በደቡብ ኢትዮጵያ የአዳዲስ ክልሎች መመስረት ስፍራው ላለበት በርካታ ተግዳሮቶች አስፈላጊ ምላሽ ቢሆንም በቂ ግን አይደለም።
በመስከረም 20፣ 2013 የከፋ ፣ ሸካ፣ ቤንች-ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እና ኮንታ ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ክልል የመሆን የየግል ጥያቄያቸውን ወደ ጎን በመተው በጋራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስትን ለመመስረት በአንድ ድምጽ ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ መወሰናቸውን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታውን በማጽደቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ኢብምቦ) ህዝበ-ውሳኔ እንዲያዘጋጅ ጠየቀ። ይህን ተከትሎ ህዝበ ውሳኔው ከስድሰተኛው ብሔራዊና ክልልላዊ ምርጫ ጋር በጋራ ሰኔ 14 እንዲካሄድ ታቅዶ የነበር ቢሆንም እስከ ጳጉሜ 1 እንዲራዘም ተደርጓል።
ህዝበ-ውሳኔው ከተካሄደ አዲስ ክልል ማለትም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የመመስረት እድሉ የሰፋ ነው።
የደቡብ ምዕራቡ ህዝበ ውሳኔ ከተለያዩ ራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነት ከሚፈልጉ በርካታ ዞኖች መካከል በርካታ ብሔሮች የሚገኙበት አንድ ውህድ ክልል ለመፍጠር መሞከሩ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል።
ታዲያ ክልል የመሆን ጥያቄዎች በአጠቃላይ በደቡብ እየጨመሩ የመጡት ለምንድ ነው? የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጲያ ክልል የመሆን ጥያቄ በተናጠል ከሚቀርቡ ክልል የመሆን ጥያቄዎች የበለጠ ትኩረት እያገኘ የመጣበት ምክንያትስ? ከህገ-መንግስቱ አቀራረጽና በተግባር ላይ ካለው የኢትዮጵያ ፌደራል ስርዓት አንፃር የደቡብ ምዕራብ ህዝበ ውሳኔ ህገ-መንግስታዊ አረዳዱና ፖለቲካዊ አንድምታውስ ምንድነው? ምናልባትም ከሁሉም ጠቃሚው ነገር የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት (ደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ) ከምዕራብ ልዩ ህዝበ ውሳኔ በኋላ ዕጣ ፈንታው ምንድነው? የሚለው ነው።
እነዚህንና ሌሎች ጥያቄዎችና ለመመለስ የአካባቢዉን ጠመዝማዛና አስቸጋሪ መንገድ በማቋረጥ ከወላይታ ሶዶ ወደ ዳውሮ ተጓዝኩእነዚህ የተጓዝኩባቸው ስፍራዎችም የተለያየ ዕጣ ፈንታ የሚጠብቃቸው ናቸው።
በጉዞዬ አስተዳዳሪዎችን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችን፣መምህራኖችን፣የንግድ ሰዎችንና መንገደኞችን አነጋግሬ ነበር። ይህንንም ያደረግኩት የደቡብ ምዕራብ ህዝበ ውሳኔ ከመደረጉ በፊት በተጨባጭ መሬት ላይ ምን እንዳለና ለተቀሪው የክልሉ ክፍሎች ምን ማለት እንደሚሆን ሰፋ ባለ መልኩ ለመረዳት ነበር።
ፈታኝ የብሔር ፌደራሊዝም
ገዢው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በ1984 ዓ.ም በርካታ ብሔሮችን ያቀፈና የተለያዩ የደቡብ ህዝቦችንና ብሔረሰቦችን የያዘ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት (ደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ) በመባል የሚታወቅ ክልል ለመመስረት ሲወስን ገና ከጅማሬው ውዝግብ አስነስቶ ነበር። እውነትም ገና ከመመስረቱ ከፍተኛ ሙግቶችና ክልል እንሁን በሚል ጥያቄ ምክንያት ግጭቶች አዘውትረው መፈጠራቸው የተለመደ ሆነ።
አሁን የኢትዮጵያ የብሔር ፌደራሊዝም ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶች ለበርካቶች እንግዳ ነገር አይደሉም። ስርዓቱ ከብሔራዊ አንድነት ይልቅ ከተመሳሳይ ብሔር መሆንን ማዕከል ያደረገ ህገ-መንግስት በመፍጠሩ፣የክልልና ንዑስ ክልል አስተዳደሮችን በብሔር ርስት (ወሰን) በማዋቀሩና በርካታ ገጽታ ያላቸውንና የተለያዩ ፍላጎቶችን በአስተዳደራዊ መንገድ እንዲፈታ ታልሞ ቢቀረጽም ይህንን ለማድረግ ባለመቻሉ በከፍተኛ ሁኔታ ይወገዛል።
በሌላ መልኩ ደግሞ ህገ-መንግስቱ ለኢትዮጵያ ህዝቦች/ብሔሮች ቅድመ ሁኔታ የሌለው ነገር ግን ጥያቄ ሊነሳበት የሚችል የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ልዩ ቃል ገብቷል።
ህጉ ብሔሮች ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክን ጨምሮ የራሳቸውን የማንነት መገለጫዎች ተግባር ላይ እንዲያውሉ፣ እንዲጠብቁና እንዲያጎለብቱ፤ በመንግስት አስተዳደሮች ትርጉም ባለው መንገድ እንዲሳተፉና በእኩልነት በተለያዩ የመንግስት ደረጃዎች እንዲወከሉ እንዲሁም ራስን በራስ ማስተዳደሪያ ተቋማት እንዲመሰርቱና ሉዓላዊነትን እስከ መገንጠል ድረስ እንዲተገብሩ መብቶችን ያቀዳጃል።
ማንነት ልዩነትን መፍጠሪያ መንገድ ሆኖ ጥቅም ላይ መዋሉ ላይ አክብሮትና እውቅና እንደተራ ነገር መወሰዳቸው ወይም እነኚህ ነገሮች በአገሪቱ ባሉ የተለያዩ ክልሎች በእኩል መንገድ አለመተግበራቸው ሲታከልበት ወደ ግጭት ማምራቱ አያስገርምም። ብሔርን በማስቀደም በታሪክ በእኩልነት ላይ ያልተመሰረቱ ግንኙነቶችን ማስተካከል ይቻላል የሚለው የኢህአዴግ አስተሳሰብ በቂ አልነበረም። ታሪካዊ ግጭቶችን ለመፍታት ትክክለኛ ክትትልና ቁርጠኝነት፤ ፍትሃዊነትንና እኩልነትን ለማረጋገጥ ፍትሃዊ የሆነ ልማት ላይ ትኩረት በማረግ ልዩነቶችን ማጥበብና የጋራ ፍላጎቶችና ራዕዮች ላይ ተመስርቶ ትብብርን ማዳበር ያስፈልግ ነበር።
በመልክዓ ምድራዊ አቀማማመጡ የተለያየ በሆነው በደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ ወደ ሃምሳ የምጠጉ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች የሚገኙ በመሆኑ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መምጣቱ የማይቀር ጉዳይ ነበር።
ልዩ ግዛቶች
የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን እንደ ገንዘብ፣ ደኅንነትና የትምህርት ፖሊሲ ባሉ ዘርፎች ክልሎች በራሳቸው እንዲወስኑ ነጻነት ይሰጣል፤ ነገር ግን አብዛኛው የገንዘብ አቅም ከፌዴራል መንግስት ዝውውር (ድጎማ) የሚገኝ ሲሆን እንደ የመሬት ባለቤት ህዝብ እንደሆነ የሚደነግጉ ዋና ዋና (ሁሉን አቀፍ) ፖሊሲዎችንም የሚያረቀው ማዕከላዊ መንግስት ነው። ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ከክልሎች በታች ሲሆኑ ከወረዳ ጋር ሲነፃፀሩ ግን የተሻለ ነፃነት አላቸው፡፡ ለምሳሌ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ከክልል አስተዳደር በጀት ተቀብለው ያስተዳድራሉ።
የፌዴራልና ክልላዊ ህገ-መንግስታዊ መብቶችን ተከትለው ባለፉት ሶስት አመታት በደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ የሚገኙ በህዝብ ቁጥር ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዙት አስራ አንዱ ዞኖች ወደ ክልልነት ለማደግ የክልል መንግስቱን ህዝበ ውሳኔ የጠየቁ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ከሲዳማ፣ወላይታ እና ዳውሮ ውጪ ጉራጌ፣ጎፋ፣ጌድዮ፣ከፋ፣ጋሞ፣ከምባታ-ጠምባሮ፣ቤንች-ማጂ፣ሀዲያና ደቡበ ኦሞ ዞኖች ይገኙበታል።
እነዚህ ጥያቄዎች ቀደም ሲል ብሔሮች ራስን በራስ ለማስተዳደር ያደረጉት ሙከራ ተደርገው ነበር የተወሰዱት። ነገር ግን ይህ ጉዳዩን እጅግ ማቃለል ይሆናል ምክንያቱም ክልል መሆን የብሔር እውቅና ከማግኘት የበለጠ ተግባራዊ አንድምታዎች አሉት፤ከነዚህም ውስጥ በኢኮኖሚ ልማት የተሻለ ነፃነት ማግኘት ከፍተኛው ጠቃሚ ጉዳይ ነው።
ሀዝቤ-ዉሳኔ የጠየቁ ዞኖች | የህዝብ ቁጥር | የጠየቁበት ቀን | |
1 | ሲዳማ | 4.1 | ሐምሌ 12/2010 |
2 | ከፋ | 1.2 | ኅዳር 6/2011 |
3 | ጉራጌ | 1.8 | ኅዳር 19/2011 |
4 | ቤንች-ማጂ | 0.9 | ኅዳር 20/ 2011 |
5 | ሃዲያ | 0.8 | ኅዳር 22/ 2011 |
6 | ዳውሮ ዞን | 0.7 | ኅዳር 27/ 2011 |
7 | ወላይታ | 2.2 | ኅዳር 30/ 2011 |
8 | ጋሞ | 1 | ታህሳስ 3/ 2011 |
9 | ከምባታ ጠምባሮ | 1 | ታህሳስ 10/ 2011 |
10 | ደቡብ ኦሞ | 0.8 | ሚያዝያ 15/ 2011 |
11 | ጎፋ | 1.3 | ግንቦት 14/ 2011 |
12 | ጌድዮ | 1.2 |
ስዕል 1፡ ክልል ለመሆን የጠየቁ ዞኖች (የህዝብ ቁጥራቸው በቅርቡ ይፋ በሆነ ግምት መሰረት በሚሊዮኖች የተቀመጠ ነው)
ለነዚህ ህገ-መንግስታዊ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በተለያዩ ጊዜያት የደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ ህዝቦች በኢኮኖሚ፣ባህልና ፖለቲካ ረገድ ተለያይተው ከሚቆሙ ይልቅ በአንድነት ቢቆሙ ወይም ሌላው ቢቀር በተሻለ ለአስተዳደር አመቺ እንዲሁም የጋራ ልማትና አብሮነት ሊያመጣ በሚችል ሁኔታቢዋቀሩ የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የመንግስት ደጋፊ ምሁራኖችና ፖለቲከኞች በደቡብ አንድ የአስተዳደር አወቃቀር መኖሩ የጠነከረ የጋራ የመደራደሪያ ኃይልና የበለጠ ልማት ለማግኘት ያስችላል የሚለውን የዓብይን አቋም ይደግፋሉ ።
እንዳለመታደል ሆኖ እነኚህ ሙግቶች አብዛኛውን ጊዜ ከጥያቄዎቹ ጀርባ ላሉት ትክክለኛ ምክንያቶች እውቅናና ምላሽ ለመስጠት ሲያዳግታቸው ይታያል። ከጥያቄዎቹ ጀርባ ያሉት ምክንያቶች በመሰረታዊ ልማት ላይ በእኩል ደረጃ ኢንቨስት አለማረግና በፌዴራል፣ክልልና በአካባቢ መንግስት ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው። በዚህም የተነሳ ለሁሉም የክልል ጥያቄ እንቅስቃሴዎች (የደቡብ ምዕራብን ጨምሮ) ዋናው ፈተና እንቅስቃሴዎቹ ህዝብ ለሚጠይቀው የተሻሻለ የህዝብ አገልግሎት ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ ወይ የሚለው ነው።
የመላ ምት ደረጃዎች
ህገ-መንስቱን ተገን በማድረግ የደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ ህዝቦች አንድ በአንድ ክልል የመሆን ተልዕኳቸውን ጀመሩ። እንዳለመታደል ሆኖ ግን የፌደራል መንግስት የብሔር ፌደራሊዝም በተግባር የሚያመጣውን ውስብስብ እውነታ ለማስተናገድ ዝግጁ አልነበረም።
ለረዥም ጊዜ ክልል የመሆን ጥያቄዎች ጫና ይደረግባቸው እንዲያውም በኃይል ይታፈኑ ነበር። ነገሮች የነበሩበትን ሁኔታ መቀየር ብሔራዊ ጥቅምን የሚጎዳ ተደርጎ ሳይታሰብ አልቀረም ምክንያቱም ከደቡብ አካባቢ ይሰሙ የነበሩ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች በዋና ከተማዋና በአገሪቱ በአጠቃላይ ባሉ የመንግስት ሰራተኞች ምሁራን ዘንድ ተሰሚነት አላገኙም ነበር።
በስተመጨረሻም ድምጾች መታፈን ወይም መረገጥ የማይችሉበት ደረጃ ደረሱ፤ ለዚህም ማሳያ አንዱ የሲዳማ ጉዳይ ነው። ሲዳማ አማራጭ ሲታጣ ክልል የመሆን ጥያቄዋ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ይህ ደግሞ በክልሉ የበለጠ ግራ መጋባትና ተስፋ መቁረጥን የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል። በርካታ በተመሳሳይ የህግ አካሄድ የተመሰረቱ ጥያቄዎች ውድቅ መደረጋቸው ወይም ችላ ተብለው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ መጽደቁ የአሰራር መድልዎ እንዳለ ያመላክታል፤ ዳውሮ ዞን ለምሳሌ ክልል የመሆን ጥያቄ ቀደም ሲል አቅርባ የነበረ ቢሆንም ልክ እንደ አጎራባቿ ወላይታ እንዳቀረበችው ክልል የመሆን ጥያቄ ምንም የተስፋ ጭላንጭል ሳይሰጠው በእንጥልጥል ተትቷል።
የዳውሮና የወላይታ ጥንታዊ ግዛቶች ተመሳሳይ ታሪኮችና ቅሬታዎች ያላቸው ሲሆኑ ይህም አወዛጋቢ በሆነው በዳግማዊ ሚኒሊክ አገዛዝ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በኃይል ከመካተታቸው ጀምሮ በሀዋሳ ዋና ተቋማት ባላቸው ውክልና ላይ እስካላቸው ቅሬታ ይዘልቃል።
ከወላይታ በተለየ መልኩ ዳውሮ በቅርብ ጊዜ ከአምስት አጎራባች ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ ጋር ኅብረት በመመስረት የክልልነት ጥያቄውን በድጋሚ ለማቅረብ የታሰበበት ውሳኔ ላይ ደርሳለች። ይህም የወላይታ ጥያቄ በእንጥልጥል እንዳለ የዳውሮ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በቅርቡ በኅብረት መልክ ምላሽ የሚያገኘው በእድል እንዳልሆነ ግልጽ የሚያደርግ ነው።
ስለደቡብ ምዕራብ ክልል የመሆን ጥያቄ ታሪክ የበለጠ ለመረዳትና በክልሉ ያሉ ዞኖች የተለያየ ፍላጎት ስላላቸው ደቡብ ምዕራብ አዲስ ክልል መሆን ይችላል ወይ የሚለውን ነገር ለማጣራት (ለመፈተሽ) በመጋቢት ወር ወደ ዳውሮ አምርቼ ነበር።
የዳውሮ ጉዞ
ጉዞዬን በባሌ-አዋሳ በማድረግ ከወላይታ-ሶዶ ወደ ዳውሮ-ተርጫ የሚሄድ የህዝብ ማመላሻ ከጥዋቱ 3፡30 በመያዝ ጀመርኩ። የዳውሮ አስተዳደር ማዕከል የሆነችው ተርጫ የደረስኩት 11፡30 ላይ ነበር። ለማንኛውም ካርታ ማንበብ ለሚችል ሰው ከወላይታ-ሶዶ ዳውሮ ስምንት ረዥም ሰዓታት ቆይቼ መድረሴ የሚያስደነግጥ ነገር ነው።
ዳውሮዎች በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ ከመካተታቸው በፊት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ስርዓት ከነበራቸው ህዝቦች መካከል ነበሩ። በደርግ ጊዜ ከደርግ ስርዓትም በኋላ ለአስር አመት ገደማ ያህል ዳውሮ የሰሜን ኦሞ ዞን አካል ነበረች። እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ የሰሜን ኦሞ ዞን ጋሞ ጎፋ፣ወላይታና ዳውሮ ዞኖች እና ባስኬቶና ኮንታ ልዩ ወረዳዎች ተደርጎ አልተከፈለም ነበር።
የዳውሮ ህዝቦች መረር ያለ ክልል የመሆን ጥያቄ ያነሱት በ2011 ዓ.ም ነው። ጥያቄው ከታሪክና ማንነት ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ነው፤ በአብዛኛው ግን የጥያቄው መነሻ በደቡብ ምዕራብ ያሉ ህዝቦች በሰፊው የሚጋሩት አሳሳቢ የሚሏቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ነው።
እነዚህ አሳሳቢ ጉዳዮች በአካባቢ ደረጃ የተስፋፋ የመልካም አስተዳደር እጦትና የመንግስት ቸልተኝነት፣ በፌደራልና በክልል ደረጃ በበቂ ደረጃ ውክልና አለማግኘት፣ ኃላፊነትንና ጥቅምን እኩል ባለመጋራት የተፈጠሩ ቅራኔዎች፤መሰረታዊ ልማት ላይ በሚውለው ኢንቨስትመንት አለመርካትና በቂ ያልሆነ ልማት፣ የልህቃን የፖለቲካ ጥላቻና የማዕከሉ የክልል የገጠር ክፍሎችን ለመረዳት አለመቻል እንዲሁም ወደ ክልሉ መዲና ለመሄድ ያለው እርቀትና የመጓጓዣ ችግር ናቸው።
በስተመጨረሻም እነኚህ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው አሳሳቢ ጉዳዮች የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመሆን ጥያቄን ወደ ጫፍ ለመግፋት እገዛ አደርገዋል።
የግል ቅራኔዎችን ሳይጨምር መሰረተ ልማት ላይ የበለጠ ትኩረት እንዲሁም በተለይ በዳውሮ የበለጠ ተደራሽ የሆነ አስተዳደር የማስፈለጉ ጉዳይ የማያከራክር ነበር። የቅርብ ጊዜ የመንገድ፣ውሃና ቱሪዝም ስራዎች እንዲሁም የሚዛን ቴፒ አየር መንገድና በቤንች-ሸኮ ዞን የሚዛን አማን ስቴድየምን ጨምሮ ሌሎች የግንባታ ስራዎች ተጠቃሽ ቢሆኑም በዳውሮ ዞን ስለሚከናወኑ ስራዎች ስኬታማነት ከሀዋሳ እስከ አዲስ አበባ ባሉ ሩቅ መንግስቶች የነበረው እምነትና ክትትል አነስተኛ ነበር።
ወደ ተርጫ የሚያመራው መንገድ
ዳውሮ ከደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ መዲና ሀዋሳ 319 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስትገኝ የአስተዳደር ከተማዋ ተርጫ በሻሸመኔ-ሶዶ መንገድ ከአዲስ አበባ ደቡብ ምዕራብ 507 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፤ በሆሳዕና-ሶዶ መንገድ ደግሞ ከመዲናዋ (ዋና ከተማዋ) 435 ኪሎ ሜትር የምትርቅ ስትሆን፤ በጅማ-ኮንታ መንገድ ደግሞ 490 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
በወላይታ-ሶዶ ከተነሳሁበት ስፍራ አንስቶ ዳውሮ-ተርጫ 166 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ስትሆን ይህም በጠመዝማዛና ባረጁ መንገዶች ሲጓዙ ያለው ርቀት ነው። ከዳውሮ አጎራባች ከሆነችው ሶዶ ወደ ዳውሮ ለመጓዝ የመጓጓዣ አገልግሎት እጥረት አለ። አሽከርካሪዎች ጉዞ የሚያደርጉት ለመንግስት ስራ የሚጓዙ ባለስልጣናትንና ለግል ጉዳይ የሚጓዙ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተጓዦችን በየዕለቱ በማስላት ነው።
የሶዶ-ተርጫ ተጓዦች በወላይታ-ሶዶ የአውቶብስ ጣቢያ ከሚገኙ ደላሎች ጋር ስለአገልግሎት መኖር አለመኖርና ክፍያ መደራደር ይጠበቅባቸዋል። የትኬት ዋጋ አብዛኛውን ጊዜ በነዚህ ደላሎች ጥያቄ ላይ የሚመሰረት ሲሆን ከመጓጓዣው ክፍያ ላይ የራሳቸውን ድርሻ ይወስዳሉ። ከመነሻው የተለየ የትኛውም ስፍራ ላይ (ግማሽ መንገድ ላይ ሊሆን እራሱ ይችላል) የሚሳፈር ማንኛውም ሰው ከመነሻው ከሚከፈለው ክፍያ እኩል እንዲከፍል ይገደዳል።
የሶዶ-ተርጫ መንገድ ከአስር አመት በፊት የጊቤ 3 ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ የተቀየረ ሲሆን ተጓዦች የተሻሻለው መንገድ በቀጥታ በጊቤ ወንዝ ድልድይ ላይ ስለማያልፍ አላስፈላጊ ርቀትና መጉላላት(እንግልት) ይጨምራል በማለት ቅሬታ ያሰማሉ። አልተሳሳቱም፤ምክንያቱም የተሻሻለው መንገድ ተጨማሪ ጠመዝማዛ 60 ኪሎ ሜትር የሚጨምር ሲሆን ይህም በአማካይ 3 የጉዞ ሰዓታት ማለት ነው።
በሌላ አቅጣጫ የተቀየሰው ይህ የተሻሻለው መንገድ በባሌ-አዋሳ መንገድ አርጎ ተራራማና አለታማ በሆነችው የኪንዶ-ኮይሻ ስፍራ ያልፋል። ይህ ስፍራ በደረቅ፣ከልክ በላይ ጥቅም ላይ በዋለ እና ምርታማ ባለሆነ መሬት ምክንያት የወደመ ነው። መንገዱን አቋርጠን እያለፍን በነበረወቅት አንድ ተጓዥ ‘’እነዚህ ሰዎች ምን እየበሉ እንደሚኖሩ ግራ ነው የሚገባኝ’’ በማለት ተደነቀ።
ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር ለመሬት መንሸራተት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ሲሆን ይህም በተራው ለመጓጓዣ አደገኛ ሁኔታ ይፈጥራል። በዚህም ምክንያት በስፍራው የመኪና አደጋዎች የለተመዱ ሲሆኑ የሰው ህይወት የሚቀጥፉም ሊሆኑ ይችላሉ። ረዥምና ምቹ ያልሆነው ጉዞም እድሜያቸው የገፉና የጤና ችግር ያለባቸው ተጓዦችን አሳሳቢ አደጋ ላይ የሚጥል ነው።
ከጊቤ 3 ፡ ከመሰረተ ልማት እና ስለመንገዱ ጉዳዮች በተጨማሪ ሌሎች አሳሳቢ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ተርጫ ውስጥ ያነጋገርኳቸው ሰዎች የጊቤ 3 ንዑስ ጣቢያ ከዳውሮ ይልቅ በወላይታ መገንባቱ አግባብ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
ምንም እንኳን ግድቡ ቢገነባም የኤሌክትሪክ ስርጭት በዞኖቹ በአጠቃላይ ተመሳሳይ አይደለም። በደቡብ ምዕራብ በአጠቃላይ የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ብቻ ሳይሆን የኤሌክትሪክ ተደራሽነትም እጥረት አለባቸው።
ከተርጫ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውንና የዳውሮ የቀድሞ የአስተዳደር ማዕከል የነበረችዋን የዋካ ከተማን ጉዳይ እንመልከት።
ዋካ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠቃሚነት ካላቸው ስፍራዎች አንዷ ተደርጋ የምትቆጠር ብትሆንም እኔ በጎበኘሁ ወቅት ያረጁ የመንደር ቤቶችና ያላደጉና በቂ ያልሆኑ መሰረታዊ ልማቶችን ብቻ ነው ያየሁት። የተወሰነ ተስፋ የሚሰጠው ነገር የከተማውን መንገድ ለማውጣት ይደረግ የነበረ ነገር ግን አሁንም ያልተጠናቀቀ መጠነኛ ቁፋሮ ነበር።
በመንግስት ተነሳሽነት የተጀመረው የመንገድ ጥገና እቅድ ከዋካ እስከ ተርጫ የሚደርስ ሲሆን በተርጫ የሚገኘው ያረጀውና ጠባቡ በከተማው መኃል የሚያልፈው መንገድ ለተርጫ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለመገንባትና የኮይሻ እቅዶችን ለመጀመር በቅርቡ እንዲፈርስ ተደርጓል። እቅዶቹ አገልግሎቶችን ለማግኘት ተስፋን የሚሰጡ ሲሆን የከተማ አስተዳደር ማዕከሎችንም በአንጻራዊነት ተደራሽነት እንዲሆኑ ያደርጋሉ።
ነገር ግን አሁንም በርካታ ሰዎች ግንባታዎቹ መቼ እንደሚጠናቀቁና ጅምሮቹ እውን ይሆኑ እንደሆን ይጠይቃሉ። በተጨማሪም ፍላጎቶቹ አንድ መንገድ ሊያረካው ከሚችለው በላይ ናቸው። በዳውሮ ከሚገኙ 181 ቀበሌዎች 30ዎቹ ብቻ ናቸው ቀበሌን ከቀበሌ ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ያሏቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ አንድ መንገድ በመጠናቀቅ ሂደት ላይ እንዳለ፤ በፖለቲካው ማዕከል ያለው የውክልና ጥያቄ አለመሟላቱ እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል።
የዳውሮ ህዝበ-ዉሳኔ
የዳውሮ ህዝቦች በሀዋሳ ያሉ የክልሉ አስተዳደሮችና በአዲስ አበባ ያሉ የፌደራል አስተዳደሮች ፍላጎታቸንን ለረዥም ጊዜያት ችላ ብለዋል የሚል ቅሬታ የሚያቀርቡ ሲሆን፤ይህም በርካቶች ከነዚህ ማዕከላት የሚመጡ መፍትሔዎችን በጥርጣሬ እንዲያዩ አርጓቸዋል።
ከተርጫና ዋካ ነዋሪዎች ጋር ካደረኩት ንግግር በአስተዳደር አወቃቀር ውስጥ የተሰሩ ያለፉ ስህተቶችን የዳውሮ ህዝቦች በሚገባ እንደሚረዱ ለማወቅ ይቻል ነበር። ነዋሪዎቹ በኢህአዴግና በአባል ፓርቲው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) የተመሰረተውን ስርዓት አሁን እየሆኑ ላሉ መጥፎ ክንውኖች ተጠያቂ የሚያደርጉ ሲሆን የህዝቡን ፍላጎት በትክክል ለማንጸባረቅ አዲስ አስተዳደር ሊዋቀር ወይም አሁን ያሉት አስተዳደሮች ሊዋሀዱ ይገባል ይህም በህዝቦቹ በራሳቸው ሊካሄድ ይገባል ይላሉ።
የደቡብ ምዕራብ ክልላዊ ግዛት አስተዳደር ብሔራዊ አንድነትን እስከጠበቀ፣ በተዋሃደው ክልል ያሉ ሰዎችን በሙሉ እስከወከለና ሃላፊነትንና ጥቅምን በጋራ እስካከፋፈለ ድረስ በርካታ የዳውሮ ነዋሪዎች የጋራ የደቡብ ምዕራብ እትዮጵያ ክልላዊ ግዛትን እንደሚቀበሉ ይገልጻሉ።
ቀደምት ፖለቲከኛ የሆነውና አሁን በተርጫ ኢትዮ-ቴሌኮም ምክትል አስተዳዳሪ የሆነው ደምብሎ ገብረአቡ በአዋሳኙ ስፍራ የሚገኙ ህዝቦች የዳውሮ ህዝቦችን ጨምሮ የሚያሳስቧቸው ነገሮች መሰረታዊ እንደሆኑ ያምናል፤ እነዚህም እንደ መሰረታዊ ልማትና የእርስ በእርስ መከባበር ያሉ ነገሮች ናቸው ይላል። ደምብሎ ለዳውሮ ህዝቦች ክልል መሆን ቀዳሚ ፍላጎት አይደለም በማለት ለጥያቄው መነሳት ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል የሚላቸውን የመሰረተ ልማት ላይ እኩል ያለሆነ የኢንቨስትመንት ፍሰትና የአገልግሎቶች በእኩል መንገድ አለመዳረስን ተጠያቂ ያደርጋል።
ሲዳማን ከጌድዮ እና ወላይታን ከዳውሮ ጋር በማነጻጸር ‘’ሁለት በተምሳሳይ የአስተዳደ እርከን ላይ የሚገኙ ዞኖች እንዴት ይህን ያህል የተለያየ መሰረተ ልማት ሊኖራቸው ይችላል?’’ ሲል ይጠይቃል።
በተጨማሪም ደምብሎ ከምርጫ በፊት በአዲስ አበባ የነበረው የተካረረ የፖለቲካ ሙግት፣ግጭትና ግራ መጋባት የገጠሩ ህዝብ ፍላጎቶች ብዙ ፋይዳ የለዉም ይላል። የአካባቢ አስተዳደር አላማ ‘’ተደራሽ፣በቂና በኢኮኖሚም አዋጭ በሆነ መንገድ ሰዎችን ማገልገል ነው’’ በማለትም ያክላል።
በተርጫ አቃቤ ህግና የህግ ባለሞያ እንደ ሆነው ምህረቱ መኮንን ከሆነ ዋናው ክልል የመሆን አላማ ‘’ምላሽ የሚሰጥ ለህዝቡ የቀረበ አስተዳደር’’ እንዲኖር ማረግ ነው።
የተርጫ ነዋሪና መምህር የሆነው ሰማያት ተፈሪም ይህን ሃሳብ ይጋራል። ‘’የዳውሮ ህዝቦች ሁሉም ነገር በአንድ ጀምበር እንዲሟላላቸው አይጠብቁም። ነገር ግን ማን ምን እንደሚመለከተው ማወቅ ይሻሉ’’ ሲል ገልጿል።
1. | ቤንች ሸኮ + ምዕራብ ኦሞ | 0.9 |
2. | ዳውሮ | 0.7 |
3. | ከፋ | 1.2 |
4. | ኮንታ | 0.1 |
5. | ሸካ | 0.3 |
ስዕል 2. የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች የህዝብ ቁጥር (ግምቶቹ በሚሊየኖች የተቀመጡ ናቸው፤ የ2011 ዓ.ም የህዝብ ቁጥር ትንበያ)
የዳውሮ ምርጫ
ብሔራዊ ምርጫን በተመለከተ የዳውሮ ነዋሪዎች ተስፋ ሰጪ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጅማሮዎች ምን ያህል በተግባር (በተጨባጭ መልኩ) (እና በመንገድ ግንባት ስራ) ሊገለጹ እንደሚችሉና በምን ያህል ፍጥነትም ሊተገበሩ እንደሚችሉ ይጠራጠራሉ።
በርካቶች ካለፉት ልምዶች እንዳስተዋሉት አንድ ጊዜ ድምጽ ከተሰጠ በኋላ በሚያሳዝን ሁኔታ ቃል የተገቡ ጉዳዮች አይፈጸሙም።
ከምርጫ ቀደም ብሎ በተካሄደ ቃለ-ምልልስ በዳውሮ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሃላፊ የሆነው ከፍታዉ ጂ መሰል ጥርጣሬዎችን በመቃወም ‘’የልማት እቅዶችን ማነሳሳትና መተግበር የመንግስት የምን ጊዜም ተግባር ነው’’ በማለት አስረግጦ ተናግሯል።
ከፍታው አክሎም የዳውሮ ህዝብ ገዢው ፓርቲ በአካባቢው በሚያደርገው እንቅስቃሴዎች የተነሳ የበለጠ በጎ አመለካከት አለው በማለት በአጽንኦት በመግለጽ ‘’ህዝባችን በመንግስት እቅዶች ደስተኛ ነው’’ ሲል ተናግሯል።
የዞኑን አለማደግና ጠቃሚ ፍላጎቶችን ከግምት በማስገባት የብልጽግና ፓርቲ መንግስት በቅርብ ጊዜ በተለይም መንገድ፣ የውሃ ስራዎችና ቱሪዝም አግልግሎት ላይ ትኩረት በማረጉ በተግባር ግድ እንደሚሰጠው በግልጽ ያሳየበትና በምርጫው ድጋፍ ለማግኘት የሞከረበት መንገድ ነበር። ይህም ጥረት ተሳክቷልማለት ይቻላል።
አንድ ያናገርኳቸው የአካባቢው የሃይማኖት መሪ ‘’ህዝቦች አሁን ከበፊቱ ይልቅ እጅግ ነገሮችን ያጤናሉ። ማን የበለጠ እንደሚያገለግላቸው ያውቃሉ ፤ ህዝቦች ከሚያወራ መንግስት ይልቅ የሚተገብር ይፈልጋሉ’’ ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዳውሮ ለብሔራዊ ምርጫ የሚደረገው የፖለቲካ ፉክክር እጅግ አነስተኛ ነበር።
ኢዜማ (የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ) እና የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በተርጫ የፓርቲ ጽህፈት ቤቶችን ቢከፍቱም ሁለቱም ጽህፈት ቤቶች በመጋቢት ወር ለአንድ ሳምንት በቆየሁባቸው ጊዜያቶች ዝግ ሆነው ነው የቆዩት። የጽህፈት ቤቶቹ ስልክ ቁጥሮችም ዝግ ስለነበሩ ከፓርቲዎቹ ተወካዮች ማንንም ማግኘት አልቻልኩም።
በተርጫ ያናገርኩት የህግ ባለሞያ የሆነው አቶ ምህረቱ በዳውሮ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለሚያደርጉት እዚህ ግባ የማይባል እንቅስቃሴ ሲሰጥ ‘’ለውጡ ከጀመረ ጀምሮ አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ወደ ብልጽግና ተስበው ገብተዋል ሌሎች ደግሞ እምብዛም ጠቃሚ አይደሉም ተብለው ተትተዋል። ሌሎች ደግሞ በአሁኑ ወቅት ያለውን የፖለቲካ ለውጥ ለማስተናገድ ሳይችሉ ቀርተዋል’’ ብሏል።
አጭር እረፍት
ወደ ዳውሮ መሄጃ ላይ በመንገድ ዳር በምትገኘውና አዲስ በተመረቀችው ባሌ-አዋሳ ከተማ የተካካሪ ፓርቲዎችን ተጽእኖ በተመለከተ የሰማሁት ምስክርነት ተመሳሳይ ነው ። በስፍራው የሚገኝ አንድ ባለሱቅ ‘’ተቃዋሚዎች ተወግደዋል ጽህፈት ቤታቸውም ተቆልፏል፤ መንግስትም የተቃዋሚ ፓርቲ ተባባሪዎችን ይሰልላል በቁጥጥር ስርም ያውላል’’ ሲል ነግሮኛል።
ነገር ግን በባሌ-አዋሳ በርካቶች የተቃውሞ መታፈንን እንደ ችግር እንዳዩት የሚያሳይ ነገር አላገኘሁም። በአብዛኛው የከተማ ነዋሪዎች ከፖለቲካ ምርጫ ይልቅ ሰላም እንደሚፈልጉና ስራ ማግኘትን እንደሚመርጡ ነው የገለጹት። የሱቁ ባለቤት ‘’ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስራና ሰላምን ሊያስገኙ ይችላሉ?’’ በማለት ይጠይቃል። ‘’የለም፤ ሊያስገኙ አይችሉም’’ በማለትም ይመልሳል። ካለው የህዝብ አመለካከት አንጻር የብልጽግና ፓርቲ በሰኔ ወር በባሌ-አዋሳ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፉ አይገርምም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በወላይታ…
የዳውሮ ክልል የመሆን ጥያቄ በኅብረት ህዝበ ውሳኔ መልክ በቅርቡ ምላሽ የሚያገኝ ሲሆን የሲዳማ ለብቻው ክልል የመሆን ጥያቄ ደግሞ ተቀባይነት ካገኘ ሰንበት ብሏል ፤ ወላይታ ዞን ግን አሁንም ለ21 ወረዳዎቹና በሶዶ ለሚገኘው የአስተዳደር ማዕከሉ የአስተዳደር ነፃነት ለማግኘት ፈታኝ ትግል በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የወላይታ ከተማ ክልል የመሆን ረዥም አመታትን ያስቆጠረ ትግል በ2010 ዓ.ም ነው ከሲዳማ ጋር በገጠመ መልኩ እውቅና ያገኘው። ነገር ግን በደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ ክልል ምክር ቤት ዉስጥ የሃይል አለመመጣጠኖችና ከዚህ ጋር ተያይዘው ያሉ ውስብስብ ጉዳዮች የወላይታን ክልል የመሆን ፍላጎቶች የገቱት ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ ግን የአጎራባቾቻቸው ክልል የመሆን ጥያቄዎች ተቀባይነት አግኝተው ነበር።
የሶዶ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ አብርሃም ባቾሬ ለኢትዮጵያ ኢንሳይት እንደገለጸው ‘’ኢትዮጵያ መድሏዊ አስተዳድራዊ መዋቅሮችን ከዚህ ቀደምም ስትቀርጽ የነበረች ናት፤ የመድሏዊ አስተዳድራዊ መዋቅሮቹ መገለጫቸውም በሚተገበሩ ወቅት ሆን ተብለው በተሳሳተ መንገድ መተግበራቸው ነው’’ ይላል።
የወላይታ ክልል መሆን ጥቅምና ጉዳት
ወላይታ ለብቻዋ ክልል ትሁን የሚለውን ሃሳብ የሚደግፉ ሰዎች ክልል ለመሆን ለሚያቀርቡት ጥያቄ ታሪካዊ፣ህጋዊ፣ፖለቲካዊና ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን ይሰጣሉ። በተጨማሪም በደቡብ ክልል ከሚገኙ ሌሎች ህዝቦችና የአስተዳደር ወሰኖች ጋር ወላይታን በማነጻጸር የህዝብ ቁጥርና የወሰን ስፋት ላይ ተመስርተው ሙግታቸውን ያቀርባሉ።
ሲዳማ አራት ሚሊየን የህዝብ ቁጥር በመያዝ በአገሪቱ አምስተኛ ትልቁ ብሔር ሲሆን የተዋሀደው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጲያ ክልል ደግሞ የህዝብ ቁጥሩ 3.2 ሚሊየን ይገመታል (ስዕል 1ን ይመልከቱ)፤ የወላይታ ብሔር በ2000 ዓ.ም ሁለት ሚልየን እንደሚሆን የተገመተ ሲሆን አሁን በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል።
አብዛኛውን ጊዜ የሚቀርበው ውንጀላ በደኢህዴን-ኢህአዴግ ስር ትክክለኛ ውክልና ባለመኖሩ የተነሳ ክልል የመሆን ፍላጎቶች እንዲገቱ ሆነዋል የሚል ነው ይህም ውንጀላ የተመሰረተው ፓርቲው የህዝብ ፍላጎትን ከማሟላት ይልቅ ለማፈን ይሰራ የነበር መሆኑ ላይ ነው።
የቀድሞ ከንቲባ አብርሃም ‘’ህዝቦች ደኢህዴንን በመመስረትም ሆነ በወሳኝ ጊዜ በተገቢው መንገድ አልተወከሉም።’’ በዚህ ምትክ ‘’የደኢህዴን መስራቾች ቀደም ሲል ለደርግ ወግነው ህወኃትን ሲወጉ የነበሩ በህወኃት መንገድ የተቃኙ የጦር ምርኮኞች የሆኑ የደቡብ ተወላጆች ናቸው’’ ይላል።
የወላይታን ክልል መሆን የሚደግፉ ወጣቶች ደኢህዴን ሆን ብሎ በፖለቲካ ጉዳይ የማመዛዘን ችሎታ የሚጎድላቸውንና ልምድ የሌላቸውን አዲስ ተመራቂዎችን ይመለምላል ሲሉ ይወነጅላሉ። እነዚህ ምልምሎች ከህዝብ ፍላጎት ይልቅ ስልጣናቸው የሚያሳስባቸው ናቸው በማለት ይሞግታሉ፤ ምልምሎቹ አወዛጋቢና በዚህም የተነሳ የሚያጉላላ በመሆኑ ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታን ለመቀበል አይፈልጉም ሲሉም ያክላሉ።
ለወላይታ ነፃነት የሚሟገቱ ሰዎች የወጣቶቹን አክራሪነትና የፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ አይጋሩም ነገር ግን በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል የሚል ሙግት የሚያነሱ የክልል ጥያቄ ደጋፊዎች ፤ በተለይም በትልልቅ ከተማዎች ከሚገኙ ምሁራን፣የንግድ ባለቤቶችና ከመሳሰሉት ድጋፍ አግኝተዋል።
እነዚህ የክልል ጥያቄን የሚደግፉ መሪዎች ይህን የሚያደርጉት የበለጠ ውጤታማ የበጀት አመዳደብና ግብዓትን (ሀብትን) የበለጠ ጥቅም ላይ የማዋል አስፈላጊነት ላይ ተመርኩዘው ነው። መሪዎቹ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣የስራ እድሎችን ለመፍጠር እና የሰው ሀብትን ጥቅም ላይ የሚያውሉ የአገልግሎት ዘርፎችን ለማስፋፋት የሚያልሙ ናቸው።
ለወላይታ ልማት ማኅበር ዋና ስራ አስኪያጅ ሀብታሙ ቲማጢዎስ ግን ክልል መሆን ለህዝቦች ፍላጎት በአግባቡ ምላሽ መስጫ ብቸኛው ተግባራዊ መንገድ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታም ሀብታሙ በስተመጨረሻ ክልል የመሆን አላማን እንደሚያጠለሽና ባለፈው አመት እንደተፈጠረው ወደ ግጭትና ውድመት የሚመራ ስሜታዊ ጥሪን ይቃወማል።
ሀብታሙ የክልል ጥያቄው የጊዜ ጉዳይ እንጂ ተቀባይነት እንደሚያገኝና እስከዛው ድረስ ግን ህግና ደንብን ማክበር አስፈላጊ እንደሆነ ያምናል። ‘’ህዝቦች በሰላማዊ መንገድ ጠይቀዋል፤ እኛም ምላሽ እየጠበቅን ነው’’ ብሏል።
በወላይታ ለሚገኘው የህግ ባለሞያው አቶ ተከተል ደግሞ የክልል አስተዳደር በፖለቲካዊ፣ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ላይ የመወሰን ሰፋ ያለ ነፃነት የሚሰጥ ነው፤ ይህም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ላይ የመወሰን፣ከፌደራል መንግስት የራሱን በጀት ማግኘትና ማስተዳደር መቻል እና የህዝብን ፍላጎት ከግምት ያስገቡ ፖሊሲዎችን የመቅረጽና የመተግበር ስልጣንን ያካትታል።
ተከተል በተጨማሪም አንድ አስተዳደር ክልል ሲሆን ከሌላ ክልል ጋር ስላለው ግንኙነትና የጋራ ፍላጎቶች ላይ የራሱን ውሳኔ ማሳለፍ ይችላል በማለት የክልል አስተዳደር ያለውን የፖለቲካ አንድምታ ይገልጻል። በተጨማሪም ለህዝቡ ቅርብ የሆነ ቀጥታ የአስተዳደር ባለስልጣን መኖሩ የበለጠ ውጤታማነትና ተጠያቂነት እንዲኖር ያደርጋል ሲል ያክላል።
የወላይታን ክልል የመሆን ጥያቄ የሚቃወሙ ለቦታው የአስተዳደር ነፃነት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ተደርጎ መታየት የለበትም ብለው ያምናሉ። እነዚህ ሰዎች ክልል የመሆንን ጉዳይ ጠባብ ብሔርተኝነት አርገው የሚመለከቱ ሲሆን ይህም አመለካከት በኢህአዴግ ወቅት የተለመደ ነበር።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ከፍተኛ ባለስልጣን ተቃውሟቸውን ሲገልጹ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን በአገሪቱ በሙሉ የተበተነውን የወላይታ ህዝብ በወላይታ ዞን ባለው ውስን መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ለማስተዳደር የማይቻል እንደሆነና የወላይታ ህዝቦችን ፍላጎት በመላው አገሪቱ የወላይታ ተወላጆች በሚገኙበት ስፍራ ሁሉ ለማሟላት ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ይገልጻሉ።
አቶ ጎበዜ የወላይታ ቱሳ ፌደራሊስት ግንባር (ቱሳ) ወይም ቱሳ ዋና ጸሀፊ ፤ የአስተዳደር በጀት ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል በማለት ክልል የመሆን ጥያቄን ተቃውመው የሚቀርቡ ሙግቶች መሰረተ-ቢስ ናቸው ብሎ ይሞግታል።
እንደ ጎበዜ ከሆነ በመላው ደቡብ ኢትዮጵያ ያሉ የመሰረተ ልማት ውስንነቶችና ቅራኔዎች በበጀት እጥረት ብቻ የሚከሰቱ አይደሉም ከዚህ ይልቅ በጀትን በአግባቡ ባለመጠቀም፣ሙስናና በጀትን በተገቢው ስፍራ ባለማዋል የሚመጡ ናቸው፤ እነዚህንም ጉዳዮች አዲሱ የወላይታ ክልል አስተዳደር ሲመሰረት የሚፈታቸው ግንባር ቀደም ጉዳዮች ናቸው ይላል።
ሌሎች ከበጀት እጥረት መውጫ መንገዶች፤ የስራ እድል መፍጠር፣ የክልሉን የተፈጥሮ ሀብቶች በተገቢው መንገድ መጠቀምና ሰላማዊ ትብብርንና የተባበረ የህዝብ ኃይልን በመተግበር ኢንቨስትመንትን መሳብ ናቸው። ክልል መሆን ምናልባትም ለግብዓቶች የተሻለ ተደራሽነትን ይፈጥራል ይህም ገቢን ለመጨመር ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል።
ምንም እንኳን በሁለቱም በኩል ጠንካራ ሙግቶች ቢኖሩም የወላይታ አጎራባች የሆኑት ዳውሮዎች ከወላይታ ጋር በጋራ ክልል መፍጠርን በይፋ ከተቃወሙ በኋላ የወላይታን ክልል የመሆን ጥያቄ የሚደግፉ ሰዎች ወደ ፊት እየመጡ ነው።
በእርግጥም ነጻ ክልል መሆን ለወላይታ ህዝቦች የሚስብ የመሆኑ ጉዳይ ጨምሯል፤ይህም የሆነው በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ እንሆናለን የሚለው ጉዳይ ላይ አይናቸውን በማሳረፋቸው ነው። እንደ ሌሎች ዘርፎች ሁኔታዎች ባሉበት እንዲቆዩ መንግስት ማዘናጊያዎችን (መደለያዎችን) ሲያቀርብ ነበር፤ ለዚህም ማሳያዎች ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ ቴሌኮምና የመስኖ እቅዶችን ጨምሮ በዞኑ የተጀመሩ የተወሰኑ እቅዶች ናቸው።
ከምርጫ በኋላ ያለ ፖለቲካ
በጎበኘኋቸው የደቡብ ምዕራብ ህዝቤ-ዉሳኔ ስፍራዎች በሙሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደሌሉ በግልጽ የሚስተዋል ጉዳይ ቢሆንም ቱሳ በወላይታ ተቃዋሚ ፓርቲ በመሆን ከፍተኛ ድጋፍ እያገኘ ይገኛል።
ዋና ጸሀፊው ጎበዜ ፤ ፓርቲው ወላይታን ከጭቆና ለማላቀቅና የህዝቦቿን ሁሉን አቀፍ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እንደሚያልም ይናገራል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ቱሳ ሶስት አላማዎች አሉት፡ 1. ሙሉ በሙሉ የራስን ዕድል በራስ መወሰን 2. የኢኮኖሚ ነፃነትና 3. በወላይታና በአጎራባቾቿ መካከል መስተጋብር እንዲኖር ሰላማዊ አካባቢ መፍጠር ናቸው።
ጎበዜ ለወላይታ ህዝቦች ጭቆና ደኢህዴንን ይወነጅላል። ‘’የወላይታ ህዝቦች ለኢትዮጵያ መንግስት ግንባታ፤ ለሉዓላዊነቷንና ሰላሟን ለማስጠበቅ ያደረገዉ አስተዋጽኦ ያህል ፍትሓዊ ጥቅም እኩል ተካፋይ አልሆኑም’’ በማለት ይናገራል። ደኢህዴን የሰራውን ጥፋት ቱሳ የወላይታ ተወላጅ የሆኑ ፖለቲከኞችን ሚና በማሳደግ፣ሁሉንም ያሉ ግብዓቶችን አሰባስቦ ቀደም ሲል የተፈጠሩ የፍትህ መጓደሎችን ለመቀልበስ ጥረት በማድረግና በኢኮኖሚ ራስን በመቻልና ነፃነትን በማረጋገጥ ያስተካክላል በማለትም ያክላል።
ቱሳ በገጠር ከተማዎች የሚገኙ ጽህፈት ቤቶቹ ሆን ተብለው እንዲታገዱ በመደረጉ ይህንን ለመከላከል መገደዱን ጎበዜ ይናገራል። በተጨማሪም የፓርቲ መሪዎችና አባላቶች እንደሚሰለሉና በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ እንዲሁም ስራቸውን የሚያሳልጡ የመገናኛ መሳሪያዎችም እንደሚያዙ የጠቀሰ ሲሆን አሁንም ‘’በርካታ ተግዳሮቶች ቢገጥሙንም ቱሳ ለወላይታ ህዝቦችና ከወላይታ ህዝቦች ጋር እየሰራ ይገኛል’’ ሲል አክሏል።
በአጠቃላይ በሶዶ፣ቦዲቲና አረካ ከተማዎች ካደረኩት ቃለ-ምልልስ ቱሳ በወላይታ ዞን የብልጽግና ፓርቲን የሚገዳደር ከባድ ተፎካካሪ እንደሚሆን መረዳት ይቻላል። አንድ የቦዲቲ ነዋሩ ‘’ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ሲወዳደር ቱሳ የወላይታ ህዝቦችን ድምጽ ለማሰማት በሚገባ ሲሰራ ቆይቷል’’ በማለት አስተያየቱን የሰጠ ሲሆን በአረካ ከተማ የሚኖር አንድ ነዋሪ ደግሞ ‘’ቱሳ የመልካም አስተዳደር እጦትን በጽኑ የሚታገሉና የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኛ የሆኑ ወጣት አመራሮች አሉት’’ ሲል ተናግሯል። ምንም እንኳን በህዝቡ ዘንድ ለፓርቲው ከፍተኛ ድጋፍ ቢኖርም ቱሳ ጠንካራ እንቅስቃሴ የሚያደርግበት ስፍራ በሶዶና በአቅራቢያው ያሉ ከተሞች ላይ ብቻ ተወስኗል።
ኢዜማ በወላይታና አካባቢው ለብልጽግናና ለቱሳ ሌላ ተፎካካሪ የነበረ ሲሆን በአገሪቱ በተለያዩ ስፍራዎች ዘላቂ የስራ እድል ፍለጋ ተበትኖ ላለው የወላይታ ወጣት የኢዜማ ኢትዮጵያዊነትንና ዜጋ-ተኮር ትብብርን የሚያራምድ አስተሳሰብ የሚስቡ ጠንካራ ነገሮች ናቸው።
የቀድሞ ከንቲባ እንደነበረው አብርሃም ደግሞ ኢዜማ በወላይታ የሚገኙ የማንነት ፍላጎቶችን በኢትዮጵያዊነት ስር ማስተናገድ ቢችል ኖሮ ሁነኛ ምርጫ ይሆን ነበር። ይህን ማድረጊያ አንዱ መንገድ ደግሞ የተማረ የወላይታ ተወላጅን በእጩነት በማቅረብ ነው በማለት ሃሳብ ይሰጣል።
ጎበዜ ግን የኢዜማ የአሁን አስተሳሰብ የወላይታ ህዝቦችን አንገብጋቢ ጥያቄዎች መመለስ አይችልም፤ ‘’ተለዋዋጭ ሁኔታዎች በመኖራቸው ኢዜማ ከአስርት አመታት ወይም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ ሊሳካለት ይችላል ነገር ግን በአሁኑ ምርጫ ላይሆን ይችላል’’ ይላል።
በምርጫው ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የቀረቡ የተወሰኑ ስህተቶችና ቅራኔዎች ቢኖሩም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ብልጽግና በወላይታና በዳውሮ ዞኖች ማሸነፉን ይፋ አድርጓል።
ከ104 ወረዳዎች በ85ቱ ላይ በተካሄደው የምርጫው ሂደት ላይ ብልጽግና ያልተገባ ተጽእኖ አድርጓል በማለት ቱሳ ከምርጫው እራሱን እንደሚያገል አስጠንቅቆ የነበረ ሲሆን ከነዚህ ወረዳዎች ውስጥ በ75ቱ ወረዳዎች ብልጽግና፣ በአራቱ ኢዜማ (አማሮ ልዩ ወረዳን፤ በጉራጌ ዞን በአንድ የምርጫ ክልል እና በጋሞ ዞን የዘይዜ ወረዳ ምርጫ ክልልን ያካትታል) እና በሁለቱ ደግሞ በጌድዮ ዞን የጌድዮ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አሸንፈዋል።
ውጤቱ ምርጫውን ያሸነፈው ብልጽግና ፓርቲ የክልል ጥያቄ ላይ እንደሚወስን የሚገልጽ ነው።
ክልል መሆን መፍትሔ ነው?
በጉዞዬ በሙሉ በደቡብ ምዕራብ የሚገኙ ህዝቦች የተለያዩ አሳሳቢ ጉዳዮች ውስብስብ ብቻ ሳይሆኑ የእውነትም ለመፍታት አስቸጋሪዎች መሆናቸውን ለመገንዘብ ችያለሁ። በተርጫ ያለው የህግ ባለሞያ የሆነው ምህረቱ ኤም በቀላሉ ሲያስቀምጠው ‘’ክልል መሆን በርካታ ችግሮች ላሉባቸው ህዝቦች የመጨረሻ መፍትሔ አይሆንም ነገር ግን የመፍትሔው አንድ አካል ሊሆን ይችላል’’ ይላል።
ለዳውሮ እና ለሌሎች፤ የደቡብ ምዕራብ ህዝበ ውሳኔ ጉዳይ ክልል የመሆን ጥያቄዎችን በተወሰነ መልኩ ይመልሳል የህገ-መንግስታዊ መብቶችንም በተወሰነ መልኩ ያሟላል ነገር ግን ከመሰረተ ልማትና ከውክልና ጋር ያሉ ጉዳዮችን መመለስ ይችል እንደሆነና እንዴት ይመልስ እንደሆነ ገና የሚታይ ጉዳይ ነው። በዞኖች በአጠቃላይ ከተሰባጠሩ ፍላጎቶች ጋር የተያያዙ ያልተመጣጠኑ ወጪዎች በተጨማሪም ከሌሎች ክልሎች ጋር በመሰረተ ልማት በሚገባ ያልተገናኘ ክልልን የማስተዳደር መሰረታዊ ወጪዎች ያለመግባባቶች መንስዔ ሆነው እንደሚቀጥሉ የተረጋገጠ ነገር ነው።
በወላይታ ደግሞ ክልል መሆን የማህበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚፈታ ዋና መፍትሔ አድርጎ የማሰቡ ነገር በተቃራኒው ከሚቀርቡ ሙግቶች ጋር ሲተያይ ሚዛን ይደፋል ማለት አይቻልም። ስኬታማ አስተዳደርና የሀብት መጋራት ለምሳሌ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ነው። አንድ አስተዳዳሪ ተቋም በአካባቢ ደረጃም ሆነ በሩቅ ሆኖ ሲሰራ ክህሎትና ስነ-ምግባር የታከለበት ክትትል እንዲኖረው ማድረግ የመንግስት ዋና አላማ መሆን አለበት።
ነገር ግን አሁንም የማይካዱ እውነታዎች አሉ። ለምሳሌ የሥነ-ህዝብ መስፋፋት ለክልሎቹ ታስበው የሚዘጋጁ አገልግሎቶችን የማስፋፋትን አስፈላጊነት ይጨምረዋል፤ ልክ በተወሰኑ ክልሎች በፍጥነት የሚያድጉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ብቃት ባላቸውና ተደራሽ በሆኑ አስተዳዳሪዎች የበለጠ ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ማለት ነው።
ሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄዋ ተቀባይነት እንዲያገኝ የህዝብ ቁጥርንና የኢኮኖሚ ስኬቶችን ጭምር ለሙግቷ ተጠቅማለች ፤ ዳውሮ ደግሞ ድክመቷን ሰፋ ያለ ኅብረትን በመቀላቀል የሸፈነች ሲሆን በዚህም የህዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ክብደት ጨምራለች። ነገር ግን በወላይታ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተስፋ ያለው ሰፊ የህዝብ ቁጥር ክልል የመሆን ጉዳይን ወደ ጫፍ ለማድረስ በቂ ምክንያት ሊሆን አልቻለም።
በገንዘብ፣ህግና ፖለቲካ አለመመጣጠን
ምንም እንኳን የደቡብ ምዕራብ ኅብረት የጋራ ህዝበ-ዉሳኔ ለማድረግ ጠንካራ ሙግት ቢያቀርብም ታዛቢዎች ጥያቄው እንዲጸድቅ የቀረበበት ሁኔታ ተገቢ መንገድን የተከተለ አለመሆኑ ያስቀምጣሉ። ይህ በደኢህዴን-ኢህአዴግ ወቅት ደቡቦች በጋራ የተቃወሙትን ሌላ አይነት ከላይ ወደ ታች ያለ ፖለቲካን ያመላክታል።
ህገ-መንግስቱ ማንኛውም አይነት በተናጥል ወይም በጋራ የሚቀርብ ክልል የመሆን ጥያቄ ተቀባይነት ለማግኘት መጀመሪያ የሚቀርበው ለክልል ምክር ቤት እንደሆነ ያትታል፤ በሲዳማ ህዝበ-ዉሳኔ የሆነው ይህ ነው፤ነገር ግን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመሆን ጥያቄ ቀጥታ በምክር ቤት ነው እውቅና ያገኘው፤ በዚህም ደንብን በመተላለፍ የህግ የበላይነትን ጥሷል።
የፌደራል ምክር ቤት ለጥያቄው እውቅና መስጠቱ ከተናጥል ክልል የመሆን ጥያቄዎች ይልቅ የጋራ ክልል የመሆን ጥያቄዎች እንደሚመረጡ ያመላክታል። ይህ ምናልባትም የሚያስገርም አይደለም ምክንያቱም መጀመሪያውኑም ደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ እንዲመሰረት ያደረገው አስተሳሰብ እራሱ ይህ ነበር። ነገር ግን ምክር ቤቱ ክልል ለመሆን ጥያቄ እውቅና መስጠቱ ክልል ለመሆን ከህገ-መንግስት ውጭ የሆነ አዲስ መስፈርት እንደገባ ይጠቁማል ይህም ምናልባት የአካባቢውን ህዝቦች ድምጽ ዋጋ እንዳለመስጠት ሊቆጠር ይችላል።
ከዚህ በተጨማሪም ምንም እንኳን ክልል የመሆን ፍላጎቱ እንዳለ ቢሆንም፤ ጥንቃቄ ማረግና ከቀድሞ ካልተሳኩ እንደ ሰሜን ኦሞ ዞን (እና ከዎኣጋጎዳ ሙከራ) እና የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ያሉ ሙከራዎች ትምህርት መቅሰም አለብን። የሲዳማ በቅርብ ጊዜ ከደ/ብ/ብ/ህ/ብ መለየትም በኃይል መዋሀድ ስላለው ጉድለቶች አንድ ጠቃሚ ነገር ሊያስተምረን ይገባል።
በተጨማሪም እንደ ፖለቲካ የውስጥ አዋቂዎች ከሆነ ከደቡብ ምዕራብ ህዝበ-ዉሳኔ ውጪ ሌሎች አስተዳደሮች በኅብረት ክልል ለመመስረት ፍቃደኛ አይደሉም-ወይም ቢያንስ በዚህ ሰአት በአዲስ አስተዳደሮች ውስጥ ስለሚገኙ በርካታ ዘርፎች ለመግባባት አይችሉም። የዳውሮ ዞን ወላይታ ክልላቸውን ለመቀላቀል ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጓ የጥንት ቅያሜዎች አሁን ላሉ ፉክክሮች መነሻ እንደሆኑ ከሚያሳዩ ምሳሌዎች ውስጥ አንዱ ነው።
ልክ እንደሌሎች ቦታዎች በደቡብ ምዕራብ ተጽእኖ ማሳረፍ የሚችሉ ልህቃን በአነስተኛ ደረጃ የሚገኙ ግብዓቶችን (ሀብቶችን) ለመሻማት (ለመቀራመት) ሽኩቻ ውስጥ ሲገቡ ታሪካዊ ቅራኔዎችን እንደ መሳሪያ በመጠቀምና የብሔርና ሌሎች ክፍፍሎችን ለራሳቸው እንዲመች አድርገው በመጠምዘዝ ነበር። በዚህም የተነሳ አሁን ከበፊቱ በበለጠ በርካታ ክልሎች መኖር የሚችሉት ከሌሎች ጎረቤቶቻቸው ጋር ከመተባበር ይልቅ በመፎካክር እንደሆነ ማመናቸው አያስገርምም።
ጥርጣሬዎችና እምነት ማጣት
ሲዳማ የኢትዮጵያ አስረኛ ክልል መሆን መቻሏ በፌደራሊዝም ስርዓታችን አዲስ ደረጃ ላይ እንዳለን የሚያሳይ ሲሆን ህገ መንግስቱ በ1988 ዓ.ም ክልሎችን ካዋቀረ በኋላ ሲዳማ ክልል ለመሆን የቻለች የመጀመሪያው ክልል ናት። ደቡብ ምዕራብ የጋራ ክልል መመስረት ከቻለ ደግሞ የፌደራል ስርዓቱ ከሁኔታዎች ጋር እየሄደ እንደሆነ ያሳይል። ይህም ከዚህ ቀደም ያልተማከሉ ድንጋጋጌዎችን እጅግ በጣም በጥቂቱ ብቻ ለሞከረው የኢትዮጵያ ህገ መንግስታዊ ስርዓት አዲስ ችግር ይፈጥራል።
ደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ የማንነት፣የድንበርና ከሀብት ጋር የተገናኘ ግጭትና ሌሎች ተጓዳኝ ውስብስብ ጉዳዮችን እያስተናገደ ይገኛል። የቅርብ ጊዜ ምሳሌዎች በፈረሰው ሰገን ዞን ባሉ ማኅበረሰቦች መካከል ያሉ ግጭቶች፣በሸኮ ዞን በጉራፈርዳ አካባቢ በአንድ በኩል በመዥንገርና ሸኮ መካከል በሌላ በኩል ደግሞ በሻኪቾ በሂደት ላይ ያለ ግጭት እና በጉጂ የሚገኙ ታጣቂዎች በአማሮ ህዝቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ያካትታሉ። እዚህ ላይ ደግሞ በትግራይ ውስጥ ጦርነት የመክፈትን አስከፊነት፣ በምዕራብ ኦሮሚያ የማያቋርጥ የትጥቅ ትግልና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ስላለው ጥቃት ያልተነገሩ አስከፊ ነገሮችን መጨመር ነው።
የኢትዮጵያ የብሔር ፌደራሊዝምን ለሚደግፉም ሆነ ለሚቃወሙ የስርዓቱ ትግበራዎች ጫፍ ላይ የደረሱ ይመስላሉ። የብልጽግና ፓርቲ አሁን ስልጣን በመያዙ ይህንን ቀውስ ከህገ መንግስታችን አንጻር እንዴት እንደሚያስተናግደው ባይታወቅም በደቡብ ክልል የመሆን ጥያቄ መምጣቱን የሚቀጥል ሲሆን በዚህም የተነሳ በተለይም ህገ መንግስቱ ግልጽ የመደረጉ ነገር አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
በደቡብ ክልል የሚገኙ ዞኖች የሚያቀርቧቸው ክልል የመሆን ጥያቄዎች ተቀባይነት ዝግ ማለትና አለመመጣጠን በፖለቲከኞችና በፓርቲዎች ዘንድ ደስታን አልፈጠረም። በተመሳሳይ ሁኔታም ተቋማት ላይ እምነት ለመገንባትና በህዝቦችና በፖለቲከኞች መካከል መተማመን ለመፍጠር፤ የወደፊት (መጪ) ሁኔታዎች ላይ የሚደረጉ ተፎካካሪ ጤናማ ሙግቶች የሚበረታቱበትና የሚገለጹበት ትክክለኛ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ያስፈልጋል። ነገር ግን በጉዞዬ እንደተመለከትኩት ምርጫው ተፎካካሪ የሌለው እንዲሁም ከፖለቲካ ጭቆና ያልተላቀቀ በመሆኑ ይህ እየተካሄደ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል።
በተጨማሪም የደቡብ ብልጽግና ፓርቲም ከሱ ቀድሞ እንደነበረው ደኢህዴን ቀደም ሲል እርስ በእርስ የሚቃረኑ ውሳኔዎችን የመወሰን ሁኔታ እንዳለው ያሳየ ሲሆን፤ ህገ መንግስታዊ አቅጣጫን አለመከተሉና ክልል የመሆን ጥያቄዎችን ለማስተናገድ መዘግየቱ ከተለያዩ የደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ የሚቀርቡ የራስን እድል በራስ የመወሰን በርካታ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ፍቃደኛ እንዳልሆነ እንዲሁም እንደማይችል ይጠቁማሉ።
ይህ በክልሉ ሰላም ላይ ጠቃሚ አንድምታ የሚኖረው ሲሆን ቀደም ሲልም በቋፍ ያሉ እንደ ሸካና ቤንች-ሸኮ ዞኖች ያሉ አዋሳኝ ስፍራዎች ከባድ ግጭቶችን ሊያስተናግዱ ይችላሉ፤ ወላይታም እንደገና ግጭት ሊነሳ ይችላል።
ስለዚህ ምርጫው ልክ እንደተጠናቀቀና ህዝበ-ዉሳኔዉ ከመድረሱ በፊት የተመረጡ መሪዎች ክልል የመሆን ጥያቄዎችን በበለጠ ሁኔታ በተግባር፣በውይይትና በግልጽ መንገድ መፍታት ይገባቸዋል። ይህንንም ሲያደርጉ የደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ የምስረታ ታሪክን ከግምት በማስገባት፣አሁን ያሉ ውጥረቶችን ለማርገብ በማለምና ምናልባት በተሻሻለ መንገድ ቢሆንም የራስን እድል በራስ የመወሰን ግልጽ ህገ መንግስታዊ መሰረትን በማክበር መሆን አለበት።
ይህ ሲደረግም አሁን በፌደሬሽኑ የደቡብ ብሔሮችና ብሔሬሰቦች ያሉት ውስብስብ የፖለቲካ፣ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሁኔታዎች በርካታ ስፍራዎች ክልል እየሆኑ በመጡ ቁጥር የባሰ ሊወሳስቡ እንደሚችሉ ግምት ውስጥ በማስገባት ክልል የመሆን ጥያቄዎች በተመጣጠነ ሁኔታ ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገባል።
ምላሽ ያገኙ ጥያቄዎች
ክልል ለመሆን በደቡብ በተለያዩ ስፍራዎች እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ዋናዎቹ ምክንያቶች ከፖለቲካ አወቃቀሩ አቀራረጽ የሚነሱ ተደጋጋሚ ከባድ ስህተቶችና የፖለቲካ አወቃቀሩም በተለያዩ አስተዳዳሪዎች በተገቢው መንገድ አለመፈጸሙ ነው።
በፖለቲካና በመሰረተ ልማት ያሉ ልዩነቶች (መድሎዎች) በደ/ብ/ብ/ህ/ብ/ክ ክልል የሚገኙ ስፍራዎች ህገ መንግስቱ የሰጣቸውን መብት ተጠቅመው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥሪ እንዲያነሱ ያደረገ ሲሆን መድልዎ በዋናነት የሚፈጠረው አስተዳደርን በአግባቡ ባለመጠቀምና በብሔር ተኮር የፌደራሊዝም ስርዓት ውስጥ ልህቃን በሚያካሂዱት የተቀነባበር ትንኮሳ ነው።
የደቡብ ምዕራብ ጥያቄ ከሌሎች በደ/ብ/ብ/ህ/ብ ውስጥ ካሉ ክልል የመሆን ጥያቄዎች ጋር ሲነጻጸርና ከላይ እስከታች በፍጥነት ተቀባይነት ከማግኘቱ አንጻር ሲታይ የፌደራል ግዛቱ በርካታ ብሔሮችን ያቀፈ የኅብረት ክልል የመሆን ጥያቄን በተናጥል ከሚቀርብ ክልል የመሆን ጥያቄ በበለጠ መልኩ የሚደግፍ ይመስላል። ይህም ሌሎች በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ስፍራዎች በኅብረት ክልል የመሆን ጥያቄን ማቅረባቸው አንፃራዊ ነፃነት ለማግኘት ያስችላቸው እንደሆነ ማጤን (ከግምት ማስገባት) ሲጀምሩ የሚያስከትለው ነገር ይኖራል።
አሁንም አነዚህ ድምዳሜዎች ያልተረጋገጡ የፖለቲካ ሁኔታዎች በማየላቸውና ይህንንም ተከትሎ በመላው አገሪቱ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ምክንያት ሊለዋወጡ ይችላሉ። የፌደራል ስርዓቱ እጣ ፈንታም ይቀጥል አይቀጥል አይታወቅም ነገር ግን ከደ/ብ/ብ/ህ/ብ የተለያዩ ስፍራዎች ክልል የመሆን ጥያቄዎች መምጣታቸውን ይቀጥላሉ የነዚህ ጥያቄዎች ተግባራዊነትም የገዢው ፓርቲ ህገ መንግስቱን መሬት ላይ ካለው ፖለቲካ ጋር ምን ያህል ማስታረቅ ይችላል የሚለው ሁኔታ ላይ ይመረኮዛል።
Query or correction? Email us
Follow Ethiopia Insight
ይህ ጽሁፍ ምርጫ 2013ን በሚመለከት ዘለግ ያሉ ጽሁፎችን ከመላው ኢትዮጵያ በተከታታይ የምናቀርብበት የ “Ethiopia Insight Election Project (EIEP)” ክፍል ነው።
ዋና ምስል: የወላይታ ክልል መሆንን በመደገፍ በወላይታ ሶዶ የተደረገ ሰልፍ፥ ግንቦት 9፣ 2011;ወላይታ ሚድያ ሀውስ።
Join our Telegram channel
Published under Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International licence. Cite Ethiopia Insight and link to this page if republished.
Leave a Comment