎች፣ አቅጣጫዎችና ደንቦችን ወደ ማርቀቅ አልተገባም።

በተጨማሪም በጋምቤላ ከፍተኛ የስደተኞች ቁጥር ቢኖርም የኢንዱስትሪያል ፓርኮች ከሚቋቋሙባቸው ስፍራዎች አንዱ እንዲሆን አልተመረጠም። ክልሉም አፈር ቢኖረውም እንኳ ሊሰሩ ከታሰቡ አዳዲስ የእርሻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል የአንዳቸውም መገኛ አልሆነም።

ከሁለት ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ የስራውን ዓለም እንደሚቀላቀሉ ይገመታል፤ አብዛኞቹ ታዲያ ማንኛውንም አይነት ስራ ሳያቅማሙ ለመስራት የሚፈልጉ ናቸው። በጋምቤላ የሚስተዋለው በማሕበረሰቦች መካከል የሚከሰት ግጭት ውስን የሆኑ የስራ እድሎችን ለማግኘት ካለው ፉክክር ጋር የተያያዘ ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት በጋምቤላ በሚገኙ ስደተኞችና ዜጎች በተለይም በአኝዋሃና ኑዌር (በርካቶቹ ከቅርብ አመታት ወዲህ በጦርነት ከፈረሰችው ደቡብ ሱዳን የመጡ ናቸው) ማኅበረሰቦች መካከል ያለው ውጥረት ከፍተኛ ሆኖ መቆየቱ ነው።

የኔ መሬት ፤ ያንተ መሬት

በትንሿ ጎጆ ታዛ ስር ቁጢጥ ብዬ ከአዛውንቱ የጎጆዋ ባለቤት ጋር ጨዋታ ጀመርኩ፤  በገበያ ቀን ከወጣችው የምታቃጥል ጸሐይ እንደተሸሸግን በንዴት እየጦፉ ስለርካሽ አሳ ማውራቱን ተያያዙት።

የተሻሻሉት ሕግጋት ስደተኞች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ በመርህ ደረጃ ቢፈቅዱም በዚህ በጎግ ወረዳ ያሉ ባለስልጣናት ግን ከባለፈው አመት አንስቶ እስከቅርብ ጊዜ  ድረስ ስደተኞች ወደ ፑግኒዶ ከተማና ገበያዋ እንዳይመጡ ከልክለዋል።

ይህ ደግሞ በአካባቢው ለሚደረገው ንግድ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም የደንበኞች መጨመር እንደ ንያካ ኦንግዋች ላሉ ሻጮች የበለጠ ገቢ ማለት ነውና። ውሳኔው ጥያቄ አጫረብኝ።

“የአኮቦን ህዝቦች አታይም?” አቶ ንያካ ጠየቀኝ

ከአኮቦ ወንዝ በወዲያኛው በኩል የሚገኘው፤በተለምዶ በአኝዋዎች ዘንድ ችሮ በመባል የሚታወቀው የደቡብ ሱዳኑ አኮቦ በእርግጥም ከአዕምሮዬ ገና አልጠፋም። በቅርቡ ባደረኩት ጉዞ ወቅት ጆን ከሚባል አንድ ወጣት የሰማሁት ታሪክ አእዕምሮዬ ውስጥ ተቀርጾ ቀርቷል።

ጆንን ያገኘሁት ከፒኝውዶ ወደ ጎግ በሚወስደው መንገድ ላይ ከሚገኝ አንድ ሱቅ ውጪ ከሁለት ሌሎች ሰዎች ጋ ተቀምጦ ነው። በስደተኛ ተቀባይ ማኅበረሰብና ስደተኞች መካከል ስላለው ግንኙነት ሰዎቹ ያላቸውን ኃሳብ ለመስማት ጨዋታ ጀመርኩ። ጆን ለጥያቄዎቼ ምላሽ የሰጠኝ የሚረብሽ ታሪክ በመተረክ ነበር።

ጆን በጎግ ወረዳ ከሚገኘው ጎግ ዲፓች ቀበሌ ወደ ደቡብ ሱዳን የተሰደደው በሚያዝያ 2004 ዓ.ም ነበር። የተወሰኑ የሳውዲ ስታር አግሪካልቸራል ዲቨሎፕመንት ሰብ ኮንትራክተር ሰራተኞች በዛው ወር መገደላችውን ተከትሎ የፌደራል ወታደሮች የአኝዋሃ ወጣቶች ላይ ባደረሱት ከፍተኛ ጥቃት ምክንያት ነበር አገር ለመልቀቅ የተገደደው።

ሳውዲ ስታር ባለቤትነቱ የትውልደ ኢትዮጵያዊው የሳውዲ ቢሊየነር መሀመድ አል-አሙዲ ሲሆን ገና ከጅምሩ (በከፊል) በመንግስት፣ባለሀብትና የአካባቢው ማኅበረሰብ መካከል በነበረው ደካማ ቅንጅት ምክንያት በውዝግብ የተከበበ ነበር። በቅርቡ በተካሄደው የመልሶ ማልማት ጥረት ምክንያት የሩዝ እርሻው ለወጣቶች የስራ እድል ሊፈጥር ይችላል፤ ይህም እንደዚህ ካሉ የክልሉን የተትረፈረፉ ሀብቶች ከሚጠቀሙ ትልልቅ የግብርና መርኃ ግብሮች የሚጠበቅ ነው።

ጆን ወደ ደቡብ ሱዳን ሳይፈልገው ለመሰደድ በተገደደ በአመቱ (በ2005 ዓ.ም) የደቡብ ሱዳን አኮቦን አቋርጦ ወደ ትውልድ ቀዬው ለመመለስ ወሰነ።

የአኝዋሃ ሴቶች የበቆሎ ዱቄት የኑዌር ስደተኛ ሴቶች ደግሞ የሳር ጥቅል እና የማገዶ እንጨት በፑግኒዶ ገበያ እየሸጡ፥ የካቲት 8፣ 2013፥ Okello Miru

በደረሰ ጊዜ የተደበላለቅ ስሜት እንደተሰማው ይናገራል። በወንዝ አቅራቢያ ያለውን ከተማ ጆን እንደ ማንኛውም አኝዋሃ ያውቀዋል። እንደ ዶን መክሉር እና ሀርቬይ ሆክስትራ (መጽሐፍ ቅዱስን ወደ አኝዋሃ ቋንቋ የተረጎሙ የመጀመሪያው ሰው ናቸው) ያሉ እውቅ ሰዎች የሚገኙበት የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን ስራቸውን ለመጀመር ወደ አኝዋሃ ምድር ሲመጡ የተቀመጡት በደቡብ ሱዳን አኮቦ ነበር።

እንደ ፕሮፌሰር አናዴ፣ ጆሴፍ ኦቲዮ፣ ቻም አድሁም እና ሳይመን ሞሪ ያሉ የመጀመሪያዎቹ የተማሩ አኝዋዎች የመጡትም ከዛ ነው። እንደዚህ ያሉ ታላላቅ የአኝዋሃ ሰዎች ታሪኮች አኮቦ-ጭሮን እንደ ቀደምት አባቶች ርስት አድርጎ ለሚመለከተው ህዝባችን ጠንካራ የስሜት ትስስር እንዲኖር ያደርጋሉ፤ አሁን ታዲያ በስፍራው በዋናነት የሚኖሩት ከፊል አርሶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር የሆኑት ኑዌሮች ናቸው ።

ጆን እንደሚለው ወደ ስፍራው ከመጣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ የኑዌር ሰው በስካር ተጽእኖ በሚመስል ሁኔታ አኮቦ ወንዝ ውስጥ ወድቆ ሰጠመ። በተከታዩ ቀን የኑዌር ማኅበረሰብ አባላት ሰውየውን እናንተ ናቸሁ የገደላችሁት የሚል ውንጀላ ይዘው ወደ አኝዋዎች መጡ። ይህን ተከትሎ ጸብ እንዳይፈጠር በመስጋት ጆን ወደ ቀዬው በጥድፊያ መጓዝ ጀመረ።

ጋምቤላ ከተማ ሲደርስ ጆን ኑዌሮች አኝዋዎችን በብቀላ የማጥቃታቸውን ዜና ሰማ። ሃያ አምስት ሰዎች እንደሞቱ ሲገለጽ ሌሎች በርካቶች ደግሞ በፓግኒዶ ስደተኛ ሆኑ። ግጭቱ በወንዙ አቅራቢያና ድንበሩን አልፎ ተስፋፋ።

በ2007 ዓ.ም በኑዌርና አኝዋሃ የክልል ልዩ ኃይሎች መካከል በአኮቦ ሌላ ግጭት ተቀሰቀሰ። በሁለቱም በኩል ብዙ ሰዎች ሞቱ በርካታ አኝዋዎችም ፑግኒዶ በመሰደድ እስከ አሁንም ድረስ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሆነው ወደ ሚኖሩበት በከተማውና በአካቺ መንደር መካከል በሚገኘው ስፍራ ሰፈሩ። በስደተኛ ካምፑ ሰፍረው ከነበሩት ሰዎች የተወሰኑት በካምፑ ውስጥ በሁለቱ ቡድኖች መኃከል ግጭት በመኖሩ የተነሳ ቆይተው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮቹን ተቀላቀሉ፡፡

እንግዲህ እነዚህን የአኮቦ ሰዎች ነው ንያክ ኦንግዋች ‘በታለመ የጥቃት ሂደት ምክንያት ከቅድመ አያቶቻቸው መሬት ከ10 አመት በፊት ገደማ እንዲለቁ የተገደዱ ተፈናቃይ አኝዋዎች’ ሲል የገለጻቸው። በሚያሳዝን ሁኔታ አኝዋኮች ለኑዌር ያላቸውን ጎልቶ የሚታይ ጥርጣሬ በመግለጽ ንያክ “እነሱ (ኑዌሮች)መሬታችን ላይ መኖር ይፈልጋሉ እኛ ግን እንድንኖርበት አይፈልጉም” ሲል ይናገራል።

ችግር ያለባቸው ነገር ግን በስፋት የሚስተዋሉ እንደዚህ ያሉ አስተያየቶች ረዥም ታሪክ ያላቸው ሲሆን አሁን በኑዌርና በአኝዋሃ መካከል እየቀጠሉ ባሉ ፍትጊያዎችም ያጠናከራሉ። ከመሬት፣ሀብት እና በሁለቱም በኩል ከሚንጸባረቁ ፍረጃዎች (የተሳሳቱ አመለካከቶች) በስተጀርባ ያሉ ጉዳዮች መፍትሔ ሳይበጅላቸው ባለበት ሁኔታ አኝዋኮች ለኑዌር ያደላሉ የሚሏቸው የስደተኛ ፖሊሲዎች እንዴት ግጭት እንደሚያስነሱ ለማየት አይከብድም።

የመቶ አመታት ታሪክ

ጋምቤላ የኢትዮጵያ ግዛት አካል የሆነችው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ነበር። ከ1895 ዓ.ም ጀምሮ እንግሊዝ ከተማይቱን በቅኝ ግዛት ያዘቻትና የሱዳን ወደብ አድርጋ አስተዳደረቻት። ሱዳን በ1949 ዓ.ም ነፃነቷን ስትቀዳጅ፤ ጋምቤላ ወደ ኢትዮጵያ አስተዳደር ተመለሰች።

ኢትዮጵያዊው አንትሮፖሎጂስት ደረጄ ፈይሳ እንደሚለው የአኝዋና ኑዌር ግጭት ጂካኒ ኑዌሮች ከደቡብ ሱዳን ወደ ምስራቅ ከፈለሱበት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ የነበረ ነው። ደረጄ በመጽሐፉ ላይ እንደሚገልጸው ዋናው የግጭቱ መነሻ የተፈጥሮ ሀብትን የመቆጣጠር ፍላጎት ነው፤ ይህም የሶባት ወንዝ ገባር በሆኑ ወንዞች አካባቢ ያሉ የእርሻና የግጦሽ መሬቶችን ያካትታል። አኝዋዎች በዋነኛነት አራሾች ሲሆኑ ኑዌሮች ደግሞ ከብቶቻቸውን የሚያሰማሩበት ስፍራ ይፈልጋሉ።

በቅርቡ በክልል ደረጃ የተከሰቱ የስልጣን ሽኩቻዎች እንዲሁም ድንበሮች ግልጽ ወሰን ያልተበጀላቸው መሆኑ ችግሮችን አባብሷል። ለምሳሌ እንደፖቻላ ባሉ ስፍራዎች አኝዋዎች ይህ ነገር ያጋጥማቸዋል ፤ አብዛኛውን ጊዜ ኑዌሮች ከድንበሩ በሁለቱም ወገን ዘመድ ያላቸው እንደመሆኑ ይህ  ችግር የበለጠ በእነሱ ላይ ይስተዋላል። ተመራማሪዎች ድንበር ተሻጋሪ የኑዌር የግንኙነት ትስስሮች “ቤተሰቦችን፣ የዝምድና ቡድኖችን እና የኑዌር ሲንግ ተቋምን (ከብሔራዊ ዜግነት የላቀ ክብደት ያላቸው የማንነት አይነቶችን የሚጨምር ነው)” እንደሚያካትት ይገልጻሉ።

ከ1950 – 1964 እና ከ1975 – 1997 ዓ.ም የተካሄዱት የሱዳናውያን የመጀመሪያውና ሁለተኛው የእርስ በእርስ ጦርነቶች በከፍተኛ ሁኔታ በክልሉ የነበረውን የስነ-ህዝብ አወቃቀር(ዲሞግራፊ) ቀየረው። የታሪክ ተመራማሪው ሲሲ ኩሪሞቶ በ1984 ዓ.ም በሰራው ጥናታዊ ጽሁፍ 300,000 የሚሆኑ ሱዳኖች በ1970ዎቹ ዓ.ም ወደ ጋምቤላ እንደፈለሱ ግምቱን አስፍሯል። ይህ አስር አመት የኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግስት በቅጡ ባልተጠናና አስገዳጅ በሆነ የሰፈራ መርኃ ግብር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደገኞችን ወደ ጋምቤላ ያዛዋወረበት ወቅት ነበር። የተወሰኑ ኑዌሮች ስደተኛ ሆነው ተመዘገቡ ሌሎች ደግሞ እንደቀላል በባሮ ወንዝ አቅራቢያ ሰፈሩ።

በ1978 እና በ1980 ዓ.ም መካከል በጋምቤላ ሶስት ካምፖች በኢታንግ፣ቦንጋና ፑግኒዶ ተከፈቱ። ብዙም ሳይቆይ የሰው ህይወትን የቀጠፈ ግጭት ተፈጠረ። ለምሳሌ በመስከረም 1981 ዓ.ም የሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጪ ሰራዊት (ኤስ ፒ ኤል ኤ) እንደሆኑ የተጠረጠሩ ተዋጊዎች ፑግኒዶ መንደርን አነደዷት በማለት  ኩሪሞቶ በጽሑፉ አስፍሯል። ከአራት ቀናት በኋላ ሌላ የሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ግጭት በአኝዋሃ ታጣቂዎችና በኑዌር መካከል ከኢታንግ በስተሰሜን 75 ኪሎ ሜትር ርቆ ባለ ስፍራ ተቀሰቀሰ።

በአኝዋሃ ማኅበረሰብ እነዚህ ክስተቶች ተደጋጋሚ ናቸው። በተለይም በ1983 ዓ.ም ወታደራዊው አገዛዝ ከመውደቁ በፊት አኝዋዎች ለሁለት መቶ አመታት ያህል ከኖሩባቸው ከኢትዮጵያው አኮቦ፣ በጋምቤላ ከተማ ከሚገኘው ውዝግብ ካለበት ኢታንግ ወይም ሌሎች ስፍራዎች በኃይል በኑዌር ቡድኖች መፈናቀላቸው ደጋግሞ የሚፈጠር ክስተት ነበር።

ከደርግ መውደቅ በኋላ የኢህአዴግ መንግስት በ1987 ዓ.ም የመጣው የብሔር ፌደራሊዝም ህገመንግስትን ተከትሎ የአስተዳደር ወሰኖችን በብሔርና ቋንቋ ላይ በመመስረት ለየ። ኢህአዴግ በጋምቤላ የተረከባቸውን ስምንት ወረዳዎች የአስተዳደር ዞን 1 እና 2 አደረጋቸው።

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ጋምቤላ በሶስት ዞኖች ተከፈለች። የአኝዋሃ ዞን (በአምስት ወረዳ ተከፈለ) እና የኑዌር ዞን (ይህም አምስት ወረዳ ሆነ) ተፈጠሩ። ሌላኛው ዞን ወደ ኦሮሚያ አካባቢ በሚገኘው የጋምቤላ ክልል ምስራቅ ክፍል ለሚኖሩትና መገለልና ጭቆና ለደረሰባቸው የማጃንግ ህዝቦች እንዲሆን ተደረገ።

ይህ አዲስ አወቃቀር ባለፉት አስርት አመታት ሀብታቸው ከብሔራዊና ክልላዊ ሁኔታዎች አንፃር የተነካባቸው ሁለቱ አበይት ቡድኖች በክልሉ ስልጣንን ለመጋራት ያደረጉት ሙከራ አካል ነበር። ሰፋ ተደርጎ ሲታይ የንጉሳዊው አገዛዝ በመጀመሪያው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ካርቱምን እንዲወጉ ለደገፋቸው አኝዋኮች ያደላ ነበር። በምላሹም ደርግ ኑዌሮችን ጋምቤላን እንዲያስተዳድሩ በ1970ዎቹ ወደ ስልጣን እርከን አመጣቸው፡፡ ኢህአዴግ በአንፃሩ ስልጣን ከያዘ በኋላ በታቃራኒ መንገድ በመሄድ ከአካባቢው ከአኝዋሃ ምሁራን ደጋፊዎችን መለመለ፤ ኋላ ላይ ግን አካሄዱን ለማመጣጠን ጥረት አድርጓል።

በ1990 ዓ.ም ኢህአዴግ የአኝዋሃ ጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት እንቅስቃሴን (ጋህነን) ከኑዌር ጋምቤላ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ አንድነታዊ ፓርቲ ጋር በጉልበት በማዋሀድ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋህዴፓ) በማለት አንድ ፓርቲ አደረጋቸው። ያዋሃዳቸውን አካል በመጥላት የአኝዋሃ ምሁራን የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስን ማቋቋም መረጡ፤ ይህም በ1992 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባርን ለመገዳደር ቻለ። ኮንግረሱ አኝዋዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ቢያሸንፍም እንዲሁም ምርጫው ተጭበርብሯል የሚሉ ውንጀላዎች የነበሩ ቢሆንም በጋምቤላ ምክር ቤት አነስተኛ ውክልና ብቻ ነበር ያገኘው።

በመቀጠልም ከ1990 – 1992 ዓ.ም በነበረው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የነበራቸውን ሚና ተከትሎ በምክር ቤቱ የሚገኙ ኑዌሮች ቁጥር የበለጠ ጨመረ፤ ይህም በ1994 ዓ.ም ለነበረው የኑዌር-አኝዋሃ ግጭት አስተዋጽኦ አድርጓል  በማለት ደረጄ ይገልጻል።

በታህሳስ 13፤ 1994 ዓ.ም ስምንት የኢትዮጵያ ስደተኛ ኤጀንሲ ባላስልጣናት በአኝዋሃ ታጣቂዎች ተገደሉ። ግድያውን የፈጸሙትም እንደተባለው ከሆነ አዲስ ለመስራት ስለታቀደው ካምፕ ማንም ስላላማከራቸው ነው። ግድያው የፌደራል ወታደሮችንና አጋዥ ደገኞችን በማስቆጣቱ በሶስት ቀናት ውስጥ 400 የአካባቢው ነዋሪዎች ነፍስ ጠፋ። ሂውማን ራይትስ ዋች እንዳለው ሁሉም በሚባል ደረጃ አኝዋኮች ነበሩ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመሸሽ በጎረቤት አገሮች ስደተኞች ሆኑ፤ ያን ተከትሎ ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ በማዕከላዊ የሚመራ የፖለቲካ ፓርቲ አወቃቀር ተካሄደ።

ኑዌሮችና አኝዋኮች በባሮ ወንዝ አካባቢ የሚገኘውን ለእርሻ ተስማሚ የሆነ መሬት (ይህ ስፍራ ለክፍለ ዘመናት ያህል አንዱ ወደ አንዱ ሲመጣና ሲሄድ የነበረበት ስፍራ ስለነበር ድንበሩ ያልተለየ ሆኖ የቆየ ነው) ለመቆጣጠር በሚታገሉበት ሂደት ውስጥ ደምን በደም መመለስና የአጸፋ እርምጃ የሂደቱ አንድ አካል ሆነ። ለድንበር ግጭት መፍትሔ ይሆናል በሚል የኢታንግ ልዩ ወረዳን የማቋቋም ሂደቱ  በ1998 ዓ.ም  ተጠናቀቀ። ወረዳው 23 ቀበሌዎች ያሉት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 9ኙ በዋናነት ኑዌሮች ይኖሩበታል፤ የኦሞ ብሔሮች ደግሞ በሁለቱ ቀበሌዎች ይኖራሉ፤ በአስራ ሁለቱ ቀበሌዎች ደግሞ በአብዛኛው የሚኖሩት አኝዋኮች ናቸው።

ኡጁሉ ኦባንግ ተሰዶ የነበረ የጋምቤላ ፖለቲከኛ ለአኝዋሃ ሪፖርተር አግዋ ጊሎ (እሱም አሁን ከአገር ውጭ ነው ይገኛል) እንዳለው የልዩ ወረዳው አፈጣጠር በከፊል የፌደራል ሴራ ውጤት ነበር።

በ1989 ዓ.ም ኡኬሎ ኦማን የክልሉ ፕሬዝደንት በነበረበት ውቅት ኡጁሉ ኦባንግና ሌሎች የጋምቤላ ፖለቲከኞች አዲስ አበባ የሚሰጥ ስልጠና አንዳጠናቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እንዲገኙ ታዘዙ። ኡጁሉ ፕሬዝዳንት እንደሚሆን ቃል ተገብቶለት በተጨማሪም በኢታንግ አካባቢ ለኑዌሮች አምስት ቀበሌ እንዲሰጥ ታዘዘ። ኡጁሉ በበኩሉ ዕቅዱ የነበረው በአኮቦ የተደረገውን ግጭት በመሸሽ ተሰደው የነበሩትን ኑዌሮች ሰላም ከወረደ በኋላ መመለስ እንደሆነ ገለጸ።

እንደዛም ሆኖ ኡጁሉ ግዚያዊ ፕሬዝደንት ሆኖ ተወከለ፤ ከወራት በኋላ ግን እሱና ኡኬሎ ኦማን ታሰሩ፤ ኡኬሎ ኝጊሎ ደግሞ ፕሬዝደንት ሆነ። እንደ ኡጁሉ ከሆነ በስልጣኑ ወቅት ኑዌሮች በኢታንግ የሚገኙ የአኝዋሃ መንደሮችን በመውረር ሰዎችን ገድለዋል። አኝዋዎች ሲሸሹ በኢታንግ ያለው የኑዌሮች ቁጥር ደግሞ ጨመረ።

ከድንበር ወዲያ የነበረው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በ1997 ዓ.ም በተደረገው ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት  አበቃ፤ ይህም ደቡብ ሱዳን በ2003 ዓ.ም ነፃነቷን ስትቀዳጅ ተቋጨ። ነገር ግን ከአጭር ጊዜ በኋላ በአዲሲቷ አገር ግጭት እንደገና አገረሸ። በ2006 ዓ.ም 1500 ያህል የሚሆኑ ጥገኝነት ፈላጊዎች (ሁሉም ኑዌሮች ናቸው ማለት ይቻላል) በየቀኑ ወደ ጋምቤላ ይገቡ ነበር። እነሱን ለመቀበል ተጨማሪ ካምፖች ተገነቡ።

ከሰባት አመት በኋላ አሁን በጋምቤላ ሰባት ካምፖች ይገኛሉ፤ ከነዚህ አራቱ በአኝዋሃ ዞን (ፑግኒዲ 1 እና 2 ፣ጄዊ እና ኦኩጎ) ሶስቱ ደግሞ በኢታንግ (ኩሌ (በአካባቢው በነዋሪዎች ዘንድ አኩላ በመባል ይታወቃል)፣ኑጌንዪል እና ቲየርኪዲ) ይገኛሉ።

እንደ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ (ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር) ግምት ወደ 370,000 የሚጠጉ ስደተኞች ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን ጋምቤላ ከ340,000 በላይ ስደተኞችን ታስተናግዳለች። በ2007 ዓ.ም በተደረገው የኢትዮጵያ ህዝብ ቆጠራ የጋምቤላ ህዝብ ቁጥር 307,000 የነበረ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 65,000 አኝዋዎች ሲሆኑ 143,000 ደግሞ ኑዌሮች ናቸው።

የመቶ አመታት ታሪክ ኑዌር ከጋምቤላ ጋር ያለውን ቁርኝት ረዥም መሆኑን ግልጽ ያደርጋል። ነገር ግን ለአኝዋዎች መጪው ዘመን ይበልጡን የማያስተማምን እየሆነ ሄዷል።

የሰላም ዋጋ

ባለፈው አመት መጀመሪያ ላይ በአብዛኛው አኝዋዎች በሚገኙበት የጎግ ወረዳ የቀበሌ መሪዎች በጋራ በመሆን የኑዌር ስደተኞች ከወረዳቸው ወደ ሌላ ስፍራ እንዲዛወሩ በአንድ ድምጽ ጠየቁ። በከፊልም ቢሆን ከእርዳታ ለጋሾች የሚገኘውን ገንዘብ አስመልክተው “ድኃ ሆነን የልጅ ልጆቻችን መኖር እንደሚቀጥሉ ተስፋ ቢኖረን ይሻለናል” በማለት አበክረው ተናገሩ። የጎግ ካቢኔ ስደተኞች በሌላ ስፍራ እንዲሰፍሩ በመጠየቅ ለአኝዋሃ የዞንና የክልል መሪዎች ደብዳቤ አስገባ።

ጉዳዩን ለመመልከት በስብሰባ ላይ ተገኝቶ እንደነበረ አንድ ባለስልጣን ከሆነ የጋምቤላ ፕሬዝደንት ኦሞድ ኡጁሉ ኦቡብ (እንደ ሌሎች ፕሬዝደንቶች ሁሉ አኝዋሃ ሲሆን በፌደራል ዘመን የነበረ ነው) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ራሱ ስደተኞችን ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ለማዘዋወር ስልጣን እንደሌለው በመግለጽ ምላሽ ሰጠ። እንደሱ አባባል ዓለም አቀፍ ስምምነትን የፈረመ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ግዴታዎቹን ከመፈጸም ውጪ አማራጭ የለውም።

በተግባር ሲታይ ስደተኛችን ከኅብረተሰቡ ጋር የመቀላቀል ሂደት የለም ማለት ይቻላል፤ አዳዲስ ስደተኞችም ከጋምቤላ ውጭ በሚገኙ ካምፖች በጣም አልፎ አልፎ ነው እንዲሰፍሩ የሚፈቀድላችው። ሆኖም ግን የጎግ ወረዳ መሪዎች ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ ነገሮችን በራሳቸው ሥልጣን ለማድረግ ሞከሩ። ከፌደራል የስደተኛና የስደተኛ ጉዳዮች አስተዳደር (ኤ. አር. አር. ኤ) እና ከዩኤን.ኤች.ሲ.አር ፍቃድ ውጪ ስደተኞችን ወደ ፑግኒዶ ከተማ እንዳይገቡ የሚከለክል ትዕዛዝ አወጡ።

በዚህ ታህሳስ ወር የዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር ኃላፊ ፍሊፖ ግራንዲ ኢትዮጵያን ጎብኝተው ነበር። ከመድረሳቸው በፊት፤ በጋምቤላ ያሉ የክልሉ አመራርና የኤ.አር.አር.ኤ ሐላፊዎች ጎግ ውስጥ ለስብሰባ ተቀመጡ። ስብሰባው ላይ፤ አንድ ጥያቄ ብቻ ጠየቁ፤ ሰላም ትወዳላችሁ ወይስ አትወዱም? ሰዎችም አዎ ሰላም እንወዳለን ብለው መለሱ። እንደዛ ከሆነ አሉ ባለስልጣኖቹ፤ ከአሁን በኋላ ስደተኞች ወደ ከተማ ለመምጣት ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል ገንዘብም ካላቸው ከገበያው የሚፈልጉትን የመግዛት መብት አላቸው።

ገበያው ውስጥ አንድ ሻጭ ከተወሰኑ ሳምንታቶች በፊት አንድ የኑዌር ስደተኛ መጥቶ አሳ አነሳ አለኝ። ሻጩ ዋጋው 50 ብር (1.16 ዶላር) እንደሆነ ነገረው ነገር ግን ሰውየው ለመክፈል ገንዘብ አልነበረውም። ሰውየው አሳውን ለመመለስ ባለመፈለጉም ሁለቱ ሰዎች መጣላት ጀመሩ።

የማኅበረሰቡ አባላት ጣልቃ ባይገቡ ኖሮ ነገር ይባባስ ነበር። በስተመጨረሻ በኤ.አር.አር.ኤ ስብሰባ ላይ የነበሩ የአካባቢው መሪ ሰላም ለማውረድ ሲሉ የአሳውን ዋጋ ማለትም 50 ብሩን ከፈሉ።

የአኝዋሃ ሴቶች የበቆሎ ዱቄት፣ጥቅል ጎመን እና ቲማቲም ፑግኒዶ ገበያ ውስጥ እየሸጡ፥ የካቲት 2013፥ Okello Miru

ብልጽግና ለማን?

በ2010 ዓ.ም ባደረገው የመጀመሪያ ጉብኝቱ ላይ አብይ ከአካባቢው ሰዎች ጋ ለመስራት እውነተኛ ፍላጎት እንዳለው ጠቁሞ ነበር። ተሰደው የነበሩ የአኝዋሃ አክቲቪስቶችን (አንቂዎችን) ተቀበለ፤ የማኅበረሰብ መሪዎችንም በመሰብሰብ ከመሰረተ ልማት አንስቶ እስከ ስራ ፈጠራ ያሉ ጉዳዮች ላይ ተወያየ። ስደተኞችን ከማሕበረሰቡ ጋር የማዋሃድ ጉዳይ ለረዥም ሰዓታት ውይይት የተካሄደበት ነበር። የአኝዋሃ ወኪሎች የኑዌሮች ቁጥር መጨመር ጭንቀታቸውን እንደሚያባብሰውና የበለጠ ደም መፋሰስ እንደሚያመጣ ተሟገቱ።

አብይ የገባቸው ቃሎች በርካታ አኝዋዎችን ደስ አሰኘ፤ እነሱን በሚመለከቱ ፖሊሲዎች የውሳኔ ሂደት ላይ ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉበት እድል በስተመጨረሻ እንደተፈጠረ ተሰማቸው፤ በአዲስ አበባ ታህሳስ 18፤2011 ዓ.ም የተካሄደው ስብሰባ ይህን ስሜታቸውን አጠናከረ። ከዛ በኋላ ግን ኢትዮጵያ ስደተኞች ከካምፕ ውጭ የሚኖሩበትን ሁኔታ እንደምታበረታታ መወራት ጀመረ።

ህጉ ከመውጣቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት የጋምቤላው ጁሉ ጊሎ እንደሱ የፌደራል የምክር ቤት አባል የሆኑትን ሰዎች ውይይት በደንብ አልተደረገም በማለት ተጭኗቸው ነበር። በክልሉ ጥቂት ስብሰባዎች ብቻ እንደተካሄዱና እነዚህም ግጭትን እንዴት ማስተናገድ እንደሚቻል አመርቂ ምላሾች እንዳልሰጡ ተናገረ።

ጥር 13፤2011 ዓ.ም ዳልዲም የተባለ የአኝዋሃ ወጣቶች ቡድን መሪዎች ለጋምቤላ ምክር ቤት የስደተኞች ህግ እነሱ ክልል እንዲተገበር እንደማይፈልጉ ጠቅሰው ደብዳቤ ጻፉ። ሌሎች ክልሎች ስደተኞችን ተቀብሎ የማስተናገዱን ድርሻ መጋራት አለባቸው ሲሉ ተናገሩ።

የዛ እለት ከሰአት በኋላ እና በማግስቱ ሙሉውን ቀን ወታደሮች የጋምቤላን ከተማ ሲዞሩ ዋሉ። የስደተኛ ህጉ ከክልሉ ውጭ በሁሉም ሊባል በሚያስችል ሁኔታ ይሁንታን አግኝቶ ጸደቀ።

ካልተተገበሩ ፖሊሲዎች ጀርባ በቂ ምክክር ባለመካሄዱና ግጭት ይቀሰቀሳል የሚል ፍራቻ የፈጠረው እውነተኛ ቁጣ አለ። ለምሳሌ የፑግኒዶ ካምፕ ነዋሪ የሆነ ዴቪድ የሚባል ሰው እንደተናገረው ሰኔ 2012 ዓ.ም ታጣቂዎች በካምፑ አንድ ጽንፍ ይኖሩ የነበሩ ስደተኞች ላይ ጥቃት በማድረስ አንድ ሰው ሲገሉ አንዱን ደግሞ ለእድሜ ልክ አካል ጉዳት (ፓራሊስስ) ዳርገውታል ።

ከአቦቦ ወደ ዲማ እንዲሁም ከአቦቦ ወደ ፑግኒዶ በተጓዝኩባቸው 12 ቀናት የሰማኋቸው እንዲህ አይነት ታሪኮች ሰው እየተላመዳቸው የመጡ የጥቃት አይነቶችን ያሳያሉ።

 ጠብ ያላለ ጥረት

የዩ.ኤኑ ግራንዲ በቅርብ (ማለትም በዚህ አመት) ባደረጉት ጉዞ ጋምቤላን አልጎበኙም፤ በምትኩ በጥቅምት የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የኤርትራ ስደተኞችን ደኅንነት መንግስት ማስጠበቅ ባለመቻሉ በትግራይ በተፈጠረው የስደተኞች ቀውስ ላይ ነው ያተኮሩት። ጥር 24 ባደረጉት የመሰናበቻ ንግግራቸውም “ኢትዮጵያ ስደተኞችን በዘርፈ ብዙ መንገድ በማገዝ ተምሳሌት ናት፤ ይህም መንግስት በህግ ማውጣትና መተግበር ሂደት ላይ ያፀደቃቸው ፈር ቀዳጅ ፖሊሲዎች ውጤት ነው” ሲሉ ገልጸዋል። የአብይ መንግስት አሁንም እንዲህ አይነት ሙገሳ ሊያገኝ ይችላል፤ ነገር ግን ለኤርትራና ለደቡብ ሱዳን ጥገኝነት ጠያቂዎች እንደበፊቱ በቀላሉ እውቅና የሚሰጥበት አካሄድ አብቅቷል፤ በጋምቤላ የቀጠለው ግጭትም ፖሊሲዎች የሚቀረጹበትና የሚተገበሩበት መንገድ ክልሉን መክፈል ከሚገባው ዋጋ በላይ እያስከፈለ እንደሆነ ጠንካራ አመላካች ነው።

አብዛኛዎቹ በከፍተኛ የፌደራል የስራ መደቦች ላይ ያሉ ሰዎች ስደተኞችን መቀበል የሚያስከትለው ተጽእኖ አይደርስባቸውም፤ ስለዚህ ይህ ለነሱ ትልቅ ጉዳይ አይደለም። እንደ ብልጽግና ፓርቲ ወይም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ያሉ ስደተኞችን ከኅብረተሰቡ ጋር ለመቀላቀል ወይም የማኅበረስብ ውጥረቶችን ለማርገብ ምንም ዝርዝር እቅድ የሌላቸው ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ይህ አይጎዳቸውም። ስደተኞችን ከስደተኛ ተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ለማዋሀድ የሚዘጋጁ ፖሊሲዎች ጉዳዩ ተጽዕኖ የሚያሳርፍባቸውን ሰዎችን ሳያካትቱ መሃል ሃገር ላይ ነው የሚቀረጹት።

ነገር ግን ምርጫ እየተቃረበና ውጥረትም እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ሰዓት ተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋምቤላን ህዝብና ችግር ጨው የሌለው ርካሽ አሳ እንደያዘ ኩሬ አድርጎ ከመመልከት የበለጠ ቦታ ቢሰጡት መልካም ነው። መልካም አጋጣሚዎችን የሚጨምሩ ፖሊሲዎችን መቅረጽ ላይ ዘላቂ የፖለቲካ ትኩረት ከተደረገ ክልሉ ግጭቶችን መቀነስ እንዲሁም አቅሙን ጥቅም ላይ ማዋል ይችላል።

ማዋሃድና ማስፈር

በሚያዝያ 8 ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ጥገኝነት የሚሹ ስደተኞች ጋምቤላን ከደቡብ ሱዳን በሚያዋስነው ፓጋክ በተሰኘው የድንበር ከተማ በሚገኝ የመቀበያ ጣቢያ ለወራት ያህል መሄጃ አጥተው በአስከፊ ሁኔታ እንዳሉ በመግለጽ ጉልህ ተግዳሮቶች እንዳሉ ጠቅሷል ። እንደሌሎች ሁሉ እነዚህ ጥገኝነት ጠያቂዎችም (ሁሉም ከደቡብ ሱዳን የመጡ ኑዌሮች ሲሆን አሁን ቁጥራቸው ከ10,000 በላይ ይደርሳል) የሆነ ቦታ ላይ መስፈር ይኖርባቸዋል። ነገር ግን የት?

የቆዩ ቅሬታዎችና አኝዋዎችን ጎድቶ ለኑዌሮች በሚያደላ መልኩ የሚደረግ የስነ-ህዝብ (ዲሞግራፊ) ቅየራ በስደተኞችና በስደተኛ ተቀባዩ ህዝብ መካከል ያለው ግንኙነት ሰላማዊ እንዳይሆን እንቅፋት ይፈጥራል። ነገር ግን በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ሶማሌና አፋር ክልሎች በስደተኛ ተቀባዩ ህዝብና በስደተኞች መካከል ያለው ውጥረት አነስተኛ ነው፤ በጋምቤላም ቢሆን እንደ ኡዱክ፣ኑቢያ እና ሺሉክ ያሉ የተፈናቀሉ ማኅበረሰቦች በጥቅሉ ከስደተኛ ተቀባዩ ማኅበረሰብ ጋር የተሻለ ግንኙነት አላቸው።

በተመሳሳይ ሁኔታ ምንም እንኳን በድንበር አካባቢ ባሉ የመሳሪያና ሰዎች ፍሰት ላይ ከሚከሰት የቁጥጥር ማነስ የተነሳ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች ቢኖሩም ሙርል እና አኝዋም በስምምነት ይኖራሉ። አሁንም እነዚህ ግጭቶች እንደሌሎች ስር የሰደዱ ባለመሆናቸው ቀጥታ ውይይት በማድረግና ድንበር ላይ  ቁጥጥርን የበለጠ በማጠናከር መፈታት ይችላሉ።

በሌላ በኩል በጋምቤላ የኑዌር ስደተኞች ከማኅበረሰቡ ጋር መዋሃድ በፖለቲካ ውክልና ላይ አንድምታ አለው። የታደሰው የኢትዮጵያ የስደተኛ ህግ ኤ.አር.አር.ኤ ለስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች  የመኖሪያ ስፍራ እንዲያመቻች የሚፈቅድ ቢሆንም “የተዘጋጀው የመኖሪያ ስፍራ ከስደተኞቹ እናት አገር ድንበር በአንጻራዊ ቅርበት ላይ የሚገኝ መሆን አለበት” የሚል ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣል።

ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ስናስገባ የጋምቤላ ህብረተሰብ ላይ የተፈጠረውን ጫና መቀነስ የሚቻልበት እንዱ አማራጭ የተወሰኑ ስደተኞችን ወደ ሌሎች ክልሎች ማዘዋወር ነው። እንደ አዲስ አበባ ያሉ ትልልቅ ከተሞችም ለስራ የበለጠ እድሎች ስለሚገኙባቸው እንደ አማራጭ መታየት አለባቸው። እርግጥ ነው ስደተኞች እንደ ኑዌር ዞን ባሉ የራሳቸው ማኅበረሰቦች በሚገኙባችው ስፍራዎች መኖርን ይመርጣሉ።

የኑዌር ዞን አካባቢ

ከተባበሩት መንግስታት የሚገኝ መረጃ እንደሚያሳየው ጋምቤላ ከሚመጡት አስር ሰዎች ዘጠኙ ኑዌሮች ናቸው። ሆኖም በኑዌር ዞን ሁለት ካምፕ ብቻ ነው እስከአሁን የተከፈተው፤ ሁለቱም ደግሞ ተዘግተዋል። በ2007 ዓ.ም በኑዌር ዞን በኒፕ ኒፕና በሊቾር ይኖሩ የነበሩ ከ50,000 በላይ ስደተኞች በጤናና ንጽህና ችግር እንዲሁም በዝናብ ወቅት በሚከሰት ተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ የተነሳ በአኝዋሃ ዞን በሚገኙት እንደፑግኒዶ እና ጀዊ ወዳሉ ከፍተኛ ስፍራዎች እንዲዛወሩ ተደርገዋል። በርካታ የኑዌር አዲስ ገቢ ስደተኞችም ማረፊያቸው በኢታንግ ልዩ ወረዳ የሚገኙት ካምፖች ናቸው።

ከዛን ጊዜ ጀምሮ በዚሁ ምክንያት በኑዌር ዞን ምንም አይነት ካምፕ አልተከፈተም። አሁንም የዩኤን የስደተኛ ኤጀንሲ ያወጣው ኢትዮጵያ ካንትሪ ሬፊውጂ ሪስፖንስ ፕላን 2020–21 “መሬትን መለየትና በኑዌሮች በተያዙ ስፍራዎች ላይ ካምፖችን ማስፋፋት አስፈላጊ እንደሆነ ያምናል”።

በጋምቤላ በ2010 ዓ.ም በተካሄደ የሰላም ኮንፍረንስ፤ አንድ የኑዌር ተወካይ የግጭቱ መንስዔ የስደተኛ ካምፖች በአኝዋክ ዞን መሆናቸው እንደሆነ ገልጿል። በምትኩ ለምን የኑዌር ዞን እንደ አማራጭ እንደማይታይም ጠይቋል። ሁሉም የሚመለከታቸው ባለስልጣናት ይህንን ነጥብ የሚገመግሙበት ጊዜ አሁን ነው።

እምነትና ግልጽነት

ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ክልሎች ኃላፊዎች ፕሮጀክቶን የሚያስተዳድረው ኮሚቴ ቁልፍ አካል አይደሉም፤ ይህም ማለት የአካባቢው ነዋሪዎች በማያምኑባቸው መልዕክት ተቀባዮች ነው የነዋሪዎቹ ቅሬታ የሚሰማው። በዚህ መጋቢት ወር የተከሰተ አንድ ጉዳይ ለምሳሌ ይህንን ጥርጣሬ ያሳያል። በዲማ የሚገኙ አኝዋኮች ከሙርል ቡድን ያለን አንድ ሰው በነፍስ ግድያ ጠርጥረውት የነበረ ሲሆን ኤአርአርኤ ግን ግለሰቡ ራሱን አጥፍቷል  የሚል ብይን ሰጠ። ይህ በአካባቢው ሰዎች ዘንድ በቀሰቀሰው ቁጣ ምክንያት የአንድ ሰው ህይወት አለፈ። በአጠቃላይ ነዋሪዎች የኤአርአርኤ ን ሪፖርት አያምኑም፤ ይህም ግንኙነቶች ላይ ጫና ይፈጥራል።

በተግባር ሲታይ በጋምቤላ የአካባቢው ባለስልጣናት ስደተኞችን በመከታተሉ ሂደት አይሳተፉም። ነገር ግን አንድ ስደተኛ በካምፑ ሲሞትና የሞቱ መንስዔ ያልታወቀ ሲሆን የ ኤአርአርኤ ሐላፊዎች የአካባቢውን ባላስልጣናት መፍትሔ እንዲፈልጉ ይጠይቋቸዋል።

ኤ.አር.አር.ኤ ትምህርትና የጤና አገልግሎት በካምፖች እንዲቀርቡ ከበርካታ ለጋሾች ከሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ተጠቃሚ ስለሆነ በአጠቃላይ ሲታይ በኢትዮጵያ ‹የካምፕ ውጪ› አካሄድን ለመደገፍ ቀሰስተኛ ሆኖ ታይቷል። ስለዚህ ስደተኞችን ከማኅበረሰቡ ጋር ለማዋሃድ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ  የቢሮክራሲ ቀሰስተኛ ጉዞ ለማለፍ የፌደራል ስደተኞች ኤጀንሲ ሊደጎም ይገባል። የጋምቤላን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች በደንብ የሚያውቁ የአካባቢው ነዋሪዎች በ ኤአርአርኤ ውስጥ የመሪነቱን ስፍራ ሊያገኙ ይገባል።

ምንም እንኳን ስለስኬታማነታቸው ጥርጣሬ ቢኖርም የአካባቢው መሪዎች የውጭ ድርጅቶች እውቅና ከሚሰጧቸው በላይ መፍትሔ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። ለምሳሌ የሶስት አመት እድሜ ያለው መቀመጫውን ጋምቤላ ያደረገው የሲቪል ሶሳይቲ ተቋም ዲት ኒ ቲክ (ህይወት ዋጋ አላት ማለት ነው) አባል ፒተር ኡልጋክ ችግሩ የጥቂት ሴረኛ ግለሰቦች እንደሆኑና እነሱንም ማኅበረሰቡ ድርጊታቸውን ካጋለጠው በህግ መቅጣት እንደሚቻል፣ የማኅበረሰብ ተኮር ድርጅቶችም በችግሮች ዙሪያ ለመወያየት በማሕበረሰቦች መካከል የውይይት መድረክ ማዘጋጀት እንደሚችሉ ነግሮኛል።

ለትርፍ ያልተቋቋመና መቀመጫውን በጋምቤላ አድርጎ ከባቢያዊ የግብርና እንቅስቃሴን የሚያበረታታው የጎክካቦሮ ዳይሬክተር ኦኩች ኦኬሎ ችግሩ የስደተኞችና የስደተኛ ተቀባዮች ሳይሆን ተለዋዋጩ የስነ-ህዝብ አወቃቀር (ዲሞግራፊያዊ) ሚዛን ነው ይላል፤ይህም ለምሳሌ አኝዋዎች በሲቪል ሰርቪዝ ቅጥር መድልዎ ይደርስብናል የሚል ስጋታቸውን ተገቢ ያደርገዋል።

እነዚህ የአካባቢ መሪዎች፣ የማኅበረሰብ አባላት እና ስደተኞቹ እራሳቸው ግጭትን ለማስወገድና ነገሮችን በተሻለ መንገድ ለማስተዳደር የሚረዱ ጥሩ ኃሳቦች አላቸው። እንዳለመታደል ሆኖ እነዚህ የኅብረተሰቡ አካላት በፖሊሲ አውጪዎች የሚሰሙበት ጊዜ ግን እጅግ አነስተኛ ነው። ለጋሾች የስደተኛ ጉዳይ ላይ ብቻ ከማተኮር የክልሉን መንግስት ስለጋምቤላ ሰፋ ያሉ ፍላጎቶች ማናገር አለባቸው።

ወደፊት ለመራመድ የሚያስችለው ሌላኛው ጠቃሚ መፍትሔ/አማራጭ የሲቪል ድርጅቶች (ከካምፑ ጋ የቅርብ ትስስር ያላቸውን የኃይማኖት ተቋማትን ይጨምራል) ላይ መዋዕለ ነዋይን ማፍሰስና እነሱን ማሳተፍ ነው። ለምሳሌ በዲማ የሚገኙ የአኝዋሃ ቤተክርስቲያኖች ሙርሎችን ለስልጠናና ለቤተክርስቲያን ጉባኤዎች በመጋበዝና ሞት እና መሰል ችግሮች ሲያጋጥሙ በመርዳት ጥሩ ግንኙነት መስርተዋል።

እንዲህ ያሉ በስደተኞችና በስደተኛ ተቀባይ ማኅበረሰብ መካከል በሰላም አብሮ መኖርን የሚያበረታቱ እንቅስቃሴዎች የበለጠ እውቅናና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።

የጋራ ልማት

የስደተኛ ተቀባይ ማኅበረሰብን በቀጥታ የሚጠቅሙ ስራዎችና የልማት መርኃ ግብሮች ላይ መዋእለ ንዋይን ማፍሰስ ለነዋሪዎቹ ከበቂ በላይ ጸጋ በተቸረ ክልል ውስጥ የሚስተዋለውን ከባድ እጥረት አለ የሚለውን ስሜት በማቃለል ረገድ ትርጉም ያለው ሚና ይኖረዋል።

ባለፈው አስር አመት በከፍተኛ ሁኔታ ውድቀት የደረሰበት የመንደር ምስረታ እንቅስቃሴ  ከአካባቢው ነዋሪዎች ፍላጎት ውጪ የተካሄደ ነበር፤ ነገር ግን በመካከለኛ ደረጃ ላሉትና ገበያ ተኮር ግብርና ላይ ለተሰማሩት የአካባቢው ገበሬዎች ክፍት መሬት መተው የሚያስችለው ማኅበረሰብ ተኮር የመንደር ምስረታ ትልም የተሻለ ውጤት ይኖረዋል። ትራክተር ለመከራየት አቅም ያላቸው ገበሬዎች ይህንን ለማድረግ እድሉ ሊመቻችላቸውና እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል፤ እያንዳንዱ ገበሬም ከ15 እስከ 20 ሄክታር የሚሆን መሬት ሊያርስ (ሊያለማ) ይችላል።  በዚህ ሂደት የመስኖ ልማት ይበረታታል፤ ድጎማም ይደረግለታል።

በተጨማሪም በካቶሊክ ለጋሽ ድርጅት በአቦቦ  በተመሰረተው መንደር 8 እና 9 ላይ እንደተደረገው በአሳታፊ የመንደር ምስረታ ሂደት የሚገኝ መሬት እርሻ ተመስርቶበት ለግንባታ የሚውል እንጨትና ማንጎን በጅምላ ለማምረት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። ያ ስኬታማ መርኃ ግብር ለአካባቢው ነዋሪዎች የገቢ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

በጋምቤላ በአንፃራዊነት  መሬት ያለ እንደመሆኑ ሰፊ ገበያ ተኮር የእርሻ ስራ ለመስራት የሚያስችል ሁኔታ አለ፤  ይህ መሆን የሚችለው ግን ተሳታፊዎች ባለው የገበያ ዋጋ መሬት እስከተከራዩ፣ ውኃ እስከተጠቀሙ፣ የሚጠበቅባቸውን ግብር እስከከፈሉና አንዳንድ ባለሀብቶች እንዳደረጉት ደን በማቃጠል ከሰልን ከአገር በህገወጥ መንገድ በመላክ ተግባር እስካልተሳተፉ ድረስ ነው። በንግድ ተኮር ግብርና ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የምግብ ተደራሽነትንና ዋስትናን ለመጨመር እንዲቻል የተወሰነው ምርታቸውን አገር ውስጥ እንዲሸጡ፣ የአገሪቱ ዜጎችን ለመቅጠር ቅድሚያ እንዲሰጡ  እና እንደ ዘሩ ገብረ ሊባኖስ ባሉ በተፈጥሮ ጫካ ባልተሸፈኑ መሬቶች እንዲጠቀሙ የሚያስገድዱ ደንቦች ተፈጻሚ ሊሆኑባቸው ይገባል።

የኑዌር ስደተኛ ሴቶች በፒንዩዶ ሰፈር የሳር ጥቅሎች እየሸጡ፥ የካቲት 2013፥ Okello Miru

በአሁን ሰዓት በአብዛኛው ምንም እንቅስቃሴ በማይስተዋልበት የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ላይ መዋዕለ ነዋይ አፍስሶ ማደስ ቱሪዝም፣ የስራ እድልና የአካባቢ ጥበቃ ትምህርትን በማምጣት በኩል ክልሉን ተጠቃሚ ያደርጋል። በጋምቤላ መሬትን በጋራ ለመጠቀምና ለማልማት ተጀምሮ የተቋረጠው ዘዴ በድጋሚ መጀመር አለበት። ደግሞም ፓርኩ ከአፍሪካ ሁለተኛ የሆነውን ከፍተኛ አመታዊ የእንሳስት ፍልሰት (ከደቡብ ሱዳን ባለነጭ ጆሮ አጋዘን የሚያደርገው ጉዞ ማለት ነው) የሚያስተናግድ ስፍራ ነው።

ሁሉም መፍትሔዎች የወጣቶች ስራ አጥነትን መቅረፍ ዋነኛ ጉዳይ አድርገው መመልከት አለባቸው። በጋምቤላ በርካታ ወጣቶች የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ (ስደተኞች ላይ የሚሰሩትን ጨምሮ) ለመስራት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ቢያሟሉም ለቃል ፈተና እንኳ አብዛኛውን ጊዜ እንደማይጠሩ በመግለጽ ቅሬታ ያቀርባሉ። እነዚህ ድርጅቶች ለሁሉም እኩል የቅጥር እድል የሚሰጡ እንደሆኑ ቢናገሩም የፍትሐዊ ቀጣሪነታቸው ጉዳይ ግን በአካባቢው ባለስልጣኖች የበለጠ መጠናት አለበት።

የበለጠ የስራ እድል ለመፍጠር እንዲቻል ጋምቤላ የመንግስት የኢንዱስትሪ ልማትን ወደፊት ከሚያስኬዱ አካላት አንዷ እንድትሆን ማድረግ ይቻላል። በክልሉ ጥሬ እቃ ፣ ምቹ የአየር ጸባይ፣ ሸማች ለመሆን ዝግጁ የሆኑ ስደተኞችን የሚረዱ ድርጅቶች ፣ የመንገድ ግንባታዎችና የኃይል አቅርቦት መሻሻሎች እንደመኖራቸው የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መፍጠር ይቻላል።

ኢኮኖሚውን ለሁለቱም ማለትም  ለተቀባይ ማኅበረሰቡና ለስደተኞቹ ስናሳድግ ዘላቂነትን እያሰብን መሆን አለበት። ለምሳሌ ሰዎችን በጋራ አሰባስቦ ማኅበራትን እንዲመሰርቱ መንገር ፍሬያማ እንዳልሆነ ታይቷል። በምትኩ የስራ ፈጠራን ማብቃትና ንግድንና የፈጠራ ክህሎትን ጥቅም ላይ ማዋል የበለጠ የሚጠቅምና የተሻለ ውጤት የሚያመጣ ይሆናል።

እነዚህ ፖሊሲዎች ከማኅበረሰብ ጋር በመመካከር ሲተገበሩ ስኬትን አልሞ የተዘጋጀው የስደተኛ ህግ ለኢትዮጵያ መንግስት ቼክ በሚፈርሙት ወገኖች ብቻ ሳይሆን ተጽእኖው በሚያርፍባቸው ህዝቦችም ጭምር ተቀባይነት ይኖረዋል።

የሚመጣውን ምርጫ የትኛውም ፓርቲ ቢያሸንፍ አገር በቀል መፍትሔዎችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆን አለበት። ይህንንም ማድረግ ያለባቸው ድምጽ ስለሚያስገኝላቸው ሳይሆን የጋምቤላ ሰላምና ብልጽግና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ስለሆነና በክልሉ የሰው ልጆች ህይወት እንደ ኦኩራ የረከሰ መሆን ስለሌበት ነው።

ጥያቄ ወይም እርማት? ኢሜል ይላኩልን

ኢትዮጵያ ኢንሳይትን ይከተሉ

ይህ ጽሁፍ ምርጫ 2013ን በሚመለከት ዘለግ ያሉ ጽሁፎችን ከመላው ኢትዮጵያ በተከታታይ የምናቀርብበት የ “Ethiopia Insight Election Project (EIEP)” ክፍል ነው።

ዋና ምስል: በአኙዋሃ ዞን የሚገኘው ፑግኒዶ 2 የስደተኛ ካምፕ፥ ጥር 29፥ 2013፥ Okello Miru

የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ

በ Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 ዓለም አቀፍ ፈቃድ ስር የታተመ፡፡ licence. እንደገና ካተሙ የኢትዮጵያ ኢንሳይትን ስም ጠቅሰው ይህንን ገጽ ያገናኙ።

ከመላው ኢትዮጵያ የሚመጡ ዜናዎችን ለመተንተን ድጋፍዎን እንፈልጋለን
እባክዎን የኢትዮጵያ ኢንሳይትን ሽፋን ይደግፉ
Become a patron at Patreon!

About the author

Okello Miru

Okello is based in Abobo and works on security issues for a non-governmental organization. He is a Gambella State Council candidate in Abobo for the Ethiopian Citizens for Social Justice Party.

Leave a Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.